የማይክሮኔዥያ ሚሲዮናውያን
የማይክሮኔዥያ ሚሲዮናውያን እጅግ ሰፊ በሆነው የፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ተራርቀው የሚኖሩ ቢሆኑም በየዓመቱ “የቤተሰብ ስብሰባ” ለማድረግ ይገናኛሉ። እነዚህ በጣም ተራርቀው ከሚገኙት ደሴቶች የሚመጡ ወንጌላውያን የሚገናኙት የት ነው? የአካባቢው መንግሥት የይሖዋ ጎዳና ብሎ በሚጠራው ሥፍራ ነው። ይህ ጎዳና ሥራቸውን የሚቆጣጠረው የጉዋም ቅርንጫፍ ቢሮ የሚገኝበት አድራሻ ነው።
በሰኔ ወር 1992 በ“ብርሃን አብሪዎች” የወረዳ ስብሰባ ለመገኘት 56 የሚያክሉ ሚሲዮናውያን በቅርንጫፍ ቢሮው ተገኝተው ነበር። እነዚህ ሚሲዮናውያን ከቀድሞ ወዳጆቻቸውና አዳዲስ ጓደኞቻቸው ጋር ሲገናኙ የአካባቢው አየር በሳቅና በጨዋታ ተሞልቶ ነበር። ዘወትር እንደሚያደርጉት በመንግሥት አዳራሹ ደረጃዎች ላይ ሰብሰብ ብለው ፎቶግራፍ ከተነሱ በኋላ በዓመታዊው የሚሲዮናውያን ግብዣ ለመካፈል በሶስት ረዣዥም የግብዣ ጠረጴዛዎች ዙሪያ ተቀመጡ። በዚህ ዓመት የአስተዳደር ክፍል አባል የሆነው አልበርት ሽሮደር ተገኝቶ ነበር።
አብዛኞቹ ሚሲዮናውያን በሐሩር ቀበሌ ከሚገኘው አነስተኛ መኖሪያ ቤታቸው ሊወጡ የሚችሉበት አጋጣሚ ይህ በጉዋም የሚደረገው ዓመታዊ ስብሰባ ብቻ ነው። እነዚህ መኖሪያቸው የሆኑት ደሴቶች በጣም ትናንሽ ናቸው። ከማርሻል ደሴቶች አንዱ የሆነው የኤቢ ደሴት ስፋቱ 32 ሄክታር ብቻ ነው። በማርሻል ደሴቶች የሚገኘው የመጁሮና በጊልበርት ደሴቶች የሚገኘው የኪሪባቲ የሚሲዮናውያን ቤት 800 ሜትር ርዝመት ባለው ጠባብና ረዥም ደሴት ላይ የሚገኙ ናቸው። በዚህ ምክንያት ሚሲዮናውያኑ በጉዋም ጉዞአቸው በጣም ይደሰታሉ።
ራቅ ባለ በሐሩር ክልል በሚገኝ ደሴት ማገልገል በጣም የሚያስደስት መስሎ ቢታይም እንዲህ ባለው አካባቢ ማገልገል የሚያመጣውን ፈታኝ ሁኔታ ለመቋቋም የሚችሉት ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ከ56ቱ ሚሲዮናውያን መካከል ከጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተመርቀው የመጡት ሰባቱ ብቻ ናቸው። ብዙዎቹ በሐዋይና በፊሊፕንስ በአቅኚነት ሲያገለግሉ የነበሩ ስለሆኑ በሐሩር አካባቢ መኖር የተለማመዱና ከትውልድ አገራቸው በቀጥታ ወደ ሚሲዮናዊነት ምድባቸው የሄዱ ናቸው።
የማይክሮኔዥያ ደሴቶች የሚገኙት በምድር ወገብ አጠገብ ስለሆነ ምሥራቹን ለነዋሪዎቸ በሚያደርሱበት ጊዜ በጣም ከባድ የሆነውን ሙቀትና የአየር እርጥበት መቋቋም ይኖርባቸዋል። ከዚህ ይበልጥ አስቸጋሪ የሚሆነው ከሰዎች ጋር በቋንቋ የመግባባት ችግር ሊሆን ይችላል። እያንዳንዱ ደሴት የየራሱ ቋንቋ አለው። አንዳንዶቹ ቋንቋዎች በብዛት የማይታወቁ በመሆናቸው በመዝገበ ቃላት ውስጥ እንኳን ያልሠፈሩ ናቸው። አዲስ የመጣ ሰው ቋንቋዎቹን አውቆ በሚገባ ለመናገር በዓመታት የሚቆጠር ጊዜ ሊያስፈልገው ይችላል። በእነዚህ የተለያየ ባሕል በሚገኝባቸው ደሴቶች የሚኖሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲረዱ ለማስቻል የጉዋም ቅርንጫፍ ቢሮ በ11 ቋንቋዎች ጽሑፎችን ያትማል። ከእነዚህ ቋንቋዎች መካከል 9ኙ የሚነገሩት በማይክሮኔዥያ ብቻ ነው።
አንዳንዶቹ ደሴቶች ራቅ ያሉ በመሆናቸው ምክንያት በጀልባ ካልሆነ በስተቀር ሊደረስባቸው አይችልም። በቹክ (በትሩክ) የሚገኘው የቶል ከተማ ሚሲዮናውያን ቤት ከእነዚህ አንዱ ነው። በዚያ የሚኖሩት ሚሲዮናውያን በቀን ውስጥ ለጥቂት ሰዓቶች ብቻ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙት ከፀሐይ ኃይል አጠራቅሞ ኤሌክትሪክ ከሚያመነጭ መሣሪያ ነው።
ዩናይትድ ስቴትስን የሚያክል ስፋት ባለው የምይክሮኔዥያ አካባቢ በጠቅላላ 14 የሚሲዮናውያን ቤቶች አሉ። በዚህ አካባቢ ከሚኖሩት 400,000 ሰዎች መካከል 1,000 የሚያክሉት በ20 ጉባዔዎችና በ3 ገለልተኛ ቡድኖች የተደራጁ የምስራቹ አስፋፊዎች ናቸው።
የማይክሮኔዥያ ሕዝቦች በአጠቃላይ ከሰው ጋር ተግባቢ ቢሆኑም በአካባቢው ባለው ሃይማኖታዊ ልማድና በቤተሰብ ተጽእኖ ምክንያት ብዙዎቹ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመቀበል ይቸገራሉ። ስለዚህ የስብከቱ ሥራ በአጠቃላይ ሲታይ ጥሩ ዕድገት ያለው ቢሆንም (1,000 የሚያክሉት የመንግሥቱ አስፋፊዎች 2,000 የሚያክል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይመራሉ) አንዳንድ ጉባዔዎችና ቡድኖች ሊጨምሩ አልቻሉም። ለምሳሌ ያህል በቲንያን ደሴት 5 አስፋፊዎች ብቻ ሲኖሩ በናውሩ ደሴት 7 አስፋፊዎች፣ በያፕ የሚገኙት የኮስራይና የሮታ ጉባኤዎች እያንዳንዳቸው ከ40 የሚያንሱ አስፋፊዎች አሉአቸው። ቢሆንም አንዳንድ ሚሲዮናውያን በተመደቡበት አካባቢ ከ20 ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ቆይተዋል። በቤላው የተመደቡት ሚሲዮናውያን ስድስቱም በተመደቡበት ሥፍራ ለ12 ዓመት ቆይተዋል።
በምድባቸው ጸንተው የሚቆዩ ሚሲዮናውያን በአጸፋው የሚያገኙት ብድራት ብዙ ነው። በየዕለቱ የይሖዋን ፍጥረታት አይቶ የመደነቅ አጋጣሚ አላቸው። ለም የሆኑት የማይክሮኔዥያ ደሴቶች ሰማያዊ በሆነው የፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ትንንሽ አረንጓዴ እንቁዎች መስለው ይታያሉ። የብዙ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው ጭር ያሉ የባሕር ጠረፎችና የሚያማምሩ ዓሦች የሚርመሰመሱባቸው የባሕር ውስጥ ቋጥኞች የሚገኙበት ይህ አካባቢ የባሕር ውስጥ ጠላቂዎችና ዋናተኞች ከሚወዷቸው በዓለም ውስጥ ካሉት ምርጥ ሥፍራዎች አንዱ ነው። በተጨማሪም በየቀኑ መጨረሻ ላይ በውቅያኖሱ ላይ ፀሐይ ስትጠልቅ ማየት ልብን ይመስጣል።
ይሁን እንጂ ከሁሉ የሚበልጠው የጽናታቸው ዋጋ ይሖዋ ወደፊት የሚያመጣቸውን አስደናቂ ነገሮች ለሰዎች በመናገር እርሱን ለማገልገል የመቻል መብት ነው። የማይክሮኔዥያ ሚሲዮናውያን ለዚህ የድካማቸው ብድራት ራሳቸውን ብቁ ስለሚያደርጉ የኢሳይያስ 42:12ን ቃል ፈጽመዋል። “ለእግዚአብሔር [ለይሖዋ አዓት] ክብርን ይስጡ፣ ምስጋናውንም በደሴቶች ይናገሩ።”
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሚሲዮናውያን በጉዋም ተሰብስበው ሳሉ፤ ሰኔ 1992