‘ከተራሮች በፊት’
“በትውልዶች ዘመናት ሁሉ መኖሪያችን ነበርክ። ተራሮች ከመወለዳቸው በፊት፣ ምድርንና ዓለምን ከማስገኘትህ በፊት አንተ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላክ ነህ።” (መዝሙር 90:1, 2 ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን ) እነዚህ ቃላት የተነገሩት ለፈጣሪያችን ሲሆን በተለይ ሁሉ ነገር ተለዋዋጭ በሆነበት በዚህ ዘመን በጣም የሚያጽናና ቃል ነው።
የኢኮኖሚው ሁኔታ በጣም አየተበላሸ በመምጣቱ የወደፊቱን ጊዜ በእርግጠኝነት የሚጠባበቁ ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው። በአንዳንድ ከተሞች ወንጀልና መድኃኒቶችን አለአግባብ መጠቀም በጣም በመስፋፋቱ ምክንያት ከተማ መሆናቸው ቀርቶ የጦርነት ቀጠናዎች ሆነዋል። ለብዙ ዘመናት ጸንቶ የቆየው የቤተሰብ ተቋም እንኳን በመፈራረስ ላይ ይገኛል። እንደ ግብረሰዶማዊ ቤተሰቦች የመሰሉ አዳዲስ ነገሮችን መስማት ጀምረናል። በአንድ ወላጅ ብቻ የሚተዳደሩና አንደኛው ወላጅ ብቻ ብዙ ሸክም ለመሸከም የሚገደድባቸው ቤተሰቦች ቁጥር እየጨመረ ሄዶአል። የብዙ ቤተሰቦች ሰላም ተደባዳቢ በሆኑና በልጆች ላይ አስከፊ ነውር በሚፈጽሙ የትዳር ጓደኞች ይናወጣል።
በዚህ አስቸጋሪ ዘመን ማን ሊመራን ይችል ይሆን? ከሳይኮሎጂስቶች፣ ከሥነ ትምህርት ምሁራንና ከሌሎች ጠበብት ምክር አልታጣም። ግን ምን ያደርጋል፤ የእነዚህ ሰዎች ምክር ብዙውን ጊዜ እርስበርሱ የሚጋጭ ነው። በምዕራቡ ዓለም የአንድ ትውልድ ዘመን ለሚያክል ጊዜ ልጆችን በማስተማር ረገድ ግንባር ቀደም ምክር ሰጪ ሆነው የቆዩት ዶክተር ቤንጃሚን ስፖክ ናቸው። ይሁን እንጂ እሳቸው የሰጡት ምክር ስህተት የነበረ መሆኑን በመጨረሻው አምነዋል።
አምላክን “መኖሪያችን” ብናደርግ ምን ያህል ጥበበኞች እንሆን ነበር? እርሱ በዚህ ተነዋዋጭ ዘመን እንደ አለት የጸናና “ከዘላለም እስከ ዘላለም” የሚኖር ነው። በነቢዩ ሚልክያስ በኩል ስለራሱ ሲናገር “እኔ ይሖዋ ነኝ፣ እኔ አልተለወጥኩም” ብሎአል። (ሚልክያስ 3:6 አዓት) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡት የአምላክ የሥነምግባር ሕግጋት ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ናቸው። “ከተራሮች በፊት” ይኖር የነበረ አምላክ ስለሆነ ከቅዱሳን ጽሑፎች የምናገኛቸው የእርሱ ምክሮች በዘላለማዊ ጥበቡ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ደስታና የተሳካ ኑሮ ለማግኘት የሚያስፈልገን ይህ ዓይነቱ ምክር ነው።
ስለዚህ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ መታመን የጥበብ መንገድ ነው። ከአምላክ ጥበብ ለመጠቀም እንድትችሉ ቃሉን አጥኑ። በምትማሩት ነገር ሙሉ ትምክህት ይኑራችሁ። በሕይወታችሁ መንገድ የሚመራችሁ መብራት ይሁንላችሁ። (መዝሙር 119:105) የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት ለመመልከት የሚያስችል ምክንያት የሚኖራቸውና እውነትኛ የአእምሮ ሰላም የሚያገኙት ይህን የሚያደርጉ ሰዎች ብቻ ናቸው።