የተለየ ግኝት በባሃማስ
በፍሎሪዳና በኩባ መካከል በሚገኘው ደማቅ ሰማያዊ ባሕር እንደ መሸጋገሪያ ድንጋይ ሆኖ የሚታየው የባሃማስ ደሴት በ1992 የዓለምን የዜና ማሠራጫዎች ትኩረት በከፍተኛ ደረጃ ስቦ ነበር። ለምን? ምክንያቱም ብዙ የታሪክ ምሑራን ክርስቶፎር ኮሎምቦስ በ1492 አሜሪካን ለማግኘት ባደረገው ታሪካዊ የባሕር ጉዞ በመጀመሪያ የተመለከተው ደረቅ መሬት የባሃማስን ደሴት ነው ብለው ስለሚያስቡ ነው። ኮሎምቦስ በዚህ ምድር ላይ ያረፈበት 500ኛ ዓመት የተከበረበት ጥቅምት 12 ቀን የመላውን ዓለም ትኩረት ስቦ ነበር።
ይሁን እንጂ የ500ኛውን ዓመት ክብረ በዓል ደስታ የሚቀንስ ሁኔታ አልጠፋም ነበር። የዓለም አቀፍ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ጆን ከሩ ለ23ኛው የጥቁር ጠበቆች ብሔራዊ ማኅበር ባደረጉት ንግግር ኮሎምቦስ “በበርካታ የካሪቢያን ደሴት ነዋሪዎች ላይ የሞት ማዕበል በመልቀቁ በኃላፊነት ይጠየቃል” ብለዋል።— ዘ ናሳው ጋርዲያን
በአሁኑ ጊዜ 250,000 ከሚያክሉት የባሃማስ ደሴት ነዋሪዎች መካከል ኮሎምቦስ “ጥሩ ቁመና፣ ያማረ ሰውነትና የተዋበ ፊት አላቸው” ሲል ከገለጻቸውና በመጀመሪያ ካገኛቸው ሰላማዊ ሰዎች ተወላጅ እንደሆነ ሊናገር የሚችል አንድ ሰው እንኳን የለም። እነዚያ የባሃማስ ደሴት ነዋሪዎች ምን ሆኑ? የባሃማስ ታሪክ የተባለው መጽሐፍ መልሱን ይሰጠናል። “ከ1500 እስከ 1520 ባሉት ዓመታት ምናልባት 20,000 የሚያክሉት ሉካያውያን የባሃማስ ነዋሪዎች በሙሉ በሂስፓንዮላ በሚገኙት የስፓኝ የወርቅ ማዕድኖች በባርነት እንዲሠሩ ተወስደው ነበር።
በዚህ መንገድ አለነዋሪ የቀረችው የባሃማስ ደሴት ‘እንደገና የተገኘችው’ በመጀመሪያ በብሪታንያውያን በኋላ ደግሞ ለብሪታንያ ዙፋን ታማኝ በሆኑ በርካታ ጭፍሮች ነበር። እነዚህ ለብሪታንያ ዙፋን ‘ታማኝ’ የነበሩት ሰዎች በሰሜን አሜሪካ ቅኝ ግዛቶች ትላልቅ እርሻ የነበራቸው ሰዎች ነበሩ። ለዘውዱ ታማኝ በመሆናቸው ምክንያት በዚያ ጊዜ በአህጉሩ መቀስቀስ የጀመረውን ጦርነት ሸሽተው የሄዱ ነበሩ። የዛሬዎች ባሃማውያን በአብዛኛው የእነዚህ ሰዎችና የባሮቻቸው ተወላጆች ናቸው። ብዙዎች ባሮች ነጻ ከወጡ በኋላም ቢሆን በጌቶቻቸው ስም ሲጠሩ ቆይተዋል።
ሌላ ዓይነት ግኝት
ኮሎምቦስ ራሱን እንደ ሚሲዮናዊ አድርጎ ይቆጥር እንደነበረ አያጠራጥርም። “አምላክ የአዲሱ ሰማይና የአዲሱ ምድር መልእክተኛ አድርጎኛል። . . . የት እንደማገኘውም አመልክቶኛል” ብሎ እንደነበረ ተነግሯል። ይሁን እንጂ በእሱ ምክንያት የደረሰው ጥፋት ይህ አባባሉ ትክክል አለመሆኑን ይመሰክራል። አምላክ አመጣለሁ ብሎ ቃል የገባልን ጽድቅ የሰፈነበት ‘አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር’ ሌላ ዓይነት ግኝት እስኪከናወን ድረስ መቆየት ነበረበት።— 2 ጴጥሮስ 3:13
በ1926 ኤድዋርድ ማኬንዚና ባለቤቱ ወደ ባሃማስ ደሴቶች መጡ። እነዚህ ሰዎች ከእነርሱ በፊት ከነበሩት መሬት አሳሾች የተለዩ ነበሩ። እነዚህ ትሁታን የጃማይካ ተወላጆች የመጡት ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች እየፈለጉ አንድ ዓይነት ሀብት ለማካፈል ነበር። የአምላክን መንግሥት ምሥራች ወደ ባሃማስ ያደረሱት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች እነዚህ ባልና ሚስት ነበሩ። (ማቴዎስ 13:44፤ 24:14) ከአንድ ዓመት በኋላ ክላረንስ ዎልተርስና እና ሪቸል ግሪጎሪ የተባሉ ሁለት የጃማይካ ተወላጆች መጡላቸው። በ1928 በባሃማስ የመንግሥት አስፋፊዎች ቁጥር ሰባት ደርሶ ነበር። ለአራት ዓመት ያህል ለዚህ ደሴት ነዋሪዎች ምሥራቹን በትጋት ሲሰብኩ ቆዩ።
ከዚያ በኋላ በጣም ጥሩ ተናጋሪ የነበረው ኢ ፒ ሮበርትስ የተባለ ሰው ከትሪኒዳድ መጣ። በሕዝባዊ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ያደረጋቸው የሕዝብ ንግግሮች የሐሰት እምነቶችን ከሰው ልብ ውስጥ ለማውጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማድረጋቸውም በላይ የብዙዎች ልብ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዲነካ አድርገዋል። ከእነዚህ ንግግሮች አንዱን በተመስጦ ያዳምጡ ከነበሩት ሰዎች መካከል ዲ ኦ እየተባለ በቁልምጫ መጠራት የጀመረው ዶናልድ ኦስካር ሙሬይ ይገኝ ነበር። እርሱም ከጊዜ በኋላ የሥራውን አመራር ተረከበ።
ሚሲዮናዊት የሆነችው ናንሲ ፖርተር ዲ ኦ ሙሬይ በስብከቱ ሥራ የሚረዱ ሰዎች እንዲገኙ ምን ያህል አጥብቆ እንደጸለየ የነገራትን ታስታውሳለች። በ1947 የተላኩት ናንሲና ባልዋ እንዲሁም ሌሎች ሁለት ሚሲዮናውያን የመጀመሪያዎቹ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የተላኩ ሚሲዮናውያን ነበሩ። እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘንበት ስብሰባ ፈጽሞ ልንረሳው የማንችለው ነው። በስብሰባው ላይ ዘጠኝ ወይም አሥር የሚሆኑ ሰዎች ነበሩ። ሊቀመንበር የነበረው ወንድም ሙሬይ ሲሆን ሚሲዮናውያኑ በደህና በመድረሳቸው ይሖዋን አመስግኖ በጸሎት ከፈተ። እርዳታ ያስፈልገናል። ለዚህም ስንጸልይ ብዙ ጊዜ ሆኖናል አለ። ማኅበሩም እርዳታ ለመላክ በገባው ቃል መሠረት እዚህ ለመገኘት ችለናል። ጸሎቱ በጣም ልብ የሚነካ ስለነበረ ለሁልጊዜ እዚህ ለመኖር እንድንፈልግ አድርጎናል።” እህት ፖርተር ባልዋ ቢሞትም እንኳን ከ45 ዓመት በኋላም የሚያጽናናውን የመንግሥት መልእክት ለደሴቱ ነዋሪዎች በማድረስ ላይ ትገኛለች።
በተለይ ከ1947 ወዲህ በባሃማስ የሚከናወነው የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ከሙሉ ጊዜ አገልጋዮችና ደሴቱን በጀልባ ከጎበኙ ሌሎች አስፋፊዎች በርካታ ጥቅም አግኝቶአል። እነዚህ ሰባኪዎች መርከብ ሊያሰምጡ በሚችሉት የአሸዋ ክምሮችና ብዙ ጥልቀት በሌላቸው የባሕር ዳርቻዎች ጀልባቸውን ከቀዘፉ በኋላ በእግራቸው የባሕሩን ዳርቻ አቋርጠው በሩቅ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሰዎች ምሥራቹን ያደርሱ ነበር። እነዚህ ቀደም ሲሉ የተደረጉ ጥረቶች አሁንም ፍሬ በመስጠት ላይ ናቸው።
በ1950 አንድ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ። በዚህ ዓመት በታህሣሥ ወር የወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት የነበረው ናታን ኤች ኖርና ፀሐፊው የነበረው ሚልተን ጂ ሄንሸል ለመጀመሪያ ጊዜ የባሃማስን ደሴት ጎበኙ። ኖር በጄይል አሌ ጎዳና በሚገኘው ማዘርስ ክለብ አዳራሽ የተባለ የእንጨት ቤት ውስጥ ተጣብበው ለተቀመጡት 312 ሰዎች ንግግር አደረገ። ከተሰብሳቢዎቹ መካከል እውቅ የሆኑ በርካታ ሰዎች ነበሩ። ከእነዚህም መካከል አንድ የፓርላማ አባልና የአንድ ዕለታዊ ጋዜጣ አዘጋጅ ይገኙ ነበር። በዚያ ምሽት በባሃማስ የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ እንደሚቋቋም ማስታወቂያ ተነገረ።
የደሴቱ ነዋሪዎች ያሳዩት የወዳጅነት አቀባበል
ተግባቢ የሆኑት የባሃማስ ደሴት ነዋሪዎች ለመንግሥቱ መልእክት በአብዛኛው አድማጭ ጆሮ ሰጥተዋል። አሁንም ቢሆን ከባድ ችግር የሆነው ለነዋሪዎቹ በሙሉ ምሥራቹን ማዳረስ ነው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? አብዛኞቹ ሰዎች የሚኖሩት በዋና ከተማው በናሶና አጎራባችዋ በሆነችው በግራንድ ባሃማ ቢሆንም የባሃማስ ደሴቶች ክፍል በሆኑት 15 ተለቅ ያሉ ደሴቶችና 700 በሚያክሉት አነስተኛ ደሴቶች ተበታትነው የሚኖሩ ሰዎች አሉ።
በርከት ያሉ የአገሩና ከሌሎች አገሮች የመጡ ምሥክሮች ችግሩን በመመልከት በስብከቱ ሥራ እርዳታ ለማበርከት ወደ አነስተኞቹ ደሴቶች ሄደው መኖር ጀምረዋል። ይህን ለማድረግ የቻሉት በርካታ የገንዘብ ወጪና መሥዋዕትነት ከፍለው ስለሆነ በጣም የሚመሰገኑ ናቸው። ቢሆንም ያደረጉት ጥረት በአጸፋው ከፍተኛ ዋጋ አስገኝቶላቸዋል።
አንድ ወጣት ባልና ሚስት አንድሮስ ወደሚባለው ትልቅ ደሴት ተዛወሩ። አንድ ቀን ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ሲሰብኩ ከሐይቲ የመጣ ሰው አገኙ። በባሃማስ በሺህ የሚቆጠሩ የሐይቲ ተወላጆች ይገኛሉ። ሰውዬው ወዲያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ተስማማ። በዚያው ምሽት በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ በተባለው መጽሐፍ የእንግሊዝኛና የፈረንሣይኛ ቅጂዎች በመጠቀም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረለት። በሚቀጥለው ምሽት ለመጀመሪያ ጊዜ በክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ተገኘ። ወዲያው ማጨስ አቆመ፣ ፈጣን መሻሻል አደረገና በስብከቱ ሥራ መካፈል ጀመረ።
ይህ ሰው በሚጠመቅበት ቀን ጠዋት ወሬያቸውን ከሰማ ከአምስት ዓመት በኋላ በሐይቲ ከሚገኙት ቤተሰቦቹ የተቀዳ ቴፕ ደረሰው። ምን የሚነግሩት ነገር ቢኖራቸው ይሆን? እንዴት የይሖዋ ምሥክሮች ሊሆኑ እንደቻሉ ተረኩለት። እህቱ የዘወትር አቅኚ እንደሆነች ከገለጹለት በኋላ የይሖዋ ምሥክሮችን እንዲፈልግና አብሮአቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና አሳሰቡት። ይህ ሰው በዚያው ዕለት ተጠመቀ። የወሰደው እርምጃ ትክክል እንደሆነ እርግጠኛ ነበር።
ሰዎቹ ያሳዩት ይህን የመሰለው የጋለ ስሜት የአገሩን ምሥክሮች ልብ በደስታ ሞቅ አድርጎታል። በርካታ አስፋፊዎች የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊነት ሥራ ጀምረዋል። ይህም ለጭማሪው አስተዋጽኦ አበርክቶአል። በ1988 በባሃማስ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ቁጥር 1,000 የደረሰው በዚህ ምክንያት ነበር። በአሁኑ ጊዜ በዋና ዋናዎቹ ደሴቶች በ19 ጉባኤዎች የሚገኙ 1,300 የሚያክሉ የመንግሥቱ አስፋፊዎች አሉ።
ለወደፊቱ ጊዜ መዘጋጀት
የምሥክሮቹ ቁጥር በጣም እያደገ በመሄዱ ለዓመታዊ ስብሰባቸው የሚበቃ አዳራሽ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖባቸው ነበር። የተሰብሳቢዎቹ ቁጥር በጣም ብዙ በመሆኑ ምክንያት በተለያዩ ደሴቶች ሁለት ስብሰባ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖአል። በዚህም ምክንያት የክልል ስብሰባ አዳራሽና አዲስ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንጻ ለመሥራት እቅድ ወጣ። ሥራው የተጀመረው በ1989 ነበር። በመቶ የሚቆጠሩ ከተለያዩ አገሮችና ከባሃማስ የተውጣጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች በግንባታው ሥራ ላይ ለይሖዋ እንደሚገባ በሙሉ ልብ ሠርተዋል።— ቆላስይስ 3:23
እስከዛሬ ድረስ የባሃማስ ደሴቶች የይሖዋ ምሥክሮች ካደረጉአቸው ስብሰባዎች በሙሉ በጣም ትልቁና በጣም አስደሳች የነበረው የካቲት 8 እና 9, 1992 አዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮና የክልል ስብሰባ አዳራሽ በተመረቀበት ጊዜ የተደረገው ነበር። በሁሉም የደሴቶቹ ክፍሎች የሚኖሩ ወንድሞች ለዚህ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ዝግጅት በሚያደርጉበት ጊዜ ሁሉ ከፍተኛ ቅንዓት ይታይባቸው ነበር። አየሩ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ቀዝቀዝ ያለ ነበር። ከምረቃው ፕሮግራም በፊት በነበረው ምሽት ዝናብ ጥሎ ነበር። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር ክፍል አባል የሆነው ጆን ባር “የቲኦክራሲ ጭማሪ ዝማሬ” የተባለውን የምረቃ ንግግር ሲሰጥ ያዳምጡ የነበሩትን 2,714 የሚያክሉ ተሰብሳቢዎች ደስታ ሊያቀዘቅዝ የሚችል ነገር አልነበረም።
ተሰብሳቢዎች እንዲህ ያለ ደስታና ሐሴት እንዲያገኙ ላስቻላቸው ሰማያዊ አባት ለይሖዋ አምላክ የጠለቀ አመስጋኝነት ተሰምቶአቸው ነበር። በምረቃው ላይ የተገኙ ሁሉ ይህን የሕንጻ መስፋፋት አስፈላጊ ያደረገውን የመንፈሳዊ ትምህርት ሥራ በሙሉ ኃይል ለመፈጸም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል።
ኮሎምበስ ይህን ደሴት ማግኘቱ ለደሴቱ ነዋሪዎች አዲስ የተሻለ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑና አለመሆኑ አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ ይቆያል። በባሃማስ ደሴቶች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ግን ራስን መሥዋዕት በማድረግ መንፈስ ተነሳስተው የማያውቁትን አካባቢ አቋርጠው ታላቁን ምሥራች ከዚህ በፊት ወዳልታወቀ መንፈሳዊ ባሕር ያመጡትን የመንግሥት ምሥራች ሰባኪዎች አምላክ ስለላከላቸው አመስጋኞች ናቸው። ሥራቸውና “ግኝታቸው” በባሃማስ ደሴቶች ለሚኖሩ እውነት ፈላጊዎች በሙሉ ተወዳዳሪ የሌለው መንፈሳዊ ብልጽግና አስገኝቶአል።
[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ግራንድ ባሃማ
አባኮ
አንድሮስ
ኒው ፕሮቪዳንስ
ናሶ
ኤልቴራ
ካት ደሴት
ግሪት ኤክሱማ
ረም ኬይ
ሳን ሳልቫዶር
ሎንግ ደሴት
ክሩክድ ደሴት
አክሊንስ ደሴት
ማያጉና
ሊትል ኢናጉዋ
ግሬት ኢናጉዋ
ካሪቢያን ባሕር
ፍሎሪዳ
ኩባ
[ሥዕል]
በገበያ ላይ በጭድ ተራ የሚደረግ ስብከት
ምሥራቹን ለማካፈል ባሕሩን በእግር መሻገር
ቅርንጫፍ ቢሮው በክልል ስብሰባ አዳራሹ ትይዩ በሚገኝ ኮረብታ ላይ ይገኛል