“የሕይወትን አክሊል” ተሸለመ
ሐዋርያው ዮሐንስ በስምርኔስ ጉባኤ ለነበረው መልአክ “እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ” ብሎ እንዲጽፍ ተነግሮት ነበር። (ራእይ 2:8, 10) የፔንስልቫንያው እና የኒው ዮርኩ የመጠበቂያ ግንብ፣ ትራክትና መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር እንዲሁም የሌሎች ቲኦክራቲካዊ አካሎች ፕሬዘዳንት የነበረው ፍሬዴሪክ ዊልያም ፍራንዝ ምድራዊ ሕይወቱን ታኅሣሥ 22 ቀን 1992 ጠዋት ላይ መፈጸሙን የሚገልጽ ማስታወቂያ ሲነገር ሐዘንና ደስታ በተቀላቀለበት ስሜት ነበር።
ማስታወቂያው አሳዛኝ የነበረው በጣም ተወዳጅ የነበረና እጅግ ታማኝ የሆነ የይሖዋ አገልጋይ ከምድር መድረክ ማለፉን የሚገልጽ በመሆኑ ነው። ይሁን እንጂ አሁን “ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው። . . . ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ሥራቸውም ይከተላቸዋል” የሚለው የራእይ 14:13 ቃል በተወደደው ወንድማችን ፍራንዝ ላይ ተፈጻሚነት ስለሚኖረው አስደሳች ዜና ነው። ወንድም ፍራንዝ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ፣ ትሁት፣ በጣም ትጉህና ፍሬያማ የሆነ አገልጋይ ነበር። ይሖዋ አምላክ ‘የታማኝና ልባም ባሪያ’ ክፍል የሆነውን ወንድም ፍራንዝን “ለቤተሰዎቹና” ለተባባሪዎቻቸው መንፈሳዊ ምግብ በማቅረቡ ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቅሞበታል። — ማቴዎስ 24:45–47
ወንድም ፍራንዝ በኮቪንግተን ኬንታኪ የተወለደው መስከረም 12 ቀን 1893 ነበር። ከእውነት ጋር የተዋወቀው በታላቅ ወንድሙ አማካኝነት ነበር። በዚያ ጊዜ በሲንሲናቲ ዩኒቨርስቲ እየተማረ የፕሪስቢተርያን ቄስ ለመሆን በመዘጋጀት ላይ ነበር። ከዚህ በኋላ ግን ከፕሪስቢተርያን ቤተ ክርስቲያን ወጥቶ በዚያ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ ከነበሩት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተባበረ። ኅዳር 30 ቀን 1913 ተጠመቀና በሚቀጥለው ዓመት ከዩኒቨርስቲ ወጥቶ የአቅኚነት አገልግሎት ጀመረ። ሰኔ 1 ቀን 1920 የብሩክሊን ቤቴል ቤተሰብ አባል ሆነ። ብዙም ሳይቆይ የአቅኚዎች ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ ሆነ። በ1926 ደግሞ ወደ ጽሑፍ ዝግጅት ተዛውሮ ከፍተኛ አገልግሎት አበረከተ። በ1945 የመጠበቂያ ግንብና የሌሎች ተባባሪ አካላት ምክትል ፕሬዘዳንት ሆነ። በጊዜው ፕሬዘዳንት የነበረው ናታን ኤች ኖር በ1977 ሲሞት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት ሆነ። በዚህም ቦታ እስከ ዕለተ ሞቱ ድርስ አገልግሎአል። ወንድም ፍራንዝ በሕይወት ዘመኑ የይሖዋ ምሥክሮች ብዛት ከጥቂት ሺዎች ተነስቶ አራት ተኩል ሚልዮን ሲደርስ ተመልክቶአል። በርካታ የአገልግሎት መብቶችንም አግኝቶአል። በዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ንግግር ሰጥቶአል፣ በብዙ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎችንና የሚሲዮናውያን ቤቶችን ጎብኝቶአል። የሕይወት ታሪኩ መጠበቂያ ግንብ 9–108 ገጽ 15–20 ላይ ወጥቶአል።
ሰኞ ታኅሣሥ 28 ቀን 1992 ምሽት ላይ በብሩክሊን ቤቴል የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ የቀብር ንግግር ተደርጎ ነበር። የአስተዳደር ክፍል አባል የሆነው አልበርት ሽሮደር በጣም ሞቅ ያለና የሚያንጽ ንግግር ሰጠ። በመጠበቂያ ግንብ እርሻ፣ በፓተርሰን፣ በማውንቴይን እርሻ፣ በመንግሥት እርሻና በካናዳ ቅርንጫፍ የሚገኙ የቤቴል ቤተሰቦች ከዚሁ አዳራሽ ጋር በቴሌፎን መስመር ተገናኝተው ነበር።
ወንድሞች በሙሉ፣ በተለይም አብረውት የሠሩ ሁሉ ወንድም ፍራንዝን በማጣታቸው አዝነዋል። አብረውት ለሚያገለግሉና ለሚጓዙ ሁሉ የሚያዝን፣ የሚያስብ፣ የሚያበረታታና የሚታገስ ወንድም ነበር። የእምነት ባልደረቦቹ በሙሉ በዕብራውያን 13:7 ላይ በተገለጸው መንፈስ ይመለከቱት ነበር። “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ። የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው።”
ታኅሣሥ 30 ቀን 1992 ወንድም ሚልተን ጂ ሄንሸል የማኅበሩ አምስተኛ ፕሬዘዳንት በመሆን ወንድም ፍራንዝን እንዲተካ ተመርጦአል።
[በገጽ 31, 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፍሬዴሪክ ፍራንዝ በ1913
በሚርትል ጎዳና በሚገኘው የማኅበሩ ፋብሪካ በ1920
በ1953 በያንኪ ስታዲየም ከናታን ኖር ጋር