“የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” የተመላለሱባቸው የጉያናውኃዎች
ጉያና።a ይህ ቃል በአሜሪዲያን ቋንቋ “ውኃ ያለበት ምድር” ማለት ነው። ይህ አባባል በደቡብ አሜሪካ የምትገኘውን ብቸኛ እንግሊዝኛ ተናጋሪ የሆነች አገር መሬት እንዴት ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል! ምድሪቱ ከጉያና ተራራዎች ተነስተው በደኑ በኩል በማለፍ አትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ በሚገቡ በብዙ ወንዞችና በገባሮቻቸው የተጠላለፈች ናት። እነዚህ ወንዞች በውኃው ዳር ተበታትነው ለሚገኙ ለብዙ መንደሮችና እርሻዎች የኑሯቸው መሠረት ናቸው።
በጉያና ያሉ የይሖዋ ምስክሮች ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” ሲል በዚህ አካባቢ በወንዙ ዳርቻ ለሚኖሩ ሰዎችም ጭምር ምሥራቹ እንደሚሰበክ መናገሩ እንደነበረ ይገነዘባሉ። (ማቴዎስ 24:14) ስለዚህ ብዙዎቹ አቅኚዎች የሆኑ ምስክሮች ያሉባቸው ቡድኖች ለሰዎቹ ምሥራቹን ለማድረስ ሲሉ ትልልቅና ትንንሽ ጀልባዎችን በመጠቀም በጉያና ውኃዎች ላይ ተመላልሰዋል።
ለዚህ ሥራ እገዛ ለማድረግ በጉያና የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ቁጥር 1 እስከ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ቁጥር 5 ድረስ የሚጠሩ ከእንጨት የተሠሩ አምስት መርከቦችን ተጠቅሟል። እነዚህ ጀልባዎች ምስክሮች የሆኑ አባሎች ባሉበት አንድ ቤተሰብ የተሠሩና የዚያ ቤተሰብ ንብረት ሲሆኑ 7 ሜትር ርዝመትና ከወደላይ ሰፋ ብለው ከታች ሾጠጥ በማለት የ“V” ቅርጽ ያላቸው ባላሁ ተብለው የሚጠሩ የእንጨት ጀልባዎች ናቸው። የአገሪቱ ምስክሮች አዋጅ ነጋሪዎች ብለው በፍቅር ከሚጠሯቸው ጀልባዎች ሁለቱ ለአሥርተ ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በማርጀታቸው ሥራቸውን አቁመዋል። ቁጥር 3, 4 እና 5 ጀልባዎች በፖሜሩን፣ በማሀይካና በዴመራራ ወንዞች ላይ በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
በዴመራራ ወንዝ ላይ
በብሪታንያና በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች “ዴመራራ” የሚለው ቃል በዚህ ማጥና ደለላማ በሆነ ወንዝ ዳር ባለው የእርሻ ማሳ ውስጥ ከሚበቅለው የሸንኮራ አገዳ የሚገኘውን ቡናማ ቀለም ያለው ስኳር ያስታውሳቸዋል። ሸንኮራ የሚመረትበት ቦታ የሚያበቃው ከወንዙ በስተ ምዕራብ ባለው ዳርቻ ላይ በሚገኘው መንገድ ላይ ነው። ከዚያ መንገድ ባሻገር ለሚኖሩት የሂንዱዎች፣ እስላሞችና በስም ክርስቲያን ለሆኑት በወንዙ ዳርቻ ለሚኖሩ ሰዎች ስለ ይሖዋ መንግሥት የሚናገረውን አስደሳች መልዕክት ለመንገር ምስክሮቹ በመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ መርከቦች ይሄዳሉ።
በዴመራራ ወንዝ አካባቢ የሚደረጉ የስብከት ዘመቻዎች ለአንድ ቀን ወይም ለበርካታ ሳምንታት ከጠዋት አንስቶ ለዓይን እስኪይዝ ድረስ ከአንዱ የጀልባ ማቆሚያ ቦታ ወደ ሌላው መጓዝን የሚጠይቁ ሊሆኑ ይችላሉ። ማደር በሚያስፈልግባቸው ጉዞዎች አቅኚዎቹ በጀልባው ላይ ማብሰልና መብላት ብቻ ሳይሆን የሚተኙትም እዚያው ላይ ነበር። ሌሊት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ተብሎ የሚጠራው ጀልባ ማንግሮቭ ከሚባል ዛፍ ጋር አለዚያም ወደብ ላይ ያለ የመርከብ ማቆሚያ ከተገኘ ከእርሱ ጋር ይታሰራል። ሁለት ተኩል ሜትር ርዝመት ያላቸው ሁለት ጥርብ እንጨቶች ጎበጥ ተደርገው በጀልባው የፊተኛ ክፍል ላይ በጥብቅ ይታሰራሉ። ጣሪያ ወይም ከላይ የሚደረግ ሽፋን ለማበጀት ደግሞ በእነዚህ ከላይ ወደታች የሚወርዱ ቀጥ ያሉ እንጨቶች ላይ ገመድ ተወጥሮ ይዘረጋና ትልቅ ሸራ ይለብሳል። የእንጨት ሳንቃዎች እንደ አልጋ፣ ብርድ ልብስና አንሶላ ደግሞ እንደ ፍራሽ ሆነው ያገለግላሉ። ሁኔታው እንዲህ ቢሆንም ከረጅም የሥራ ቀን በኋላ በቀላሉ እንቅልፍ ይወስዳቸዋል።
“በዚህ የደፈረሰ ውኃ ውስጥ ገላችሁን ትታጠባላችሁ?” ተብለው አቅኚዎቹ ተጠየቁ።
መልሳቸው “ሌላ ምርጫ ካገኘን አንታጠብበትም!” የሚል ነበር። “ንጹሕ ውኃ ባለበት ጅረት አካባቢ ካለፍን ለምግብ፣ ለመጠጥና ለገላ መታጠቢያ እንዲሆነን የውኃ መያዣዎቻችንን እንሞላቸዋለን።”
ጽናታቸው ጥሩ ጥሩ ተሞክሮዎችን አስገኝቶላቸዋል። አንድ ጊዜ አንድ ሰው ወደ ወደቡ መጣና እግሮቹን አንፈራጦ በመቆም እጁን አገጩ ላይ አድርጎ በከፍተኛ ስሜት በመመሰጥ ይመለከተን ጀመር። በጀልባው ፊት ለፊት የተጻፈውን የጀልባውን ስም “የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር 5”! በማለት ድምፁን ከፍ አድርጎ አነበበ። “እናንተ የይሖዋ ምስክሮች መሆን አለባችሁ። ‘መንግሥት’ የሚለውን ቃል በዚህ መንገድ የምትጠቀሙበት እናንተ ብቻ ናችሁ። የመንግሥት አዳራሽ አላችሁ፤ አሁን ደግሞ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ የተባለ ጀልባ አገኛችሁ።”
ከጊልያድ ወደ ፖሜሩን
ፍሬድሪክ ማክአልማን በፖሜሩን ወንዝ ዳር መሥራት ትንሽ ለየት ያለ ባሕርይ እንደነበረው ያስታውሳል። በ1970 ከመጠበቂያ ግንብ የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ከተመረቀ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ከፖሜሩን ወንዝ ዳርቻ 34 ኪሎ ሜትሮች ገባ ብላ ወደምትገኘው ቻሪቲ የተባለች ወንዝ ያለባት የገጠር መንደር መጣ። በዚያች ከተማ የመንግሥቱ አስፋፊዎች የሆኑ አምስት ቡድኖች ይገኙባት ነበር።
ወንድም ማክአልማን ለጀልባችን “ባለ ስድስት ፈረስ ጉልበት ሞተር ከማግኘታችን በፊት ለአምስት ረጃጅም ዓመታት አዋጅ ነጋሪ 2 ን በፖሜሩን ወንዝ ላይና ታች የመቅዘፍን ‘ደስታ’ አግኝተናል” በማለት ይዘረዝራል። “ከማዕበል ጋር እየታገልን ከወንዙ መግቢያ 11 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ሃክኔይ እስከምንደርስ ድረስ በወንዙ ዳርቻ ላይ እንሰብክ ነበር። እዚያ ስንደርስ በዚያን ጊዜ በአካባቢው አዋላጅ ሆና ታገለግል በነበረችው በእህት ዴካምብራ ቤት ሌሊቱን በጥሩ እንቅልፍ እናሳልፈው ነበር። በማግሥቱ ጠዋት በማለዳ ተነስተን ወደ ምዕራባዊው የወንዙ ዳርቻ ከመሻገራችን በፊት ወደ ወንዙ መግቢያ እንሄዳለን። ከዚያም 34 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ወደ ቻሪቲ እንመለሳለን።”
አዲሱ ባለ ስድስት ፈረስ ጉልበት ሞተር ለአሥር ዓመታት በሚገባ አገለገላቸው። ከዚያም በ1986 ባለ 15 ፈረስ ጉልበት በሆነ አዲስ ሞተር ተተካ። ወንድም ማክአልማን በፓሜሩን ወንዝ ከ21 ዓመታት በላይ በታማኝነት ካገለገለ በኋላ በቻሪቲ ውስጥ አዲስ የሠራውን የመንግሥት አዳራሽ ግዴታውን እንዳከናወነ ያህል እየተሰማው ሊመለከተው ይችላል። በዚህ የመንግሥት አዳራሽ የሚጠቀሙት ካላይኛውና ከታችኛው ወንዝ የመጡ 43 አስፋፊዎች ናቸው። የተሰብሳቢዎች አማካይ ቁጥር ከ60 በላይ ሲሆን በ1992 የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ የተገኙ 190 ሰዎች ነበሩ!
“የመጠበቂያ ግንቡን ሰውዬ” መፈለግ
በቻሪቲ መንደር ሰኞ የገበያ ቀን ነው። የምሥራቹን ለመስበክ የሚያመች ጥሩ ጊዜና ቦታ ስለሆነ ምስክሮቹ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶችን ይዘው ይሄዳሉ። በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ አንድ ቀን በሞሩካ ከምትገኘው ከዋሪሙሪ የመጣች ሞኒካ ፊትዛለን የተባለች ሴት ወደ ገበያ መጥታ ሳለ ሁለት መጽሔቶችን ከወንድም ማክአልማን ተቀበለች። እቤቷ ሄዳ ግን ከልብስ ማስቀመጫዋ ሥር አስቀመጠቻቸው።
ሞኒካ “ለሁለት ዓመታት ሳላነባቸው እዚያው ተቀመጡ” ስትል ታስታውሳለች። “ከዚያም ታመምኩና ለጥቂት ጊዜ አልጋ ላይ ቆየሁ። እየተሻለኝ ሲሄድ ራሴን በሥራ ለማስያዝ ስል በቤት ውስጥ ያሉትን እያንዳንዱን የሚነበብ ጽሑፍ መመርመር ጀመርኩ። በመጨረሻ በልብስ ማስቀመጫዬ ውስጥ ያሉትን ሁለት መጽሔቶች አስታወስኳቸውና እነሱን መመርመር ጀመርኩ።” የእውነትን ድምፅ ወዲያውኑ ተገነዘበች።
ሞኒካ ሲሻላት እነዚያን መጽሔቶች የሰጣትን ሰው ለማግኘት ትችል ዘንድ ባለቤቷ ዮጅን በፖሜሩን ወንዝ አጠገብ ሥራ እንዲፈልግ ጠየቀችው። ዮጅን የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን አባል ቢሆንም በነገሩ ተስማማ። ሊያገኝ የቻለው ሥራ ግን በፖሜሩን ዳርቻ ባለ እርሻ ውስጥ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ እኩለ ቀን ድረስ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ሥራ ብቻ ነበር።
ቅዳሜ ዕለት እንኳን ሞኒካ መጽሔቶቹን የሰጣትን ሰው አላገኘችውም። ወደ እኩለ ቀን ላይ “የመጠበቂያ ግንቡን ሰውዬ” ለማግኘት ትችል ዘንድ ማዕበሉ ወደ ቻሪቲ ለመሄድ ያስችላቸው እንደሆነ ባለቤቷን ጠየቀችው። ልክ ይህንን እንደተናገረች በመንገዱ ላይ የሚራመድ ሰው ኮቴ ሰሙ። ከዚያም ፈገግ ብላ የምትመጣ አንዲት እህት ተመለከቱ። እህት ወደ እነርሱ የመጣችው አዲስ የወጡትን የመጽሔቶቹን ቅጂዎች ልታበረክትላቸው ነበር። ሞኒካ “ከመጠበቂያ ግንብ ሰዎች አንዷ ነሽ?” ስትል ጠየቀቻት። በጣም ብዙ ተጨማሪ ጥያቄዎች ስለጠየቀቻት ይህች እህት የሚያግዛት ሰው ለማግኘት ስትል ወደ ጀልባው ተመለሰች። እህትን ሊረዳ የመጣው ማን ይመስላችኋል? ከወንድም ማክአልማን ሌላ ማን ሊሆን ይችላል!
ደብዳቤ በመጻጻፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ ዝግጅት ተደረገ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሞኒካ ከቤተ ክርስቲያኑ መውጣቷን የሚገልጽ ደብዳቤ ለአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ላከች። ቄሱም በምላሹ “የይሖዋ ምስክሮችን አትስሚያቸው። መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት አልተረዱትም። መጥቼ ነገሩን እንወያይበታለን” የሚል ማስታወሻ ላኩላት። እስከ ዛሬ ድረስ ቄሱ ብቅም አላሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሞኒካ በ1975 ተጠመቀች። ወንድሞች አሁን አጎት ዮጅን ብለው በፍቅር የሚጠሩት ባለቤቷ ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥንቃቄ ከመረመረ በኋላ አንድ ዓመት ቆይቶ ተጠመቀ። (ሥራ 17:10, 11) ምንም እንኳ በቻሪቲ ከተማ ከሚገኘው ለእነርሱ ከሚቀርበው ጉባኤ በታንኳ የ12 ሰዓት ጉዞ በሚወስድ ርቀት ላይ የሚኖሩ ቢሆንም እስከዚህ ቀን ድረስ በንቃት የሚሠሩ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ናቸው።
ወደ መሐል አገር የተደረጉ ሚስዮናዊ ጉዞዎች
በቅርብ ዓመታት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ወደ አገሪቱ መሐል ዘልቀው በመግባት የሚደረጉ መደበኛ የሚስዮናዊ ዘመቻዎችን እያስተዋወቀ ነው። በባለ ሞተር ጀልባዎች በመጠቀም ፈቃደኛ የሆኑ ወንድሞች ራቅ ባሉ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የወንዝ ዳርቻዎች ባለው በአሜሪዲያን ክልል ውስጥ ለሚኖሩ ዛፎችን እየመነጠሩ ለሚያርሱ ማኅበረሰቦች የምሥራቹን መውሰድ የሚያስገኘውን አስደሳች ተሞክሮ ቀምሰዋል። አቅኚ የሚለውን ቃል በትክክል የሚተገብሩ አቅኚዎች በነዚህ ሩቅ ሥፍራዎች ለሚገኙ ነዋሪዎች ሕይወት አድን የሆነውን “የይሖዋን ስም” ለመጀመሪያ ጊዜ የማስተዋወቅ መብት አግኝተዋል። (ሮሜ 10:13–15) እነዚያ ወንድሞች ብዙ ችግሮችን ችለው ማሳለፍ ነበረባቸው። ወደ አንዳንዶቹ አካባቢዎች ለመድረስ አንዳንድ ጊዜ ለሦስት ቀናት ሙሉ በውኃ ላይ መቆየት ይኖርባቸው ነበር። ይሁን እንጂ የሚገኙት ውጤቶች ይህ ዓይነቱ ልፋት ሊደረግላቸው የሚገባቸው ናቸው።
በሐምሌ 1991 ወደ አካባቢው በተደረገ የመጀመሪያ ሚስዮናዊ ጉዞ ላይ ወንድሞች ዛፎችን በመቁረጥ የሚተዳደሩ ሰዎች ባሉበት በዋይኒ ወንዝ ዳርቻ ግዌባና በሚባል መንደር አቅራቢያ የሚኖር የጰንጠቆስጤ እምነት ተከታይ የሆነ አንድ ወጣት አገኙ። በጥቅምት በተደረገው ቀጣይ ጉብኝት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረለት። በራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ፣ ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ አለመሆኑንና የሥላሴ መሠረተ ትምህርትም ቅዱስ ጽሑፋዊ አለመሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ተመለከተ። (መዝሙር 83:18፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3) በተማረው ነገር በጣም ከመደሰቱ የተነሳ ወንድሞች ከሄዱ በኋላ የጰንጠቆስጤ አማኞች የሆኑ መሰሎቹን አንድ ላይ ሰብስቦ ከራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገልጸውን እውነት ያሳያቸው ጀመር። አብዛኞቹ በእውነት ላይ ጀርባቸውን ቢያዞሩም እርሱ ግን ያንን ሃይማኖት በመተው “ከታላቂቱ ባቢሎን” የሚወጣበት ጊዜው አሁን እንደሆነ ወሰነ። (ራእይ 18:2, 4) በየካቲት 1992 ወንድሞች ሊጎበኙት ተመልሰው ሲመጡ የሆነውን ነገር ነገራቸው፤ ጨምሮም “የእናንተ አባል ለመሆን እፈልጋለሁ። ከይሖዋ ምስክሮች አንዱ ለመሆን እፈልጋለሁ። እውነትን ለሰዎች ለማስተማር እፈልጋለሁ!” አላቸው።
እንዲህ ያሉ ተሞክሮዎች ወንድሞች በዚህ ፈታኝ ሥራ ለመቀጠል እንዲችሉ ረድተዋቸዋል። በሚስዮናዊነት ጉዞው የሚሰማሩ ወንድሞች በቤት ውስጥ የመኖርን ምቾት መሥዋዕት ያደርጋሉ፣ እንደ ወባ ላሉ በሽታዎች ይጋለጣሉ፤ እንዲሁም ጫካ ውስጥ መኖር ሊያመጣባቸው የሚችለውን አደጋ መቻል ይኖርባቸዋል። እቤት ያሉትም ቢሆኑ መሥዋዕት ይከፍላሉ። ቤተሰቦች የሚወዷቸውን ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ለሣምንታት ጭምር አያገኟቸውም። በአንዳንድ አጋጣሚዎች ጉባኤዎች ያለ ሽማግሌዎችና ሌሎች ወጣቶች ይቆያሉ። አንድ ጊዜ ለጉባኤው በሚያስፈልጉት ነገሮች እርዳታ የሚያደርግ አንድ ወንድም ብቻ ቀርቶ ነበር። ሆኖም እነዚህ ወንድሞች ከጉዟቸው ሲመለሱ ጉባኤዎች በጣም የሚያነቃቁ ተሞክሮዎችን በመስማት ምን ያህል ደስታና ማበረታቻ ያገኛሉ! ከሚያገኙት ደስታ ጋር ሲወዳደር እነሱን በማጣት የሚከፍሉት መሥዋዕት ከምንም የሚገባ አይደለም።
ምሥራቹን ይዘው በጉያና ውኃዎች ላይ የሚመላለሱ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በእውነትም ልዩ የሆነ ተሞክሮ በማግኘት ይደሰታሉ። በዓለም ዙሪያ ከሚገኙት የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን “ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ” በድፍረትና በፈቃደኝነት ያቀርባሉ። — ዕብራውያን 13:15
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በፊት የብሪቲሽ ጉያና ትባል ነበር። ጉያና በመባል ስሟ የተለወጠው በ1966 ከብሪታንያ ነጻ ከወጣች በኋላ ነው።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሆንዱራስ
ኒካራጓ
ኮስታ ሪካ
ፓናማ
ኮሎምቢያ
ቬንዙዌላ
ጉያና
ሱሪናም
የፈረንሳይ ጉያና
ብራዚል
ቦሊቪያ
አትላንቲክ ውቅያኖስ
[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስተግራ:- በገበያ ቀን ለሰዎች መመስከር
ከላይ:- በዴመራራ ወንዝ አካባቢ ምሥራቹን ሲናገሩ
ከላይ በስተቀኝ:- ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ እየቀዘፈ የሚሄድ የሚስዮናውያን ቡድን