የዘላለም ሥቃይ አእምሮን የሚረብሽ መሠረተ ትምህርት የሆነው ለምንድን ነው?
“ሰባኪያችሁን እንዳባረራችሁ ሰምቼአለሁ። ምን አድርጎ ነው?”
“ሁልጊዜ ሁላችሁም ወደ ሲኦል መሄዳችሁ ነው ይለናል።”
“አዲሱስ ሰባኪ ምን ይላል?”
“አዲሱም ሰባኪ ወደ ሲኦል ትሄዳላችሁ ይላል።”
“ታዲያ ልዩነቱ ምንድን ነው?”
“ልዩነቱማ የፊተኛው ሰባኪ ሲናገር ወደ ሲኦል የምንሄድ በመሆናችን ደስ ያለው ይመስል ነበር። አዲሱ ሰውዬ ግን ሲናገር በጣም ያዘነ ይመስላል።”
ይህ ሥዕላዊ መግለጫ ባለው አንድ መጽሐፍ ውስጥ የቀረበው ጭውውት ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎችም ሆኑ ቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች በሲኦል መሠረተ ትምህርት እንደማይደሰቱ ያመለክታል። ሰፋ አድርገን ስንመለከተው ደግሞ ክላርክ ኤች ፒኖክ የተባሉ ካናዳዊ የሃይማኖት ሊቅ የተናገሩትን ያረጋግጣል። “ባለፉት መቶ ዘመናት የሰውን ልጅ ሕሊና ከበጠበጡት ሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርቶች በሙሉ ሲኦል ሥጋም ሆነ ነፍስ እየተሰማቸው የዘላለም ሥቃይና ቅጣት የሚቀበሉበት ቦታ ነው እንደሚለው ያለ የሰውን ልጅ የበጠበጠ መሠረተ ትምህርት የለም።”
በሥነ ምግባር በኩል የሚነኩ ነገሮች
ታዲያ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ በሚታየው የኢንፌርኖ ሥዕል ብዙዎች የሚረበሹት ለምንድን ነው? (ሣጥኑን በገጽ 5 ተመልከት) ፕሮፌሰር ፒኖክ እንዲህ በማለት ይገልጻሉ:- “ስሜት ያለው አንድ ፍጡር ፍጻሜ ለሌለው ዘመን የአካልና የአእምሮ ሥቃይ እንዲቀበል ይደረጋል ብሎ ማሰብ አእምሮን ይረብሻል። ይህ ዓይነቱ ሥቃይ የሚደርሰው በመለኮታዊ ትዕዛዝ መሆኑን ማሰቡ ደግሞ ስለ አምላክ ፍቅር ያለኝን እምነት ይጻረርብኛል።”
አዎ፣ የዘላለም ሥቃይ ትምህርት የሥነ ምግባር ጥያቄ ያስነሳል። ለምሳሌ ያህል ቅን ልብ ያላቸው ክርስቲያኖች የሮማ ካቶሊክ የሃይማኖት ሊቅ የሆኑት ሀንስ ኩንግ ስላነሱት ጥያቄ አጥብቀው ያስባሉ። “የፍቅር አምላክ የሆነው ፈጣሪ . . . ፍጥረቶቹ በዚህ ዓይነት ፍጻሜ ለሌለው ዘመን፣ አለምንም ተስፋ፣ አለምንም ሐዘኔታ፣ ፍቅር በጎደለው ሁኔታ በአካልና በአእምሮ ሲሠቃዩ ዝም ብሎ ይመለከታልን? እርሱ ይህን የመሰለ ጨካኝ ልብ ያለው አበዳሪ ነውን? . . . የማያባራና ከመጠን ያለፈ የበቀል ጥማት ስላለው ሰው ምን ይሰማናል?”a በእርግጥም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ጠላቶቻችንን መውደድ አንደሚገባን የሚናገር አምላክ እንዴት የጠላቶቹን ለዘላለም ያሠቃያል? (1 ዮሐንስ 4:8–10) አንዳንድ ሰዎች የሲኦል ትምህርት ከአምላክ ባሕርይ ጋር አይጣጣምም ከሥነ ምግባር አንጻር ሲታይም የማይመስል ነው ብለው መደምደማቸው አያስደንቅም።
ሌሎች ብዙ አማኞች ደግሞ እንደነዚህ ካሉት አእምሮን የሚረብሹ ጥያቄዎች በመሸሽ ሕሊናቸውን ዝም ለማሰኘት ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ እነዚህን ጥያቄዎች ችላ ብሎ ማለፍ ስለዚህ ጉዳይ የሚነሳውን ግራ መጋባት ሊያስወግድ አይችልም። ስለዚህ ይህን ጥያቄ ፊትለፊት መጋፈጥ ይኖርብናል። ይህ መሠረተ ትምህርት የሚነካካቸው ስነ ምግባርን የሚመለከቱ ነገሮች ምንድን ናቸው? ፕሮፌሰር ፒኖክ ክሪስዌል ቲኦሎጂካል ሪቪው በተባለው መጽሔት ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የዘላለም ሥቃይ አምላክን እንዲሞቱ እንኳን ለማይፈቅድላቸው ተቀጪዎች ዘላለማዊ ኦሽዊትዝ (የናዚዎች የማጎሪያ ካምፕ) ያዘጋጀ ደም የተጠማ አውሬ ስለሚያደርገው በሥነ ምግባር አንጻር ሲታይ ተቀባይነት ሊያገኝ አይችልም። ጥቂት የሰብዓዊ ርህራሄ ባሕርይ ያለው ሰው እንኳን እንዴት እንዲህ ያለውን [የሲኦል መሠረተ ትምህርት] በእርጋታ ሊያሰላስል ይችላል? . . . ክርስቲያኖች አምላክ ይህን ያህል ጨካኝና ተበቃይ ይሆናል ብለው እንዴት ሊያስቡ ይችላሉ?”
ይህ መሠረተ ትምህርት በሰው ልጅ ባሕርይ ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ ሊያስከትል እንደሚችል ፒኖክ ሲያመለክቱ እንዲህ ብለዋል:- “እንዲያውም ጠላቶቹን በሚያሠቃይ አምላክ የሚያምኑ ሰዎች ምን የጭካኔ ተግባር ፈጽመዋል? በማለት እደነቃለሁ።” በመጨረሻም ሲደመድሙ “ታዲያ ይህ መታረም የሚያስፈልገው አእምሮን የሚረብሽ ጽንሰ ሐሳብ አይደለምን?” ብለዋል። አዎ፣ አምላክ እንዲህ ያለ የጭካኔ ባሕርይ አለው ከተባለ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ስለ ሲኦል እሳት መመራመር መጀመራቸው አያስደንቅም። ታዲያ ምን ተገንዝበዋል? የዘላለም ሥቃይን ጽንሰ ሐሳብ የሚጻረር ሌላ ችግር አስተውለዋል።
ሲኦልና ፍትሕ
ስለተለመደው የሲኦል መሠረተ ትምህርት የሚያስቡ ብዙ ሰዎች ይህ መሠረተ ትምህርት አምላክን ፍትሕ እንደሌለው አድርጎ ስለሚያሳይ ከተፈጥሮው የፍትሕ ባሕርያቸው ጋር ይጻረርባቸዋል። በምን መንገድ?
አንደኛውን መንገድ የዘላለም ሥቃይን መሠረተ ትምህርት አምላክ ራሱ ከሰጠው አንድ የፍትሕ ሥርዓት ጋር በማወዳደር መረዳት ይቻላል። “ዓይን በዓይን፣ ጥርስ በጥርስ።” (ዘጸአት 21:24) ይህ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን የተሰጠው ከጥፋቱ ጋር የሚተካከል ቅጣት ይሰጥ የሚል ሕግ በሲኦል እሳት መሠረተ ትምህርት ላይ ይሥራ ቢባልስ? ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል? የዘላለም ሥቃይ ሊቀበሉ የሚገባቸው ዘላለማዊ ቅጣት ያደረሱ ሰዎች ብቻ ናቸው። በዚህ ሕግ መሠረት ዘላለማዊ ቅጣት ለዘላለማዊ ቅጣት ነውና። ይሁን እንጂ ሰዎች ምን ያህል ክፉ ቢሆኑ ሊያደርሱ የሚችሉት ሥቃይ የጊዜ ገደብ ያለው በመሆኑ የዘላለም ቅጣት ቢፈረድባቸው ወንጀላቸውና የተወሰነባቸው የሲኦል እሳት ዘላለማዊ ቅጣት ተመጣጣኝ አይሆንም።
በቀላል አነጋገር ፍርዱ ከመጠን በላይ ከባድ ይሆናል። “ዓይን በዓይን ጥርስ በጥርስ” የሚለውን መሠረታዊ ሕግ የሚተላለፍ ይሆናል። የኢየሱስ ትምህርት አጸፋ መመለስን ወይም መበቀልን ስላሻሻለው የዘላለም ሥቃይ ፍትሐዊ ነው ብሎ ማሰብ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች አዳጋች እንደሚሆን ትስማማ ይሆናል። — ማቴዎስ 5:38, 39፤ ሮሜ 12:17
የመሠረተ ትምህርቱን ትክክለኛነት ለማስረዳት የሚደረግ ሙከራ
ይሁን እንጂ ብዙ አማኞች መሠረተ ትምህርቱ ትክክለኛ መሆኑን ለማሳመን ዛሬም ይሞክራሉ። እንዴት? ክሊቭ ኤስ ሉዊስ የተባሉት እንግሊዛዊ ደራሲ ዘ ፕሮብሌም ኦቭ ፔይን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ የአብዛኞቹን የሲኦል እሳት መሠረተ ትምህርት ደጋፊዎች ሐሳብ ገልጸዋል። “ሥልጣን ቢኖረኝ ኖሮ ከክርስትና ለማስወጣት ፈቃደኛ የምሆንበት የዚህን መሠረተ ትምህርት ያህል ሌላ ትምህርት የለም። ነገር ግን የቅዱሳን ጽሑፎችና ከሁሉ በላይ ደግሞ የጌታችን ቃል ድጋፍ አለው።” በዚህ መንገድ የዘላለም ሥቃይ መሠረተ ትምህርት ደጋፊዎች ትምህርቱ አሰቃቂ መሆኑን ባይክዱም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ትምህርት ስለሆነ የግዴታ መቀበል እንደሚያስፈልግ ይሰማቸዋል። የሃይማኖት ሊቅ የሆኑት ፒኖክ እንዲህ ብለዋል:- “የትምህርቱን አስከፊነት በመቀበል ለመጽሐፍ ቅዱስ የማያወላውል ታማኝነት እንዳላቸውና መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያስተምረው ብቻ እንዲህ ያለውን አሰቃቂ እውነት ማመናቸው ትልቅ ጀግንነት እንደሆነ ለማረጋገጥ ተስፋ ያደርጋሉ። በሲኦል መሠረተ ትምህርት አለማመኑ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛነት እንደሚፈታተን ነገር አድርገው ያቀርባሉ። ይሁን እንጂ በእርግጥ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኝነት ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ነውን?”
አንተም ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለህ ታማኝነትና ጥብቅ አቋም ይህን መሠረተ ትምህርት ከማመን የተለየ አማራጭ እንደማይሰጥህ እንድታምን ያደርግህ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሲኦል ምን ይናገራል?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a Eternal Life?—Life After Death as a Medical, Philosophical, and theological Problem, page 136.
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሦስት ተመሳሳይ ሥዕሎች
የዌስትሚኒስተር ኮንፌሽን ኦቭ ፌይዝ የተባለው ብዙዎች የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት የተቀበሉት የእምነት ቀኖና ወደ ሰማይ የማይሄዱት ያልተመረጡ ሰዎች “ወደ ዘላለም ሥቃይ ተጥለው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ” ይላል። ዘ ኢንሳይክሎፒድያ ኦቭ ሪሊጅን ደግሞ “በሮማ ካቶሊክ ክርስትና ሲኦል የእሳት ቃጠሎና ሌላ ዓይነት ሥቃይ ያለበት ፍጻሜ የሌለው ቅጣት የሚሰጥበት ሁኔታ እንደሆነ ይታሰባል” ይላል። ይህ ኢንሳይክሎፒድያ በመጨመር “የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ክርስትናም ሲኦል ለተኮነኑ ሰዎች የተጠበቀ የዘላለም እሳትና ቅጣት ዕጣ እንደሆነ ያምናል” ይላል። — ጥራዝ 6 ገጽ 238–9