የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎችን ያሳፈረው ጠፍቶ የነበረው መንግሥት
“ቀደም ባሉት ጊዜያት የአሦር መንግሥት ታሪክ በዓለም ዜና ታሪክ ውስጥ በጣም ከደበዘዙት ምዕራፎች ውስጥ አንዱ ነበር።” “ስለ ጥንቷ ነነዌ የሚታወቅ ነገር ቢኖር በየቦታው ተበታትነው በሚገኙ ስለጉዳዩ በተዘዋዋሪ በሚገልጹ ጽሑፎችና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቀጥተኛ ባልሆነ ሁኔታ በተጠቀሱ ትንቢቶች እንዲሁም በአጋጣሚ በተገኙ በዲዮዶረስ ሲኩለስ በተጻፉ ያልተሟሉ የአሦር ታሪክ ማስታወሻዎችና በሌሎችም ነው።” — ሳይክሎፔዲያ ቢብሊካ ሊትሬቸር ጥራዝ 1 እና 3 1862
የግሪክ ታሪክ ጸሐፊ የሆነው ዲዮዶረስ ሲኩለስ ይኖር የነበረው ከ2000 ዓመታት በፊት ነበር። ዲዮዶረስ የጠቀሳት ነነዌ አራት ማእዘን የሆነች ከተማ ነበረች። የአራቱም ጎኖቿ ጠቅላላ ርዝመት 480 ስታዲያ ነው። ይህም ማለት ጠቅላላ ዙሪያዋ 96 ኪሎ ሜትር ነው! መጽሐፍ ቅዱስም ነነዌ “የሦስት ቀን መንገድ ያህል እጅግ ታላቅ ከተማ” እንደሆነች በመጥቀስ ተመሳሳይ መግለጫ ይሰጣል። — ዮናስ 3:3
የ19ኛው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ግን አንዲት የማትታወቅ በጥንቱ ዓለም የነበረች ከተማ ይህን ያህል ሰፊ ልትሆን ትችላለች ብለው ለማመን አሻፈረኝ ብለው ነበር። በተጨማሪም እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ነነዌ በዚያን ጊዜ የነበረች ከሆነ ከባቢሎን በፊት የነበረው ስልጣኔ ክፍል መሆን አለባት ብለው ነበር።
እንዲህ ዓይነቱ አስተያየት የኖኅ የልጅ ልጅ የነበረው ናምሩድ በባቤል ወይም በባቢሎን አካባቢ የመጀመሪያውን የፖለቲካ ግዛት እንዳቋቋመ ከሚገልጸው ከዘፍጥረት ምዕራፍ 10 ጋር ይቃረናል። መጽሐፍ ቅዱስ በመቀጠል “ከዚያም ወደ አሦር ሄደና ነነዌን፣ ረሖቦት፣ ካላሕ፣ እንዲሁም በነነዌና በካላሕ መካከል ያለውን ታላቅ ከተማ ሬሴን የተባሉትን ከተሞች መሠረተ” ይላል። (ዘፍጥረት 10:10–12 የ1980 ትርጉም) ቅዱስ ጽሑፉ አራቱን አዲስ የአሦር ከተሞች እንደ አንድ “ታላቅ ከተማ” አድርጎ እንደሚገልጻቸው ልብ በል።
በ1843 በቁፋሮ የጥንት ታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ፈረንሳዊው ፖል ኤሚል ቦታ የአንዲት የአሦር ከተማ ክፍል የሆነ የአንድ ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ አግኝተው ነበር። ይህን ግኝት የሚገልጸው ዜና ለሕዝብ በይፋ በተገለጠበት ጊዜ ታላቅ መገረምን አስከተለ። አለን ሚላርድ ትሬዠርስ ፍሮም ባይብል ታይምስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “ይህ ቤተ መንግሥት በኢሳይያስ 20:1 ላይ የተጠቀሰው የአሦር ንጉሥ የሳርጎን መሆኑ በተረጋገጠበት ጊዜ የሕዝቡ ደስታ በጣም ከፍ ብሎ ነበር። ምክንያቱም የሳርጎን መኖር አጠራጣሪ የሆነ ጉዳይ ነበር” በማለት ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌላው በቁፋሮ የጥንት ታሪክ ተመራማሪ የሆኑት አውስቲን ሄነሪ ሌያርድ ከኮርሳባድ ደቡባዊ ምዕራብ 42 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ በሚገኝ ኒምሩድ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ላይ ያለውን ፍርስራሽ መቆፈር ጀመሩ። ፍርስራሹም በዘፍጥረት 10:11 ላይ ተጠቅሰው ከነበሩት አራት ከተሞች ውስጥ የአንዱ የካለህ መሆኑ ተረጋገጠ። ከዚያም ሌያርድ በ1849 በካለህና በኮርሳባድ መካከል ኩዩንጂክ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ላይ የሚገኝ የአንድ ትልቅ ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ ቆፍረው አወጡ። ቤተ መንግሥቱ የነነዌ ክፍል እንደነበረ ተረጋገጠ። በኮርሳባድና በካለህ መካከል ካራምለስ ተብሎ የሚጠራውን ጉብታ ጨምሮ የሌሎች መንደሮች ፍርስራሾችም ይገኛሉ። “የኒምሩድን [ካለህን] የኩዩንጂክን [ነነዌን]፣ የኮርሳባድን እንዲሁም የካራምለስን አራት ትልልቅ ጉብታዎች የከተማይቱ አራት ጎን ማዕዘኖች አድርገን ከወሰድን የከተማዋ ስፋት የመልከዓ ምድር አጥኚው ካስቀመጠው 480 ስታዲያ ወይም 96 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዲሁም ከነቢዩ [ዮናስ] የሦስት ቀን መንገድ ጋር በትክክል የሚስማማ ሆኖ እናገኘዋለን።”
እንግዲያው ዮናስ እነዚህን መንደሮች በዘፍጥረት 10:11 ላይ ነነዌ በመባል መጀመሪያ በተመዘገበችው ከተማ ስም “ታላቅ ከተማ” ብሎ በመጥራት በአንድ ላይ እንዳጠቃለላቸው ግልጽ ነው። በዘመናችንም ተመሳሳይ ነገር ይደረጋል። ለምሳሌ ያህል መጀመሪያ በነበረችው ለንደንና አሁን በዳር ባሉት ከተማዎች መካከል ልዩነት አለ። እንዲያውም እነዚህ ከተማዎች በመኖራቸው አንዳንድ ጊዜ “ታላቋ ለንደን” ተብላ እንድትጠራ አድርገዋታል።
እብሪተኛ የአሦር ንጉሥ
በነነዌ የነበረው ቤተ መንግሥት ከ70 በላይ ክፍሎችን የያዘ ሦስት ኪሎ ሜትር ያህል ርዝመት ያላቸው ግድግዳዎች ነበሩት። በእነዚህ ግድግዳዎች ላይ ወታደራዊ ድሎችንና ሌሎች ትልልቅ ክንውኖች ሲከበሩ የሚያሳዩ የተቃጠሉ የቅርጻ ቅርጽ ፍርስራሾች አሉ። አብዛኞቹ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። ይሁን እንጂ ሌያርድ ከዚያ አካባቢ ሊሄዱ ሲሉ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተጠብቆ የቆየ አንድ የእንግዳ መቀበያ ክፍል ፍርስራሽ አገኙ። በግድግዳዎቹም ላይ የአንዲትን የተመሸገች ከተማ መማረክ የሚያሳዩ ሥዕሎች ነበሩ። ከከተማዋ ውጭ በዙፋን ላይ ተቀምጦ በነበረው ወራሪ ንጉሥ ፊት ምርኮኞች በሰልፍ ሲያልፉ የሚያሳዩ ናቸው። ከንጉሡ በላይ አንድ ጽሑፍ አለ። የአሦር ጽሕፈት አዋቂዎች “የዓለም ንጉሥ፣ የአሦር ንጉስ የሆነው ሰናክሬብ በኒመዱ ዙፋን ላይ ተቀምጦ የለኪሶ ምርኮ በፊቱ በሰልፍ ሲያልፍ” በማለት ይተረጉሙታል።
ዛሬ ይህን ሥዕልና ጽሕፈት በብሪትሽ ሙዚየም ውስጥ ማየት ይቻላል። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በ2 ነገሥት 18:13, 14 ላይ ከተመዘገበው ታሪካዊ ሁኔታ ጋር ይስማማል። እንዲህ ይላል:- “በንጉሡም በሕዝቅያስ በአሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ይሁዳ ወደ ተመሸጉት ከተሞች ሁሉ ወጣ፣ ወሰዳቸውም። የይሁዳም ንጉሥ ሕዝቅያስ:- በድያለሁ፣ ከእኔ ተመለስ፤ የምትጭንብኝን ሁሉ እሸከማለሁ ብሎ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ለኪሶ ላከ። የአሦርም ንጉሥ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ላይ ሦስት መቶ መክሊት ብርና ሠላሳ መክሊት ወርቅ ጫነበት።”
ሰናክሬም ይሁዳን ስለ መውረሩና ሕዝቅያስ ስለከፈለው ግብር ተጨማሪ ዝርዝር መግለጫዎችን የሚሰጡ ሌሎች ጽሑፎች በነነዌ ፍርስራሾች መካከል ተገኝተዋል። ሌያርድ “ተመዝግበው ከሚገኙት በጣም አስደናቂ ታሪካዊ ማስረጃዎች አንዱ ከሕዝቅያስ የተወሰደው የሠላሳ መክሊት ወርቅ ብዛት በሁለት ፍጹም የተለያዩ ታሪኮች ላይ ይስማማል” ሲሉ ጽፈዋል። በአሦር ቋንቋ የተጻፈውን በመተርጎም የረዱት ሰር ሄንሪ ሮውልሰን እነዚህ ጽሑፎች “የሰናክሬምን ታሪካዊ ማንነት በማያሻማ ሁኔታ በግልጽ አስቀምጠውታል” በማለት ተናግረዋል። ከዚህም በላይ ሌያርድ ኒነቫህ ኤንድ ባቢለን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጠይቀዋል:- “ነነዌ የነበረችበትን ቦታ የሚያመለክቱት ከመሬት በታች የሚገኙ የፍርስራሽ ክምሮችና ጥራጊዎች ከመገኘታቸው በፊት በሕዝቅያስና በሰናክሬም መካከል ስለተደረገው ጦርነት የሚገልጽ ታሪክ ተገኝቶ ነበር፣ የተጻፉትም ሰናክሬም ራሱ ጦርነቱን ባስነሳበት በዚያው ጊዜ ነበር፣ በጥቃቅን ዝርዝር ሁኔታዎች እንኳን የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ እውነተኛነት ያረጋግጣሉ፤ ይህ ሊሆን ይችላል ብሎ ያመነ ማነው?”
እርግጥ አንዳንዶቹ የሰናክሬም ታሪክ ዝርዝር መግለጫዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አይስማሙም። ለምሳሌ ያህል በቁፋሮ የጥንት ታሪክ ተመራማሪ የሆኑት አለን ሚላርድ እንደሚከተለው በማለት ያስገነዝባሉ:- “በጣም አስገራሚ የሆነው ሐቅ [በሰናክሬም ታሪክ] መጨረሻ ላይ ይገኛል። ሕዝቅያስ ‘በኋላ በነነዌ’ ወደነበረው ወደ ሰናክሬም መልእክተኞቹንና ግብሩን ላከ። የአሦር ሠራዊት እንደተለመደው ድል ተጎናጽፎ ወደ አገሩ ይዟቸው አልተመለሰም።” መጽሐፍ ቅዱስ ወርቁና ብሩ የተከፈለው የአሦር ንጉሥ ወደ ነነዌ ከመመለሱ በፊት እንደሆነ ይገልጻል። (2 ነገሥት 18:15–17) ይህ ልዩነት የተፈጠረው ለምንድን ነው? ሰናክሬም የተመሸገችውን የይሁዳን ከተማ ለኪሶን ድል ባደረገበት ጊዜ በጉራ እንደተናገረው የይሁዳን ዋና ከተማ ኢየሩሳሌምን ድል ማድረጉን በጉራ ለመናገር ያልቻለው ለምንድን ነው? ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መልሱን ይሰጡናል። ከእነሱም መካከል የዓይን ምስክር የነበረው አንዱ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የእግዚአብሔርም መልአክ ወጣ፣ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፣ እነሆ፣ ሁሉ በድኖች ነበሩ። የአሦርም ንጉሥ ሰናክሬም ተነሥቶ ሄደ፣ ተመልሶም በነነዌ ተቀመጠ።” — ኢሳይያስ 37:36, 37፤ 2 ነገሥት 19:35፤ 2 ዜና መዋዕል 32:21
ሚላርድ ትሬዠርስ ፍሮም ባይብል ታይምስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ አጠቃለዋል:- “ይህን መግለጫ የምንጠራጠርበት በቂ ምክንያት የለንም። . . . ሰናክሬም እሱን የሚተኩት ነገሥታት እንዳያነቡት ሲል ይህ ታሪክ እንዳይጻፍ እንዳደረገ መረዳት ይቻላል፤ ምክንያቱም ስሙን ያጎድፍበታል።” ከዚህ ይልቅ ሰናክሬም በይሁዳ ላይ ያደረገው ወረራ እንደተሳካለት እንዲሁም ሕዝቅያስ ግብሩን ወደ ነነዌ በመላክ ተገዢ ሆኖ መቀጠሉን ለማሳመን ሞክሯል።
የአሦር አመጣጥ ተረጋገጠ
በተጨማሪም በነነዌ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በሸክላ ላይ የተጻፉ ጽሑፎችን የያዙ ቤተ መጻሕፍት ተገኝተዋል። ዘፍጥረት 10:11 እንዳመለከተው ሁሉ የአሦር መንግሥት መነሻውን ያደረገው በደቡብ በባቢሎን እንደነበረ እነዚህ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። በቁፋሮ የጥንት ታሪክ ተመራማሪዎች እነዚህን መረጃዎች በመከተል ጥረታቸው ሁሉ በደቡብ በኩል እንዲያተኩር አደረጉ። ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ ቢብሊካ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “አሦራውያን የነበሯቸው ቅርሶች መገኘታቸው ከባቢሎናውያን የመጡ መሆናቸውን አጋልጠውባቸዋል። ቋንቋቸውና የአጻጻፍ ስልታቸው፣ ስነ ጽሑፋቸው፣ ሃይማኖታቸው እንዲሁም ሳይንሳቸው በደቡብ ከነበሩት ጎረቤቶቻቸው የተወሰዱ ቢሆኑም ትንሽ ማሻሻያ የተደረገባቸው ነበሩ።”
ከላይ እንደተገለጹት ያሉ ግኝቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች አስተያየታቸውን ለስለስ እንዲያደርጉ አስገድደዋቸዋል። በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስን በቅንነት መመርመር መጽሐፍ ቅዱስ ጠንቃቃና ታማኝ በሆኑ ሰዎች እንደተጻፈ ያሳያል። የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞው የመሀል ዳኛ የነበሩት ሳልሞን ፒ ቼዝ መጽሐፍ ቅዱስን ከመረመሩ በኋላ እንዲህ ብለዋል:- “ረጅም፣ ከባድና ጥልቀት ያለው ጥናት ነበር፤ ሥራዬን ሥሠራ ጉዳዮችን ዘወትር በማስረጃ ካረጋገጥሁ በኋላ ወደ ውሳኔ እንደምደርስ ሁሉ በዚህ ሃይማኖታዊ ጉዳይ ላይም መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የመጣና ከሰብአዊ ችሎታ በላይ የሆነ መጽሐፍ ነው ወደሚል መደምደሚያ ደርሻለሁ።” — ዘ ቡክ ኦቭ ቡክስ:- አን ኢንትሮዳክሽን
እርግጥ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ የሆነ ታ ሪክ የያዘ መጽሐፍ ብቻ አይደለም። ለሰው ዘር ጥቅ ም ሲባል የተሰጠ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) መጽሐፍ ቅዱስ የ ሚጠቅሰውን መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ በመመር መር እውነተኛነቱን ማረጋገ ጥ ይቻላል። ይህም በሚቀጥ ለው እትም ላይ ይብራራል።
[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከላይ:- ከግድግዳው ፍርስራሾች የተገኙ ሦስት ዝርዝር ሁኔታዎች
ከታች:- የለኪሶ ከተማ መያዟን የሚያሳይ አሦራውያን የሳሉት በግድግዳ ፍርስራሽ ላይ የሚገኝ ሥዕል
[ምንጭ]
(Courtesy of The British Museum)
(From The Bible in British Museym, published by British Museum Press)
[ምንጭ]
Courtesy of the Trustees of The Biritish Museum