ሊያመልጥዎ የማይገባው ለምንድን ነው?
በመጭው የክረምት ወራት በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች በሚካሄደው “መለኮታዊ ትምህርት” በተባለው የወረዳ ስብሰባ ላይ መንፈሳዊ ትምህርቶች የሚተላለፉባቸው አራት አስደሳች ቀኖች ከፊትዎ ይጠብቁዎታል። እነዚህ ስብሰባዎች በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ እንኳ በሰኔ፣ በሐምሌና ነሐሴ ውስጥ ከ150 በላይ በሆኑ ቦታዎች ይደረጋሉ። በአብዛኛው ፕሮግራሙ የሚጀምረው ሐሙስ በ7:20 ላይ ሲሆን የሚደመደመው ደግሞ እሁድ በ10:15 ላይ ይሆናል። በዚህ አስደሳች አጋጣሚ በአንዳንድ ስብሰባዎች ላይ ጎላ ብሎ የሚታየው ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ዝግጅት የተደረገላቸው ሚስዮናውያን የሚያቀርቡት አስደሳች ሪፖርት ነው።
በዕድሜ የገፉም ሆኑ ወጣት፣ ባል፣ ሚስት፣ አባት፣ እናት ወይም በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ፣ ግልጽና ቀስቃሽ በሆነ መንገድ ጠቃሚ የሆነ ትምህርት ያገኛሉ። ለምሣሌ በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የመኖር ትርጉሙ ምንድን ነው? በማለት ይጠይቃሉ። ዓርብ ዕለት ጠዋት ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥና ሌሎች ለጥያቄው መልስ እንዲያገኙ እንዴት መርዳት እንደምትችል ማብራሪያውን መስማቱ ያስደስትዎታል።
ዓርብ ከምሳ በኋላ “ጋብቻን ዘላቂ አንድነት ማድረግ፣” “ቤተሰባችሁ ይድን ዘንድ ጠንክራችሁ ሥሩ” እና “ወላጆች ሆይ፤ ልጆቻችሁ ልዩ ትኩረት ያሻቸዋል” የሚሉ ንግግሮች ይሰጣሉ። ከዚያም በመቀጠል ወጣቶች የሚገጥሟቸው ችግሮች ምን እንደሆኑና እንዴት ሊፈቷቸው እንደሚችሉ ለማብራራት ልዩ ትኩረት ይደረጋል። በአሁኑ ጊዜ ፈጣሪያቸውን የሚያስታውሱ ወጣቶች በሚለው ዘመናዊ ድራማ ሊበረታቱ ይችላሉ።
ቅዳሜ ዕለት የሚኖረው ፕሮግራም ኢየሱስ ስለመጨረሻው ቀን በተናገራቸው ትንቢቶች ላይ በተለይም “ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል” ብሎ በተናገረው ትንቢት ላይ ያተኩራል። (ማቴዎስ 24:29) ያ መከራ መቼ እንደሚመጣ የሚያብራራውን ንግግር ማዳመጥ ይፈልጉ ይሆናል። በተጨማሪም የቅዳሜው ዕለት ፕሮግራም ዘመናዊውን የይሖዋ ምስክሮችን ታሪክና እስከ አሁን ያከናወኗቸውን ሥራዎች የሚከልስ ይሆናል።
እሁድ ዕለት በዘመናችን እየተዘወተሩ ያሉት ቪዲዮ እና ሙዚቃ በአንድ ክርስቲያን ንፁሕ አቋም ላይ የሚያመጡትን ፈታኝ ሁኔታዎች አትሳቱ፣ ወይም በአምላክ ላይ አትዘብቱ የሚል ርዕስ ባለው ድራማ ውስጥ ሲቀርብ ይመለከታሉ። ከሰዓት በኋላ የሚቀርበው የሕዝብ ንግግር “በአስጭናቂው ዘመን ስንኖር የሚረዳን ጠቃሚ ትምህርት” በሚል አጠቃላይ መልዕክት ላይ ያተኩራል። “መለኮታዊውን ትምህርት አጥብቃችሁ ያዙ” በሚል ምክር ፕሮግራሙ ይደመደማል።
በአራቱም ቀኖች ላይ በመገኘት እንደሚጠቀሙ አያጠራጥርም። በስብሰባው ላይ እንዲገኙ በማክበር ጠርተንዎታል። በሚኖሩበት አካበቢ ስብሰባው የሚደረግበትን ቦታ እንዲያውቁ በአቅራቢያዎ በሚገኘው የይሖዋ ምስክሮች የመንግሥት አዳራሽ ሄደው ይጠይቁ ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች ይጻፉ። ወይም ደግሞ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በካናዳ፣ በብሪታንያ እና በአየርላንድ ስብሰባ የሚደረግባቸውን ቦታዎች የሚጠቁመውን የሰኔ 8 የእንግሊዘኛ አዌክ! መጽሔትን ይመልከቱ።