የማይረግፍ ውበት
“ውበት ይረግፋል፤ ውበት ያልፋል” በማለት የግጥም ደራሲ የሆኑት ዋልተር ዲ ላ ሜር ተናገሩ። ይህ በተለይ በዚህ ሥዕል በሚታዩት በጣም በሚያምሩት የቁልቋል አበባዎች ላይ የሚታይ ነገር ነው። ያን የመሰለ መልክ በቶሎ ይረግፋል።
ክርስቲያኑ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “እንደ ሣር [ሀብታሙ ሰው] ያልፋልና። ፀሐይ ከትኵሳት ጋር ይወጣልና፣ ሣርንም ያጠወልጋልና፣ አበባውም ይረግፋልና፣ የመልኩም ውበት ይጠፋልና፤ እንዲሁ ደግሞ ባለ ጠጋው በመንገዱ ይዝላል።”— ያዕቆብ 1:10, 11
በዚህ የማያስተማምን ዓለም፣ ሀብት በአንድ ሌሊት ሊጠፋ ይችላል። ከዚህም በላይ፣ ሀብታም ሰው እንደማንኛውም ሰው ‘እንደ አበባ ዕድሜው አጭር ነው።’ (ኢዮብ 14:1, 2) ኢየሱስ በአንድ ምሳሌው ላይ ቁጭ ብሎ የተዝናና ኑሮ ለማሳለፍ ሀብት በመሰብሰብ ሥራ ሰለተጠመደ ስለ አንድ ሰው ተናግሮ ነበር። ለተዝናና ኑሮ የሚበቃኝን ያህል አከማችቻለሁ ብሎ ባሰበበት ሰዓት ላይ ሞተ። ኢየሱስ “ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፣ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው” በማለት አስጠንቅቋል። (ሉቃስ 12:16-21)
“በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ”፤ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነው? በዚህ መንገድ ባለጠጋ የሆነ ሰው “በሰማይ መዝገብ [ውድ ሀብት አዓት]” ማለትም በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም አለው ማለት ነው። ይህን የመሰለው ውድ ሀብት ለመቼውም አይጠፋም። (ማቴዎስ 6:20፤ ዕብራውያን 6:10) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደዚህ ያለው ሰው የሚረግፈውን አበባ ሳይሆን የማይጠወልጉ ቅጠሎች ያሉትን ዛፍ እንደሚመስል ተደርጎ ተገልጿል። “የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” የሚል ዋስትናም ተሰጥቶታል። — መዝሙር 1:1-3, 6