በሀንጋሪ ይሖዋ ሕዝቦቹን ጠበቀ
ሀንጋሪ በመካከለኛው የአውሮፓ ክፍል የምትገኝ እንደመሆኗ አብዛኛውን ጊዜ የታሪክ ውጣ ውረድ ስታስተናግድ ቆይታለች። ሕዝቦቿ ለድንግል ማሪያም ያደሩና በ1001 በመጀመሪያው ንጉሣቸው በስቴፈን ተገደው በስም ብቻ ክርስቲያኖች ቢሆኑም ብዙ መከራ ደርሶባቸዋል።
ባለፉት መቶ ዘመናት በሙሉ ሀንጋሪ ብዙ ቁጥር ባላቸው የውስጥ ግጭቶች ተዳክማለች፤ ይህም በተደጋጋሚ በሌሎች ሕዝቦች እንድትገዛ ምክንያት ሆኗል። በእነዚህ ግጭቶች ሳቢያ የመንደሮቹ ነዋሪዎች በማለቃቸው በአካባቢው ከውጭ የመጡ ነዋሪዎች ተተኩባት፤ በዚህም ምክንያት ነዋሪዎቹ የብዙ ብሔሮች ድብልቅ ሆኑ። ምንም እንኳን ፕሮቴስታንቶች የቀሰቀሱት ሃይማኖታዊ ተሃድሶ ወደ አንዳንድ አካባቢዎች ቢዛመትም ሁለት ሦስተኛ የሚሆነው ነዋሪ ካቶሊክ ሆኖ ቆይቷል።
አነስተኛ ጅምር
በሀንጋሪ የመጽሐፍ ቅዱስ የእውነት ዘር በመጀመሪያ የተዘራው በ1908 ነበር። ይህም በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ ከነበሩት የይሖዋ ምስክሮች እውነትን በተማረች ሴት አማካኝነት ነበር። ባከናወነችው የስብከት ሥራ ምክንያት ብዙዎች ለምሥራቹ ፍላጎት አሳዩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሁለት ሀንጋሪያውያን ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሀንጋሪ በመመለስ ኮልፖርተሮች [የአቅኚዎች የቀድሞ መጠሪያ ነው] በመሆን በሙሉ ጊዜአቸው ምሥራቹን አሠራጩ። እውነት ቀስ በቀስ ይሁን እንጂ በአስተማማኝ ሁኔታ ተስፋፋ፤ በኮሎዘቫርም ማተሚያ ተቋቁሞ ነበር።
የመጀመሪያው አስተማማኝ ሪፖርት የተገኘው በ19 22 ከአሥር ከተሞች የወጡ 69 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ በተገኙበት ወቅት ነበር። የስብከት ሥራቸው ፈጣን ውጤት ስለነበረው ቀሳውስቱ በመንግሥት እና በሕዝብ መገናኛዎች ላይ ተጽዕኖ በማሳደር የስብከት ሥራቸው እንዲታገድ በመገፋፋት ተቃውሞ አስከተሉ።
ጥቃቱ ተፋፋመ
በ1928 ዞልተን ኒዮስተር የተባሉ የካቶሊክ ቄስ ሚሊኒያሊስት ባይብል ስቱደንትስ በሚል ርዕስ አንድ ፓምፍሌት አሣተሙ። በውስጡም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ እንዲህ አሉ:- “እነርሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ በስተጀርባ ሆነው ቅን ሰዎችን የሚያስቱ በመሆናቸው በጦር መሣሪያ ከሚዋጉት የቀዩ ቦልሸቪክ አብዮተኞች የከፉ ናቸው።” የሀንጋሪ ንጉሣዊ መንግሥት ፖሊስ እንቅስቃሴአቸውን በጥብቅ እየተከታተለ ነው።
በዚያን ወቅት ጆሴፍ ኪስ የተባለ ቅንአት ያለው ወንድም ጉባኤዎችን ጎብኝቶ ነበር። የታጠቁ ፖሊሶች በድብቅ ይከታተሉት ነበር። በ1931 በአንድ ወንድም ቤት እያለ ነበር ፖሊሶች በድንገት ደርሰው እንዲወጣ ያዘዙት። ወንድም ዕቃዎቹን መጠቅለል ሲጀምር አንድ ወታደር በጠብመንጃው ሰደፍ መታውና:- “ቶሎ በል አለበለዚያ እሰካብሃለሁ” በማለት አስፈራራው። ወንድም ኪስም ፈገግ አለና “ይህ ከሆነማ ቶሎ ወደ ቤቴ እሄዳለሁ ማለት ነው” ሲል መለሰለት። ቅቡዕ ክርስቲያን እንደመሆኑ ስለ ሰማያዊ ተስፋው መጥቀሱ ነበር።
ወታደሮቹ ወንድም ኪስን እስከ ባቡሩ ድረስ ተከተሉት። በሰኔ 20, 1931 ደብረሴን በሚገኘው ጉባኤ እንደሚደርስ ይጠበቅ ነበር። ነገር ግን ሳይደርስ ቀረ። ወንድሞችም ጠላቶቹ በእርግጥ ገድለውታል፤ ሰማያዊ ሽልማቱን ወደሚያገኝበት ‘ቤቱ’ ሄዷል ብለው ደመደሙ። ምንም እንኳ የእርሱ ሥራ ቢያቆምም ባለ ሥልጣኖቹ የእውነትን ብርሃን ለማጥፋት ግን አልቻሉም ነበር።
ምስክርነቱን ለመስጠት ብዙ ጊዜ ብልሃት ይጠቀሙ ነበር። ለምሳሌ ያህል በ1930ዎቹ አጋማሽ ላይ በቲሶኮራድ አንድ ወንድም ሞተ። በዚያን ወቅት የቀብር ስነ ሥርዓቶች የሚከናወኑት በባለ ሥልጣኖቹ ፈቃድ ብቻ ነበር። ወንድሞችም የአንድ ደቂቃ ጸሎት እና የአንድ ደቂቃ መዝሙር ብቻ ተፈቀደላቸው። ተግባራዊነቱንም ለመከታተል ጠብመንጃ እና ሳንጃ የታጠቁ የጸጥታ አስከባሪ አባላት በቀብር ስነ ሥርዓቱ ላይ ተገኙ። በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የቀብር ስነ ሥርዓቱ እንዴት ሊከናወን እንደሚችል ለማየት ጓጉተው ስለ ነበረ በዚያ ተገኙ።
አንድ ወንድም ከሬሳ ሣጥኑ ጎን ቆመና ለግማሽ ሰዓት ያህል ጸለየ፤ ያም ሆኖ ግን ሰዎቹ እንዲህ ያለ ነገር ሰምተው እንደማያውቁ ተናገሩ። “የቀብሩን ሥነ ስርዓት ስድስት ቄሶች እንኳን ቢመሩት እንደዚህ ቀስቃሽ አይሆንም ነበር” አሉ። ከዚያም አንድ ጥሩ ድምፅ ያለው ወንድም መዝሙሩን መምራት ጀመረ። ነገር ግን ወታደሩ “ጸጥ በል አለው።” ፖሊሶቹ ተጨንቀው የነበረ ቢሆንም ጸሎቱን ግን ማቋረጥ አንዳልቻሉ በሌላ ጊዜ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል።
ጥቃቶቹ እየቀጠሉ ሲሄዱ ላዮሽ ዛቦ የተባሉ የሪፎርምድ ቤተ ክርስቲያን ቄስ በ1935 አንቲ ክራይስት ባይ ዘ ሪቨር ቲዛ በተባለው ብሮሹር ውስጥ የሚከተለውን ጽፈዋል:- “በሃይማኖት ሽፋን ቦልሸቪዝምን በሰዎች አእምሮ ውስጥ መቅረጽ የተንኮል ዘዴ ነበር። . . . ማርክስ ክርስቶስን መስሎ መጥቷል። . . . የይሖዋ ምሥክሮች ቀይ ካባቸውን ለብሰው ፀረ ክርስቶስ ሆነው መጥተዋል።”
በእገዳ ሥር የነበሩባቸው በርካታ ዓመታት
በ1939 የይሖዋ ምስክሮች ሥራ በግልጽ ታገደ። “ፀረ ሃይማኖታዊ እና ፀረ ሕብረተሰብ” እንቅስቃሴ እንደሆነ ተቆጥሮ ነበር። አድቬንቲስቶች፣ ባብቲስቶች፣ ኢቫንጄላውያንና ፕሪስቢቴሪያኖች ምስክሮቹን በመቃወም ፓምፍሌቶችን አሳተሙ። ነገር ግን ይሖዋ አገልጋዮቹን አልተዋቸውም። በሌላ አገር ያሉትም ምስክሮች ይረዷቸው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በሀንጋሪ ውስጥ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች ብዙ እምነትን የሚያጠነክሩ ተሞክሮዎች ነበሯቸው።
ለምሳሌ አንድ ወንድም ከቼኮዝሎቫኪያ መጽሔቶቻችንን በሻንጣ ሙሉ ይዞ ሲመጣ የጉምሩክ መኮንኑ “በሻንጣህ ውስጥ ያለው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ወንድምም ፊት ለፊት “መጠበቂያ ግንብ” በማለት መለሰለት። በዚያን ጊዜ መኮንኑ ወንድምን እብድ ነው በማለት ፈረመና መንገዱን እንዲቀጥል ነገረው። በዚህ መንገድ መንፈሳዊው ምግብ በደህና ወደ ሀንጋሪ ደረሰ።
በወንድሞች ላይ የሚደርሰው ሥቃይ ግን ገና አላቆመም ነበር። በተለያዩ ጊዜያት ብዙ ቁጥር ያላቸው ወንድሞች ታስረዋል፤ እንዲሁም በቁም እስር ተይዘው ነበር። ከዚያም አንድ ልዩ የምርመራ ቡድን የይሖዋ ምስክሮችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ ተሰጠው። በ1942 ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕፃናት በአንድ ላይ በጋጥ እና በባዶ የአይሁዶች ትምህርት ቤት ውስጥ ተከማችተው ነበር። ከሁለት ወር ሥቃይ በኋላ ለፍርድ ቀርበው ተወነጀሉ። አንዳንዶቹ ዕድሜ ልክ ተፈረደባቸው፣ ሌሎቹም ከ2 እስከ 15 ዓመታት በወህኒ ቤት እንዲያሳልፉ ተፈረደባቸው። ደኔሽ ፋሉቫጌ፣ አንድራሽ ባርታ፣ ያኖሽ ኮኖሮድ የተባሉት ሦስት ወንድሞች በስቅላት ሞት ተፈረደባቸው፤ በኋላ ግን ፍርዱ ተቀየረና በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ። ከዚያም 160 ወንድሞች የሞት ሰፈር እየተባለ ወደሚጠራው ቦር አጠገብ ወደሚገኘው ስፍራ ተወሰዱ። ድንበሩን እንደተሻገሩም ፈጽሞ በሕይወት እንደማይመለሱ ተነገራቸው። ወደዚህ ጦር ሰፈር ከመጡት 6,000 አይሁዳውያን የቀሩት 83 ብቻ ነበሩ። ከምስክሮቹ ግን ከአራቱ በስተቀር ሁሉም ተመልሰዋል።
ከይሖዋ ምስክሮች መሃልም ሰማእት የሆኑ አሉ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጨረሻ አካባቢ ናዚዎች ብዙ ቁጥር ያላቸው ወንድሞችን ገድለዋል። ባርትለን ዛቦ፣ ያኖሽ ዞንደር እና አንታል ሆኒሽ በጥይት ሲገደሉ ላዬሽ ዴሊ ግን በስቅላት ተገድሏል። — ማቴዎስ 24:9
የነበረው ለውጥ ጊዜያዊ ነበር
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነገሮች እንደገና ተለወጡ። የተቋቋመው ጥምር መንግሥት የሰብዓዊ መብቶች እንደሚከበሩ ቃል ገባ። ወንድሞች ከጦር ሰፈሮች በመመለስ ወዲያውኑ መስበክ እና ጉባኤዎችን ማደራጀት ጀመሩ። ይሖዋ ነፃነት የሰጣቸው ለራሳቸው ቁሳዊ ንብረትን ለማከማቸት እንዲጥሩ ሳይሆን ታላቁን ስሙን እንዲያወድሱ እንደሆነ ተገነዘቡ። በ1945 መጨረሻ ላይ 590 ቀናተኛ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ነበሩ። በ1947 ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር እንደ ቅርንጫፍ ቢሮ ሆኖ እንዲያገለግል አንድ ቪላ ተገዛ እና የመጀመሪያው አገር አቀፍ ስብሰባ በአንድ የስፖርት አዳራሽ ውስጥ ተካሄደ። በስብሰባው የተገኙት ቁጥር 1,200 ሲሆን የሀንጋሪ መንግሥት የባቡር መንገድ ድርጅት እንኳን ወደ ስብሰባው ለሚጓዙት የ50 በመቶ ቅናሽ አድርጐ ነበር።
ይሁን እንጂ ነፃነቱ ብዙም አልቆየም። ወዲያዉኑ የኮሚኒስቱ ፓርቲ ስልጣን ያዘና አስተዳደሩ ተለወጠ። የይሖዋ ሕዝቦች በ1947 ከነበራቸው የ1,253 የአስፋፊዎች ብዛት በ1950 ወደ 2,307 ደርሰው ስለ ነበር አዲሱ መንግሥት በቁራኛ ይመለከታቸው ነበር። በዚያው ዓመት ባለ ሥልጣኖቹ በስብከቱ ሥራ ላይ እንቅፋት መፍጠር ጀመሩ። ለሥራው ፈቃድ ያስፈልግ ነበር፤ ነገር ግን መንግሥት ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረም፤ ማመልከቻ ያስገቡትም በወታደሮች ተደበደቡ። የዜና መጽሔት ርዕሶች ያለማቋረጥ ምስክሮቹን ‘የኢምፔራሊስት ወኪሎች ናቸው’ በማለት ያወግዙ ነበር። የሚያስገርመው ደግሞ ኮሙኒዝም ሥልጣን ከመያዙ በፊት ምስክሮቹ ‘የኮሙኒስት አይሁዳውያን ግብረአበሮች’ ናቸው ተብለው በየካምፑ ታስረው ነበር።
ሽብሩ ተጀመረ
በኅዳር 13, 1950 የቅርንጫፉ የበላይ ተመልካች እና ተርጓሚው (ቀደም ብሎ ሞት ከተፈረዳበቸው ሁለቱ) ከመጀመሪያው ክልል የበላይ ተመልካች ጋር አብረው ታሠሩ። 60 አንድራዜ በተባለው ጐዳና ወደሚገኘው ከመሬት በታች ወዳለ አስከፊ እስር ቤት “እንዲለሰልሱ” በማለት ወሰዷቸው። የፍርድ ውሳኔ ያገኙት በሚቀጥለው ዓመት የካቲት 2 ነበር። የቅርንጫፉ የበላይ ተመልካች የአሥር ዓመት፣ ተርጓሚው የዘጠኝ ዓመት፣ የክልል የበላይ ተመልካቹ የስምንት ዓመት እስራት ተፈረደባቸው። የሦስቱም ንብረት ተወርሶ ነበር። በፍርዱ ወቅት ሌሎች አራት የጉባኤ የበላይ ተመልካቾች መንግሥት ለመገልበጥ ሞክራችኋል በመባል ተወንጅለው ከአምስት እስከ ስድስት ዓመት ተፈረደባቸው።
ወንድሞች ደብዳቤና ዕቃ መቀበል ወይም ጠያቂዎች መግባት ወደማይችሉበት ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግበት እስር ቤት ተወሰዱ። ቤተሰቦቻቸው ስለ እነርሱ ምንም ወሬ አይሰሙም ነበር። ጠባቂዎቹ እንኳን ስማቸውን አይጠሩም። እያንዳንዳቸው ተለይተው እንዲታወቁ በእንጨት ላይ የተጻፈ ቁጥር በአንገታቸው ላይ ያንጠለጥሉ ነበር። በግድግዳው ላይ እንኳን ሳይቀር “እስረኞቹን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ጥሏቸው” የሚል ጽሑፍ የያዘ ምልክት ነበር።
ምሥክሮቹ በድብቅ መሥራት ጀመሩ፤ የስብከት ሥራው ግን አላቆመም ነበር። የታሰሩትን ተክተው ሌሎች ምስክሮች መሥራት ጀመሩ። ውሎ አድሮ ግን ተተክተው የሚሠሩትም ተያዙ። እስከ 1953 ድረስ ከ500 የሚበልጡ ወንድሞች ተወንጅለው እሥራት ተፈርዶባቸው ነበር። ሊታሠር ያልቻለው ግን ምሥራቹ ብቻ ነበር። ጥቂት ወንድሞች ብቻ የጠባቂዎቹን የማባበያ ቃል ሰምተው አቋማቸውን አላልተዋል።
ብሩሕ ተስፋዎች
በ1956 ማብቂያ ላይ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ማመፅ ጀመሮ ነበር። የሶቭየት ጦር ዓመፁን አፈነውና የኮሙኒስቱ ፓርቲ ሥልጣኑን መልሶ ያዘ።
የታሠሩት ምስክሮች ሁሉ ተለቅቀው ነበር። ነገር ግን በኋላ ቀደም ሲል ያልተወነጀሉት አዲሶቹ ብቻ ሲቀሩ በደንብ የታወቁት ጥቂት ወንድሞች ግን ፍርዳቸውን እንዲጨርሱ ወደ እስር ቤት እንዲመለሱ ተደረገ። በመጨረሻም በ1964 ነገሮቹ እየቀለሉ መጡ። ከዚያ በኋላ ባለ ሥልጣኖቹ የቀብር ስነ ሥርዓቶችንም ሆነ የሠርግ ግብዣዎችን ለማቋረጥ አልሞከሩም። የክልል ስብሰባዎች በጫካ ውስጥ ይካሄዱ ነበር። ከእነዚህ ስብሰባዎች አንዳንዶቹን ወታደሮች መጥተው ቢያስቆሟቸውም ሌሎች ተጨማሪ ምስክሮች ግን አልታሠሩም።
በ1979 በበላይ ተመልካችነት ያሉ ወንድሞች በቪየና የተደረገውን ስብሰባ እንዲካፈሉ ተፈቀደላቸው። በዚያው ዓመት ባለ ሥልጣኖቹ ለይሖዋ ምስክሮች ሕጋዊ ነፃነት እንደሚሰጡ ቃል ገቡ። ነገር ግን ይህ ከመሆኑ በፊት ተጨማሪ አሥር ዓመታት አለፉ። በ1986 የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች አውቀውት የመጀመሪያ የወረዳ ስብሰባ በካማራ ጫካ በዩዝ ፓርክ ውስጥ ተካሄደ። “መለኮታዊ ሰላም” በሚል ርዕስ የሚደረግ የይሖዋ ምስክሮች የወረዳ ስብሰባ በዚያ መኖሩን የሚያሳይ ምልክት እንኳ ሳይቀር ተሰቅሎ ነበር። በሚቀጥለው ዓመት “በይሖዋ ታመኑ” የተባለ የወረዳ ስብሰባ ተካሄደ። ከዚያም በ1988 ወንድሞች “መለኮታዊ ፍትሕ” የተባለውን የወረዳ ስብሰባ አደረጉ።
በመጨረሻም ነፃ ወጡ!
ሰኔ 27, 1989 በሀንጋሪ ለይሖዋ መስክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት ሕጋዊ እውቅና የተሰጠበትን ሰነድ ወንድሞች የተቀበሉበት ቀን በመሆኑ ግሩም ቀን ነበር። በሐምሌ ወር ሰፊ በሆነው የቡዳፔስት ስፖርት አዳራሽ ውስጥ 9,477 ተሰብሳቢዎች በተገኙበት “ለአምላክ ያደሩ መሆን” የተባለው የወረዳ ስብሰባ ተካሄደ። በ1990ም “ንጹሕ ልሳን” የተባለው የወረዳ ስብሰባ በዚሁ አዳራሽ ውስጥ ሲደረግ በሌሎችም ሦስት የሀንጋሪ ትላልቅ ከተሞች ተካሂዷል።
አሁን እገዳው ሙሉ በሙሉ ተነስቶ ስለነበር የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ ስብሰባ ለማካሄድ አመቺ ነበር። አየሩ አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳ በቡዳፔስት ውስጥ በናፋሽታዮን በልባዊ የወንድማማች ፍቅር ለመደሰት 40,601 የሚያክሉ ተገኝተው ነበር። የአስተዳደር አካል አባላት በስብሰባው ላይ በመገኘት በንግግሮቻቸው የወንድሞችን እምነት አጠነከሩ፤ እንዲሁም በዚሁ ስብሰባ ላይ ባለ ሙሉ ቀለም አዳዲስ መጽሐፍትና ብሮሹሮች ወጥተዋል።
ዛሬ ምን እየተከናወነ ነው?
በአሁኑ ጊዜ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች በሀንጋሪ ቋንቋ እንደ እንግሊዝኛው ውብ በሆነ አቀራረብ በአንድ ጊዜ ይታተማሉ። በ1992 የዓመቱ መጽሐፍ በሀንጋሪ ቋንቋ መታተም ጀምሯል። በ1971 6,352 የነበረው የምስራቹ አስፋፊዎች ቁጥር በ1993 ወደ 13,136 ከፍ ብሏል።
ዛሬ በሀንጋሪ ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምስክሮች የሃይማኖት ነፃነት በማግኘታቸውና በነፃነት ከቤት ወደ ቤት መስበክ በመቻላቸው ይደሰታሉ። 205 ጉባኤዎች ሲኖሩ በሚያዚያ 17 1992 በመታሰቢያው በዓል ላይ 27,844 ተገኝተዋል። በቂ የሆኑ የመንግሥት አዳራሾች እስኪገኙ ድረስ ጉባኤዎች በትምህርት ቤቶች፣ በባሕል ማዕከሎች፣ ባዶ በቀሩት የጦር ሰፈሮች፣ በተለቀቁት የኮሙኒስቱ ፓርቲ ቢሮዎች እንኳን ሳይቀር መሰብሰባቸውን ቀጥለዋል። በ1992 አሥር ጉባኤዎች የራሳቸውን የመንግሥት አዳራሽ አስመርቀዋል፤ ሌሎች አዳራሾችም ደግሞ በግንባታ ላይ ናቸው።
እነዚህ ሁሉ ለውጦች እና አብዮቶች ሲካሄዱ ወንድሞች ከይሖዋ አምላክ እና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በታማኝነት በመቆምና ምስራቹን በመስበክ ቀጥለዋል። በሀንጋሪ ያሉትን ሕዝቦቹን በየጊዜው የተፈራረቁት የመከራ ማዕበሎች አላጠፏቸውም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ጠብቋቸዋል። — ምሳሌ 18:10
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ቨየና
ኦስትሪያ
ቡዳፔስት
ድብረሴን
ሀንጋሪ
ሩማንያ
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ሕዝቦች በቡዳፔስት ትልቅ ስብሰባ አደረጉ