የሕይወት ውኃ
“ የሚሰማም:- ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ።” (ራእይ 22:17 ) “ የሕይወት ውኃ” አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ያዘጋጃቸውን የመዳን ዝግጅቶች በሙሉ ያመለክታል። እነዚህን ዝግጅቶች በነፃ ማግኘት ይቻላል። አምላካችን ይህን ማድረጉ እንዴት ያለ አስደናቂ ልግስና ነው! ታዲያ እነዚህ ዝግጅቶች በውኃ የተመሰሉት ለምንድን ነው?
እውነተኛው ውኃ ተክሎች በአፈር ላይ እንዲያድጉ ያስችላል። ሰው በሕይወት የሚኖረው ተክሎችን በመመገብ ነው። ውኃ ከሌለ ዕፅዋት ሊኖሩ አይችሉም። ዕፅዋት ከሌሉ ደግሞ ሰው መኖር አይችልም። በተጨማሪም ከሰውነትህ 65 በመቶ የሚሆነው ውኃ ነው። አንዳንድ የጤና ጠበብት እንኳ በየቀኑ ሁለት ተኩል ሊትር ውኃ በመውሰድ ይህንን የውኃ መጠን መጠበቅ ጥሩ እንደሆነ ይመክራሉ። ምግብን ከመፍጨት አንስቶ ቆሻሻን ከሰውነት እስከ ማስወገድ ድረስ ያሉት የውስጣዊ አካል ሂደቶች በሙሉ ውኃ ያስፈልጋቸዋል። ያለ ውኃ ለአንድ ሳምንት ብትቆይ ትሞታለህ።
በተመሳሳይም “ የሕይወት ውኃ” መንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ ይህን ሕይወት ይመግበዋል። የሕይወትን ውኃ ካልጠጣን የዘላለም ሕይወት አናገኝም። (ዮሐንስ 3:36 ) ተቀብለን ከጠጣን ግን የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንችላለን። ሳምራዊቷ ሴት ኢየሱስ:- “ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፣ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ” ባላት ጊዜ በጉጉት ይህን ውኃ እንዲሰጣት መጠየቋ አያስደንቅም። (ዮሐንስ 4:14 ) እኛም ይህን የመሰለ ጉጉት በማሳየት የሕይወትን ውኃ በነፃ እንውሰድ።
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Garo Nalbandian