የአውሮፓ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በግሪክ ውስጥ የመስበክ መብት አስከበረ
አንድ በጎረቤቶቹ ዘንድ የተመሰገነ ሰው ከ1938 ጀምሮ 60 ጊዜ የታሰረው ለምን ነበር? ይህ በግሪክ ደሴት በቀርጤስ የሚገኝ ሐቀኛ ባለሱቅ 18 ጊዜ በግሪክ ፍርድ ቤቶች ፊት የቀረበውና ከስድስት ዓመት በላይ የታሰረው ለምንድን ነው? ሚኖስ ኮኪናኪስ የተባለ ቤተሰብ ያለው ታታሪ ሰው ከሚስቱና ከአምስት ልጆቹ ተለይቶ ወደተለያዩ ደሴቶች ለቅጣት በግዞት የተወሰደው ለምንድን ነው?
በ1938 እና በ1939 የተላለፉት ሃይማኖት ማስቀየርን የሚከለክሉት ሕጐች ለዚህ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው። እነዚህ ሕጎች የተቋቋሙት በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተጽዕኖ ውሳኔዎችን ያደርግ በነበረው የግሪክ አምባገነን ኢዮኒስ ሜታክስ በተባለው ሰው ነው።
በዚህ ሕግ ምክንያት ከ1938 እስከ 1992 ድረስ 19,147 የይሖዋ ምስክሮች ታስረዋል። ፍርድ ቤቱ በጠቅላላ ሲደመር 753 ዓመት ሲፈርድባቸው ከዚህ ውስጥ 593ቱ ዓመት ተፈጻሚነት አግኝቷል። በግሪክ የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች ይህ ሁሉ የደረሰባቸው በሌሎች አገሮች እንደሚገኙት የይሖዋ ምስክሮች ሁሉ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለውን የኢየሱስ ክርስቶስን መመሪያ በመከተላቸው ነው። — ማቴዎስ 28:19, 20
ይሁን እንጂ በግንቦት 25, 1993 የአምልኮ ነፃነትን በተመለከተ አንድ ታላቅ ድል ተገኘ! በዚህ ቀን በፈረንሳይ ስትራስበርግ ውስጥ የተሰበሰበው የአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት አንድ የግሪክ ዜጋ እምነቱን ለሌሎች ለማስተማር ያለውን መብት አስከበረ። ይህ የአውሮፓ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይህን ውሳኔ በማስተላለፉ በየትም ቦታ በሚኖሩ ሕዝቦች ሕይወት ላይ ትልቅ ውጤት ሊኖረው የሚችል ሰፊ የሃይማኖት ነፃነት መከላከያ አስገኝቷል።
ወደዚህ ከፍተኛ ውሳኔ ያደረሱትን በአንድ የግሪክ ዜጋ ላይ የተፈጸሙት ሥቃዮችን ጨምሮ የተከሰቱትን ሁኔታዎች አንድ በአንድ እንመልከት።
የነገሩ ሥረ መሠረት
በ1938 ሚኖስ ኮኪናኪስ የተባለው ይህ የግሪክ ዜጋ ሰብኮ ሃይማኖት ማስቀየር የሚያስቀጣ ወንጀል ነው በሚለው የግሪክ ሕግ መሠረት የተፈረደበት የመጀመሪያው የይሖዋ ምስክር ሆነ። ያለ ምንም የፍርድ ቤት ውሳኔ በአሞርጎስ በምትገኘው በኤጂን ደሴት ለ13 ወራት በእስር ቤት እንዲቆይ ተላከ። በ1939 ሁለት ጊዜ ተፈረደበትና በእያንዳንዱ ጊዜ ሁለት ወር ተኩል ታሰረ።
ኮኪናኪስ በ1940 በሜሎስ ደሴት ለስድስት ወር ታሰረ። በሚቀጥለው ዓመት ማለትም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአቴንስ ወታደራዊ እስር ቤት ውስጥ ለ18 ወራት ታሰረ። ኮኪናኪስ ያን ጊዜ ሲያስታውስ እንዲህ ይላል:-
“በእስር ቤት ውስጥ የነበረው የምግብ እጥረት በጣም እየከፋ ሄደ። በጣም ከመድከማችን የተነሳ መራመድ አቅቶን ነበር። በአቴንስ በፒሪኤስ አካባቢ ያሉ ምስክሮች ያለቻቸውን እያመጡ ባይሰጡን ኖሮ እንሞት ነበር።” ከዚያም በኋላ በ1947 በድጋሚ ተፈረደበትና አራት ወር ተኩል ታሰረ።
በ1949 ሚኖስ ኮኪናኪስ ወደ ማክሮኒሰስ ደሴት በግዞት ተወሰደ። በዚያ ከሚገኘው እስር ቤት የተነሳ ግሪኮች ማክሮኒሰስ የሚለው ስም ሲነሳ በጣም ይዘገንናቸዋል። በማክሮኒሰስ ከታሰሩት 14,000 የሚሆኑ እስረኞች መካከል 40 የሚያክሉት የይሖዋ ምስክሮች ነበሩ። ፓፒሮስ ላሩስ የተባለው የግሪክ ኤንሳይክሎፒዲያ እንደሚከተለው ይላል:- “በጭካኔ የሚያሠቃዩበት መንገድ፣ . . . በአንድ የሰለጠነ መንግሥት ዘንድ ተቀባይነት የሌለው የኑሮ ሁኔታና ጠባቂዎቹ ለእስረኞቹ የሚያሳዩት ወራዳ ባሕርይ . . . ለግሪክ ታሪክ በጣም አሳፋሪ ነገሮች ናቸው።”
በማክሮኒስ እስር ቤት አንድ ዓመት ያሳለፈው ኮኪናኪስ ሁኔታውን እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “ወታደሮቹ ልክ እንደ መርማሪ አባላት እያንዳንዱን እስረኛ ከጠዋት እስከ ማታ ይመረምሩታል። ወታደሮቹ የሚያደርሱትን ሥቃይ በቃላት መግለጽ ያስቸግራል። ብዙ እስረኞች አብደዋል፤ ሌሎችም ተገድለዋል፤ ብዙዎች ደግሞ አካለ ስንኩል ሆነዋል። እየተገረፉ ያሉትን እስረኞች ልቅሶና ጩኸት በምንሰማባቸው በእነዚያ አሰቃቂ ሌሊቶች ወቅት ተሰብስበን እንጸልይ ነበር።”
ኮኪናኪስ ከማክሮኒሰስ እስር ቤት ከደረሰበት ስቃይ ተርፎ ከወጣም በኋላ በ1950ዎቹ ዓመታት ስድስት ጊዜ ተይዞ አስር ወር ታስሯል። በ1960ዎቹ ደግሞ አራት ጊዜ ተይዞ ስምንት ወር ታሰረ። ይሁን እንጂ ስለ እምነታቸው ለሌሎች በመናገራቸው ምክንያት እየተያዙ ከሚታሰሩት በመቶ ከሚቆጠሩት የይሖዋ ምስክሮች መካከል ኮኪናኪስ አንዱ ብቻ እንደሆነ አስታውስ።
በግሪክ በሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች ላይ የተፈጸመው አሳዛኝ የፍትህ መጓደል በመጨረሻ ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት የቀረበው እንዴት ነበር?
የሕጉ መፈተኛ
ክርክሩ የጀመረው መጋቢት 2, 1986 ነበር። በዚያን ጊዜ በጡረታ ላይ የሚገኘው የ77 ዓመቱ የንግድ ሰው ሚኖስ ኮኪናኪስና ሚስቱ በቀርጤስ ሲቲያ ወደምትገኘው ወደ ሚስስ ኪሪያካኪ ቤት ሄደው አነጋገሯቸው። በዚያ አካባቢ የሚገኘው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄስ የሆነው የሚስስ ኪሪያካኪ ባል ለፖሊስ ይጠቁማል። ፖሊስ ይመጣና ሚስተር ኮኪናኪስንና ሚስስ ኮኪናኪስን ይዟቸው በአካባቢው ወደሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ይወስዳቸዋል። እዚያው ፖሊስ ጣቢያ እንዲያድሩ አስገደዱአቸው።
የተከሰሱበት ነገር ምን ነበር? ቀደም ባሉት 50 ዓመታት የይሖዋ ምስክሮች ለብዙ ሺህ ጊዜ ሲከሰሱበት የነበረው ማለትም እየሰበኩ የሰዎችን ሃይማኖት ያስለውጣሉ የሚል ተመሳሳይ ክስ ነው። የግሪክ ሕገ መንግሥት (1975) አንቀጽ 13 “እየሰበኩ ሃይማኖት ማስቀየር ክልክል ነው” ሲል ይገልጻል። በተጨማሪም እየሰበኩ ሃይማኖትን ማስቀየር የሚያስቀጣ ወንጀል አድርጎ የሚገልጸውን ክፍል 4 ቁጥር 1363/1938 እና 1672/1939 የግሪክ ሕግ ተመልከት። እንዲህ ይላል:-
“‘እየሰበኩ ሃይማኖት ማስቀየር’ ማለት በተለይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአንድ ሰው ሃይማኖታዊ እምነቶቹ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት መሞከር፣ . . . በማንኛውም ዓይነት ማባበያ ወይም በሚያባብል ተስፋ ወይም የሞራል ድጋፍ ወይም ቁሳዊ እርዳታ በመስጠት ወይም ደግሞ በማጭበርበር ወይም በአንድ ሰው ተሞክሮ ማጣት፣ በሚታመንበት፣ በሚያስፈልገው ነገር፣ በዝቅተኛ ትምህርቱ ወይም በሞኝነቱ ተጠቅሞ እነዚያን እምነቶቹን ለማዳከም መሞከር ማለት ነው።”
በቀርጤስ ላሲቲ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት ክሱን አዳመጠና ሚስተር ኮኪናኪስና ሚስስ ኮኪናኪስን እየሰበኩ ሃይማኖት አስለውጠዋል በማለት ወንጀለኞች አደረጋቸው። ሁለቱም የአራት ወር እስራት ተፈረደባቸው። ፍርድ ቤቱ በባልና ሚስቱ ላይ ሲፈርድ ተከሳሾቹ “የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ያላቸው አነስተኛ ተሞክሮ፣ ያላቸውን ዝቅተኛ እውቀት እንዲሁም ሞኝነታቸውን ተጠቅመው በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ እምነት ውስጥ” ጣልቃ ገብተዋል ሲል ገልጿል። ተከሳሾቹ ከዚህም በተጨማሪ “ነገሮችን በብልሃትና በዘዴ በማብራራት [ሚስስ ኪሪያካኪ] . . . ያላትን የኦርቶዶክስ ክርስቲያን እምነት እንድትለውጥ አበረታተዋል” ሲል ከሷቸዋል።
ውሳኔው በቀርጤስ ለሚገኘው የይግባኝ ፍርድ ቤት ቀረበ። ይህ የቀርጤስ ፍርድ ቤት ሚስስ ኮኪናኪን በነፃ ሲያሰናብታት ምንም እንኳን የእስራት ፍርዱን ወደ ሦስት ወር ዝቅ ቢያደርገውም የባሏን ፍርድ ግን አጸደቀ። የተላለፈው ፍርድ [ሚስተር ኮኪናኪስ] “[የሚስስ ኪሪያካኪን] ተሞክሮ የሌላት፣ ዝቅተኛ እውቀትና ሞኝ የመሆኗን አጋጣሚ ተጠቅሞበታል” ይላል። “በቂ የሆነ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት እውቀት የሌላት ሴት ምንም መልስ ልትሰጥ እንደማትችል በመረዳት በዘዴ ከቅዱሳን ጽሑፎች እያነበበ ያስረዳት ጀመር” ይላል።
ከይግባኝ ዳኞች አንዱ የተቃውሞ አስተያየቱን ሲሰጥ ሚስተር ኮኪናኪስም “በነፃ መለቀቅ ነበረባቸው። ምክንያቱም ጆርጂያ ኪሪያካኪ የቄስ ሚስት እንደመሆኗ መጠን ተከሳሹ የይሖዋ ምስክሮች ኑፋቄ አባል እንድትሆን ሊያባብላት የሚችል በኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ትምህርት ተሞክሮ የሌላት ወይም ዝቅተኛ እውቀት ያላት ወይም ምንም የማታውቅ ሞኝ መሆኗን የትኛውም ማስረጃ አያሳይም” ሲል ጽፏል።
ሚስተር ኮኪናኪስ ጉዳዩን ለግሪክ ከፍተኛ የይግባኝ ፍርድ ቤት ይግባኝ አለ። ይሁን እንጂ ይህ ፍርድ ቤት በሚያዝያ 22, 1988 ይግባኙን ሰረዘው። ስለዚህ ሚስተር ኮኪናኪስ ነሐሴ 22, 1988 ለአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ይግባኝ አለ። በመጨረሻም የካቲት 21, 1992 አቤቱታው ተቀባይነት አገኘና ለአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት ቀረበ።
ጉዳዩ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም
የግሪክ መንግሥት የአውሮፓ ምክር ቤት አባል ስለሆነ የአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ያወጣቸውን አንቀጾች እንዲያከብር ይገደዳል። ጉባኤው ያወጣው ውሳኔ አንቀጽ 9 እንዲህ ይነበባል:- “ማንም ሰው የሐሳብ፣ የኅሊናና የሃይማኖት ነፃነት እንዲኖረው የሚያደርግ መብት አለው። ይህ መብት ሃይማኖቱን ወይም እምነቱን የመለወጥ ነፃነት፣ ብቻውን ወይም ከሌሎች ጋር በኅብረት በመሆን ሃይማኖቱን ወይም እምነቱን በአምልኮ፣ በማስተማር፣ በተግባር በማሳየትና በማክበር ለሕዝብ ወይም ለግለሰብ የመግለጽ ነፃነት ይጨምራል።”
ከዚህ የተነሳ የግሪክ መንግሥት በአውሮፓ ፍርድ ቤት ተከሳሽ ሆነ። የግሪክ መንግሥት ‘እያስተማራችሁ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ የሚለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ትዕዛዝ በመጠበቅ ሃይማኖቱን እንዳያከናውን በመከልከል የአንድን የግሪክ ዜጋ መሠረታዊ የሆነ ሰብአዊ መብት በግልጽ በመጣስ ተከስሷል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘ለሕዝብም እንድንሰብክና እንድንመሰክር [ኢየሱስ] አዘዘን’ ብሏል። — ሥራ 10:42
ሂዩማን ራይትስ የተባለው መጽሔት በ1992 ልዩ እትሙ “ግሪክ ሆን ብላ ሰብአዊ መብቶችን ረግጣለች” የሚል ርዕስ በመጽሔቱ ሽፋን ላይ ይዞ ወጥቷል። መጽሔቱ በገጽ 2 ላይ “አንድ ሰው ሃይማኖቱን እንዲለውጥ በሚገፋፋ ሰው ላይ ቅጣት የሚያስከትልና እስራት እንዲፈረድበት የሚያደርግ ሕግ ያላት በአውሮፓ ማኅበረሰብና በአውሮፓ ውስጥ የምትገኝ ብቸኛዋ አገር ግሪክ ናት” በማለት አብራርቷል።
ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ በሕግ ሰዎችም ዘንድ ሆነ በሌሎች ሰዎች ዘንድ ከፍተኛ መደናገጥ ተፈጥሯል። የአንድን ሰው እምነት ለሌላ ማስተማር የሚከለክለውን የግሪክ ሕግ በተመለከተ ምን ይወሰን ይሆን?
በትራስበርግ ጉዳዩ ሲሰማ
በመጨረሻም ኅዳር 25, 1992 ጉዳዩ የሚሰማበት ቀን ደረሰ። በስትራስበርግ ከባድ ደመና አለ፤ አየሩ በጣም ይቀዘቅዛል። ይሁን እንጂ በፍርድ ቤቱ ውስጥ ያሉት ጠበቆች የጋለ ክርክር ይዘው ነበር። ለሁለት ሰዓት ያህል ማስረጃዎቹ ቀረቡ። የኮኪናኪስ ጠበቃ ፕሮፌሰር ፈደን ቨግለሪስ እንደሚከተለው በማለት ልብ የሚነካ ጥያቄ አቀረቡ:- “የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ወደ ሌላ ሃይማኖታዊ እምነት እንዳይለወጡ ለመከላከል ሲባል የወጣው የእገዳ ሕግ እንዳለ ሊቀጥልና ሊሠራበት ይገባልን?”
ፕሮፌሰር ቨግለሪስ ስለ ጉዳዩ በእርግጥ ግራ እንደተጋቡ በማሳየት እንዲህ ሲሉ ጠየቁ “ይህ [እየሰበኩ ሃይማኖት የማስቀየር] ሕግ ኦርቶዶክስነትን ከጅልነትና ከድንቁርና ጋር ለምን እኩል አድርጎ እንደሚያየው አላውቅም። የኦርቶዶክስ እምነት ከጅልነትና ከመንፈሳዊ እውቀት ማነስ በማሳበብ ከለላ ለማግኘት ለምን እንደሚፈልግ በፍጹም አይገባኝም። . . . በጣም የሚያሳፍረኝና የሚያበሳጨኝ ነገር ቢኖር ይህ ነው።” የመንግሥት ተወካይ የነበረው ሰው ይህ ሕግ በይሖዋ ምስክሮች ላይ ካልሆነ በስተቀር በሌሎች ላይ እንደተሠራበት የሚገልጽ አንድ ማስረጃ እንኳን ማቅረብ አልቻለም ነበር።
የኮኪናኪስ ሁለተኛ ጠበቃ የሆኑት ሚስተር ፓናዮትስ ቢትሳሂስ ሃይማኖት ማስቀየርን በተመለከተ የወጣው ሕግ ምን ያህል ምክንያተቢስ እንደሆነ አስረዱ። እንዲህ አሉ:- “በትልልቅ ሰዎች መካከል በሚደረገው ውይይት መግባባት ደረጃ ላይ መድረስ አንዱ ቅድመ ሁኔታ ነው። አለዚያማ የሚያስቡ ነገር ግን ሐሳባቸውን የማይገልጹ፣ የሚናገሩ ነገር ግን የሐሳብ ግንኙነት የማያደርጉ፣ ሕያዋን የሆኑ ነገር ግን ተባብረው የማይኖሩና ምንም የማይናገሩ የአራዊት ኅብረተሰብ እንሆን ነበር።”
ሚስተር ቢትሳሂስ በተጨማሪም “ሚስተር ኮኪናኪስ የተወገዙት ‘ባደረጉት ነገር ሳይሆን’ ‘በማንነታቸው ነው’” ሲሉ ተከራከሩ። ከዚህም የተነሳ ሚስተር ቢትሳሂስ የሃይማኖታዊ ነፃነት መሠረታዊ ሥርዓቶች ከመጣስ አልፈው ሙሉ በሙሉ የተደመሰሱ መሆናቸውን አስረዱ።
የግሪክ መንግሥት ተወካዮች “ግሪክ የሰብአዊ መብቶች ገነት ነች” በማለት ከእውነት የራቀ መልክ ለማቅረብ ሞክረው ነበር።
ውሳኔው
ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን ግንቦት 25, 1993 ደረሰ። ፍርድ ቤቱ የግሪክ መንግሥት የ84 ዓመቱን የሚኖስ ኮኪናኪስን የሃይማኖት ነፃነት ጥሷል ሲል ስድስት ለሦስት በሆነ ድምጽ አጸደቀ። ለሕዝብ የመስበክ መብቱ እንዲከበር ከማድረጉም በተጨማሪ 14,400 ዶላር ካሳ እንዲያገኝ አድርጓል። ፍርድ ቤቱ በዚህ ኮኪናኪስና የይሖዋ ምስክሮች ስለ እምነታቸው ከሌሎች ጋር በሚወያዩበት ጊዜ አስገድዶ በማሳመን ዘዴ ይጠቀማሉ ሲል የግሪክ መንግሥት ያቀረበውን ክስ ውድቅ አደረገው።
ምንም እንኳን የግሪክ ሕገ መንግሥትና የጥንቱ የግሪክ ሕግ ሃይማኖት ማስቀየርን ቢከለክሉም በዚህ ሕግ ተጠቅሞ የይሖዋ ምስክሮችን ማሳደድ ስህተት መሆኑን የአውሮፓ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አጽድቋል። ይህ ድርጊት የአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ካጸደቀው ሕግ ከአንቀጽ 9 ጋር ይጋጫል።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲህ ሲል ተብራራ:- “ሃይማኖት ‘ያለማቋረጥ የሚታደሰው የሰብዓዊ አስተሳሰብ’ ክፍል በመሆኑ የሕዝብ መወያያ እንዳይሆን መከልከል አይቻልም።”
በሐሳቡ ከተስማሙት ከዘጠኙ ዳኞች ውስጥ አንዱ አስተያየታቸውን ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል:- “‘እምነትን የማሰራጨት ቅንዓት’ የሚል ፍቺ የተሰጠው ሃይማኖትን ማስቀየር የሚያስቀጣ ሊሆን አይችልም፤ ሃይማኖትን ማስቀየር ‘አንድ ሰው ሃይማኖቱን የሚገልጽበት’ ፍጹም ሕጋዊ የሆነ መንገድ ነው።’
“መጀመሪያ ነገር ተከሳሹ [ሚስተር ኮኪናኪስ] የተፈረደበት መጥፎ ባሕርይ ኖሮት ሳይሆን እንዲህ ዓይነቱን ቅንዓት ስላሳየ ብቻ ነው።”
ውሳኔው ያስከተላቸው ውጤቶች
የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ግልጽ መመሪያ የግሪክ መንግሥት ባለ ሥልጣኖች ሃይማኖት ማስቀየርን በሚከለክለው ሕግ አላግባብ መጠቀማቸውን እንዲያቆሙ የሚያሳስብ ነው። ግሪክ የፍርድ ቤቱን መመሪያ እንደምትከተልና የይሖዋ ምስክሮችን ማሳደድዋን እንደምታቆም ተስፋ እናደርጋለን።
ማኅበራዊ ለውጥ ማምጣት ወይም ሕጋዊ ሥርዓትን ማሻሻል የይሖዋ ምስክሮች ዓላማ አይደለም። የእነሱ ዋና ዓላማ በኢየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዝ መሠረት የአምላክን መንግሥት ምስራች መስበክ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ለማድረግ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳደረገው ‘ለምሥራቹ ሕጋዊ መከላከያ ሲቀርብና ምሥራቹ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሲከበር ማየት’ ደስ ያሰኛቸዋል። — ፊልጵስዩስ 1:7
የይሖዋ ምስክሮች በሚኖሩበት አገር ሁሉ ሕግ አክባሪ ዜጎች ናቸው። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተመዘገበው ከሁሉ በላይ የአምላክን ሕግ ለመታዘዝ ይገደዳሉ። ስለዚህ የማንኛውም አገር ሕግ ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን እምነታቸውን ለሌሎች እንዳይናገሩ ቢከለክላቸው “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባናል” የሚለውን ሐዋርያዊ አቋም ለመያዝ ይገደዳሉ። — ሥራ 5:29
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ቀሳውስት ያስነሱት ተጨማሪ ስደት
በግሪክ የሚገኙ ቄሶች ‘በሕግ አማካኝነት ችግር’ ለመፍጠር የሚያደርጉት ሙከራ ለአሥርተ ዓመታት ቀጥሎ ነበር። (መዝሙር 94:20) በቀርጤስ ደሴት ላይ የተከሰተ አንድ ሌላ ሁኔታ በቅርቡ መፍትሄ አግኝቷል። በ1987 አንድ የአካባቢው ጳጳስና 13 ቄሶች ሃይማኖት ያስቀይራሉ በማለት ዘጠኝ የይሖዋ ምስክሮችን ከስሰው ነበር። በመጨረሻም ጥር 24, 1992 ጉዳዩ ለፍርድ ቤት ቀረበ።
ፍርድ ቤቱ በሰዎች ተሞልቶ ነበር። የከሳሾቹን ክስ ለመደገፍ ወደ 35 የሚያክሉ ቄሶች በዚያ ነበሩ። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ወንበሮች ወንድሞቻቸውን ሊያበረታቱ በመጡት የይሖዋ ምስክሮች ቀደም ብለው ተይዘው ነበር። ገና መደበኛው ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት የተከሳሾቹ ጠበቃ ከሳሾቹ የሠሩትን አንድ ከባድ የሆነ ሕጋዊ ስህተት ጠቆመ።
ከዚያም የፍርድ ቤቱ ዳኞች በግል ለመመካከር ወጡ። ከዚያም ለሁለት ሰዓት ተኩል ከተመካከሩ በኋላ የፍርድ ቤቱ ፕሪዘዳንት የተከሳሾቹ ጠበቃ ትክክል እንደሆነ አስታወቀ። ስለዚህ በዘጠኙ ምስክሮች ላይ የቀረበው ክስ ተሰረዘ! ተከሳሾቹ ሃይማኖት የማስቀየር ጥፋት መፈጸማቸውና አለመፈጸማቸውን ለማረጋገጥ እንደገና ምርመራ መጀመር ያስፈልጋል ሲል አጸደቀ።
ወዲያው ማስታወቂያው እንደተነገረ በፍርድ ቤቱ ውስጥ ረብሻ ተነሳ። ቄሶቹ መደንፋትና መሳደብ ጀመሩ። አንድ ቄስ የይሖዋ ምስክሮችን ጠበቃ በመስቀል መታውና በግድ መስቀሉን ካላሳለምኩህ ሲል ተናነቀው። ፖሊስ የግድ ጣልቃ ገባና የይሖዋ ምስክሮች በሰላም ሊወጡ ቻሉ።
ክሱ ከተሰረዘ በኋላ ከሳሾቹ በዘጠኙ የይሖዋ ምስክሮች ላይ አዲስ ክስ አዘጋጁ። ክሱ ለሚያዝያ 30, 1993 ተቀጠረ። ይህም የአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት የኮኪናኪስን ጉዳይ በተመለከተ ውሳኔ ከማስተላለፉ ልክ ከሦስት ሳምንት በፊት ማለት ነው። አሁንም ብዙ ቄሶች ተገኝተው ነበር።
የዘጠኙ ተከሳሾች ጠበቆች የምስክሮቹ ከሳሾች በፍርድ ቤት አልተገኙም ሲሉ አስቀድመው ተቃውሟቸውን አቀረቡ። አቃቤ ሕጉ አዲስ ክስ ለመመስረት ሲጣደፍ ለከሳሾቹ መጥሪያ ሳይሰጣቸው በመቅረቱ ከባድ ስህተት ፈጸመ። ስለዚህ የምስክሮቹ ጠበቆች ይህን ከባድ ስህተት መሠረት በማድረግ ፍርድ ቤቱ ክሱን እንዲሰርዝ ጠየቁ።
ከዚህ የተነሳ ዳኞቹ ፍርድ ቤቱን ትተው ወጡና ለአንድ ሰዓት ያህል ተመካከሩ። ዳኞቹ ሲመለሱም የፍርድ ቤቱ ፕሬዘዳንት ወደ ዘጠኙ ምስክሮች ጎንበስ በማለት ሁላችሁም ከክሱ ነፃ ናችሁ አላቸው።
በግሪክ ያሉ የይሖዋ ምስክሮች በዚህ ክስ ውጤትና የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የኮኪናኪስን ጉዳይ በተመለከተ በዚህ ዓመት ግንቦት 25 ባስተላለፈው ውሳኔ ደስተኞች ናቸው። ጸሎቶቻቸው ባስገኙት በዚህ ሕጋዊ ድል አማካኝነት ‘ለአምላክ ያደሩ በመሆንና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለው’ ክርስቲያናዊ ሕይወታቸውን መምራታቸውን መቀጠል ይችላሉ። — 1 ጢሞቴዎስ 2:1, 2
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሚኖስ ኮኪናኪስ ከባለቤቱ ጋር