በበረዶና በእሳት ምድር በጽናት መስበክ
አይስላንድ በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ መካከል በሰሜን አትላንቲክ የምትገኝ አገር ናት። በአርክቲክ ክልል የምትገኝ ብትሆንም ከባሕር ተነስቶ ውቅያኖሱን ሰንጥቆ የሚያልፈው ኃይለኛና ሞቃታማ ውኃ ተስማሚ የሆነ ሙቀት የሚያስከትል በመሆኑ የአየር ንብረቷ ከሚጠበቀው በላይ ነው። አይስላንድ በአውሮፓ ውስጥ ከፍተኛው የበረዶ ግግር ያለባትና በዓለም ውስጥ ካሉት ኃይለኛ እሳተ ገሞራ ካለባቸው ሥፍራዎች አንዷ በመሆኗ የበረዶና የእሳት ምድር የሚል ስያሜ ተሰጥቷታል። እንዲሁም ብዛት ባላቸው ፍልውኃዎቿና ሶልፋታራስ ተብለው በሚጠሩት እንፋሎትና ድኝ አዘል ጋዞችን በሚረጩት የእሳተ ገሞራ ስፍራዎቿ የታወቀች ናት።
ከአውሮፓ ደሴቶች በስፋት ሁለተኛ የሆነችው የዚህች ደሴት 260,000 ነዋሪዎች ቫይኪንግ የተባሉት ጐሣዎች ተወላጆች ሲሆኑ ወደዚህ ሥፍራ የፈለሱት ከ1,100 ዓመታት በፊት ነው። የአይስላንድ ቋንቋ በቫይኪንግ ዘመን ከነበረው ኦልድ ኖርስ ከሚባለው የስካንዲኔቪያ ቋንቋ ጋር አንድ ዓይነት ነው። የአይስላንድ ዜጎች በአብዛኛው በ13ኛው መቶ ዘመን የተጻፈውን የጥንቱን አፈታሪካቸውን ማንበብ በጣም ስለሚወዱ ቋንቋው ሳይለወጥ እንዳለ ቆይቷል ማለት ይቻላል።
በ16ኛው መቶ ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ በአይስላንድ ቋንቋ መተርጎም ጀመረ። “አዲስ ኪዳን” በ1540፣ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ በ1584 ወጣ። ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ የአገሩ መንግሥት ሃይማኖት የሆነው የኢቫንጀሊካል ሉተራን ቤተ ክርስቲያን ተከታይ ነው። ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ በአብዛኛዎቹ ሰዎች ቤት የሚገኝ ቢሆንም የአምላክ ቃል እንደሆነ አድርገው የሚያምኑት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ብዙዎቹ የአይስላንድ ዜጎች ሃይማኖትን በተመለከተ ላላ ያለ አመለካከት አላቸው። በጥቅሉ በራሳቸው አስተሳሰብ የሚመሩ ናቸው።
ምሥራቹ አይስላንድ ደረሰ
የመንግሥቱን ምሥራች መጀመሪያ የሰሙት የአይስላንድ ዜጎች በዚያን ጊዜ በካናዳ ይኖሩ ነበር። ከእነርሱ መካከል ጆርጅ ፍዮልኒር ሊንዳል ይገኝበታል። ወላጆቹ የአይስላንድ ዜጎች ስለነበሩ የአይስላንድ ቋንቋ ይናገር ነበር። ሕይወቱን ለይሖዋ አምላክ ከወሰነ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የምሥራቹ የሙሉ ጊዜ ሰባኪ ሆነ። በ1929፣ ይኸውም 40 ዓመት ሲሞላው በዚያ የበረዶና የእሳት ምድር ወደሚገኙት ሰዎች ምሥራቹን ይዞ ሄደ።
ለአንድ ሰው እንዴት ያለ ሰፊ ሥራ ነበር! አይስላንድ ከሰሜን እስከ ደቡብ 320 ኪሎ ሜትር ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ደግሞ 500 ኪሎ ሜትር ያህል ስፋት አላት። በተራሮች መሃል የሚገኘውን ጠባቡን ባሕረ ሰላጤና ባሕረ ገብ በሆኑ መሬቶች መሃል ያለውን አነስተኛ ባሕረ ሰላጤ ጨምሮ የባሕሩ ጠረፍ 6,400 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። በዚያ ወቅት አውራ ጎዳናዎችና መኪናዎች ወይም ሌላ ዓይነት ዘመናዊ የመጓጓዣ ዘዴዎች አልነበሩም ለማለት ይቻላል። ሆኖም ወንድም ሊንዳል በአሥር ዓመት ውስጥ ደሴቷን በሙሉ በማዳረስ በሺህ የሚቆጠሩ መጽሐፎችን አሠራጨ። በባሕሩ ዳርቻ በጀልባ ይጓዝ ነበር። የእርሻ ማሳዎቹን ሲጎበኝ አንዱ እርሱ እንዲጓዝበት ሌላው ደግሞ ጓዙን እንዲሸከምለት ሁለት ፈረሶችን ይጠቀም ነበር።
ለ18 ዓመታት ያህል በአይስላንድ ውስጥ ብቸኛው ምሥክር ወንድም ሊንዳል ነበር። ተግቶ ቢሠራም በዚያ ወቅት ከመንግሥቱ ጎን አቋም የወሰደ አንድም ሰው አልተመለከተም። መጋቢት 25, 1947 የመጀመሪያዎቹ የመጠበቂያ ግንብ የጊሊያድ ትምህርት ቤት ተመራቂዎች እዚያ ሲደርሱ የረጅም ጊዜ የብቸኝነት ኑሮው አበቃ። ተጨማሪ የመከሩ ሠራተኞች እንዲመጡ ላቀረባቸው ጸሎቶች በመጨረሻ ይሖዋ መልስ ሲሰጠው የተሰማውን ደስታ ልትገምቱ ትችላላችሁ። (ማቴዎስ 9:37, 38) ወንድም ሊንዳል በ1953 ወደ ካናዳ እስከተመለሰበት ጊዜ ድረስ በአይስላንድ አገልግሎቱን ቀጥሏል።
ለመከሩ ተጨማሪ ሠራተኞች
በ1947 የመጡት ሚስዮናውያን ሁለት የዴንማርክ ወንድሞች ነበሩ። ከሁለት ዓመት በኋላ ተጨማሪ ሚስዮናውያን መጡ። ወደ አይስላንድ ሄደው ከነበሩ ጥቂት ወንድሞችና እህቶች ጋር በመሆን የስብከቱን ሥራ ቀጠሉበትና በሺዎች የሚቆጠሩ ጽሑፎች አሠራጩ። አብዛኛዎቹ የአይስላንድ ዜጎች ኃይለኛ የማንበብ ፍቅር ያላቸው ናቸው፤ ሆኖም ብዙዎቹ ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ አልሰጡም። በመትከሉና በማጠጣቱ ሥራ 27 ዓመታት ካሳለፉ በኋላ ትዕግሥተኞቹ ወንድሞች የሥራቸውን ፍሬ ማየት ጀመሩ። በ1956 ሰባት አዲስ ሰዎች ከመንግሥቱ ጎን አቋም ወሰዱና ሕይወታቸውን ለይሖዋ ወሰኑ።
ባለፉት አሥር ዓመታት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሯል። በአሁኑ ጊዜ ሰባት ጉባኤዎችና በአንድ ገለልተኛ ስፍራ አንድ አነስተኛ ቡድን ያሉ ሲሆን በድምሩ 280 የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪዎች አሉ። እስቲ እነዚህን ጉባኤዎች ለመጎብኘት ወደ ደሴቲቷ የተለያዩ ክፍሎች እንጓዝ።
በዋና ከተማዋ አካባቢ
በእነዚህ ዓመታት ሁሉ በትዕግሥት የጸኑት ወንድሞችና እህቶች በብዙው ተባርከዋል። በአሁኑ ጊዜ በዋና ከተማዋ በሬይክጃቪክ ውስጥ ጥሩ ዕድገት የሚያሳዩ ሁለት ጉባኤዎች አሉ። በ1975 በተመረቀው ቅርጫፍ ቢሮ ህንጻ ውስጥ በሚገኝ ግሩም የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ይሰበሰባሉ።
ቀደም ሲል በ1956 ከተጠመቁት ሰባት ሰዎች መካከል ፍሪዮሪክና ኤዳ ይገኙበታል። “ሚስዮናውያኑ ይኖሩበት በነበረው ደርብ ላይ በሚገኝ አንድ ትንሽ ክፍል ውስጥ እንሰበሰብ እንደነበረ አስታውሳለሁ” ሲል ፍሪዮሪክ ይናገራል። “12 ወንበሮች የሚይዝ ክፍል ነበር፤ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ቁጥሩ ከወትሮው በላይ ሲጨምር የሚቀጥለውንም አነስተኛ ክፍል በር ከፍተን እንጠቀም ነበር። ዛሬ የመንግሥት አዳራሹን የሚሞሉ ሁለት ጉባኤዎች በመኖራቸው ሁኔታው ምንኛ የተለየ ሆኗል!”
ፍሪዮሪክ በመጀመሪያዎቹ ትልልቅ ስብሰባዎች ወቅት የምግብ አቅርቦት ክፍል ኃላፊ ሆኖ ያገለግል ነበር። “አብዛኛውን ሥራ አከናውን የነበርኩት እኔ ነኝ፤ በዚያው ጊዜም በፕሮግራሙ ላይ በየቀኑ ሦስት ወይም አራት ክፍል ማቅረቤ እንግዳ አልነበረም። ወጥ ቤት በምሠራበት ጊዜ ሽርጥ አሸርጥ ነበር። ንግግር የምሰጥበት ጊዜ ሲደርስ ኮቴን እለብስና እየተጣደፍኩ ወደ አዳራሹ እሄድ ነበር። በተደጋጋሚ ጊዜያት ወንድሞች ሽርጡን እንዳወልቅ ማስታወስ ነበረባቸው። በአሁኑ ጊዜ የፕሮግራሙን የተለያዩ ክፍሎች የመምራት ኃላፊነት የሚወስዱ ጥሩ ሽማግሌዎችን ጨምሮ ከ400 እስከ 500 የሚደርሱ ሰዎች በትልልቅ ስብሰባዎቹ ላይ ይገኛሉ። በምግብ አቅርቦት ክፍልም እርዳታ ለማበርከት የተዘረጉ ብዙ እጆች አሉ።”
ለሬይክጃቪክ የሚቀርበው ጉባኤ በምዕራብ በኩል 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ከፍላቪክ ነው። በመኪና የምናደርገው ጉዞ በእሳተ ገሞራ አመድ በተሸፈኑ ሜዳዎች ላይ ይወስደናል። አይስላንድ አሥር በመቶ በእሳተ ገሞራ አመድ የተሸፈነች ናት። በእነዚህ ሜዳዎች ላይ መጀመሪያ የሚታየው ተክል የድንጋይ ሽበት ነው፤ ሆኖም በቀድሞዎቹ የእሳተ ገሞራ ሜዳዎች ላይ እንደ ቀጋ ያሉ ተክሎችና አጫጭር ቁጥቋጦዎችን ታገኛላችሁ።
ከፍላቪክ ውስጥ የሚገኘው ጉባኤ የተቋቋመው በ1965 ሲሆን 19 አስፋፊዎች አሉት። በአቅራቢያው ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያና የአሜሪካ ወታደራዊ የጦር ሰፈር ይገኛል። ምንም እንኳን ምሥክሮቹ በጦር ሰፈሩ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መሥራት ባይችሉም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እየተመሩ ነው፤ የተወሰኑ ግለሰቦችም እውነትን ሰምተው ተቀብለዋል።
ከሬይጃቪክ በስተምስራቅ 55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በሰልፎስ ውስጥ ሌላ ጉባኤ ይገኛል። በዚህ ቦታ በአይስላንድ ውስጥ በስፋቱ አቻ የማይገኝለትን የከብት ርቢ ጣቢያን ጨምሮ ከብቶችና በጎች ያሉበት በልምላሜ የተሸፈነ እርሻ የሚካሄድበት ገጠር እንመለከታለን። እግረ መንገዳችንን ውብ በሆነው ሸለቆ ውስጥ በምትገኘው አነስተኛ ከተማ በከቨሮገርዚ በኩል እናልፋለን። በሸለቆው ውስጥ ከሚገኘው ፍልውኃ እንፋሎት ወደ ላይ ሲወጣ እንመለከታለን። ይህም በአገሪቷ ውስጥ ካሉት በጣም ሰፊ የፍልውኃ ሥፍራዎች አንዱ ነው። እነዚህን ሃብቶች ጥቅም ላይ ለማዋልና ሙቀት በሚሰጡ ከመስተዋት በሚሠሩ ቤቶች ውስጥ የሚመረቱ ቲማቲሞችን፣ ኪዩከምበርና የተለያዩ ዓይነት አበቦችን ለማፍራት ለአትክልት መትከያ የተዘጋጁ ቤቶችም አሉ።
በዚህ ሥፍራ አነስተኛ የሆነ ነገር ግን 19 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ያሉት አንድ ጠንካራ ጉባኤ አለ። ሲኩርዙርና ግቬዝሩን ስቮቮ ይህን አነስተኛ ቡድን ለመርዳት ጉባኤው በ1988 በተቋቋመበት ገደማ ከሬይክጃቪክ ተዛወሩ። በዚህ ጉባኤ ውስጥ ያለው ሽማግሌ ሲኩርዙር ብቻ ነው። የይሖዋ ምስክር ከመሆኑ ከአሥር ዓመታት በፊት በተለያዩ የሙዚቃ ቡድኖች ውስጥ ከበሮ በመምታት የታወቀ ሙዚቀኛ ነበር። ዛሬ መስኮት የማጽዳት ሥራ በመሥራት ይተዳደራል፤ እንዲሁም ሙዚቃም ያስተምራል። የሙዚቃ ተጫዋች ሆኖ ያሳለፈው የአኗኗር ዘይቤ አደንዛዥ ዕጽ መውሰድን፣ ከመጠን በላይ መጠጣትንና የትዳር መፍረስን የመሰሉ ችግሮች አስከትሎበታል። በአሁኑ ጊዜ ለሕይወቱ ዓላማ በማግኘቱና ይሖዋን ማገልገል በመቻሉ ምንኛ ደስተኛ ነው!
ወደ ምስራቅ ጫፍ
ሰልፎስን ትተን በአብዛኛው ጠባብና ወጣ ገባ በሆኑ የኮረኮንች መንገዶች ላይ 680 ኪሎ ሜትር አቋርጠን እንጓዛለን። በምሥራቅ ጠረፍ በሬይዙርፎርዞር ከተማ ውስጥ ወደሚገኘው ወደሚቀጥለው ጉባኤ እናቀናለን። በግማሽ ሰዓት ውስጥ በአይስላንድ እጅግ ታዋቂ የሆነውን ሄክላ የተባለውን እሳተ ገሞራ እንመለከታለን። ይህ እሳተ ገሞራ በዚህኛው መቶ ዘመን ውስጥ አራት ጊዜ ፈንድቷል።
በ1973 በቬስት ሞኔዮር (በዌስትማን ደሴቶች) ድንገተኛ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ተከሰተ። በጥቂት ሰዓታት ውስጥ 5,300 የሚያህሉት ነዋሪዎቿ በሙሉ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ከደሴቲቷ ወጥተው ወደ መሃል አገር ገቡ። ከተማዋ ከተጠገነች በኋላ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ቀስ በቀስ ተመለሱ። በአሁኑ ጊዜ በዚህ ቦታ ሁለት ምስክሮች ይኖራሉ፤ በዚህ አነስተኛ ኅብረተሰብ ውስጥ ለሚገኙት ሰዎችም ምሥራቹን ይሰብካሉ። ሌላ የሁለት ሰዓት ጉዞ ካደረግን በኋላ በአይስላንድ ውስጥ ግግር በረዶ ካለባቸው ሥፍራዎች ግርማ ሞገስ የተላበሰውን በጣም ትልቁን 8,300 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት የሚሸፍነውን የቮትኖያኩል ውብ እይታ በማየት እንማረካለን። እግረ መንገዳችንን ብዙ ውብ የሆኑ ፏፏቴዎችንና ወንዞችን አልፈን እንሄዳለን።
አሥር ሰዓት ያህል በመንገድ ላይ ካሳለፍን በኋላ ካሰብንበት ቦታ እንደርሳለን። በአይስላንድ ውስጥ በቅርብ ጊዜ የተቋቋመውን 12 አስፋፊዎች ያሉትን ጉባኤ በሬይዙርፎርዙር እናገኛለን። በ1988 መጨረሻ አካባቢ የሚስዮናዊ ቤት እስከተቋቋመበት ጊዜ ድረስ እዚህ ቦታ የሚኖር አንድም ምስክር አልነበረም። በአይስላንድ ውስጥ ከ1963 ጀምሮ ያገለገሉት ስዊድናውያኖቹ ሚስዮናውያን ባልና ሚስት ሸልና አይሪስ 15,000 ሕዝብ በሚገኝበት በዚህ ገጠር ውስጥ እንዲሠሩ ተመደቡ። ብዙዎች 500 ኪሎ ሜትር ያህል በተዘረጋው የባሕር ዳርቻ አጠገብ በትናንሽ የዓሣ ማጥመጃ ሰፈሮች ውስጥ ይኖራሉ።
ሸል እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በዚህኛው የአይስላንድ ክፍል ውስጥ ያለውን የመንግሥቱን ሥራ ይሖዋ አብዝቶ እንደባረከው ምንም አያጠራጥርም። በጥር 1, 1993 አንድ ጉባኤ የተቋቋመ ሲሆን ግሩም የሆነ ዕድገት ከሚያደርጉ ግለሰቦች ጋር ብዙ ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንመራለን። ወንድም ሊንዳል በፈረስ ላይ ሆኖ ከተጓዘ ወዲህ የመጓጓዣው ዘዴ የተለወጠ ቢሆንም ጨለማ ባጠላባቸው የክረምት ወራት በተራራው ላይ በበረዷማዎቹ መንገዶች አራቱም ጎማዎቹ መሽከርከር በሚችሉት ጂፕ መኪና እንኳን ለመጓዝ ሁልጊዜ ቀላል አይሆንም። አንድ ቀን በበረዷማዎቹ መንገድ ላይ ተንሸራተተና ሁለቴ ወይም ሦስቴ ተንከባሎ ቁልቁል ወደ ታች ወረደ። ያለምንም ጉዳት በመትረፋችን ምንኛ ተደስተን ነበር!”
በአይስላንድ ውስጥ 30 ዓመታት ካሳለፈች በኋላ አይሪስ እንዲህ በማለት ትናገራለች:- “ባለፉት ዓመታት እኛን ለመርዳት ከሌሎች አገሮች ብዙዎች መጡ። ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ተመልሰው ቢሄዱም በመትከሉና በማጠጣቱ ሥራ ትልቅ ድርሻ አበርክተዋል። እየደረሰ ያለውን መከር የማየት መብት ያገኘን በመሆኑ እዚህ መቆየት በመቻላችን ደስተኞች ነን። ይሖዋ ሥራውን እዚህም እያፋጠነው ነው።”
አብዛኛው ጭማሪ የተገኘው አዲሶች ለሥራ ባልደረቦቻቸው ስለሚመሰክሩ ነው። አትሊ እውነትን ከሚስዮናውያኖቹ ተማረና በሚሠራበት የኮንስትራክሽን ኩባንያ ውስጥ ለሌሎች መናገር ጀመረ። ባሁኑ ጊዜ ሁለቱ የሥራ ባልደረቦቹ በስብከቱ ሥራ እየተሳተፉ ሲሆን አንዱ ከሚስቱ ጋር ነሐሴ 1992 ተጠምቋል። ሦስተኛ የሥራ ባልደረባው ከምሥክሮቹ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እያጠና ነው።
ሰሜናዊውን አቅጣጫ ይዞ መጓዝ
ሬይሱርፎርዞርን ትተን ወደ ምዕራብ እናቀናለን። የሚቀጥለው ጉባኤ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአካሬሪ ከተማ ውስጥ ይገኛል። ልዩ የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ በዚህ ቦታ እንዲሠሩ ተመደቡ። ገና ከጅምሩ ሥራው ከአንዳንድ ቀሳውስት ኃይለኛ ተቃውሞ ገጠመው። የአካባቢው ጋዜጦች ሕዝቡ ከይሖዋ ምሥክሮች እንዲርቅ የሚያስጠነቅቁ ጽሑፎችን ይዘው ወጡ። ብዙዎቹ የከተማው ሰዎችም በመናፍስታዊ ሥራ የተጠላለፉ ነበሩ። ሆኖም በብዙዎቹ አቅኚዎችና ሚስዮናውያን ጽናት ምክንያት ዛሬ በዚህ ቦታ 35 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ያሉበት ንቁና አፍቃሪ የሆነ ጉባኤ አለ።
እዚህ ከሚገኙት ሽማግሌዎች አንዱ የሆነው ፍሪዮሪክ ዓሣ አጥማጅ ነበር። በ1982 የተካሄደውን የወረዳ ስብሰባ ከተካፈለ በኋላ የተማረው ነገር እውነት መሆኑን እርግጠኛ ሆነ። ለቤተሰቡ፣ ለጓደኞቹና ለሥራ ባልደረቦቹ ለመመሥከር ቆርጦ በመነሳት ወደ ኦካሬሪ ተመለሰ። ፍሪዮሪክ ከጉባኤው ጋር የበለጠ ጊዜ ማሳለፍ እንዲችል ዓሣ የማጥመድ ሥራውን ለመተው ዕቅድ አወጣ። የይሖዋ ምስክር ሊሆን በመዘጋጀት ላይ ስለሆነ እስከሚጋቡ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አንድ ላይ መኖር እንደማይችሉ ለፍቅረኛው ለሄልጋ ነገራት። እንዲሁም ፍሪዮሪክ ‘የማታምን ሴት እንዳያገባ’ ሲል መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና ፈለገ። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ሄልጋ ማጥናት ስትጀምር ያልጠበቀው ነገር ነበር። ሚያዝያ 1983 ተጋቡና ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ተጠመቁ። ውሎ አድሮ የፍሪዮሪክ እናትና እህቱ እውነትን ተቀበሉ።
የጉዞአችን ማብቂያ ሦስት ሸንተረሮችንና ብዙ ውብ ሸለቆዎችን አልፈን ከአካሬሪ 350 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምናገኛት አክሮኔስ ናት። እዚህ ቦታ የሚገኘው መንገድ አስፋልት ነው። ይህም አልፈናቸው ከመጣነው ወጣ ገባና ጠባብ የሆኑ ብዙ የኮረኮንች መንገዶች ጋር ሲወዳደር ለጉዞ የተመቸ ነው። በአክሮኔስ ሁለቱ ሽማግሌዎች ሆነው የሚያገለግሉበት አምስት አስፋፊዎች ያሉትን በአይስላንድ ውስጥ አነስተኛ የሆነውን ጉባኤ እናገኛለን። ይበልጥ አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ለማገልገል በሬይክጃቪክ ከሚገኙት ትልልቅ ጉባኤዎች ውስጥ አንዱን ትተው በመምጣት እዚህ መኖር የጀመሩትን ለመቄዶንያ ጥሪ ምላሽ የሰጡ ሁለት ቤተሰቦች ያቀፉ ናቸው። (ሥራ 16:9, 10) ይሖዋ ተክሉን እንደሚያሳድገው በመተማመን ከሁለት ዓመታት በላይ በዚህ ክልል ምሥራቹን በትዕግሥት ሰብከዋል። — 1 ቆሮንቶስ 3:6
ጭማሪ ሊመጣ እንደሚችል የሚጠቁሙ ብሩህ ሁኔታዎች
ከመሬት በሚወጣው ሙቀትና ሰው ሠራሽ በሆነ ብርሃን የሚሞቁ ለአትክልት መትከያ የተዘጋጁ ከመስተዋት የተሠሩ ቤቶችን በመጠቀም የአይስላንድ ገበሬዎች የተለያዩ ዓይነት ብዙ ፍራፍሬዎችን፣ ቅጠላቅጠሎችንና ሌሎች ተክሎችን ማፍራት ችለዋል። ልክ እንደዚሁም ምሥክሮቹ መንፈሳዊ እውነትን በመያዝ፣ ሞቅ ባለ መንፈስ ሰዎችን በማነጋገርና በይሖዋ መንፈስ ቅዱስ በረከት በአይስላንድ መስክ ላይ ግሩም ውጤቶችን አግኝተዋል።
በዚህ ዓመት 542 ሰዎች በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተዋል፤ ወደ 200 የሚጠጉ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም እየተመሩ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለማንም ጉባኤ ባልተመደቡ የአገልግሎት ክልሎች አገልግሉ ተብሎ ለሚሰጠው ማበረታቻ የተገኘው አዎንታዊ ምላሽ በዚህ ሰፊ ደሴት ውስጥ የሚገኙ በግ መሰል ሰዎች ሁሉ የመልካሙን እረኛ የኢየሱስ ክርስቶስን ድምፅ እንደሚሰሙ እንድንተማመን ያደርገናል። (ዮሐንስ 10:14–16) ባለፉት 64 ዓመታት የበረዶና የእሳት ምድር በሆነችው አገር ምሥራቹን በመስበክ ከፍተኛ የሆነ ትዕግሥትና ጽናት ላሳዩት የታመኑ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንዴት ያለ አስደሳች ውጤት ነው!
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሬይክጃቪክ
ቮትኖያኩል
አኩሪየሪ
አክሮኔስ
ከፍላቪክ
ሰልፎስ
ቬስትሞኔዮር
ሬይዙርፎርዞር
ሔከላ
ጌይሲር
[ምንጭ]
Based on map by Jean-Pierre Biard