ልክ እንደ ፌንጣ ናቸው
በበጋ ወራት በመስክ ላይ በእግርህ ተንሸራሽረህና በምትሄድበት መንገድ ላይ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ፌንጣዎች ሲዘሉ አይተህ ታውቃለህን? ትኩረት ባትሰጣቸውም በየትም ቦታ የሚገኙ ይመስላሉ። ጉዳት የማያደርሱና ከቁጥር የማይገቡ መስለው ይታያሉ።
ሆኖም ፌንጣዎች ከቁጥር የማይገቡ መሆናቸው ለሰው ዘር ተስማሚ ምሳሌ ሆነው እንዲያገለግሉ ያደርጋቸዋል። ምንም እንኳን አንዳንድ ታላላቅ ሰዎች ራሳቸውን እጅግ ከፍ አድርገው ቢመለከቱም ፈጣሪያችን ግን እነርሱን የሚመለከተው እንደዚያ አይደለም። የእሱ ነቢይ የነበረው ኢሳይያስ:- “እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀመጣል፣ በእርስዋም የሚኖሩት እንደ አንበጣ [ፌንጣ አዓት] ናቸው” ብሏል። — ኢሳይያስ 40:22
ሰው ከፌንጣ በማሰብ ችሎታና በኃይል እጅግ ታላቅ እንደሆነ ሁሉ ይሖዋ አምላክም ግርማ ሞገሱ፣ ኃያልነቱና ጥበቡ እዚህ ግባ ከማይባለው የሰው ልጅ የላቀ ያደርገዋል። ይሁን እንጂ የአምላክ ታላቅ ባሕርይ ፍቅር ነው። እርሱን የምናፈቅረውና የምንታዘዘው ከሆነም አቻ የሌለው ፍቅሩ እንዲያስብልን፣ እንዲረዳንና ከአደጋ እንዲያስጥለን ይገፋፋዋል። ከቁጥር እንደማይገቡት ፌንጣዎች ብንሆንም እንኳን ይሖዋ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ይይዘናል። መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል:- “እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው? በላይ የሚኖር፤ በሰማይና በምድር የተዋረዱትን የሚያይ፤ . . . ችግረኛን ከመሬት የሚያነሳ።” — መዝሙር 113:5–7
ይህ መዝሙር እንደሚገልጽልን ይሖዋ ለዝቅተኛ ሰዎች የእርዳታ እጁን በፍቅር ይዘረጋላቸዋል። አዎን፤ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ‘አምላክን ለማግኘት የሚፈልጉትን’ ይረዳቸዋል። (ሥራ 17:27) አልፎ ተርፎም አምላክን የሚፈልጉትና የሚያገለግሉት በእርሱ ዘንድ ክቡር ናቸው። (ከኢሳይያስ 43:4, 10 ጋር አወዳድር።) በዚህ መንገድ ከቁብ የማይቆጠረው ፌንጣ ከቁጥር የማንገባ መሆናችንና ለታዛዥ ሰዎች ወዳጅነቱንና ይገባናል የማንለው ደግነቱን የሚያሳየው ሁሉን ማድረግ የሚችለውን የፈጣሪያችንን ፍቅር መለስ ብለን እንድንመለከት ይረዳናል። ለአምላክ ፍቅር አድናቆት እያሳየህ ነውን?