የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 10/15 ገጽ 8-11
  • በትዕግሥት መጠበቅን ለመማር ያለብን ችግር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በትዕግሥት መጠበቅን ለመማር ያለብን ችግር
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በትዕግሥት መጠበቅን የመማር ጥበብ
  • ለብዙዎች አዲስ የሆነ ፈታኝ ሁኔታ
  • ከሌሎች መማር
  • መልካሙን ገድል መጋደል
  • በሁሉም ነገር በትዕግሥት መጠበቅን መማር
  • በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ ናችሁ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
  • ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
  • የነጠላነት ኑሮ የኢኮኖሚ ችግር ባለበት ጊዜ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ይሖዋን በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2021
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 10/15 ገጽ 8-11

በትዕግሥት መጠበቅን ለመማር ያለብን ችግር

እኛ የሰው ልጆች ለመቀበል ከሚያዳግቱን ከባድ ትምህርቶች አንዱ የምንፈልጋቸውን ነገሮች ለማግኘት በትዕግሥት መጠበቅን መማር ሳይሆን አይቀርም። ትንንሽ ልጆች በተፈጥሮአቸው ትዕግሥት የለሾች ናቸው። ትኩረታቸውን የሳበውን ነገር ሁሉ ማግኘት ይፈልጋሉ፤ እርሱንም በቅጽበት ለማግኘት ይሻሉ! ይሁን እንጂ የሚፈለግ ነገር ሁሉ ወዲያው ሊገኝ የማይችል መሆኑ አሌ የማይባል እውነታ እንደሆነ ከተሞክሮ ተረድተኸው ሊሆን ይችላል። አግባብነት ያላቸው ፍላጎቶች ቢሆኑም እንኳን እነዚህን ፍላጎቶች ለማርካት የሚቻልበትን ተገቢ ጊዜ በትዕግሥት መጠበቅን መማር አለብን። ብዙዎች በትዕግሥት መጠበቅን ተምረዋል፤ ሌሎች ዕድሜ ልካቸውን ሳይማሩት ይኖ⁠ራሉ።

መለኮታዊ ተቀባይነት ለማግኘት የሚሹ ሰዎች በትዕግሥት መጠበቅን የሚማሩባቸው ለየት ያሉ ምክንያቶች አሏቸው። ከክርስትና ዘመን በፊት ይኖር የነበረው የይሖዋ አገልጋይ ኤርምያስ “ለእኛ የሚበጀን የእርሱን አዳኝነት በትዕግሥት መጠበቅ ብቻ ነው” ሲል ይህን ነጥብ ጫን አድርጎ ገልፆታል። ከጊዜ በኋላ ክርስቲያኑ ደቀ መዝሙር ያዕቆብ “እንግዲህ፣ ወንድሞች ሆይ፣ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ” ብሏል። — ሰቆቃው ኤርምያስ 3:​26 የ1980 ትርጉም፤ ያዕቆብ 5:7

ይሖዋ መለኮታዊ ዓላማዎቹን የሚፈጽምበት የራሱ ፕሮግራም አለው። እርሱ በወሰነው ጊዜ የሚያከናውናቸውን አንዳንድ ነገሮች በትዕግሥት መጠበቅ የሚሳነን ከሆነ ቅር ልንሰኝና ልንበሳጭ፣ በዚህም ሳቢያ ደስታችን ሊጠፋ ይችላል። ነህምያ ለአገሩ ሰዎች:- “የእግዚአብሔርም ደስታ ኃይላችሁ ነውና” እንዳለው ደስታ ያጣ የአምላክ አገልጋይ በመንፈሳዊ ደካማ ይሆናል። — ነህምያ 8:10

በትዕግሥት መጠበቅን የመማር ጥበብ

ነጠላ የሆኑ ሰዎች ለማግባት ወይም ልጆች የሌላቸው ባልና ሚስቶች ልጆች እንዲኖራቸው መፈለጋቸው በተፈጥሮ ያለ ፍላጎት ነው። ከዚህም በላይ ተገቢ የሆኑ ፍላጎቶቻቸንን ለማርካት መፈለጋችን ስህተት አይደለም። የሆነ ሆኖ በሥርዓቱ ማብቂያ ደፍ ላይ እንደምንገኝና በመጪው አዲስ ሥርዓት አምላክ ‘እጁን ከፍቶ ሕይወት ላለው ሁሉ መልካምን ነገር እንደሚያጠግብ’ ስለሚያምኑ ብዙ ክርስቲያኖች ከእነዚህ ፍላጎቶች አንዳንዶቹ ይበልጥ ተስማሚ በሆነ ጊዜ እንዲሟሉላቸው በትዕግሥት ለመጠበቅ ወስነዋል። — መዝሙር 145:​16

ይህ ጥልቅ መሠረት ያለው ክርስቲያናዊ ተስፋ የሌላቸው ሰዎች ግን አንድን ነገር ለሌላ ጊዜ የሚያስተላልፉበት ምክንያት እምብዛም አይታያቸውም። “በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ” በሚሰጠው በይሖዋ ላይ እምነት ስለሚጐድላቸው ጨርሶ ላይመጡ ይችላሉ እያሉ የሚጠራጠሩባቸውን ነገሮች ወደፊት ይሆናሉ ብሎ የመጠበቅን ጥበባዊነት አጠያያቂ ያደርጉታል። “ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣ” በሚል መፈክር እየተመሩ ይኖራሉ። — ያዕቆብ 1:​17፤ 1 ቆሮንቶስ 15:​32፤ ኢሳይያስ 22:13

በበለጸጉት አገሮች የንግዱ ማስታወቂያ ዓለም አሁን በግልጽ የሚታየውን ቶሎ እርካታ የማግኘት ዝንባሌ ይጠቀምበታል። ሰዎች ራሳቸውን እንዲያቀማጥሉ ግፊት ይደረግባቸዋል። የንግዱ ዓለም ዘመናዊ ምቾትና ቅንጦት የግድ አስፈላጊ ነገሮች እንደሆኑ አድርገን እንድናምን ይፈልጋል። በተለይ የብድር ገንዘብ ማግኛ በሆኑ ወይም በብድር ዕቃ በሚገዛባቸው ካርዶች፣ በየጊዜው ተከፍለው በሚያልቁ የክፍያ አሠራሮችና “በዱቤ” ሁሉንም ነገር አሁንኑ ማግኘት የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ እነዚህን የቅንጦት ዕቃዎች የማናገኝበት ምን ምክንያት አለ? የሚል ክርክር ይቀርባል። ከዚህም ሌላ ‘ጥሩ ነገር ማግኘት የሚገባህ ሰው ነህ፤ ራስህን አታስጨንቅ! አሁን ካላገኘኸው ጭራሽኑ ለሁልጊዜው ላታገኘው እንደምትችል አስታውስ!’ በማለት የሚያስተጋቡ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ መፈክሮች አሉ።

በአንጻሩ ደግሞ ታዳጊ በሆኑ አገሮች ውስጥ የሚገኙ በአሥር ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ወይም ከዚያ ባነሰ ሁኔታ ውስጥ ይኖራሉ። የሰውን ልጅ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት መዛባትና ፍትህ አልባነት ከዚህ የበለጠ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነገር ሊኖር ይችላልን?

በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በትዕግሥት ለመጠበቅ አሻፈረኝ በማለታቸው ወይም ቢያንስ ቢያንስ በትዕግሥት ለመጠበቅ የሚያበቃ ምንም ምክንያት ስለማይታያቸው ወዲያውኑ ማግኘት የሚፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት በከባድ ዕዳ ውስጥ በመዘፈቃቸው በትዕግሥት መጠበቅን መማር ጥበብ እንደሆነ ታይቷል። እንደ ህመም ወይም ሥራ ማጣት የመሳሰሉ ያልታሰቡ ሁኔታዎች ከባድ ውድቀት ሊያመጡባቸው ይችላሉ። ፍራንክፈርተር አልገማይነ ሴቱንግ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ በጀርመን ውስጥ አንድ ሚልዮን ሰዎች ለምን ቤት አልባ እንደሆኑ ሲያትት “ብዙውን ጊዜ የቤት እጦት ሥራ አጥነትን ወይም ከባድ የሆነ ዕዳን ተከትሎ የሚመጣ ነገር መሆኑ የተለመደ ነው” ብሏል።

ዕዳቸውን መክፈል የተሳናቸው እንዲህ የመሰሉ ብዙ ግለሰቦች አሳዛኝ የሆነ የቤት ወይም የንብረት ማጣት ይደርስባቸዋል። ውጥረት እየጨመረ ሲሄድ ደግሞ በቤተሰብ ውስጥ አለመግባባት ያስከትላል። ያዘመሙ ትዳሮች መፍረስ ይጀምራሉ። የመንፈስ ጭንቀትና ሌሎች የጤንነት ችግሮች የተለመዱ ነገሮች ይሆናሉ። ክርስቲያኖች ደግሞ በመንፈሳዊ ተዳክመው ወደ ተሳሳተ አስተሳሰብና ተገቢ ወዳልሆነ ተግባር ሊያመሩ ይችላሉ። ጥበብ በጎደለው ሁኔታ ሁሉንም ነገር ለማግኘት መፈለግ የጀመሩ ሰዎች ጅምራቸው ውጤት አልባ ሆኖ ይደመደማል።

ለብዙዎች አዲስ የሆነ ፈታኝ ሁኔታ

ኢየሱስ መጠንቀቅ እንደሚኖርብን በግልጽ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ።” (ማርቆስ 4:​19) ኢየሱስ የተናገረላቸውን የኢኮኖሚ ችግሮች ጨምሮ ስጋት የሚፈጥሩ ነገሮችን አሸንፎ ያስወገደ አንድም የፖለቲካ ሥርዓት እንደሌለ ማስታወስ ይኖርብናል።

በአሁኑ ጊዜ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች የጣሉት ኮሚኒዝም በመንግሥት ዕዝ ሥር በሚካሄድ ኢኮኖሚ አማካኝነት ሁሉንም ሰው እኩል ለማድረግ ሞክሮ ነበር። ከነፃ ገበያ ሥርዓት ጋር ሲወዳደር የኮሚኒስቱ ሥርዓት በእነዚህ አገሮች ለሚገኙት ግለሰቦች በአብዛኛው የካፒታሊስቱ ሥርዓት መስጠት የተሳነውን መጠነኛ የሆነ የኢኮኖሚ ዋስትና አስገኝቶላቸው ነበር። ያም ሆኖ ኢየሱስ የተናገረለት ሥጋት በሸቀጣሸቀጥ እጥረትና የግል ነፃነት በተመናመነበት መልኩ መኖሩ አልቀረም።

በአሁኑ ወቅት ከእነዚህ አገሮች ብዙዎቹ የንግድ ገበያ ኢኮኖሚን በማስተዋወቅ ዜጎቻቸውን አዲስ በሆነ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ከተዋቸዋል። በቅርቡ የወጣ አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “ለነገሮች እንግዳ መሆናቸው የምዕራቡ ዓለም የፍጆታ መጠን ላይ በፍጥነት ለመድረስ ካለው ፍላጎት ጋር ተዳምሮ ችግር ፈጥሯል።” ይህን ከግቡ ለማድረስ “በምሥራቅ ጀርመን በሚገኘው በአዲሱ ለንዴር ውስጥ ቁጥራቸው እያደገ የመጣ ሰዎች ወደማይወጡበት የዕዳ ማጥ ውስጥ እየተዘፈቁ ነው።” ሪፖርቱ አክሎ:- “በአዲሱ የኢኮኖሚ ነፃነት ከተገኘው የመጀመሪያ ደስታና ፍንደቃ በኋላ ፍርሃትና ተስፋ መቁረጥ እየተስፋፋ ነው” ይላል። ሥጋቱ እንዳለ ነው፤ ብቻ የካፒታሊዝምን ካባ ለብሷል።

የበለጠ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነት መገኘቱ ለኢኮኖሚ መሻሻል አዲስ በር ከፍቷል። በመሆኑም ብዙ ግለሰቦች የራሳቸውን የንግድ ሥራ ለመጀመር ወይም የተሻሉ የሥራ አጋጣሚዎችን ለማግኘት ወደ ሌላ አገር በመሄዱ ሐሳብ ሊፈተኑ ይችላሉ።

እንደነዚህ ያሉ ውሳኔዎች የግል ጉዳዮች ናቸው። አንድ ክርስቲያን የኢኮኖሚ ሁኔታዎቹን ለማሻሻል መፈለጉ ስህተት አይደለም። “ለእርሱ ስለሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው” የሚለውን ቃል በማስታወስ ቤተሰቡን በተሻለ መንገድ ለመያዝ ፈልጎ ሊሆን ይችላል። — 1 ጢሞቴዎስ 5:8

ስለዚህ ሌሎች የሚወስዱትን ውሳኔ መተቸት ተገቢ አይደለም። የዚያኑ ያህል ደግሞ ክርስቲያኖች ወጥመድ ሊሆንባቸው በሚችል ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ በመዘፈቅ ከኢኮኖሚ ችግሮች እፎይታን ለማግኘት መፈለግ ጥበብ አለመሆኑን ማስታወስ ይኖርባቸዋል። እንደዚሁም መንፈሳዊ ግዴታዎችንና ፍላጎቶችን ቸል እንድንል በሚያደርግ መንገድ ከኢኮኖሚ ችግር እፎይታን ለማግኘት መፈለግ ስህተት ነው።

ከሌሎች መማር

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በነበሩት ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ጀርመናውያን በጦርነት ከፈራረሰችው አውሮፓ ወደ ሌሎች አገሮች በተለይም ወደ አውስትራሊያና ወደ ካናዳ ሄደዋል። ብዙዎቹ በዚህ መንገድ የኢኮኖሚ ሁኔታቸውን ማሻሻል ቢችሉም አንዳቸውም ቢሆኑ ኢየሱስ ከተናገረለት የኢኮኖሚ ሥጋት ማምለጥ አልቻሉም። የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረግ ጥረት አንዳንድ ጊዜ የትውልድ አገርን መናፈቅ፣ እንግዳ የሆነ ቋንቋ መማር፣ አዲስ ምግቦችን መልመድ፣ ልዩ የሆኑ ባህሎችን መቀበል፣ ከአዲስ ጓደኞች ጋር ተግባብቶ መኖር ወይም ልዩ የሆኑ አመለካከቶችን መቋቋምን የመሰሉ አዲስ ችግሮችን ይፈጥራል።

ከእነዚህ አገር ከቀየሩት መካከል አንዳንዶቹ የይሖዋ ምስክሮች ናቸው። አብዛኛዎቹ አገርን ለቆ ከመሄድ ጋር ብቻ የተያያዙ መንፈሳዊነታቸውን ሊያዳፍኑ የሚችሉ ችግሮችን በመቋቋማቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ሆኖም በችግሮቹ የተሸነፉም አልጠፉም። አንዳንዶች አታላይ የሆነው የብልጽግና ሰለባ ሆነዋል። ቲኦክራሲያዊ ዕድገታቸው ከኢኮኖሚ ደህንነታቸው ጋር እኩል ሊራመድ አልቻለም።

በእርግጥም ይህ ሁኔታ ጥበብ የጎደላቸውን ውሳኔዎች ከማድረግ በፊት ሁኔታችንን በጥንቃቄ ማመዛዘኑ ጥበብ መሆኑን ያሳያል። ቁሳዊ ነገሮችን የመውደድ ዝንባሌዎች ክርስቲያኖች እንዲሠሩት ለአንዴና ለመጨረሻ በተሰጣቸው ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ያለንን እንቅስቃሴ ያዳክምብናል። ዜጎቹ ከኢኮኖሚ ሥጋት ነፃ የሆኑበት አንድም አገር ስለሌለ የትም እንኑር የት ይህ እውነት መሆኑ አይቀሬ ነው።

መልካሙን ገድል መጋደል

ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንዲህ ሲል አሳስቦታል:- “ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል [ለአምላክ ያደሩ መሆንን አዓት] እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል። መልካሙንም የእምነት ገድል ተጋደል፣ የተጠራህለትንም የዘላለም ሕይወት ያዝ።” ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖችም:- “የምትደላደሉ፣ የማትነቃነቁም፣ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ” ብሏቸዋል።  — 1 ጢሞቴዎስ 6:​11, 12፤ 1 ቆሮንቶስ 15:58

ፍቅረ ንዋይን ተዋግቶ ለማሸነፍ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ይህን ጥሩ ምክር መከተል ነው። እውነትም አንድ ክርስቲያን የሚሠራው ብዙ ሥራ አለ! የመንግሥቱ ሰባኪዎች ቁጥር ከፍተኛ ባልሆነባቸው አገሮች በጣም ብዙ ሰዎች ለእውነት ያላቸው ግንዛቤ የተወሰነ ነው። ኢየሱስ:- “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው” በማለት በትክክል አስቀድሞ ተናግሯል። — ማቴዎስ 9:37

በእነዚህ አገሮች ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ጭንቀት በፊታቸው ካለው መንፈሳዊ ሥራ እንዲያዘናጋቸው ከመፍቀድ ይልቅ የይሖዋ ምስክሮች በወቅቱ ባሉት አጋጣሚዎች ሙሉ በሙሉ ይጠቀማሉ። ለጊዜው ሥራ በሚፈቱበት ጊዜም ብዙዎቹ የስብከት እንቅስቃሴያቸውን ሰፋ ያደርጉታል። አገልግሎታቸው ለይሖዋ የሚቀርበውን ምስጋና ከመጨመሩም በላይ የኢኮኖሚ ችግሮቻቸውን ለመቋቋም የሚያስፈልገውን ደስታ ይሰጣቸዋል።

እነዚህ ምስክሮች ለስብከቱ ሥራ ቅድሚያውን በመስጠት የኢኮኖሚ ችግሮቻቸውን በሁለተኛ ደረጃ ያስቀምጧቸዋል። ይህም በዓለም ዙሪያ ለሚገኙት ወንድሞቻቸው ይሖዋ እንደሚንከባከባቸው ያላቸውን ጠንካራ እምነት ያሳያል። የአምላክ የተስፋ ቃል እንዲህ ይላል:- “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።” — ማቴዎስ 6:33

እውነተኛ አምልኮ መልሶ ከተቋቋመበት ከ1919 ጀምሮ ይሖዋ ሕዝቦቹ እንዲቀዘቅዙ አልፈቀደም። ከባድ በሆነ ስደትና በአንዳንድ ቦታዎችም ለአሥርተ ዓመታት በእገዳዎች ሥር ባደረጓቸው እንቅስቃሴዎች ወቅት ጠብቋቸዋል። የይሖዋ ምስክሮች ዲያብሎስ በስደት ያልተሳካለትን ነገር መሠሪ በሆነው የፍቅረ ንዋይ ወጥመድ እንዳይሳካለት ለመታገል ቆርጠዋል።

በሁሉም ነገር በትዕግሥት መጠበቅን መማር

ሰፋፊ የመንግሥት አዳራሾች፣ ውድ የሆኑ የድምፅ ማጉያ መሣሪያዎች፣ የክልል ስብሰባ አዳራሾችና ማራኪ የሆኑ የቤቴል ቤቶች ለአምላክ ክብር ያመጣሉ፤ እንዲሁም ሕዝቡን እየባረከ እንዳለ ያለአንደበት ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። ሥራው ለረጅም ጊዜ ታግዶ በቆየባቸው አገሮች የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች በዚህ ረገድ ሌሎች አገሮች የደረሱበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ መሥራት እንዳለባቸው ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ትልቁ ቁም ነገር በመንፈሳዊ ዕድገት በማድረግ የመቀጠሉ ጉዳይ ነው። በቁሳዊ መንገድ ይሖዋ እየባረከን መሆኑን የሚያሳዩ ውጫዊ ምልክቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው ይመጣሉ።

ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች የግል ፍላጎቶችን በመከታተል ረገድ ጠንቃቆች መሆን ያስፈልጋቸዋል፤ አለዚያ አንዳንድ ቁሳዊ ነገሮች ሳይኖሩን ለረዥም ጊዜ ቆይተናልና አሁንስ ይብቃን የሚል ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ሁኔታዎች ካለው አለመመጣጠን ለመገላገል መናፈቁ ያለ ነገር ነው፤ ሆኖም የይሖዋ ሕዝቦች የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ እፎይታን ለማግኘት እንደሚናፍቁ አይዘነጉም። ዓይነ ስውሮች እንደገና የሚያዩበትን፤ ሥር የሰደደ ህመም ያለባቸው ጤንነታቸው የሚመለስበትን፣ የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ሁሉም ነገር ብሩህ የሚሆንበትን፣ የሚወዱት ዘመድ ወይም ወዳጅ የሞተባቸው ሰዎች ደግሞ የሚያፈቅሩአቸውን ሙታን ዳግም ማየት የሚችሉበትን ጊዜ ይናፍቃሉ።

ባሉት ሁኔታዎች የተነሳ ማንኛውም ክርስቲያን ለችግሮቹ መፍትሄ ለማግኘት በሆነ መልኩ የይሖዋን አዲስ ዓለም በትዕግሥት እንዲጠብቅ ይገደዳል። ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፤ ‘ምግብና ልብስ ካለኝ በእነዚህ ነገሮች መርካትና ከኢኮኖሚ ችግሮች እፎይታን ለማግኘት በትዕግሥት መጠበቅ አይኖርብኝምን?’ — 1 ጢሞቴዎስ 6:8

በይሖዋ ሙሉ በሙሉ የሚተማመኑ ክርስቲያኖች በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኞች ከሆኑ ተገቢ የሆኑ ፍላጎቶቻቸው ሁሉ በቅርቡ እንደሚሟሉላቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። ማንም ሰው በትዕግሥት መጠበቁ ከንቱ አይሆንም። የጳውሎስን ቃላት ደግመን እንናገራለን:- “ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፣ የማትነቃነቁም፣ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።” — 1 ቆሮንቶስ 15:58

እንግዲያው በትዕግሥት መጠበቅን መማር ይህን ያህል ትልቅ ችግር ሊሆን ይገባዋልን?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በትዕግሥት መጠበቅን መማር ሕይወትህን ከሕልፈት ሊያድነው ይችላል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ