የተለያዩ ገጽታዎች በሚንጸባረቁባት ምድር ላይ መስበክ
ሰዎች ስለ አውስትራሊያ ሲያስቡ ካንጋሮ፣ ኩዋላ፣ ውምባትና ፕላቲፐስ የተባሉ እንስሳት እንዲሁም አየርስ የተባለ አለትና ታላቁ አለታማ የባሕር ጠረፍ የሚሉት ስሞች ወደ አእምሮአቸው ይመጣሉ። ነገሩ ሊያስገርም ቢችልም አብዛኛዎቹ የአውስትራሊያ ነዋሪዎች አየርስ የተባለውን አለት ወይም ታላቁን አለታማ የባህር ጠረፍ ጎብኝተው ወይም ኩዋላ፣ ውምባት ወይም ፕላቲፐስ የተባሉትን እንስሳት ከእንስሳት ፓርክ ውጪ አይተው አያውቁም። ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት 17.3 ሚልዮን ከሆነው የአገሪቱ ሕዝብ ብዛት ውስጥ 85 በመቶው በባህር ዳርቻ ላይ በሚገኙት አምስት ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ የከተማ ነዋሪዎች በመሆናቸው ነው።
አንድ ሰው የባህሩን ዳርቻ ትቶ 200 ኪሎ ሜትር ያህል ወደ መሐል አገር ሲጓዝ ወደ ዝነኛው የአህጉሩ የገጠር አካባቢ ይደርሳል። ምድሩ ለምለም ከሆነ ጥቅጥቅ ያለ ደንና ለም ከሆነ የእርሻ መሬት ሞቃትና ደረቅ ወደ ሆነ አየር፣ ቁጥቋጦዎችና የጠወለገ ሣር ብቻ ወዳሉበት ገላጣ ገጠር እየተለወጠ ይሄዳል። ይሁን እንጂ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ይገኛሉ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ስኩዌር ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍኑ ለበግና ለከብት ርቢ የተከለሉ ሰፋፊ መሬቶች አሉ። ወደ መሐል አገር ጠለቅ ብለን ስንገባ የሚያቃጥል ሙቀት ያላቸው በረሃዎች ይገኛሉ። አንዳንድ ጊዜ በነዚህ በረሃዎች ተገቢው ጥንቃቄ ካልተወሰደ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ።
ምሥራቹ ተስፋፋ
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው የአምላክ መንግሥት የምሥራች በዚህ የአውስትራሊያ ምድር ውስጥ እየተሰበከ ያለው። በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይሖዋ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ የሰጠውን የተስፋ ቃል ሰምተው እርምጃ በመውሰድ ላይ ናቸው። የአስፋፊዎች ቁጥር ባለፈው የአገልግሎት ዓመት ከ57,000 በላይ ወደሆነ ከፍተኛ ቁጥር ላይ የደረሰ ሲሆን ይህም ከአሥር ዓመት በፊት ከነበረው እጥፍ ነው ለማለት ይቻላል። ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ አስፋፊዎች እንደ አብዛኛው ሕዝብ በጠረፍ ከተሞች የሚኖሩ ቢሆንም ምሥራቹ መሐል አገር ድረስ ተስፋፍቷል።
በዚህ የተለያዩ ገጽታዎች ባሉበት ሰፊ ምድር ውስጥ የሚካሄደው ስብከት ምን እንደሚመስል ፍንጭ ለማግኘት እስቲ ከአምስቱ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች መካከል ከአንዱና ከሚስቱ ጋር ሆነን ራቅ ባሉ የገጠር ሥፍራዎች የሚገኙትን አንዳንድ ጉባኤዎች እንጎብኝ። ጉዞአቸው ከ4.7 ሚልዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር በላይ የሆነ ቦታን ማለትም ምዕራብ አውስትራሊያን፣ የኩዊንስ ላንድን ግማሽ ግዛት እንዲሁም ሰሜናዊውን የግዛት ክልል ይሸፍናል። የቀድሞዋን የሶቭዬት ኅብረት ግዛት የነበረውን ሳይጨምር አውሮፓን ያህላል ማለት ይቻላል።
ጉዞአችን የምዕራብ አውስትራሊያ ዋና ከተማ ከሆነቸው ከፐርዝ ይጀምራል። በዚህች ሙሉ በሙሉ ዘመናዊ በሆነችው 1.2 ሚልዮን ሰዎች በሚኖሩባት ከተማ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ 49 የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤዎች አሉ። ከእንግሊዝኛው ጉባኤ ሌላ የግሪክኛ፣ የጣሊያንኛ፣ የፖርቹጊዝና የስፓኒሽ ጉባኤዎች በተጨማሪም በሌሎች ቋንቋዎች አነስተኛ ቡድኖች አሉ። አቦርጂን ከተባሉ ጎሳዋች የመጡ ወንድሞችና እህቶች ብቻ የያዘ አንድ ጉባኤ አለ። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች የስብከት ሥራቸው በይበልጥ የሚያካሂዱት በእነዚህ የአህጉሪቷ ተወላጆች በሆኑ ሰዎች መካከል ነው። በአሁኑ ጊዜ ከእነዚህ ትሁት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ለመንግሥቱ መልእክት ምላሽ እየሰጡ ነው። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ከትልልቆቹ ከተሞች ውጪ ያሉት ሁኔታዎች ምን ይመስላሉ?
ከፐርዝ ተነስተን የክልል ስብሰባ ወደሚካሄድበት በሰሜን 1,800 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ ፓርት ሄድላንድ እናቀናለን። 289 ከሚሆኑት ተሰብሳቢዎች መካከል አብዛኛዎቹ እዚህ ቦታ ለመገኘት ከ200–700 ኪሎ ሜትር የሚያህል መንገድ ተጉዘዋል። እነዚህ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የመኪና ጎማዎችን የሚበሱ ሹል ድንጋዮች ያሉባቸውን ኮረኮንቻማ መንገዶች አቋርጠው ራቅ ካሉ ሥፍራዎች የሚመጡ ሲሆን ቅርብ ነው ተብሎ የሚታሰበው ጉባኤ እንኳ 250 ኪሎ ሜትር ያህል ይርቃቸዋል። በዚህ ቦታ የሚገኙ ሦስት ጉባኤዎች በአጭር ጊዜ ሰርቶ በመጨረስ ዘዴ ተጠቅመው በቅርቡ የመንግሥት አዳራሾችን ሰርተዋል።
ራቅ ብለው በሚገኙ ሥፍራዎች በአጭር ጊዜ የተሠሩ አዳራሾች
አንድ የመንግሥት አዳራሽ በእነዚህ ሥፍራዎች በመሥራትና በዋና ከተማዎችና በትልልቅ ከተማዎች ውስጥ በመሥራት መካከል እንዴት ያለ ልዩነት አለ! አብዛኛዎቹ ለግንባታ የሚሆኑ እቃዎች በመኪና ተጭነው የሚመጡት በደቡብ በኩል 1,600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ከፐርዝ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች አብዛኛዎቹ በተወሰነላቸው የቅዳሜና የእሁድ ቀናት ከ40–45 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በሆነ ሙቀት ውስጥ የመንግሥት አዳራሽ ለመሥራት ይህን ርቀት አቋርጠው መጥተዋል። ገለል ብለው ወደሚኖሩ ማኅበረሰቦች ይህን ያህል ወንድሞች መጉረፋቸው ራሱ ምስክርነት ነበር። የብረት ማዕድን በሚወጣባት ቶም ፕራይስ በተባለች አነስተኛ ከተማ ውስጥ የመንግሥት አዳራሽ በተሠራበት ጊዜ የከተማው ጋዜጣ በመጀመሪያ ገጹ ላይ:- “ሦስት ቀን በወሰደው በቶም ፕራይስ ውስጥ በተካሄደው የይሖዋ ምስክሮች የመንግሥት አዳራሽ የአጭር ጊዜ ግንባታ የተሳተፉትን ፈቃደኛ ሙያተኞችና ረዳቶቻቸውን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የሞቀ ሰላምታችንን እናቀርባለን” ሲል ገልጿል።
በከተማው የሚገኝ ሰው ሁሉ ለመተባበር የጓጓ ይመስል ነበር ለማለት ይቻላል። 500 ኩንታል የሚመዝኑ ዕቃዎችን ለማምጣት የተለመደውን ዋጋ 11,000 የአውስትራሊያ ዶላር ከመክፈል ይልቅ የጭነት መኪና ባለቤት የሆነ አንድ ደግ ሰው ወንድሞች ነዳጁን ብቻ እንዲችሉ ጠየቃቸው። የከተማው የቀለም ቅብ ሥራ ተቋራጮች 100 ሊትር ቀለም በእርዳታ ሰጡ። የቁፋሮ ሥራ ተቋራጮች ለሥራው የሚያስፈልጉትን ማሽኖች አቀረቡ፤ የማዕድን ማውጫ ኩባንያው ደግሞ አንድ ክሬን በነፃ አቀረበ። ለ300 እንግዶች ማረፊያ ማግኘቱ ችግር ነበር፤ ሆኖም የከተማው ሰዎች ያደረጉት ትብብር የጎላ ነበር። አንዳንዶች ስልክ እየደወሉ መኝታ መስጠት እንደሚችሉ ገለጹ። አንድ ሰው ቅዳሜና እሑድ ወደ ሌላ ቦታ እንደሚሄድ፣ ነገር ግን በስተጀርባ በኩል ያለውን የቤቱን በር ክፍት አድርጎ እንደሚተወው ለመንገር ስልክ ደውሎ ነበር። “ፕሮጀክቱ እስከሚያልቅ ድረስ ቤቱ የእናንተ ነው” ሲል ተናገረ።
የተወሰኑ ወንድሞች የአካባቢው ጉባኤዎች ክልል ንብረት የሆነ አንድ ተሳቢ መኪና እንዲያመጡ አድራሻ በተሰጣቸው ጊዜ አንድ አስቂኝ ነገር ተፈጽሞ ነበር። ወደ ቦታው እንደደረሱ መግቢያው በር ላይ “ስለ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ሊያነጋግሩን የሚመጡ እንግዶችን አንቀበልም” የሚል ምልክት ማየታቸው ግራ አጋብቷቸው ነበር። ተሳቢው መኪና ግን እዚያ ቆሞአል። ስለዚህ በቆሻሻ የተሞላውን ተሳቢ መኪና ሊወስዱት መሆናቸውን የቤቱ ባለቤት ለሆነችው ሴት ገለጹላት። ቆሻሻውን እያራገፉ እያሉ ተሳቢው መኪና የክልሉ አለመሆኑን ተገነዘቡ! የተሳቢው መኪና ባለቤት ወደ ቤት ሲመጣ ሚስቱ ተሳቢ መኪናውን የይሖዋ ምስክሮች እንደወሰዱት ነገረችው። ብዙም ሳይቆይ ወንድሞች የተፈጸመውን ስህተት በመግለጽ ከቆሻሻ የጠራውን ተሳቢ ይዘው ተመለሱ። ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ተደረገና እነዚህ ቀደም ሲል ተቃዋሚዎች የነበሩ ሰዎች ስለ እኛና ስለ ሥራችን ብዙ ጥያቄዎች አቀረቡ። ወደ አዲሱ የመንግሥት አዳራሽ ለመምጣትና ለማየትም ጉጉት አደረባቸው።
በዚህ ሥፍራ የምሥራቹን መስበክ ጽናትን ይጠይቃል። በመጀመሪያ ደረጃ ረጅም ርቀት የመጓዝ ጉዳይ አለ። አንድ አቅኚ እህትና ባልዋ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለመምራት ኮረኮንችና አቧራ በበዛባቸው መንገዶች ላይ በየጊዜው ከፖርት ሄድላንድ እስከ ማርብል ባር በመኪና ደርሶ መልስ 350 ኪሎ ሜትር ይጓዛሉ። ማርብል ባር በአውስትራሊያ ውስጥ እጅግ ሞቃታማ ከሆኑት ቦታዎች አንዷ ስትሆን ከጥቅምት ጀምሮ እስከ መጋቢት ድረስ ብዙውን ጊዜ የሙቀቱ መጠን ከ50 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ይደርሳል።
ወደ “ላይኛው ጫፍ” ስናቀና
በስተ ሰሜን 2,500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን የክልል ስብሰባ የሚካሄድባትን ሌላዋን ከተማ ዳርዊንን እናገኛለን። የወረዳ የበላይ ተመልካቹና ሚስቱ በመኪና በመጓዝ የሚያሳልፉትን ረጅም ሰዓት የግል ጥናት ለማከናወን ይጠቀሙበታል። በመጀመሪያ የዕለት ጥቅሱን ያነቡና ይወያዩበታል። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ በቴፕ ያዳምጣሉ። በየተራ መኪናውን እንደሚነዱ ሁሉ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ርዕሶችንም በየተራ ያነባሉ።
በጐዳናው ላይ ያሉ ምልክቶች “ከመንገድ ባቡሮች” ጋር እንዳይጋጩ ያስጠነቅቋቸዋል። እነዚህ መኪናዎች ከፍተኛ ኃይል ያላቸው ሦስት ወይም አራት ተሳቢዎች የሚጎትቱ እስከ 55 ሜትር ያህል ርዝመት ያላቸው ከባድ መኪናዎች ናቸው። ስለዚህ በሚያልፉበት ጊዜ ሰፊ ቦታ ያስፈልጋቸዋል። ከብቶችንና ሌሎች ሸቀጦችን ራቅ ባሉ ቦታዎች ወደሚገኙ ከተሞች ለማጓጓዝ ያገለግላሉ።
አየሩ ሁልጊዜ ሞቃታማ ሲሆን ገጠሩም ዝናብ አያውቀውም። እምብዛም ተክሎች የማይበቅሉበት ደረቅ የሆነው የመሬቱ ገጽታ ጉንዳኖች ቤታቸውን ሲሠሩ በተመጣጠነ ርቀት የሠሩት ኩይሳ ስላለበት ሰፊ የመቃብር ሥፍራ መስሎ ሊያሳስት ይችላል። እነዚህ ጉንዳኖቹ የሠሯቸው ኩይሳዎች ጉንዳኖቹ ለመሥራት እንደተጠቀሙበት የአፈር ዓይነት ቀለማቸው ይለያያል፤ ከ1–2.5 ሜትር በሚደርስ ከፍታም በየቦታው ሊኖሩ ይችላሉ። ተጓዦቻችን የቪክቶሪያ ወንዝን እንዳቋረጡ በአካባቢው ሰዎች የተሠሩት ማስጠንቀቂያ ምልክቶች ትኩረታቸውን ይሰርቋቸዋል። “አደገኛ ስለሆነ መዋኘት ክልክል ነው። በእነዚህ ወንዞች ውስጥ ሰው የሚበሉ አዞዎች አሉ!” ይላል አንዱ ምልክት። ሰውነታቸውን ለመታጠብና ቀዝቀዝ ለማድረግ ሌላ መላ ለመፈለግ በጥበብ ይወስናሉ!
በመጨረሻም በተለምዶ “የላይኛው ጫፍ” ተብሎ ወደሚታወቀው የአውስትራሊያ ጫፍ ደረሱ። የሰሜናዊው ክልል ዋና ከተማ የሆነቸው ዳርዊን ሁለት የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤዎች ይገኙባታል። የዳርዊን ከተማ ብዙ ዓይነት ባህሎች እንዳሏት በክልል ስብሰባው ላይ በመገኘት በቀላሉ ማየት ይቻላል። በኢንዶኔዥያ ውስጥ ከምትገኘው በጦርነት ከፈራረሰችው ምስራቅ ቲሞር የመጣውን የ30 ዓመቱን ቻርልስን ተዋወቁት። ቻይናውያን የሆኑት ወላጆቹ የቀድሞ አባቶችን አምልኮ እንዲከተል አስተምረውት ነበር። እንደ ጅዶና ካራቴ ባሉ የውትድርና ጥበቦችም ተሳትፎ ያደርግ ነበር። ከመናፍስትነት ጋር ኃይለኛ ትስስር ስለነበረው በቀላሉ እርግፍ አድርጎ ሊተወው አልቻለም። ሆኖም ኢየሱስ “እውነት አርነት ያወጣችኋል” በማለት የሰጠውን ቃል በአእምሮው በመያዝ ከእንዲህ ዓይነቱ ሕይወት ተላቀቀ። (ዮሐንስ 8:32) “ዛሬ” ይላል ቻርልስ “በይሖዋ ፊት ንጹህ ህሊና አለኝ፤ በአሁኑ ጊዜ ዲያቆን ሆኜ እያገለገልኩ ነው። ግቤ በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት መካፈል ነው።”
ቀጥሎም ከፓፕዋ ኒው ጊኒ የመጣችውን ቤቫርሊን ተዋወቋት። “በመጀመሪያ ለነጮች ለመመስከር የነበረኝ ድፍረት እምብዛም ነበር” ስትል ቤቫርሊ ትገልጻለች። “እንግሊዝኛ ሁለተኛ ቋንቋዬ ስለነበረና አንዳንድ አገላለጾች ከአውስትራሊያ አነጋገር ጋር ተዳምረው ቋንቋውን ለመረዳት አዳጋች አድረገውብኝ ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋ እንድንተማመንና ጥሩ መሆኑን እንድንቀምስና እንድናይ የሚናገር መሆኑን በማስታወስ ጥር 1991 የሙሉ ጊዜ የአቅኚነት አገልግሎት ጀመርኩ። የመጀመሪያዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዬ በአሁኑ ጊዜ አቅኚ ናት። ሁለቱ ሴቶች ልጆቿ እውነትን የተቀበሉ ሲሆን ከእነርሱ መካከል አንዷ ከባልዋ ጋር አቅኚ ሆና እያገለገለች ነው።”
ዳርዊንን ለቀን ከመውጣታችን በፊት በምሥራቅ በኩል 250 ኪሎ ሜትር በፍጥነት አቋርጠን ሥፍር ቁጥር በሌላቸው ወፎች እጅግ ወደሚታወቀው ካካዱ ብሔራዊ ፓርክ እንጓዝ። በዚህ ገለልተኛ ሥፍራ ብቻዋን የምትሰብከውን ዴቢን እናገኛለን። እንዲህ ዓይነት ብቸኝነት ባለበት ሁኔታ በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆና መቀጠል የቻለችው እንዴት እንደሆነ እንጠይቃታለን። እንዲህ ስትል ትመልሳለች:- “አንደኛ በጸሎት አማካኝነት ነው . . . እንደ ኢሳይያስ 41:10 ካሉት ጥቅሶችም ማጽናኛ አገኛለሁ። እንዲህ ይላል:- ‘እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፣ እረዳህማለሁ፣ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።’”
ከዳርዊን በስተደቡብ 450 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በጂልክሚንጋን የአቦሪጂናል ተወላጆች ያሉበት አነስተኛ ቡድን እናገኛለን። ምንም እንኳን አንዳቸውም ተጠምቀው የነበረ ባይሆንም በጣም ብዙዎቹ አዘውትረው በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ይገኙ ስለነበር ይህ የአቦሪጂኖች ማህበረሰብ ለብዙ ዓመታት የይሖዋ ምስክሮች ማኅበረሰብ ተደርጎ ይታይ ነበር። ማኅበረሰቡ በንጽህናው የታወቀ ነው። በአሁኑ ጊዜ አንዳንዶቹ ለእውነት የጸና አቋም መውሰዳቸውና መጠመቃቸው ደስ የሚያሰኝ ነው። ይህን እርምጃ ለመውሰድ ከመጀመሪያዎቹ የአቦርጂናል የገጠር ነዋሪዎች መካከል እነርሱ ናቸው። የጎሳቸው ሰዎች ከሚፈጽሟቸው መናፍስታዊ ሥራዎችና ለዘመናት ከቆየው ባህላቸው ለመላቀቅ እነዚህ ትሁት ሰዎች ድፍረትና በይሖዋ መንፈስ ቅዱስ ላይ መመካትን ጠይቆባቸዋል።
ከገጠሩ ምድር እንውጣና ወደ አሊስ ስፕሪንግስ እናቅና
ከዚህ በኋላ ሰሜናዊውን ጫፍ ትተን በቅጽል ስሙ “ሬድ ሴንተር” ተብሎ ወደሚጠራው የአህጉሪቷ መካከለኛ ክፍል በደቡብ 1,600 ኪሎ ሜትር አቋርጠን ዝነኛው የአየርስ አለት አጠገብ ወደሚገኘው አሊስ ስፕሪንግስ እናቀናለን። በዚህ ቦታ የአየር ማቀዝቀዣ መሣሪያ ባለው የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በአካባቢው ካሉት ሁለት ጉባኤዎች የሚመጡትን 130 ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ተሰብሳቢዎች የሚያስተናግዱ ምቹ መቀመጫዎች አሉ። እዚህም ላይ የፖሊኔዥያ ተወላጆች፣ አውሮፓውያንና የአቦርጂናል ተወላጆች በክርስቲያናዊ ስብሰባ የተገናኙበት አስደሳች እይታ እንመለከታለን።
በመጨረሻም አሊስ ስፕሪንግስን ለቀን በመውጣት ተጓዥ ከሆነው የወረዳ የበላይ ተመልካቻችንና ከሚስቱ ጋር ሆነን የመጨረሻ ጉዞአችንን እንጀምራለን። ይህ ጉዞ አህጉሪቷን አቋርጦ በሰሜንና በምስራቅ በኩል 2,000 ኪሎ ሜትር ያህል ይዞን ይሄዳል። ይህን ጉዞ ስንጀምር በሞቃታማው የአየር ክልል ውስጥ ወደሚገኘው ለምለም ወደሆነው የኩዊንስ ላንድ ጥቅጥቅ ያለ ደን እየተቃረብን ስለምንሄድ የገጠሩን ክፍል ደህና ሰንብት እንለዋለን። በዚህ ታላቁ አለታዊ የባህር ጠረፍ በሚገኝበት ሰሜናዊ የኩዊንስ ላንድ ዳርቻ ከነዋሪው ሕዝብ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምስክሮች የሚገኙባቸው ጉባኤዎች አሉ።
ጉዞአችንን የምንደመድመው አንድ ተጨማሪ የክልል ስብሰባ ከተካፈልን በኋላ ይሆናል። ዝነኛው አለታዊ የባህር ጠረፍ ከሚገኝበት የኩዊንስላንድ ሞቃታማ ከተማ ከሆነው ከከራንዝ አውሮፕላን ተሳፍረን የአውስትራሊያን የብስ በመልቀቅ ቶረስ ስትሬይትን አቋርጠን በኬፕ ዮርክ ባህረገብ መሬት ሰሜናዊ ጫፍ ላይ ወደ ተርስዴይ ደሴት እንበራለን። በዚህ ቦታ 23 አስፋፊዎች ብቻ ያሉት አንድ አነስተኛ ጉባኤ አለ። በዚህ ጉዞ የመጨረሻ ስብሰባችን ላይ 63 ተሰብሳቢዎችን ማየቱ ምንኛ ደስ ይላል!
በዚህ የተለያዩ ገጽታዎች በሚንጸባረቁበት ምድር ላይ ስለሚካሄደው የመንግሥቱ የስብከት ሥራ ፍንጭ በማግኘት እንደተደሰታችሁ ተስፋ እናደርጋለን። ምናልባት አንድ ቀን በዚህ ስሜትን በሚማርክ የአውስትራሊያ ምድር ውስጥ የምንገኘውን ሰዎች ልትጎበኙንና በዚህ ልዩ የሥራ ምድብ የታመኑ በመሆን አገልግሎታቸውን የሚያከናውኑትን ወንድሞችና እኅቶች አግኝታችሁ በቀጥታ ልታነጋግሯቸው ትችሉ ይሆናል።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፐርዝ፤ የምዕራብ አውስትራሊያ ዋና ከተማ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከመንገድ ወደ መንገድ የሚደረገው ስብከት ጥሩ ውጤቶች አስገኝቷል