ቁጣ ወይስ ጤንነት?
የማይቆጣ ማን አለ? ሁላችንም እንቆጣለን። አንዳንድ ጊዜ ለቁጣችን በቂ ምክንያት ይኖረናል። ይሁን እንጂ ሐቀኞች ሆነን እንናገር ካልን ብዙ ጊዜ የምንቆጣው ያለ በቂ ምክንያት አይደለምን?
መጽሐፍ ቅዱስ “ከቁጣ ራቅ መዓትንም ተው፤ እንዳትበድል አትቅና” ይለናል። (መዝሙር 37:8) እንደዚህ የመሰለው ምክር ምን ያህል ጥበብ የሞላበት ነው? የወደፊቱን ጤንነትህን ሊነካብህ ይችላልን?
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “ጤና” በሚለው ዓምዱ ሥር እንዲህ ብሏል:-
“ብዙ ጊዜ ግልፍተኛ የሆኑ ወይም በጥቃቅን ነገሮች እርር ድብን የሚሉ ሰዎች ራሳቸውን ኀዘን ውስጥ ይጨምራሉ። ምናልባትም ራሳቸውን እየገደሉ ሊሆኑ ይችላሉ።
“ተመራማሪዎች ሥር የሰደደ ቁጣ በአካል ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ዕድሜ በማሳጠራቸው ከታወቁት ከሲጋራ ማጨስ፣ ከውፍረትና በጣም ቅባት የበዛበት ምግብ ከመብላት ጋር የሚተካከል እንዲያውም የሚብስ መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን በቅርቡ አግኝተዋል።
“‘የባሕርይ ሕክምና ተመራማሪ የሆኑትና በዱክ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ሴንተር ውስጥ የሚሠሩት ዶክተር ሬድፈርድ ዊልያም ጥላቻን የተሞላና ከጥርጣሬ የመነጨ ቁጣ ከምናውቀው ከማንኛውም ጤናን የሚጎዳ ነገር ጋር እኩል ነው’ በማለት ተናግረዋል።”
በዕለታዊ ኑሮ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ከሚገባ በላይ የሚያስጨንቋቸው ሰዎች ብዙ የጭንቀት ሆርሞኖች ያመነጫሉ። ቶሎ ቶሎ በቁጣ መገንፈላቸው ተከላካይ በሆኑት እና ጎጂ በሆኑት ኮሌስትሮሎች መካከል የሚዛን መዛባት ይፈጥርና በልብ በሽታ ለመጠቃት አደጋ የተጋለጡ ይሆናሉ።
አንዳንዶች ‘ተፈጥሮዬ ነው’፣ ወይም ‘አስተዳደጌ እንዲህ ነው’ የሚል ሰበብ ያቀርቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ማለት መለወጥ አትችልም ማለት አይደለም። የአምላክን ምክር በቅንነት በሥራ ላይ ለማዋል ከጣርክ ልትለወጥ ትችላለህ። በራስህ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምሳሌ 14:29, 30፤ 22:24, 25፤ በኤፌሶን 4:26፤ በያዕቆብ 1:19, 20 ላይ የሚገኙትን ስለ ቁጣ የሚናገሩ ምክሮች ተመልከት።
ይህንን መለኮታዊ ጥበብ በሥራ ላይ ብታውል ጤንነትህ እንዲሻሻልና ዕድሜህም እንዲረዝም ሊያደርግልህ ይችላል። ታይምስ “ብዙ ተመራማሪዎች ቁጣ የሚቀናቸው ሰዎች ጥላቻ የተሞላውን የቁጡነት ጠባያቸውን ቢተዉ ዕድሜያቸው እንዳያጥር ለመከላከል ይችላሉ” በማለት ጠቅሷል።