ምሥራቅና ምዕራብ ሲገናኙ
“ምሥራቅም ምሥራቅ፣ ምዕራብም ምዕራብ ነው፤ አይገናኝም አንደኛው ከሌላው።” እነዚህ የእንግሊዛዊው ባለቅኔ የሩድያርድ ኪፕሊንግ ቃላት ዛሬ በዙሪያችን ለሚታዩትና ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እየጨመረ ለሚሄደው የጎሳ፣ የዘርና የብሔር ጥላቻ አስተዋጽዖ የሚያደርጉትንና የሰውን ዘር የሚከፋፍሉትን ሰፊ ባሕላዊ ልዩነቶች ያስታውሱናል። ብዙዎች አምላክ ይህን ጉዳይ ለማስተካከል አንድ ነገር ማድረግ አይችልምን? ብለው ይጠይቃሉ። አዎን፣ ማድረግ ይችላል። አሁንም እንኳን የሚያደርጋቸው ነገሮች አሉ። የሚቀጥለው የኪፕሊንግ ስንኝ ይህን ይጠቅሳል። ምሥራቅና ምዕራብ እንደተለያዩ የሚቆዩት ለምን ያህል ጊዜ ነው? ገጣሚው “ምድርና ሰማይ ባምላክ የፍርድ ችሎት እስኪታዩ ቆመው” ይላል።
አምላክ የመፍረዱን ሥልጣን ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰጥቶታል። (ዮሐንስ 5:22–24, 30) ይሁን እንጂ ይህ የፍርድ ጊዜ የሚጀምረው መቼ ነው? የሚፈረዱት እነማን ናቸው? የፍርዱስ ውጤት ምን ይሆናል? ከ1914 ጀምሮ የሰው ዘሮችን በማሰቃየት ላይ የሚገኙትን የዓለም ጦርነቶችና ከጦርነቶቹ ጋር አብረው የተከሰቱትን ችግሮች በቅድሚያ የተነበየው ኢየሱስ ነው። እነዚህ ሁኔታዎች የእሱን በማይታይ ሁኔታ ‘መገኘትና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ መድረሱን የሚያሳየውን ‘ምልክት’ የሚጠቁሙ መሆናቸውን ገልጿል።”—ማቴዎስ 24:3–8
ኢየሱስ ይህን ታላቅ ትንቢት ስለራሱ በተናገረው ቃል ሲያጠቃልል ይህ የእኛ ዘመን የፍርድ ዘመን እንደሚሆን አመልክቷል። “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፣ በጎችንም በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል።” አሁን የምድር ሕዝቦች በሙሉ በምሳሌያዊ ሁኔታ በዳኛው ፊት ተሰብስበዋል። ለደህንነት መልእክቱ ስለሚሰጡት አቀባበል ለዚህ ዳኛ መልስ ይሰጣሉ። በቅርቡ በሚመጣው ታላቅ መከራ ፍርድ ሲሰጥ አመጸኞቹ ፍየል መሰል ሰዎች “ወደ ዘላለም ቅጣት፣ ጻድቃን [ታዛዦቹ በግ መሰል ሰዎች] ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።”—ማቴዎስ 25:31–33, 46፤ ራእይ 16:14–16
‘ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ’
የዚህ ዓለም ፍርድ የጀመረው አንደኛው የዓለም ጦርነት በተካሄደባቸው አስቸጋሪ ዓመታት ነው። በጦርነቱ ወቅት የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ለተዋጊዎቹ ወገኖች የሙሉ ልብ ድጋፍ ሰጥተዋል። ይህን በማድረጋቸውም “የእግዚአብሔር ቁጣ” ሊወርድበት የሚገባው ምግባረ ብልሹ ዓለም ክፍል መሆናቸውን አሳይተዋል። (ዮሐንስ 3:36) በአምላክ የታመኑት ሰላም ወዳድ ክርስቲያኖችስ? ከ1919 ጀምሮ ከንጉሡ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጎን ሲሰበሰቡ ቆይተዋል።
በመጀመሪያ ከሁሉም የምድር ክፍል የተሰበሰቡት በክርስትና ዘመን ሁሉ ሲመረጡ ከቆዩት 144,000 ቅቡዓን የቀሩት ናቸው። እነዚህ በሰማያዊ መንግሥት ‘ከክርስቶስ ጋር አብረው ወራሾች’ የሚሆኑ ናቸው። (ሮሜ 8:17) ስለነዚህ የአምላክ ነቢይ እንደሚከተለው ይላል፦ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፣ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ። ሰሜንን፦ መልሰህ አምጣ፣ ደቡብንም፦ አትከልክል፤ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፣ በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፣ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ።”—ኢሳይያስ 43:5–7
ይሁን እንጂ የመሰብሰቡ ሥራ በዚህ አላበቃም። በተለይ ከ1930ዎቹ ዓመታት ጀምሮ በአሁኑ ጊዜ በሚልዮን እስከመቆጠር የደረሱት እጅግ ብዙ ሰዎች መሰብሰብ ጀመሩ። ኢየሱስ በማቴዎስ 25:31–46 ላይ የጠቀሳቸው “በጎች” እነዚህ ናቸው። እነዚህ “በጎች” ከእነሱ በፊት እንደነበሩት ቅቡዓን ቀሪዎች ‘እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፣ እኔም አምላክ ነኝ’ በሚለው አምላክ ያምናሉ። (ኢሳይያስ 43:10–12) እነዚህን እጅግ ብዙ ሰዎች የመሰብሰቡ ሥራ ‘ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ እንዲሁም እስከ ምድር ጫፍ ድረስ’ ቀጥሏል።
እነዚህ ሰላም ወዳድ የሆኑ በግ መሰል ሰዎች በአንድ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር እየተሰባሰቡ ነው። እነሱም በሚኖሩባቸው 231 አገሮች የሚነገሩትን የተለያዩ ቋንቋዎች ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ‘አንድ ሆነው ያገለግሉት ዘንድ የይሖዋን ስም እንዲጠሩ’ የመጽሐፍ ቅዱስን የመንግሥት መልእክት “ንጹሕን ልሳን” በመማር በመንፈሳዊ አንድ ሆነዋል። (ሶፎንያስ 3:9) በመካከላቸው ያለው የእምነት፣ የዓላማና የድርጊት አንድነት በሁሉም የምድር ማዕዘናት የሚኖሩ ሕዝቦች ሉዓላዊ ገዥ የሆነውን ይሖዋን ለማገልገልና ከፍ ከፍ ለማድረግ አንድ በመሆናቸው ምሥራቅ ከምዕራብ ጋር እንደተገናኘ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሆኖአል።
የሚከተሉት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ይህ የመሰብሰቡ ሥራ በአንዳንድ አገሮች የሚከናወነው በጣም አስደናቂ በሆኑ ሁኔታዎች ነው።