የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ጽናት ብዙ ዋጋ አለው
ኢየሱስ ተከታዮቹ ስደት እንደሚደርስባቸው አስቀድሞ ተናግሯል፤ ሐዋርያው ጳውሎስም እንዲሁ በ2 ጢሞቴዎስ 3:12 እንደሚከተለው ብሏል፦ “በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ [ለአምላክ ያደሩ በመሆን አዓት] ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።” ነገር ግን ይሖዋ አምላክን በማገልገል መጽናት ብዙ ዋጋ አለው።
ይህ በማሌዥያ ሰሜናዊ ምስራቅ ዳርቻ በምትገኘው ከተማ በደረሰው ሁኔታ ላይ ታይቷል። አንድ አባት የቡድሂስት እምነት አክራሪና ልጆቹንም አጥብቆ የሚያስተምር የነበረ ቢሆንም እንኳ ሦስት ሴቶች ልጆቹንና ሦስት ወንዶች ልጆቹን ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናታቸውን ለማስቆም አልቻለም ነበር። ሚስቱም ጭምር ለእውነት ፍላጎት አሳየች። አንድ ቀን አንድ ጎረቤቱ “የይሖዋ ምስክሮች እስኪሆኑ ድረስ ልጆችህን መቆጣጠር እንዴት ያቅትሃል? የእኔ ልጆች ሁሉም ከእኔና ከአባቶቻችን የቡዲሂስት ሃይማኖት እንደተጣበቁ ናቸው። አንተ ግን ታሳዝናለህ” ሲል አሾፈበት።
አባትየው በቁጣ ወደ ቤቱ እየተንደረደረ ገብቶ ልጆቹን የምታስጠናቸውን እኅት ሊደበድባት ተጋበዘ። ይሁን እንጂ ልጆቹ አረጋጉትና ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናታቸውንና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘታቸውን ቀጠሉበት፤ እናታቸውም ደገፈቻቸው።
በመጨረሻም አባታቸው ቤተሰቡን በሙሉ ሰበሰበና “ከእኔ ጋር ሆናችሁ እቤት ከመቀመጥና ክርስቲያን ሆናችሁ ከቤት ከመውጣት አንዱን ምረጡ” በማለት ጠየቃቸው። በጣም ልስልስ ያለ አነጋገር ያለው ትልቁ ልጁ ወዲያውኑ ለመውጣት ዕቃዎቹን መጠቅለል ጀመረ። አባቱም “አታደርገውም!” ሲል ጮኸ። “እናንተ ሁላችሁም ዓመፀኞች ልጆች ስለ ሆናችሁ ብሞት ይሻለኛል” አለ። ይህንን ብሎ እየተቻኰለ ከቤቱ ሲወጣ ቤተሰቦቹ ተከትለውት በመሮጥ ሕይወቱን እንዳያጠፋ ለመኑት። ልመናቸው ልቡን ስለነካው ወደ ቤቱ ተመልሶ ገባ።
የተወሰነ ጊዜ አለፈ። አባታቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በልጆቹ ባሕርይ ላይ ያመጣውን መልካም ውጤት ማስተዋል ጀመረ። አንድ ቀን ያሾፈበትን ጎረቤቱን አገኘው፤ በዚህ ጊዜ ግን ሰውዬው በጣም አዝኖ ስለነበር እንዲህ አለ፦ “በልጆቼ በጣም ተበሳጭቻለሁ። ያታልሉኛል፣ ይሰርቁኛል።” ልጆቹ ከይሖዋ ምስክሮች ጋር የሚያጠኑለት ሰው ግን እንዲህ አለ፦“የእኔ ልጆች የተለዩ ናቸው! ለእኔ ደግ ሆነዋል፤ እንዲያውም ከሥራ ወጥቼ ሳለሁ እንኳ የነበረብኝን የመኪና ዕዳ ከፍለውልኛል።”
ዛሬ ሦስቱ ሴት ልጆችና እናታቸው ተጠምቀዋል። አንዱ ወንድ ልጃቸው ልዩ አቅኚ ሆኗል። ቀድሞ አጥባቂና ቁጡ የነበረው አባታቸውስ? ዛሬ ተግባቢ ሆኖ በክርስቶስ የሞት መታሰቢያ በዓል ላይም ተገኝቷል።
ይሖዋ ወንዱን ልጅ ሦስቱን እኅቶቹንና እናታቸውን ለእርሱ ባሳዩት ጽናት ምክንያት ዋጋቸውን ሰጥቷቸዋል። የይሖዋን ልብ ደስ አሰኝተዋል።—ምሳሌ 27:11