ከሁለት አባቶች አንዱን የመምረጥ ፈተና
“ከአሁን በኋላ ልጄ አይደለህም! አሁኑኑ ከዚህ ቤት ውጣልኝ፤ ይህን ሃይማኖት እስካልተውክ ድረስ እዚች ቤት ድርሽ እንዳትል!”
ከለበስኩት ልብስ በቀር ምንም ነገር ሳልይዝ ከቤት ወጣሁ። ያን ዕለት ምሽት የመድፍ ጥይት እሩምታ በሰፈሩ አካባቢ ይሰማ ነበር፤ የት እንደምሄድ አላውቅም ነበር። ወደ ቤት የተመለስኩት ከስድስት ዓመታት በኋላ ነበር።
አንድ አባት የገዛ ልጁን ከቤት እስኪያባርር ድረስ እንዲህ ሊያስቆጣው የሚችለው ነገር ምንድን ነው? ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው እንዴት እንደሆነ እስቲ ልንገራችሁ።
ጥላቻ በተሞላ ዓለም ውስጥ ማደግ
ወላጆቼ የሚኖሩት በአንድ ወቅት በቱሪስት መስብህነቷ ዝናን አትርፋ በነበረችው በሊባኖስ ቤሩት ውስጥ ነው። ይሁን እንጂ ከ1975 አንስቶ እስከ 1990 ድረስ ከተማዋ የጦርነት አውድማ ሆና ነበር። በ1969 በአንድ የአርመን ቤተሰብ ውስጥ ተወለድኩ፤ ከሦስት ልጆች መካከል የመጀመሪያው ነበርኩ። በመሆኑም የልጅነት ትዝታዎቼ ሰላማዊውን ጊዜ የሚያስታውሱኝ ናቸው።
ወላጆቼ የአርመን ሐዋርያዊ ቤተ ክርስቲያን አባላት የነበሩ ቢሆንም እናታችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ትወስደን የነበረው በዓመት ሁለት ጊዜ ማለትም በትንሣኤና በገና በዓል ወቅት ብቻ ነበር። ስለዚህ ቤተሰባችን አጥባቂ ሃይማኖተኛ አልነበረም። ሆኖም በአንድ የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በመማሬ ሃይማኖታዊ ትምህርት ተከታትያለሁ። በዚያን ጊዜም ቢሆን ሃይማኖት ትኩረቴን አልሳበውም ነበር።
ብዙዎቹ አርመናውያን ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚሰሙት ነገር ቱርኮችን እንዲጠሉ ያደርጋቸው ነበር። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቱርኮች በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አርመናውያንን የጨፈጨፉ ሲሆን አብዛኛውን የአርመን ግዛት ወስደዋል። በ1920 ደግሞ ቀሪው የአገሪቷ ምሥራቃዊ ክፍል የሶቭየት ኅብረት አካል ሆነ። ወጣት በነበርኩበት ጊዜ ፍትሕ ሰፍኖ ለማየት ስል በውጊያ ለመካፈል ቆርጬ ነበር።
የአስተሳሰብ ለውጥ
ይሁን እንጂ በ1980ዎቹ ዓመታት በአሥራዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ሳለሁ የእናቴ ወንድም የነገረኝ ነገር አስተሳሰቤን ይለውጠው ጀመር። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በቅርቡ ሁሉንም ዓይነት የፍትሕ መጓደል እንደሚያስወግድ ነገረኝ። ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹ እንዲጸልዩለት ባስተማራቸው መንግሥት አማካኝነት በጅምላ ጭፍጨፋው ያለቁት ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ በምድር ላይ ለመኖር ከሞት እንደሚነሱ ገለጸልኝ።—ማቴዎስ 6:9, 10፤ ሥራ 24:15፤ ራእይ 21:3, 4
በደስታ ፈነጠዝኩ። ብዙ ማወቅ ስለፈለግኩ የተለያዩ ጥያቄዎችን እጠይቀው ጀመር። ከዚያም በአንድ ሌላ ምሥክር ቤት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ።
ስለ ሰማያዊ አባቴ ስለ ይሖዋ እየተማርኩና ይበልጥ እየወደድኩት ስሄድ አንድ ቀን ከቤተሰቤና ከይሖዋ አምላክ አንዱን የመምረጥ ከባድ ውሳኔ ከፊቴ ሊደቀን ይችላል የሚል ስጋት አደረብኝ።—መዝሙር 83:18
ለ17 ዓመት ልጅ እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ምርጫ
ውሎ አድሮ እናቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ግንኙነት እንደጀመርኩ ሰማች። በጣም ተበሳጭታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴን እንዳቋርጥ አስጠነቀቀችኝ። ከአቋሜ ፍንክች እንደማልል ስትገነዘብ ለአባትህ እነግርብሃለሁ ብላ አስፈራራችኝ። በወቅቱ ሁኔታውን በተሳካ መንገድ ልወጣው እንደምችልና አቋሜን ለአባቴ ግልጽ ማድረግ እንደምችል ተሰምቶኝ ስለነበር ብዙም አልተጨነኩበትም ነበር። ሆኖም ተሳስቼ ነበር።
አባቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ግንኙነት መጀመሬን ሲሰማ በጣም ተናደደ። የጀመርኩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ካላቆምኩ ከቤት እንደሚያባርረኝ አስጠነቀቀኝ። እየተማርኩት ያለሁት ነገር እውነት ስለሆነ ጥናቴን ላቋርጥ እንደማልችል ነገርኩት። የቁጣ ውርጅብኝና የስድብ ናዳ ካወረደብኝ በኋላ ልክ እንደ ሕፃን ልጅ ስቅስቅ ብሎ ማልቀስ ጀመረ። ከምሥክሮቹ ጋር ያለኝን ግንኙነት እንዳቋርጥ እጅግ ተማጸነኝ።
ልቤ ለሁለት ተከፈለ፤ ከሁለት አባቶች ማለትም ከይሖዋና ከእሱ ማንን እንደምመርጥ ግራ ገባኝ። ሁለቱም በጣም እንደሚወዱኝ አውቃለሁ፤ በመሆኑም ሁለቱንም ለማስደሰት ፈለግኩ። ሆኖም የማይቻል ነገር ሆነብኝ። ግፊቱ ልቋቋመው ከምችለው በላይ ሆነብኝ። ሳድግ ጥናቴን መቀጠልና ምሥክር መሆን እችላለሁ ብዬ በማሰብ ያለውን ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኔን ለአባቴ ገለጽኩለት። በዚያ ወቅት ገና የ17 ዓመት ልጅ ነበርኩ።
ከዚያ በኋላ በነበሩት ቀናት በሠራሁት ነገር በጣም አፈርኩ። ይሖዋ እንደሚያዝንብኝና በሚከተሉት የመዝሙራዊው ዳዊት ቃላት ላይ እንዳልታመንኩ ሆኖ ተሰማኝ:- “አባቴና እናቴ ትተውኛልና፣ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ።” (መዝሙት 27:10) ሆኖም ገና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ስለነበርኩ የትምህርት ወጪዬን የሚሸፍኑልኝ ወላጆቼ ነበሩ።
ይበልጥ ጥብቅ የሆነ አቋም
ወላጆቼ እያንዳንዷን እንቅስቃሴዬን እንደሚከታተሉ አውቅ ስለነበር ከሁለት ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ከአጎቴም ሆነ ከሌላ ምሥክር ጋር ግንኙነት ሳላደርግ ቆየሁ። በ1989 አንድ ቀን ከአንድ ከማውቀው ምሥክር ጋር ተገናኘሁ። በዚህ ወቅት 20 ዓመት ሆኖኝ ነበር። ደግነት በተሞላበት መንፈስ እቤቱ መምጣት እችል እንደሆነ ጠየቀኝ። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትን በተመለከተ ምንም ነገር ስላላነሳብኝ ሄጄ ጠየቅኩት።
ውሎ አድሮ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። ማንም ሰው እንዳይረብሸኝ ስል በሥራ ቦታዬ አጠና ነበር። በዚህም የተነሣ የይሖዋን ፍቅራዊ ባሕርይ በተሻለ መንገድ መረዳት ከመቻሌም በላይ በማንኛውም ሁኔታ ሥር ከእሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና መያዙ ያለውን ጠቀሜታ ይበልጥ ተገነዘብኩ። በዚያው ዓመት በነሐሴ ወር የተማርኩትን ነገር ለሌሎች ማካፈል ጀመርኩ።
እስከዚያ ጊዜ ድረስ ቤተሰቦቼ ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ይሁን እንጂ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከአባቴ ጋር እንደገና ፊት ለፊት ተፋጠጥን፤ ሆኖም በዚህ ወቅት ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ ራሴን አዘጋጅቼ ነበር። “ልጄ፣ አሁንም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ትገናኛለህ የሚባለው ነገር እውነት ነው?” ሲል በዝግታ ጠየቀኝ። የእኔን ምላሽ ሲጠብቅ ዓይኖቹ እንባ አቅርረው ነበር። እናቴና እህቴ ጸጥ ብለው እያለቀሱ ነበር።
ከምሥክሮቹ ጋር መገናኘት የጀመርኩት በቅርቡ እንደሆነና እኔም የይሖዋ ምሥክር ለመሆን የቆረጥኩ መሆኔን ነገርኩት። በዚህ ጊዜ ነገሮቹ ሁሉ በፍጥነት ተለዋወጡ። አባቴ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ ያሉትን ቃላት አዥጎደጎደብኝ። ከዚያም ጨምድዶ ያዘኝና ከዚህች ቤት ሬሳህ ይወጣል እንጂ በሕይወት አልለቅህም ብሎ በጩኸት ተናገረ። እንደምንም ብዬ ራሴን ከእጁ ካስለቀቅኩ በኋላ እየሮጥኩ ደረጃውን ስወርድ ታናሽ ወንድሜ አባቴን ለማረጋጋት ሲሞክር ሰማሁት። “ከአሁን ጀምሮ አባቴ አንተ ነህ። አንተን መርጫለሁና እባክህ እንክብካቤህ አይለየኝ” ብዬ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ።
የብቀላ እርምጃ
ከጥቂት ቀናት በኋላ አባቴ እኔን እንደሚያገኘኝ በማሰብ ወደ አጎቴ ቤት ሄደ። አጎቴን በመደብደብ ካልገደልኩት ሲል አጎቴን ሊጠይቁ መጥተው የነበሩ ምሥክሮች ጣልቃ ገብተው ገላገሉ። አባቴ ተመልሶ እንደሚመጣ ዝቶበት ሄደ። እንዳለውም አልቀረም፣ ብዙም ሳይቆይ መሣሪያ የታጠቁ ሚሊሽያዎች አስከትሎ መጣ። እነርሱም ምሥክሮቹንና በጣም ታሞ የነበረውን አጎቴን ይዘው ወደ ወታደራዊ ዋና መሥሪያ ቤት ወሰዷቸው።
ከዚያ በኋላ በአካባቢው ያሉ ሌሎች ምሥክሮችንም ማሰስ ጀመሩ። የአንዱ ምሥክር ቤትም ተወረረ። መጽሐፍ ቅዱሶችን ጨምሮ መጻሕፍትን መንገድ ላይ ከምረው አቃጠሉ። ሆኖም በዚህ አላበቃም። ስድስት ምሥክሮችና ከእነርሱ ጋር ያጠኑ የነበሩ ጥቂት ሰዎች ተያዙ። ሁሉም አንድ ትንሽ ክፍል ውስጥ ታጉረው ምርምራ ከተካሄደባቸው በኋላ ተደበደቡ። አንዳንዶቹን በሲጋራ አቃጠሏቸው። ወሬው በፍጥነት በአካባቢው ሁሉ ተሰራጨ። ሚሊሽያዎቹ እኔን ለማግኘት በየቦታው ፍለጋቸውን ቀጠሉ። አባቴ ፈልገው እንዲያገኙኝና የፈለጉትን መንገድ ተጠቅመው አቋሜን እንዲያስለውጡኝ ጠይቋቸው ነበር።
ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ አንድ ጉባኤ ስብሰባ እያካሄደ ሳለ ሚሊሽያዎቹ ወደ መንግሥት አዳራሹ ዘው ብለው ገቡ። ጉባኤውን በጠቅላላ ማለትም ወንዶቹን፣ ሴቶቹንና ሕፃናቱን ጨምሮ ሁሉንም ከአዳራሹ አስወጧቸው። መጽሐፍ ቅዱሶቻቸውን ከቀሟቸው በኋላ ለምርመራ ወደ ዋናው የሚሊሽያ ጽሕፈት ቤት በእግር ወሰዷቸው።
ወደ ግሪክ ማምለጥ
ይህ ሁሉ ሲሆን ከነውጡ መድረክ ራቅ ብሎ የሚገኝ አንድ የምሥክሮች ቤተሰብ እንክብካቤ እያደረገልኝ ነበር። ከአንድ ወር በኋላ አገሪቷን ለቅቄ ወደ ግሪክ ተጓዝኩ። እዚያም እንደደረስኩ ራሴን ለይሖዋ አምላክ ወስኜ ተጠመቅኩ።
በግሪክ፣ ቱርኮችን ጨምሮ ከተለያዩ ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ያቀፈውን የመንፈሳዊ ወንድማማች ማኅበር ፍቅራዊ እንክብካቤ አግኝቻለሁ። የሚከተሉት የኢየሱስ ቃላት እውነት ሆነው አግኝቻቸዋለሁ:- “ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፣ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንም እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።”—ማርቆስ 10:29, 30
ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ግሪክ ውስጥ ቆየሁ። ለአባቴ በተደጋጋሚ ብጽፍለትም ምንም ምላሽ አልሰጠኝም። ቤተሰባችንን ሊጠይቁ የመጡ ወዳጆቻችን ስለ እኔ ከጠየቁት “እንዲህ የሚባል ልጅ የለኝም” ይላቸው እንደነበር ከጊዜ በኋላ ሰማሁ።
ከስድስት ዓመታት በኋላ ዳግም መገናኘት
ጦርነቱ ካበቃ በኋላ በ1992 በቤሩት ለመኖር ወደዚያ ተመለስኩ። ወደ ቤት መመለስ እንደምፈልግ በአንድ ጓደኛችን በኩል ለአባቴ ገለጽኩለት። መመለስ የምችለው እምነቴን ከተውኩ ብቻ እንደሆነ ገለጸልኝ። ስለዚህ ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት አንድ አፓርታማ ላይ ተከራይቼ ስኖር ቆየሁ። ከዚያም ኅዳር 1995 አባቴ በድንገት እኔን ፍለጋ ወደምሠራበት ቦታ መጣ። እኔ በወቅቱ ስላልነበርኩ እቤት ና የሚል መልእክት ትቶልኝ ሄደ። መጀመሪያ ላይ ለማመን ተቸግሬ ነበር። ስለዚህ በጣም እያመነታሁ ላነጋግረው ሄድኩ። ዳግመኛ ስንገናኝ ስሜታችንን ልንቆጣጠረው አልቻልንም። ከአሁን በኋላ የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ እንደማይቃወመኝና ወደ ቤት እንድመለስ እንደሚፈልግ ነገረኝ!
በአሁኑ ጊዜ በአንድ የአርመን ቋንቋ ተናጋሪዎች ጉባኤ ውስጥ ክርስቲያን ሽማግሌና የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆኜ በማገልገል ላይ እገኛለሁ። የቤተሰቦቻቸው አባላት ይሖዋን ለማገልገል በመፈለጋቸው ልክ እንደ አባቴ የሚቃወሙ ሰዎች ብዙ ጊዜ ያጋጥሙኛል። አባቴ የእኔን አምልኮ መቃወሙ ትክክል እንደሆነ አድርጎ በቅንነት ያስብ እንደነበረ ተገንዝቤያለሁ። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች የቤተሰብ ተቃውሞ ሊደርስባቸው እንደሚችል መጠበቅ እንዳለባቸው በመግለጽ ለእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ዝግጁ ያደርጋቸዋል።—ማቴዎስ 10:34–37፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:12
አንድ ቀን አባቴና የተቀሩት የቤተሰቤ አባላት የተሻለ ዓለም እንደሚመጣ በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ በማመን ከጎኔ እንደሚቆሙ ተስፋ አደርጋለሁ። በዚያ ጊዜ ጦርነትም ሆነ የጅምላ ጭፍጨፋ አይኖርም፤ ሰዎች አገራቸውን ለቅቀው እንዲሰደዱ አይደረግም ወይም በጽድቅ ምክንያት አይሰደዱም። (2 ጴጥሮስ 3:13) በመሆኑም ሰዎች በጣም ከሚወዷቸው ሁለት ነገሮች አንዱን እንዲመርጡ የሚገደዱበት ሁኔታ አይኖርም።—ተጽፎ የተላከልን።