የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
“የእግዚአብሔር [የይሖዋ አዓት] ስም የጸና ግንብ ነው”
የምንኖረው ተለዋዋጭ በሆነ ዘመን ነው። የተደላደለ የሚመስለው ሕይወታችን በአንድ ሌሊት ተለውጦ ሊያድር ይችላል። አንዳንዶቹም ሳያስቡትና አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደሚቸል የሚያስጠነቅቅ ምንም ምልክት ሳያዩ ትልቅ አደጋ ውስጥ ገብተው ይገኛሉ። በፖለቲካ ዓመጾች፣ በወንጀለኞች የማስፈራሪያ ደብዳቤ፣ በተፈጥሮ አደጋ ወይም በከባድ ሕመም ምክንያት አደጋ ሊደርስባቸው ይችላል። መምጫው ምንም ይሁን ምን አንድ ክርስቲያን ሕይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲያጋጥመው የማንን እርዳታ መጠየቅ ይኖርበታል?
ከመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮዎች በአንዱ ውስጥ የሚኖር ሚስዮናዊ የሆነው ዴቪድ ካጋጠመው አስፈሪ ተሞክሮ የዚህን ጥያቄ መልስ አግኝቷል። ዴቪድ በሾፌርነት በተመደበበት አንድ ቀን በተመላላሽነት የሚኖሩትን የቅርንጫፍ ቢሮ ፈቃደኛ ሠራተኞች ለማምጣት ማልዶ ተነሳ። ገና ማለዳ ነበር። ሮዛሊያን አሳፍሮ በአንድ ፖሊስ ጣቢያ በኩል ሲያልፍ የመጀመሪያውን የተኩስ ድምጽ ሰማ።
ከዚያም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተከታታይ ነገሮች ተፈጸሙ። ከፍተኛ ኃይል ያለው የፍንዳታ ድምጽ ሲሰማ አንደኛው የመኪና ጐማ እንደፈነዳ ተገነዘበ። በድንገት አንድ ወታደር መንገዱ መሀል ላይ ቆሞ መሳሪያውን ወደ እርሱ እንደደገነ ተመለከተ። ሦስት ነገሮች በአንድ ቅጽበት ተፈጸሙ፦ የተኩሱ እሩምታ የመኪናዋን ጎን በሳስቶ መስታወቶቿን አረገፈ፣ ዴቪድና ሮዛሊያ ለጥ ብለው ተኙ፣ ከፊት ለፊት ያለው ወታደር በፊተኛው መስታወት በኩል አነጣጥሮ ተኮሰባቸው።
መኪናዋ በጥይት በመደብደብ ላይ እንዳለች ዴቪድ እንደተኛ እንደ ምንም ብሎ ፍሬን ይዞ አቆማት። ዴቪድና ሮዛሊያ መሞታችን ነው ብለው አስበው ነበር። ይሖዋ እንዲጠብቃቸው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ጸለዩ። በዚያን ወቅት ሮዛሊያ ቤተሰቦቼ መሞቴን ሲሰሙ እንዴት ይሰማቸው ይሆን! እያለች ትጨነቅ እንደነበር በኋላ ተናግራለች!
በሕይወት ተርፈዋል!
በመጨረሻ የተኩሱ ጩኸትና የመስታወቱ መሰባበር ሲያቆም ዴቪድ አይኑን ወደ ሮዛሊያ ወርወር አደረገ። ጀርባዋ ላይ የነበረውን ደም ሲያይ በፍርሐት ልቡ ልትቆም ምንም አልቀራትም። ሰውነቷን ቀዶ የገባው ግን ጥይት ሳይሆን የመስታወቱ ስብርባሪ ነበር። ጉልበቶቿ በወዳደቁት ስብርባሪዎች ተወጋግተው ደምተው ነበር፤ ከዚህ ሌላ ግን ምንም ጉዳት አልደረሰባትም።
የወታደር ልብስ የለበሱና እጃቸው ላይ ነጭ ጨርቅ ያደረጉ ሰዎች ወደ መኪናዋ በመቅረብ ከመኪናው ውስጥ እጃቸውን ወደ ላይ አንስተው እንዲወጡ አዘዟቸው። ከመካከላቸው የሁሉም የበላይ የሚመስል ሰው ወደ አንዱ ወታደር ዘወር ብሎ “በሲቪሎች ላይ ተኩስ እንዳትከፍት ተነግሮህ አልነበረም” አለው። ወታደሩም ተኩስ እንደሰማና ተኩሱም ከመኪናው ላይ የመጣ መስሎት እንደነበር በመናገር ለማስተባበል ሞከረ።
ዴቪድ ሮዛሊያና እርሱ የይሖዋ ምስክሮች መሆናቸውን ሲነግራቸው ለስለስ አሉ። ምን እየሠራ እንደነበረም ነገራቸው። ያም ሆኖ ግን ወታደሮቹ አስረው ሊያቆዩአቸው ፈልገው ነበር። በዚያ ዕለት ማለዳ አንድ ወታደራዊ አንጃ መፈንቅለ መንግሥት አድርጎ ስለነበር ወታደሮቹ ዴቪድና ሮዛሊያ በሚያልፉበት ጊዜ ፖሊስ ጣቢያውን በቁጥጥራቸው ሥር በማድረግ ላይ ነበሩ።
ሮዛሊያ በጣም ደንግጣ የነበረ ቢሆንም ዴቪድ እንዲለቅቋቸው በሚለምንበት ጊዜ በድፍረት ረጋ ብላ ቆመች። በመጨረሻም መኪናዋን ትተው እንዲሄዱ ተፈቀደላቸው። በአቅራቢያው እስከሚገኘው ጐዳና ድረስ በእግራቸው ሄደው ከዚያ ሮዛሊያ ሕክምና ወዳገኘቸበት ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው በሚያደርሳቸው አውቶቡስ ተሳፈሩ።
የጸሎት ኃይል
ዴቪድ ካጋጠመው ተሞክሮ ልባዊ ጸሎት የሚያስገኘውን ውጤት አቃልሎ መመልከት ተገቢ አለመሆኑንና ምንጊዜም የይሖዋ ምስክር መሆናችንን በድፍረት ማሳወቅ ከችግር እንደሚጠብቀን ተምሯል። “የእግዚአብሔር [የይሖዋ አዓት] ስም የጸና ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል” የሚሉት ቃላት ቃል በቃልም ተፈጻሚነት የሚያገኙበት ጊዜ አለ።—ምሳሌ 15:29፤ 18:10፤ ፊልጵስዩስ 4:6
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Fotografia de Publicaciones Capriles, Caracas, Venezuela