“ከጸናች ከተማ ይበልጥ”
“በአሁኑ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙት ሕፃናት 40% የሚሆኑት ገና 18 ዓመት ሳይሞላቸው የወላጆቻቸው ትዳር ሲፈርስ ይመለከታሉ።” (ሳይንስ፣ ሰኔ 7, 1991) እንዴት የሚያስደነግጥ አኀዛዊ መግለጫ ነው! እንዲህ የሚሆነው ለምንድን ነው?
የቤተሰብና የውርስ ጉዳይ የሚመለከት ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ኤድዋርድ ኤም ጊንግዝበርግ ዘ ቦስተን ግሎብ የተባለ ጋዜጣ ባደረገላቸው ቃለ ምልልስ በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አመለካከት ሲገልጹ “ኅብረተሰባችን ራስ ወዳድ ነው። ‘ለኔ ብቻ’ እንላለን። ምን ጥቅም አገኝበታለሁ?’ እያልን እንጠይቃለን። ቅጽበታዊ ደስታ ለማግኘት እንፈልጋለን” ብለው ነበር።
እንዲህ ያለ ብስለት የጎደለው ራስ ወዳድነት ጋብቻ ወደ መራርነትና ወደ ግጭት እንዲያመራ ያደርጋል። ዳኛ ጊንግዝበርግ እንደተናገሩት ባልና ሚስት ፍቺያቸውን በሚያጸድቀው ፍርድ ቤት ፊት ሲቀርቡ ባልየውም ሆነ ሚስቲቱ ትክክለኛነታቸው እንዲረጋገጥላቸው ይፈልጋሉ። እነሱ ትክክል የትዳር ጓደኛቸው ግን ጥፋተኛ እንደሆነ የሚነግራቸው ሰው ይፈልጋሉ። “በውጊያው አሸንፈሃል ወይም አሸንፈሻል” እንዲባሉ ይፈልጋሉ።
የዳኛው አነጋገር “የተበደለ ወንድም እንደ ጸናች ከተማ ጽኑ [ከጸናች ከተማ የሚበልጥ አዓት] ነው” የሚለውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ምሳሌ ያስታውሰናል። (ምሳሌ 18:19) አዎን፣ በጋብቻ ውስጥ ጠብ ሲፈጠር የሚጣሉት ወገኖች ምክንያተቢሶችና ግትሮች ሊሆኑ ይችላሉ። አብዛኛውን ጊዜ ልክ በቅጥር እንደተከበበች ‘ጽኑ ከተማ’ በግትርነት ከኔ ይቅር ለማለት እምቢተኞች ይሆናሉ።
ግን እንዲህ መሆን ይገባቸዋልን? አይገባቸውም፤ ሌላ አማራጭ መንገድ አለ። ጋብቻ ጠንካራና ዘላቂ የሚሆነው ገና ከጅምሩ ሁለቱም “እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፣ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ [በነፃ አዓት] ይቅር እንዳላችሁ [በነፃ አዓት] ይቅር ተባባሉ” የሚሉትን የጳውሎስ ቃላት ከተከተሉ ነው። (ኤፌሶን 4:32) እንዲህ ዓይነቶቹን ባሕርያት መኮትኮት ቀላል ነውን? ሁልጊዜ ቀላል አይሆንም። ግን ፍቺስ ቢሆን ቀላል ነው? በፍቺ የፈረሰ ትዳር የሚያመጣው ስሜታዊ ጉዳትና ገንዘብ ነክ ችግር ምን ያህል የሚያሰቃይ ነው? የወላጆቻቸው መፋታት የሚያስከትልባቸውን የማይሽር ጠባሳ ካደጉም በኋላ ለመሸከም የሚገደዱት ልጆችስ?
ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ትዳራቸው እንዳይፈርስ ለማድረግ ቢጥሩና “እንደ ጸናች ከተማ” ሐሳበ ግትር ባይሆኑ በጣም የተሻለ ነው። “የፍጹም አንድነት ማሰሪያ ስለሆነ ፍቅርን ልበሱት” የሚለው ጳውሎስ ለክርስቲያኖች የሰጠው ምክር በተለይ ለባልና ሚስት የሚሠራ ነው።—ቆላስይስ 3:14 አዓት
[ምንጭ]
The Complete Encyclopedia of Illustration/J. G. Heck