የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 6/1 ገጽ 19-23
  • ምሳሌ ሆኑን

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ምሳሌ ሆኑን
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማር
  • በአውስትራሊያ በአቅኚነት ማገልገል
  • ወደ ሌላ አገር ሄዶ እንዲያገለግል ተጋበዘ
  • ጋብቻ፣ እገዳና ጦርነት
  • በእስረኞች ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ያሳለፉት ሕይወት
  • ነፃነትና በአስደናቂ ሁኔታ እንደገና መገናኘት
  • ወደ አውስትራሊያ ተመለሰ
  • ከሞት ጋር ተፋጥጦ ድል መንሳት
    ንቁ!—1993
  • ይሖዋ ከእኔ ጋር ነበር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • በሚስዮናዊነት የተመደብንበትን ቦታ የትውልድ አገራችን አድርገነዋል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 6/1 ገጽ 19-23

ምሳሌ ሆኑን

ክሬይግ ዛንከር እንደተናገረው

ባለቤቴ ጌይልና እኔ አቅኚዎች ወይም የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ከሆንን ስምንት ዓመታችን ነው። ላለፉት ስድስት ዓመታት በአውስትራሊያ ገጠር ውስጥ በሚኖሩ የአቦርጅን ሕዝቦች መካከል አገልግለናል። በዚህም የወላጆቼንና የአያቶቼን አርዓያ እየተከተልን ነው።

እስቲ በተለይ ስለ አያቶቼ ልንገራችሁ። ሁልጊዜ ኦፓ እና ኦማ በማለት በቁልምጫ እንጠራቸዋለን። በደች ቋንቋ አባባ እና እማማ ማለት ነው። ወንድ አያቴ ቻርልስ ሐሪስ ወደ 50 ለሚጠጉ ዓመታት በኖረበት በሜልቦርን ውስጥ አሁንም በቅንዓት እያገለገለ ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማር

ኦፓ የተወለደው ታዝማንያ በምትባል ደሴት ነው። ታዝማንያ አንዷ የአውስትራሊያ ግዛት ናት። በ1924 አያቴ ገና የ14 ዓመት ልጅ ሳለ አባቱ መርከበኞች ለዕቃቸው መያዣ አድርገው የሚጠቀሙበትን ሻንጣ ከአሮጌ ዕቃ መደብር ውስጥ ገዛ። በመንፈሳዊ መንገድ ሲታይ ሻንጣው እውነተኛ ውድ ሀብት የያዘ ሆኖ ተገኘ፤ ምክንያቱም የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የመጀመሪያ ፕሬዘዳንት በነበረው በቻርልስ ቴዝ ራስል የተጻፉትን ተከታታይ መጻሕፍት ይዞ ነበር።

ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደቻልኩት መጽሐፎቹ የኦፓን አባት ብዙም አልሳቧቸውም፤ ኦፓ ግን ያነባቸው ጀመር። መጽሐፎቹ በጣም አስፈላጊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን እንደያዙ ወዲያውኑ ተገነዘበ። ስለዚህ አሁን የይሖዋ ምሥክሮች በዚያን ጊዜ ግን ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመባል የሚታወቁትን የመጽሐፉን አሳታሚ ድርጅት ወኪሎች መፈለግ ጀመረ። ከመጽሐፎቹ ስለተማራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ሊያነጋግራቸው ፈልጎ ነበር።

እነሱን ለማግኘት ለረጅም ጊዜ ሲያጠያይቅ ከቆየ በኋላ ሌሎችን በማስተማሩ ሥራ በትጋት ይካፈሉ የነበሩ ሦስት በዕድሜ የገፉ ሴቶች አገኘ። በእነሱም ሁኔታ ወጣቱ ቻርልስ በጣም ተነካ። በኋላም በ1930 ራሱን ለይሖዋ አምላክ ወስኖ በውኃ ተጠመቀ። የሉካንዳ ንግዱን ተወና ወደ ሲድኒ ሰሜናዊ ክፍል ሄደ። እዚያም የሙሉ ጊዜ ሰባኪ ሆኖ እንዲሠራ የተሠጠውን ሥራ ተቀበለ።

በአውስትራሊያ በአቅኚነት ማገልገል

በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ቻርልስ የሰበከበት የአገልግሎት ክልል በሲድኒ የባሕር ጠረፍ ከምትገኘው ከቦንዲ ከተማ ዳርቻ አንስቶ እስከ ኒው ሳውዝ ዌልስ ገጠሮች ይደርስ ነበር። ከዚያም እሱ ከነበረበት በብዙ መቶ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቃ በአህጉሩ ሌላኛ ክፍል ማለትም በምዕራብ አውስትራሊያ ወደምትገኘው ፐርዝ ከተማ ሄዶ እንዲያገለግል ተመደበ። በፐርዝ ከተማ በሚገኝ የንግድ አካባቢ ለስድስት ወራት ሲመሠክር ከቆየ በኋላ ከሁለት አቅኚዎች ጋር ሆኖ ሰፊ በሆነውና ሕዝብ ተበታትኖ በሚኖርበት ሰሜን ምዕራብ አውስትራሊያ እንዲያገለግል ተመደበ።

ሦስቱ ማለትም አርተር ዊሊስ፣ ጆርጅ ሮልስተንና ቻርልስ እንዲሰብኩ የተመደቡበት ክልል ስፋቱ የጣልያንን አራት እጥፍ ያክላል! ሕዝቡ በየቦታው ተበታትኖ የሚኖርበት፣ ጠፍ ምድረ በዳና ከፍተኛ ሙቀት ያለበት አካባቢ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ከአንዱ የከብት ርቢ ጣቢያ ቦታ ወደ ሌላው ለመሄድ 500 ኪሎ ሜትር ያህል መጓዝ ነበረባቸው። ይጠቀሙባት የነበረችው መኪና በ1930 በነበረው ደረጃ እንኳን አርጅታለች ተብላ ልትጣል የሚገባት ነበረች። እነሱ ግን ጠንካራ እምነት የነበራቸውና ቆራጦች ነበሩ።

የመኪና መንገዱ ጠባብ፣ ጉድጓድ የበዛበትና አለፍ አለፍ እያለ የግመሎች መንገድ አቋርጦት የሚያልፍ በአቧራ የተሞላ መንገድ ነበር። ቡልደስት እየተባለ የሚጠራው በጣም የላመ አቧራ እዚህም እዚያም የሚገኙትን አደገኛ ጉቶዎች ይሸፍናቸዋል። ስለዚህ የመኪናዋ ሞላ ደጋግሞ ቢሰበር አያስገርምም። የኋላ ጎማዎቿን የሚይዘው ዘንግ ሁለት ጊዜ ተሰብሮ ነበር። ጎማዎቿ ብዙ ጊዜ ተበስተውባቸዋል። ብዙውን ጊዜ አቅኚዎቹ ከአሮጌ ጎማ ላይ ትንሽ ይቆርጡና በተቀደዱ ጎማዎች ላይ ለጥፈው ጉዟቸውን ይቀጥላሉ።

ልጅ ሳለሁ ኦፓን እንዲህ ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያጋጠማቸውም በሥራው እንዲገፉበት ያበረታታቸው ምን እንደሆነ ጠይቄው ነበር። ብቻቸውን በሚሆኑበት ጊዜ ከይሖዋ ጋር በጣም ይቀራረቡ እንደነበረ ነገረኝ። አንዳንዴ የሚያጋጥመን ችግር መንፈሳዊ በረከት የሚያመጣ ይሆንልን ነበር ብሎኛል።

ከሌሎች እበልጣለሁ ለማለት ወይም ራሱን ለማመጻደቅ ብሎ ሳይሆን ኦፓ ብዙዎች ቁሳዊ ሀብት ለማከማቸት ከመጠን በላይ መጨነቃቸው እንደሚያስገርመው ይናገራል። “በተቻለ መጠን ጓዝ ሳያበዙ መኖር በጣም የተሻለ ነው። ኢየሱስ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ደጅ ማደር ከነበረበት እኛም የተመደብንበት ስፍራ እንዲህ ማድረጉ አስፈላጊ ከሆነ በደስታ ልናደርገው ይገባል” በማለት አሳስቦኛል። (ማቴዎስ 8:19, 20) እውነትም እርሱና ጓደኞቹ ያደረጉት ይህንኑ ነበር።

ወደ ሌላ አገር ሄዶ እንዲያገለግል ተጋበዘ

በ1935 ኦፓ በሰላማዊ ውቅያኖስ ደቡባዊ ክፍል በሚገኙ ደሴቶች ለሚኖሩ ሰዎች ለመስበክ አዲስ የሥራ ምድብ ተቀበለ። ከሌሎች ስድስት ጋር ሆኖ 16 ሜትር ርዝመት ባላት ብርሃን አምጪ በተባለች የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጀልባ ሆኖ ወደዚያው ተጓዘ።

አንድ ጊዜ ከአውስትራሊያ በስተሰሜን በሚገኘው በኮራል ባሕር ላይ ሳሉ ብርሃን አምጪ የተባለችው ጀልባቸው የመጠባበቂያ ሞተር ተበላሸ። ምንም ነፋስ አልነበረም። ስለዚህ ከቦታው መነቃነቅ አቃታቸው፤ ከየብስ ደግሞ ብዙ ኪሎ ሜትር ርቀዋል። ግሬት ባሪየር ሪፍ ከሚባለው ቋጥኞች ሠንሠለት ጋር የመጋጨት አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችል የነበረ ቢሆንም ኦፓ አካባቢው በነበረው እርጋታ በጣም ተገርሞ ነበር። በማስታወሻ ደብተሩ ላይ “ባሕሩ በጣም ጸጥ ብሏል። በዚያ ጸጥ ያለ ባሕር ላይ ማታ ማታ ጀንበር ስትጠልቅ እንዴት ደስ ትል እንደነበር እስከ መቼም አልረሳውም። እይታው የሚማርክ ስለነበረ በአእምሮዬ ውስጥ እንዳይጠፋ ሆኖ ተቀርጿል” ብሎ ጽፎ ነበር።

የሚያስደስተው ግን ከዓለቱ ጋር ከመጋጨታቸው በፊት ንፋስ መንፈስ ጀመረ። ስለዚህ ሸራውን ሰቀሉና ጉዟቸውን በመቀጠል በፓፑዋ ኒው ጊኒ ወዳለችው ሞርስቤይ ወደብ በደህና ደረሱ። እዚያም ሞተሩን አሠሩት። ከሞርስቤይ ወደብ ወደ ተርስዴይ ደሴት፣ ከዚያም ከኢንዶኔዥያ ደሴቶች መሃል ወደ ትልቁ ደሴት ወደ ጃቫ ተጓዙ። ኦፓ “በምድር ወገብ ላይ የተዘረጋ ሀብል” እየተባለ ለሚጠራው ለዚህ አገር ከፍተኛ ፍቅር አደረበት። በዚያን ጊዜ ኢንዶኔዥያ የደች ቅኝ ግዛት ነበረች። ስለዚህ አያቴ የደችና የኢንዶኔዥያን ቋንቋ ተማረ። በስብከት ሥራው ላይ የሚያበረክታቸው ጽሑፎች ግን በአምስት ቋንቋዎች ማለትም በደች፣ በኢንዶኔዥያ ቋንቋ፣ በቻይንኛ፣ በእንግሊዝኛና በአረብኛ የተዘጋጁ ነበሩ።

ኦፓ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማበርከት ረገድ የተዋጣለት ነበር። አንድ ጊዜ ሥራችንን በቅርበት ይከታተል የነበረ የደች ባለ ሥልጣን በባታቪያ (አሁን ጃካርታ ትባላለች) የሚገኘውን የመጠበቂያ ግንብ የጽሑፎች ማከማቻ ኃላፊ ክሌም ዴሻምፕን ጠራውና “በምሥራቅ ጃቫ ውስጥ የሚሠሩ ምን ያህል ሰዎች አሏችሁ?” ብሎ ጠየቀው።

“አንድ ብቻ” ሲል ወንድም ዴሻምፕ መለሰ።

ባለ ሥልጣኑ “ያምነኛል ብለህ ነው?” ብሎ ጮኸ። “በየቦታው ካሠራጫችኋቸው ጽሑፎች መገመት እንደሚቻለው በጣም ትልቅ ሠራዊት ሳይኖራችሁ አይቀርም!”

ኦፓ በሕይወቱ ውስጥ ከሰማቸው በጣም የሚያረኩ ሙገሳዎች አንዱ ይህ እንደሆነ ይሰማዋል። ሆኖም ሙገሳው ይገባዋል፤ ምክንያቱም በየወሩ ከ1,500 እስከ 3,000 የሚደርሱ ልዩ ልዩ ጽሑፎችን ማበርከቱ የተለመደ ነገር ነበር።

ጋብቻ፣ እገዳና ጦርነት

ኦፓ ታኅሣሥ 1938 ቪልሄልሚና የተባለች አንዲት ወጣት ኢንዶኔዥያዊት አገባ። እርሷም በኋላ አያቴ ሆነች። ኦማ ማለትም አያቴ ደግ፣ ረጋ ያለች፣ ታታሪና የለዘበ አነጋገር ያላት ነበረች። ልጅ ሳለሁ የቅርብ ጓደኛዬ እሷ ስለነበረች በደንብ አውቃታለሁ።

ኦፓና ኦማ ከተጋቡ በኋላ አብረው በአቅኚነት ማገልገላቸውን ቀጠሉ። በዚያን ጊዜ ብርሃን አምጪ በተባለችው ጀልባ ይጠቀሙ የነበሩት አቅኚዎች ግማሾቹ ወደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች ሲሄዱ ሌሎቹ ደግሞ ወደያገራቸው ተመልሰው ነበር። ኦፓ ግን በኢንዶኔዥያ ለመኖር መረጠ፤ እስከ መጨረሻው እዚያው ለመቆየት ወስኖ ነበር።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተቃረበ ሲመጣ ኢንዶኔዥያን ያስተዳድር የነበረው የደች መንግሥት በቀሳውስት ገፋፊነት የይሖዋ ምሥክሮችን አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ይከለክል ጀመር። በመጨረሻም ሥራችን ታገደ። በዚህ ምክንያት እንጠቀም የነበረው በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ስለነበረ የስብከቱን ሥራ ማካሄድ ያስቸግረን ነበር። ኦፓና ኦማ ለማገልገል በሄዱባቸው ከተሞች ሁሉ ተይዘው ወደ ባለ ሥልጣኖች ይወሰዱና ይመረምሯቸው ነበር። ልክ እንደ ወንጀለኞች ተደርገው ይታዩ ነበር። ሥራቸው ከታገደ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የኦማ አማች በክርስቲያናዊ ገለልተኛ አቋሙ ምክንያት ወኅኒ ወረደ። ከዚያም በደች እስር ቤት ውስጥ እንዳለ ሞተ።

ኦፓና ኦማ የሚኖሩት እንደ ተጎታች ቤት ሆኖ በተሠራ የጭነት መኪና ላይ ነበር። በዚህ ተጎታች ቤት ውስጥ እየኖሩ በጃቫ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር እየተጓዙ ሰብከዋል። በ1940 የጃፓን ወታደራዊ ወረራ እያንዣበበ ሳለ ሴት ልጅ በመውለድ ተባረኩ፤ እሷም እናቴ ሆነች። ከሁለት ዓመታት በፊት የወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ፕሬዘዳንት ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ ሰጥቶት በነበረው ንግግር ርዕስ መሠረት ሕፃኗን ቪክትሪ (ድል) ብለው ሰየሟት። ሕፃንዋ እስከተወለደችበት ጊዜ ድረስ በአቅኚነታቸው ቀጠሉ።

በ1942 መጀመሪያ ላይ ኦፓ፣ ኦማና ቪክትሪ በደቾች የዕቃ ማጓጓዣ መርከብ ሆነው ከቦርኔዎ ወደ ቤታቸው እየመጡ ሳሉ ከጃፓኖች የጦር መርከብ ከፍተኛ የመድፍ ድምፅ ተሰማ። መብራት ጠፋ፤ ሰው ሁሉ ጮኸ። በዚህ መንገድ ጦርነቱ የቤተሰቤንም ሕይወት መንካት ጀመረ። ምንም እንኳን በደህና ወደ ወደቡ መድረስ ቢችሉም ከጥቂት ቀናት በኋላ ጃፓኖች ጃቫን ወረሯት። አንድ የደች ባለ ሥልጣን ኦፓና ኦማ የት እንደሚኖሩ ለጃፓን ወታደሮች ጠቆማቸው።

ጃፓናውያኑ አገኟቸውና ያላቸውን ንብረት በሙሉ፣ የቪክትሪን መጫወቻዎች ሳይቀር ወሰዱባቸው። ከዚያም ወደ ሁለት የተለያዩ የእስረኞች ማጎሪያ ካምፖች ተወሰዱ። ቪክትሪ ከኦማ ጋር እንድትሆን ተፈቀደላት። ኦፓ ከዚያ በኋላ ለሦስት ዓመት ተኩል አላያቸውም።

በእስረኞች ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ያሳለፉት ሕይወት

ኦፓ በቁጥጥር ሥር ሆኖ ባሳለፋቸው ዓመታት ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው ያዛውሩት ነበር። ከሰራባያ ወደ ኢንጋዊ፣ ከዚያ ወደ ባንደንግ፣ በመጨረሻ ወደ ቺማሂ አዛወሩት። ያለማቋረጥ ከቦታ ቦታ የሚያዘዋውሯቸው አንድ ላይ የማምለጥ ሙከራ ቢደረግ ያንን ለማክሸፍ ሲሉ ነበር። አብዛኞቹ እስረኞች የደች ተወላጆች ሲሆኑ ጥቂት እንግሊዛውያንና አንዳንድ አውስትራሊያውያንም ነበሩባቸው። ኦፓ ካምፕ ውስጥ እያለ ጸጉር ማስተካከል ለመደ። አሁንም አንዳንድ ጊዜ ጸጉር ያስተካክላል። እንዲይዝ የተፈቀደለት ሃይማኖታዊ መጽሐፍ የኪንግ ጀምስ ትርጉም የሆነውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሱን ብቻ ነበር።

በዚህ ጊዜ ኦማንና ቪክትሪንም ከአንዱ ካምፕ ወደ ሌላው ሲያዛውሯቸው ነበር። የካምፑ አዛዥ ሴቶቹ ከካምፑ እየወጡ “ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲያበረክቱ” ያዛቸው ነበር። በሆነ ምክንያት ኦማ አንድ ጊዜም ለዚህ ተመርጣ አታውቅም። ከጊዜ በኋላ ግን ሴቶቹ ከካምፑ የሚወጡት ለጃፓን ወታደሮች ዝሙት አዳሪ ሆነው እንዲያገለግሉ ሲባል እንደነበረ ሰማች።

የጃፓን ወታደሮች ሴቶች ልጆችን ስለሚጠሉ ኦማ ሁልጊዜ ቪክትሪን እንደ ወንድ ታለብሳትና ጸጉሯን በአጭሩ ትቆርጥላት ነበር። ቪክትሪ (ድል) የተባለው ስሟ ትልቅ ችግር ፈጠረ። የካምፑ አዛዥ የስሟ ትርጉም ምንድን ነው? ድል ለጃፓን ንጉሠ ነገሥት ሠራዊት ወይስ ለአሜሪካውያን? ብሎ ጠየቃት።

አያቴም “የአምላክ መንግሥት የምድር መንግሥታትን በሙሉ ድል ታድርግ!” ስትል በኩራት መለሰችለት።

“ድል ለጃፓን ንጉሠ ነገሥት ሠራዊት” አልልም በማለቷ ኦማና የአምስት ዓመት ልጅዋ ቪክትሪ በጣም በሚያቃጥለው የሐሩር ፀሐይ ላይ ለስምንት ሰዓታት ቀጥ ብለው በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ተደረጉ። ጥላ የለም፣ ውኃ የለም፣ መቀመጥ አይቻልም፣ ዘና ብሎ መቆምም አይፈቀድም፤ ሆኖም በይሖዋ እርዳታ ይህን አሰቃቂ የመከራ ጊዜ አለፉት።

ኦማ ከታሰረች ከአንድ ዓመት በኋላ የካምፑ አዛዥ ባልሽ ሞቷል ብሎ ነገራት። እያዘነች የኦፓን ፎቶ ባረጀው ሻንጣዋ ውስጥ ከሥር በኩል አስቀመጠችው። ሐዘን ቢኖርባትም በአቋሟ ቀጠለች።

የእስር ቤቱ ኑሮ አስቸጋሪ ነበር። በየቀኑ ለያንዳንዱ ሰው ይሰጥ የነበረው የምግብ ራሽን ለቁርስ አንድ ስኒ የካሳቫ ገንፎ፣ ለምሳ 190 ግራም የሚመዝን ሳጎ ከሚባል ዱቄት የተሠራ ዳቦ፣ ለራት ደግሞ ሩዝ ያለበት ቀጭን አንድ ስኒ የአትክልት ሾርባ ነበር። የሚሰጠው ምግብ ስለማያጠግብ በተመጣጠነ ምግብ እጦት የሚመጣ በሽታ ተነሳ። በየቀኑ በተቅማጥ በሽታ የተያዙ ሰዎች ይሞቱ ነበር።

ኦፓ ታስሮ በነበረበት ጊዜ ፔላግራ የሚባልና በምግብ ዕጦት የሚመጣ የእብጠት በሽታ ይዞት ነበር። ኦማ ትንሿ ልጅዋ በረሃብ እንዳትሞባት ብላ የራሷን የምግብ ራሽን ብዙውን ጊዜ ለቪክትሪ ትሰጣት ስለነበረ እሷም ልትሞት ተቃርባ ነበር። ጭካኔና ረሐብ ጐን ለጐን የሚሄዱ ነገሮች ሆኑ። በሕይወት ሊተርፉ የቻሉት ወደ አምላካቸው ወደ ይሖዋ በጣም በመጠጋታቸው ነው።

“ነፃነት ማለት መለኮት ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ጋር ተስማምቶ መኖር ነው” የሚለውን የኦፓን የዘወትር አባባል በደንብ አስታውሰዋለሁ። ስለዚህ ኦፓ ጥብቅ በሆነ እስራት ሥር በነበረበትም ጊዜ ቢሆን ነፃ እንደሆነ ይሰማው ነበር። በርግጥም እርሱና ኦማ ለይሖዋ የነበራቸው ፍቅር ‘በዚያ ሁሉ እንዲጸኑ’ ረድቷቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 13:7) አሁን ጌይልና እኔ የምንጥረው ከአምላክ ጋር እንዲህ ያለ የቅርብ ግንኙነት እንዲኖረን ነው።

ነፃነትና በአስደናቂ ሁኔታ እንደገና መገናኘት

በመጨረሻ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1945 አበቃ። ጃፓን እጅዋን ከሰጠች በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኦፓ በባቡር ወደ ሌላ ቦታ ተወሰደ። ከጃካርታ ወደ ባንደንግ ሲጓዝ የኢንዶኔዥያ ወታደሮች ባቡሩን አስቆሙት። ምንም እንኳን ከጃፓን ጋር የነበረው ጦርነት ቢያበቃም ኢንዶኔዥያውያን ከቅኝ ገዣቸው ከደች ነፃ ለመውጣት ይዋጉ ነበር። ኦፓ በድንገት ከባቡሩ እንዲወርድ ስለተደረገ በጣም ከመደናገጡ የተነሣ በእንግሊዝኛ መናገሩን ረስቶ በደች መናገር ጀመረ። ኢንዶኔዥያውያኑ ደግሞ ደችን ቋንቋ የጠላት ቋንቋ አድርገው ይቆጥሩት ነበር፤ ጠላት ደግሞ መገደል አለበት።

እንዳጋጣሚ ወታደሮቹ ኦፓን ሲፈትሹት አውስትራሊያዊ መሆኑን የሚገልጽ መንጃ ፈቃዱን አገኙ። እሱ ግን ያ መንጃ ፈቃድ ያለው መሆኑን እንኳን ረስቶት ነበር። የሚያስደስተው ኢንዶኔዥያውያን ከአውስትራሊያ ጋር ጦርነት አልገጠሙም ነበር። እስከዛሬ ድረስ ኦፓ የአውስትራሊያ ዜግነት ያለው መሆኑን ያረጋገጠው ያ መንጃ ፈቃዱ እንዲገኝ ያደረገው አምላክ ነው ይላል፤ ምክንያቱም ወታደሮቹ እነሱን ካስቆሟቸው ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በባቡሩ ይጓዙ የነበሩ 12 የደች ተወላጆችን ገደሉ።

ይህ ሁኔታ ከደረሰ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኦማና ቪክትሪ በጦርነት ከፈራረሰው አካባቢ ርቀው ለመሄድ መጓጓዣ ይጠብቁ ነበር። መንገድ ዳር ቁጭ ብለው ሳሉ ወታደሮችንና ሲቪሎችን የያዙ ብዙ የጭነት መኪናዎች ተከታትለው ያልፉ ነበር። ለምን እንደሆነ አይታወቅም መኪኖቹ በድንገት እንዲቆሙ ተደረገ። ኦማ ዞር ብላ እነሱ አጠገብ ወደቆመው የጭነት መኪና ስትመለከት አንድ በጣም የከሳ ሰው በጨረፍታ አየች፤ ሰውየው ማን እንደሆነ ወዲያው አወቀችው። ያስገርማል፤ ያ ሰው ባለቤቷ ነበር! በተገናኙበት ጊዜ የተሰማቸውን ስሜት በቃላት መግለጽ አይቻልም።

ወደ አውስትራሊያ ተመለሰ

አያቴና ቤተሰቡ በኢንዶኔዥያ ውስጥ ለ11 ዓመታት ከኖሩ በኋላ በ1946 ወደ አውስትራሊያ ሲመለሱ ኑሮ ቀላል አልሆነላቸውም። ወደ አውስትራሊያ የተመለሱት በጦርነት ምክንያት የተሰደዱ ችግረኞችና የተመጣጠነ ምግብ በማጣት የከሱ ስደተኞች ሆነው ነበር። የአካባቢው ሰዎችም በጥርጣሬ ይመለከቷቸው ነበር። እስያውያን ስደተኞች የዘር ጥላቻ ይደርስባቸው ስለነበር ኦማና ቪክትሪ የአካባቢው ሕዝብ በስድብ መከራ አበላቸው። ኦፓ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ምግብ ለማቅረብ፤ እንዲሁም የቤት ኪራይ ለመክፈል እንዲችል ለረጅም ሰዓታት ብዙ መሥራት ነበረበት። ይህ ሁሉ ችግር ቢኖርባቸውም መንፈሳዊነታቸው ምንም ሳይነካ ጸንተው ያን ጊዜ አሳለፉት።

አሁን ከ48 ዓመታት በኋላ ኦፓ የሚኖረው በሜልቦርን ሲሆን ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ይካፈላል። ቪክትሪና ልጆቿ እውነትን ተቀብለው ራሳቸውን ለይሖዋ ሲወስኑና እያንዳንዳቸው በየተራ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ አቅኚዎች ሲሆኑ ተመልክቷል።

በኋላ አባቴ የሆነው ዴስ ዛንከርና ቪክትሪ የተጠመቁት በ1950ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ነበር። ዴስ በ1958 የአውስትራሊያ ቤቴል ቤተሰብ አባል ሆነ። ልዩ አቅኚ ሆና ታገለግል የነበረችውን ቪክትሪን ካገባ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ በአቅኚነት ሲያገለግሉ ቆዩ። ከዚያም ተጓዥ አገልጋዮች እንዲሆኑ ተጋበዙ። በመሃሉ እኔ ስለተወለድኩ እኔን ለማሳደግ ሲሉ የተጓዥነት ሥራቸውን ለማቆም ተገደዱ። ሆኖም ይህ ከሆነ 27 ዓመታት ቢያልፉም አባቴ እስካሁን በአቅኚነት እያገለገለ ነው።

በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ኦማ እናቴ ባደገችበት ቤት ውስጥ እያለች በሰላም አረፈች። እኔ፣ ታናሽ ወንድሜና እህቴም ያደግነው ሜልቦርን በሚገኘው በዚሁ ቤት ውስጥ ነበር። ሁላችንም በአንድ ቤት ውስጥ መኖራችን ለቤተሰባችን እውነተኛ በረከት አምጥቷል። አንዳንድ ጊዜ ቤቱ በጣም ይጣበብ የነበረ ቢሆንም ሁኔታው አስጨንቆኝ የሚያውቅበት ጊዜ ትዝ አይለኝም። እንዲያውም ከጌይል ጋር ከተጋባን በኋላ ለመጀመሪያዎቹ አራት ዓመታት የኖርነው እዚሁ ቤት ውስጥ ነበር። ቤታችን የተጣበበ ቤት ቢሆንም ባለቤቴ ትወድደው ነበር። አዲስ የአገልግሎት ምድብ ተሰጥቶን ከዚያ ቤት ስንወጣ አለቀስኩ። ያ ቤት ትልቅ ድጋፍና ፍቅር ያገኘሁበት ቤት ነበር።

ይሁን እንጂ አሁን ጌይልና እኔ የምንደሰትባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉን፤ ምክንያቱም ወላጆቼና የነሱ ወላጆች ያደረጉትን እያደረግን ስለሆነ ነው። ቤታችንን የለቀቅን ጊዜ የምንሄድበትን ምክንያት ማለትም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም የምንሄድ መሆኑን ስናስብ ተጽናናን። አስቸጋሪ የሥራ ምድብ በተሰጣቸው ጊዜ፣ ከባድ ድኽነት ባጋጠማቸው ጊዜ፣ ለብዙ ዓመታት በጃፓኖች የእስረኞች ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ በታሰሩበት ጊዜ ሳይቀር ይህንኑ መጽናኛ አግኝተው የነበሩት አያቶቻችን የተዉልንን መልካም አርዓያ ለመከተል ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

ኦፓ ንጉሥ ዳዊት በመንፈስ አነሣሽነት ለይሖዋ የተናገራቸው “ምሕረትህ [ፍቅራዊ ደግነትህ አዓት] ከሕይወት ይሻላል” የሚሉት ቃላት ሁልጊዜ ያጽናኑታል። (መዝሙር 63:3) አያቴ ያንን ፍቅራዊ ደግነት አግኝቶ ለዘላለም መደሰት ዘወትር አጥብቆ የሚፈልገው ነገር ነው። ከእርሱ ጋር ሆኖ ያንን ፍቅራዊ ደግነት ማግኘት የመላው ቤተሰቡ ፍላጎት ነው።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኦማና ኦፓ ሃሪስ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክሬይግ ዛንከር (ከኋላ)፣ ከባለቤቱ፣ ከወላጆቹና ከታናናሽ ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ