በፊጂ ባሕሮች ውስጥ ‘ዓሣ ማስገር’
ፊጂ የሚለው ስም፣ በደቡባዊ የሰላማዊ ውቅያኖስ የሚገኙ ገነት መሰል ደሴቶችን ምስል በአእምሮአችን ውስጥ ይደቅንብናል። ሰማያዊና አረንጓዴ ቀለማት የሚንጸባረቁባቸው ውኃዎች፣ የዛጎሎች ክምር የሆኑ በባሕር ውስጥ የሚገኙ ትልልቅ አለቶች፣ ወዲያና ወዲህ የሚወዛወዙ የኮከነት ዛፎች፣ ልምላሜን የተላበሱ ተራራዎች፣ አነስተኛ የአሣ ዝርያዎች፣ እንግዳና ማራኪ የሆኑ ፍራፍሬዎችና አበቦች፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ከኒው ዚላንድ በስተሰሜን 1,800 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በደቡብ ሰላማዊ ውቅያኖስ ላይ ባለችው የ300 ደሴቶች ስብስብ በሆነችው በዚህች አገር ላይ እንደ ልብ ልታገኛቸው ትችላለህ። በዚህም ምክንያት ፊጂ ማንኛውም ሰው የሚቋምጥላት በሐሩር ክልል የምትገኝ ገነት ነች ቢባል ትስማማ ይሆናል።
ይሁን እንጂ ፊጂ መስህቧ ተፈጥሮአዊ ውበት ብቻ አይደለም። አዎን፣ በባሕር ውስጥ ባሉ የዛጎል ክምሮች ዙሪያ የሚኖሩ ብዙ የዓሣ ዘሮች እንዳሉ ሁሉ በየብሱም ላይ ብዙ ዓይነት ዓሦች ይገኛሉ። በፊጂ ውስጥ የሚኖሩት ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች ብዛት በሌሎቹ የደቡብ ሰላማዊ ውቅያኖስ ደሴቶች ውስጥ ከሚኖሩት ከፍተኛ ብልጫ አላቸው። ወደ 750,000 ከሚጠጉት ነዋሪዎቿ መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሁለቱ ጎሳዎች ከሜላኔዢያ የፈለሱት የፊጂ ተወላጆችና በብሪታንያ የቅኝ አገዛዝ ዘመን ከሕንድ የተጋዙት ሠራተኞች ዝርያዎች የሆኑት ፊጂ ውስጥ የተወለዱ ሕንዶች ናቸው። ሆኖም የባናና ደሴት ተወላጆች፣ ቻይናውያን፣ አውሮፓውያን፣ የጊልበርት ደሴት ተወላጆች፣ የሮቱማ ደሴት ተወላጆች፣ የቱቫሉ ደሴት ተወላጆችና ሌሎችም በዚህች አገር ውስጥ ይገኛሉ።
በዚህ ብዙ ድብልቅ ባሕሎችን አቅፎ በያዘው ኅብረተሰብ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ‘ዓሣ የማስገሩን’ ሥራ ተያይዘውታል። (ማርቆስ 1:17) ይህን በመሰለ የብዙ ዓይነት ዘሮች ቅልቅል በሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ የአምላክን መንግሥት የምሥራች መስበክ እንዲህ ቀላል ሥራ አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ የቋንቋና የባሕል እንቅፋቶችን መቋቋም ያስፈልጋል። ምንም እንኳን እንግሊዝኛ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ ቢሠራበትም የፊጂ፣ የሂንዱ፣ የሮቱማ ወይም ሌሎች ቋንቋዎችን መጠቀም ግድ የሚሆንበትም ጊዜ አለ።
የተለያዩ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ካሏቸው ከእነዚህ ሰዎች ጋር ለመወያየት የተለያዩ የአቀራረብ ዘዴዎችንም መጠቀም ያስፈልጋል። አብዛኛዎቹ የፊጂ ተወላጆችና ሌሎች የደሴቶቹ ነዋሪዎች የተለያዩ የክርስትና እምነቶችን ይከተላሉ። ሕንዶቹ ሂንዱይዝምን፣ እስልምናንና ሲኪዝምን የሚከተሉ ሲሆን አብዛኛዎቹ የሂንዱይዝም እምነት ተከታዮች ናቸው። በከተሞቹና በመንደሮቹ ውስጥ ብዙ ቤተ ክርስቲያኖች አሉ፤ ሆኖም በሁለቱ የፊጂ ትልልቅ ደሴቶች ውስጥ ልክ እንደዚሁ ብዙ የሂንዱይዝም ቤተ መቅደሶችና የእስልምና መስጊዶች አሉ።
በዚያ አገር የሚኖሩት ብዙዎቹ ምሥክሮች ሦስቱን ዋና ዋና ቋንቋዎች ማለትም እንግሊዝኛ፣ የፊጂንና የሂንዲን ቋንቋ እየተናገሩ ያደጉ ናቸው። ይህ ችሎታ ያላቸው መሆኑ ‘ዓሣ ለማስገሩ’ ሥራ ትልቅ ጥቅም አለው። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች አንድ የፊጂ ተወላጅ የሂንዲን ቋንቋ አቀላጥፎ ሲናገር ወይም አንድ ሂንዱ የፊጂን ቋንቋ አቀላጥፎ ሲናገር ሲሰሙ ይደነቃሉ። የባሕል፣ የሃይማኖትና የቋንቋ ልዩነቶችን አሸንፎ ‘ምሥራቹን ለሌሎች ማካፈል’ ሁለገብ መሆንን ይጠይቃል።—1 ቆሮንቶስ 9:23
በአንድ የፊጂዎች መንደር ‘ዓሣ ማስገር’
የፊጂ ተወላጆች ተግባቢና እንግዳ ተቀባይ የሆኑ ሕዝብ ናቸው። ከአንድ መቶ ዘመን እምብዛም ከማይበልጥ ጊዜ በፊት የጎሳ ጦርነት ተስፋፍቶ ነበር ብሎ መገመት ያዳግታል። እንዲያውም ፊጂ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአውሮፓውያን ጋር ግንኙነት ስትመሠርት ፊጂ ሰው በላ ደሴቶች በመባል ትታወቅ ነበር። በመጨረሻ፣ አንድ ከፍተኛ ባለ ሥልጣን የመሪነት ሥልጣን ከጨበጠና እምነቱን ከቀየረ በኋላ ጦርነትና ሰው በላነቱ እየቀረ መጣ። በስፋት የሚታወቀው ቦአን የተባለው ቋንቋ ቢሆንም የጎሳ ልዩነቶች እንዳሉ የዘለቁት ብዙ ተመሳሳይ የጎሳ ቋንቋዎች ባሉባቸው ክፍላተ ሃገር ውስጥ ብቻ ነው።
ከዋና ከተማዋ ከሱቫ ሌላ በመላዋ ፊጂ ውስጥ ብዙ ከተሞች አሉ። አብዛኛዎቹ የፊጂ ተወላጆች በቱራጋ ኒ ኮሮ ወይም በጭቃ ሹም በሚመሩ መንደሮች ውስጥ ይኖራሉ። ‘ዓሣ ለማስገር’ ወደ አንድ መንደር ሲገባ የተለያዩትን ቡሬዎች ወይም የአካባቢውን ቤቶች ለማንኳኳት የጭቃ ሹሙን ፈቃድ መጠየቅ የተለመደ ነገር ነው። አንዳንድ የመንደር ቄሶች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ በሚያደርጉት ተቃውሞ የተነሣ ካልሆነ በስተቀር ፈቃድ እምብዛም አይከለከልም። ወደ አንድ ፊጂያዊ ቤት ስንሄድ የሚያጋጥመን ሁኔታ ምንድን ነው?
ወደ ቡሬው ከገባን በኋላ እግራችንን አቆላልፈን በወለሉ ላይ እንቀመጣለን። የሰዎችን ስሜት ለመማረክ በምዕራባውያን አገሮች እንደሚደረገው ዓይነት በጥንቃቄ የተመረጡ የመግቢያ ቃላትን መጠቀም በዚህ ቦታ አያስፈልግም። ስለ አምላክ ለመነጋገር ወደ ቤታቸው ለመጣ ሰው ሁሉ በራቸው ክፍት ነው። መጽሐፍ ቅዱሱን እንዲይዝ ግብዣ ሲቀርብለት የቤቱ ባለቤት “ቱሎ” (ይቅርታ አንድ ጊዜ) ካለ በኋላ ደስ እያለው ተነሥቶ ወደ መጽሐፍ መደርደሪያው በመሄድ በፊጂ ቋንቋ የተጻፈ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ይዞ ይመጣና ሊያነጋግረው የመጣው ሰባኪ የሚጠቅሳቸውን የተለያዩ ጥቅሶች በጉጉት ያነባል። ይሁን እንጂ የፊጂዎች የእንግዳ ተቀባይነትና የሰው አክባሪነት ጠባይ ለየት ባለ መንገድ ፈታኝ ሁኔታን ይፈጥራል። የቤት ባለቤቶች በውይይቱ ውስጥ እንዲካፈሉ፣ የሚቀርቡላቸውን ምክንያታዊ ነጥቦች አንድ በአንድ እንዲከታተሉ ለማበረታታት ወይም የእነርሱን እምነቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር ለምን ማነጻጸር እንደሚገባቸው ለማስገንዘብ በጣም አስተዋይና ዘዴኛ መሆን ያስፈልጋል።
ፊጂያውያን የቤት ባለቤቶች በጥቅሉ ስለማኅበራዊ ሁኔታዎች ወይም ጉዳዮች ከመነጋገር ይልቅ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ትምህርቶች መወያየት የበለጠ ያስደስታቸዋል። እንዲያውም ፊጂ ውስጥ ከሚገኙት ከ1,400 በላይ ከሚሆኑት ትጉ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ብዙዎቹ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሊሳቡ የቻሉት ሲኦል ምን ዓይነት ቦታ ነው? ወደ ሰማይ የሚሄዱት እነማን ናቸው? ምድር ትጠፋለችን? በሚሉትና እነዚህን በመሳሰሉት ጥያቄዎች ላይ በተደረገ ውይይት አማካኝነት ነው። ይሁን እንጂ ሰዎቹ ያሳዩትን ፍላጎት ለማጎልበት የሚፈጠሩትን አዳዲስ ሁኔታዎች ለማስተናገድ እንዳስፈላጊነቱ ማስተካከያ ማድረግንና ጽናትን ይጠይቃል። አንድ ሰው በቀጠሮ ሰዓት ወደ ቤቱ ባለቤት ተመልሶ ሲሄድ ብዙውን ጊዜ ሰውዬው ወደ ቴቴ (እርሻ) ወይም ወደ ሌላ ቦታ እንደሄደ ይነገረዋል። ይህ የሚሆነው ጉብኝቱን ስለማይፈልጉ አይደለም፤ ለጊዜ ያላቸው አመለካከት የተለየ ስለሆነ ብቻ ነው። እርግጥ የአገሬው ተወላጅ ለሆኑት ምሥክሮች ይህ አዲስ ነገር አይደለም። በሌላ ጊዜ ሄደው ከማነጋገር ወደ ኋላ አይሉም። የመንገድ ስሞች ወይም የቤት ቁጥሮች የሉም፤ ስለዚህ አንድ ሰው ከዚህ በፊት ያነጋገረውን ሰው ተመልሶ ለማነጋገር ጥሩ የማስታወስ ችሎታ እንዲኖረው ያስፈልጋል።
በፖሊኔዣውያን መንገድ ‘ዓሣ ማስገር’
እስቲ አሁን አንድ ተጓዥ አገልጋይ ወይም የክልል የበላይ ተመልካች በሮቱማ የሚገኘውን አነስተኛ ጉባኤ በሚጎበኝበት ጊዜ ‘ዓሣ ለማስገር’ አብረነው እንጓዝ። በእሳተ ገሞራ ሳቢያ የተፈጠሩ ደሴቶች የተከማቹበት ይህ አካባቢ ከፊጂ በስተሰሜን 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ወደዚህ ቦታ ለመድረስ 19 መቀመጫዎች ባሉት አውሮፕላን ተሳፍረን እንበራለን። ዋነኛው ደሴት በድምሩ ወደ 3,000 የሚጠጋ የሕዝብ ብዛት ያለው ሲሆን የቆዳ ስፋቱ 50 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ብቻ ነው። ወደ 20 የሚጠጉ መንደሮችን የሚያገናኝ አሸዋማ መንገድ በባሕሩ ዳርቻ ተዘርግቷል። ሮቱማ በፊጂ የምትተዳደር ብትሆንም ለየት ያለ ባሕልና ቋንቋ አላት። ከፖሊኔዥያ የፈለሱት ነዋሪዎቿ በአቋማቸው ከሜላኔዥያ ፊጂዎች ይለያሉ። በሃይማኖት ረገድ አብዛኛዎቹ የሮማ ካቶሊኮች አለዚያም ሜቶዲስቶች ናቸው።
አውሮፕላኑ ዝቅ እያለ መጥቶ ለማረፍ ሲያኮበኩብ የደሴቷን ለምለም ተክሎች እንመለከታለን። ላባ የመሰሉ ቅጠሎች ያንዠረገጉትን የኮከነት ዛፎች በየቦታው ማየት ይቻላል። በሳምንት አንድ ጊዜ በሚደረገው በረራ የሚመጡትን ሰዎች እንኳን ደህና መጣችሁ ብሎ ለመቀበል በርካታ ሰዎች በቦታው ተገኝተዋል። በመሐከላቸው አንድ የምሥክሮች ቡድን ይገኛል። ሞቅ ያለ ሰላምታ ካቀረቡልን በኋላ ጥማችንን ለማርካት ከበላያቸው ክፍተት ያላቸውን በርከት ያሉ ትልልቅና አረንጓዴ ኮከነቶችን ሰጡን።
ጥቂት ከተጓዝን በኋላ ወደ ምናርፍበት ቤት ደረስን። መሬት ውስጥ ተቆፍሮ በተሠራ ምድጃ ውስጥ የበሰሉ ምግቦች ተዘጋጅተዋል። የተጠበሰ የአሳማ ሥጋ፣ የተጠበሰ ዶሮ፣ በዘይት የተጠበሰ አሣ፣ አምስት ጥንድ እግሮች ያሉት አነስተኛ አሣና በዚያ ሥፍራ የሚበቅል ሥሩ የሚበላ ታሮ የተባለ ተክል በፊታችን ተደርድረዋል። እንዴት ያለ ግብዣ ነው! በለጋዎቹ የኮከነት ዛፎች ሥር ተቀምጦ መመገብ እውነትም ገነት መሰል ትርዒት ነው!
በማግሥቱ በሮቱማ ቋንቋ ሁአጋ ተብለው በሚጠሩት መንደሮች ውስጥ የሚኖሩትን ሰዎች እናነጋግራለን። ወደ መጀመሪያው ቤት ስንደርስ ከአንዱ የአሳማ ማርቢያ ጣቢያ ያመለጠች የአሳማ ግልገል እየጮኸች ታልፋለች። የቤቱ ባለቤት ስንመጣ ተመልክቶ በፈገግታ በሩን ይከፍትና በሮቱማ ቋንቋ “ኖያ!” በማለት ሰላምታ ካቀረበልን በኋላ እንድንቀመጥ ይጋብዘናል። የበሰለ ሙዝ በሳህን ይቀርብልናል። የኮከነት ጭማቂ እንድንጠጣም ግብዣ ይቀርብልናል። በሮቱማ እንግዳን ማስተናገድ ከሁሉም ነገር ቅድሚያ የሚሰጠው ነው።
በዚህ ሥፍራ ስለ አምላክ መኖር የሚጠራጠሩም ሆነ የዝግመተ ለውጥ አማኞች የሉም። ሁሉም ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ያምናል። አምላክ ለምድር ያለው አላማ የሚለውን የመሰሉ ርዕሰ ጉዳዮች በቀላሉ ትኩረታቸውን ይማርካሉ። የቤቱ ባለቤት ምድር እንደማትጠፋ ከዚህ ይልቅ በእርሷ ላይ ለዘላለም በሚኖሩ ጻድቅ ሰዎች እንደምትሞላ ሲያውቅ አድናቆት ያድርበታል። (መዝሙር 37:29) ይህን ነጥብ የሚደግፉ ጥቅሶች ሲነበቡ በደንብ ይከታተላል፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ እንዲወስድ ሲቀርብለትም በጉጉት ይቀበላል። ለመሄድ ስንዘጋጅ መጥተን ስላነጋገርነው ያመሰግነንና በመንገድ ስንሄድ ልንበላው እንድንችል በላስቲክ ከረጢት ውስጥ የበሰሉ ሙዞች ሞልቶ ይሰጠናል። በዚህ ቦታ የሚሰብክ ሰው በቀላሉ ሊወፍር ይችላል!
ከህንድ ማኅበረሰብ ጋር ለመግባባት አቀራረብን መለወጥ
ሌሎች በደቡብ ሰላማዊ ውቅያኖስ የሚገኙ ብዙ ደሴቶችም ብዙ ዓይነት ዘሮችና ባሕሎች ያሉባቸው ቢሆንም እንኳን ፊጂን በዚህ ረገድ የሚተካከላት የለም። ከሜላኔዥያዎች፣ ከማይክሮኔዥያዎችና ከፖሊኔዥያዎች ባሕሎች ጎን ለጎን አንድ ከእስያ የፈለሰ ባሕልም አለ። ከ1879 እስከ 1916 ባሉት ዓመታት ውስጥ በሸንኮራ አገዳ ማሳዎች ላይ ለተወሰነ ጊዜ እንዲሠሩ ከህንድ የመጡ የኮንትራት ሠራተኞች ነበሩ። ይህ ጊርሚት (ስምምነት) ተብሎ የሚጠራው ዝግጅት በሺዎች የሚቆጠሩ ሕንዶች ወደ ፊጂ እንዲመጡ ምክንያት ሆነ። የእነዚህ ሠራተኞች ዝርያዎች ብዛት ያላቸው የአገሪቷ ሕዝብ ክፍል ናቸው። ባሕላቸውን፣ ቋንቋቸውንና ሃይማኖታቸውን እንደያዙ ቀሩ።
በፊጂ ዋነኛ ደሴት ንፋስ በሚነፍስበት አቅጣጫ ሎቶካ የተባለችው ከተማ ትገኛለች። ይህች ከተማ የፊጂ የስኳር ኢንዱስትሪ ማዕከልና ህንዶች በብዛት የሚኖሩባት ከተማ ናት። እዚህ የሚገኙት የሦስቱ ጉባኤዎች አባላት የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ‘ዓሣ የማስገሩ’ ሥራ እንዲሳካላቸው አቀራረባቸውን መለወጥ ያስፈልጋቸዋል። አንድ ሰው ከቤት ወደ ቤት እየሄደ ሰዎችን በሚያነጋግርበት ጊዜ ለሰውዬው ዘርና ሃይማኖት የሚስማማ ርዕስ ማዘጋጀት አለበት። በዚያ አካባቢ የሚኖሩ በዛ ያለ ቁጥር ያላቸው ምሥክሮች ከሎቶካ ወጣ ብለው በሚገኙት የሸንኮራ አገዳ ማሳዎች ውስጥ ተሰበጣጥረው ወደሚገኙት ቤቶች እየሄዱ ሰዎችን ሲያነጋገሩ እስቲ አብረናቸው እንሁን።
ወደ መጀመሪያው ቤት ስንደርስ ጫፎቻቸው ላይ ቀይ ጨርቆች ታስሮባቸው በአጥር ግቢው ማዕዘን ላይ የተተከሉ አንዳንድ ረጃጅም ሸምበቆዎችን እንመለከታለን። ቤተሰቡ የሂንዱይዝም እምነት ተከታይ ነው ማለት ነው። አብዛኛዎቹ ሂንዱዎች ቤቶቻቸው በአማልክቶቻቸው ምስሎች ያጌጡ ናቸው። ብዙዎቹ እንደ ክሪሽና አብልጠው የሚወዱት አምላክ አላቸው። ብዙውን ጊዜም አንድ አነስተኛ ቅዱስ የአምልኮ ስፍራ ይኖራል።a
አብዛኛዎቹ ሂንዱዎች ሁሉም ሃይማኖቶች ጥሩ ናቸው፤ እንዲሁ የተለያዩ የአምልኮ መንገዶች ብቻ ናቸው ብለው ያምናሉ። ስለዚህ የቤቱ ባለቤት በትሕትና ሊያዳምጥ፣ አንዳንድ ጽሑፎችን ሊቀበል፣ ምግቦችንና የሚጠጡ ነገሮችን ሊያቀርብና ግዴታውን እንደተወጣ ሆኖ ሊሰማው ይችላል። የቤት ባለቤቶችን ይበልጥ ትርጉም ወዳለው ውይይት ውስጥ ለማስገባት ተገቢ ጥያቄዎችን ለማንሣት ብዙውን ጊዜ የእምነታቸው ክፍል የሆኑ አንዳንድ ታሪኮችን ማወቁ ይጠቅማል። ለምሳሌ ያህል ከታሪኮቻቸው መካከል አንዳንዶቹ አማልክቶቻቸው አጠያያቂ ድርጊቶችን እንደፈጸሙ የሚገልጹ መሆናቸውን በማወቅ “እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት በሚስትህ (በባልሽ) ላይ እንዲፈጸም ትፈቅዳለህን (ትቅጃለሽን)?” የሚል ጥያቄ ልናቀርብ እንችላለን። በጥቅሉ የሚሰጠው መልስ፦ “በፍጹም፣ በምንም ዓይነት አልፈቅድም!” የሚል ነው። ከዚያ በኋላ “እንግዲያው አንድ አምላክ እንዲህ ዓይነት ድርጊት መፈጸም ይገባዋልን?” የሚለውን ጥያቄ ለሰውዬው ልናቀርብለት እንችላለን። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት ውይይቶች የመጽሐፍ ቅዱስን ዋጋማነት ለማሳየት በር ይከፍታሉ።
አንድ ሰው ከሞተ በኋላ እንደገና በሌላ መልክ ሕያው ሆኖ ይመጣል የሚለው ሌላው የሂንዱይዝም እምነት ለውይይት እጅግ ምቹ የሆነ ርዕስ ነው። በቅርቡ አባቷ የሞቱባት አንዲት ምሑር ሂንዲ ሴት እንዲህ የሚል ጥያቄ ቀረበላት፦ “አባትሽን በድሮው መልካቸው ብታያቸው ደስ ይልሽ ነበርን?” “አዎን፣ ይኸማ በጣም ደስ ይል ነበር” ስትል መልሳለች። ከሰጠችው መልስና በኋላም ከተደረገው ውይይት አንጻር ሲታይ አባቷ በአሁኑ ጊዜ ሌላ መልክ ይዘው እንደሚኖሩና ዳግመኛ ልታውቃቸው እንደማትችል በሚገልጸው እምነት እንዳልረካች ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ስለ ትንሣኤ በሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ አስደሳች ትምህርት ልቧ ተነካ።
አንዳንድ ሂንዱዎች ጥያቄዎች አሏቸው፤ ለጥያቄዎቻቸውም አጥጋቢ መልስ ለማግኘት ይዳክራሉ። አንድ ምሥክር ወደ አንድ ሂንዱ ቤት ሄዶ ሲያነጋገረው ሰውዬው “የአምላክህ ስም ማነው?” ሲል ጠየቀው። ምሥክሩ መዝሙር 83:18ን በማንበብ የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነና ሮሜ 10:13 መዳንን ለማግኘት ስሙን መጥራት እንዳለብን እንደሚናገር ገለጸለት። ሰውዬው አድናቆት አደረበት፤ የበለጠ ለማወቅም ፈለገ። እንዲያውም ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት አድሮበት ነበር። ለቤተሰባቸው ጣዖት ሙሉ በሙሉ ያደረው አባቱ በፊቱ ሲሰግድ ቆይቶ ታሞ እንደወደቀና ከዚያ ብዙ ሳይቆይ እንደሞተ ገለጸ። በወንድሙም ላይ ይኸው ሁኔታ ደርሶበታል። ከዚያም በማከል እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “ያ ምስል ሕይወትን ሳይሆን ሞትን አምጥቶብናል። ስለዚህ ከእርሱ አምልኮ ጋር የተያያዘ አንድ ችግር መኖር አለበት። ምናልባት ይህ ይሖዋ የተባለው አምላክ ወደ ሕይወት የሚመራውን መንገድ እንድናገኝ ሊረዳን ይችላል።” ስለዚህ ከእርሱ፣ ከሚስቱና ከሁለቱ ልጆቹ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ። ፈጣን እድገት አድርገው ብዙም ሳይቆይ ተጠመቁ። ከጣዖቶቻቸው ተላቀው በአሁኑ ጊዜ የሕይወት አምላክ በሆነው በይሖዋ መንገድ እየተመላለሱ ነው።
ከዚህ ቀጥሎ ወደ አንድ የእስላም ቤተሰብ ቤት እናመራለን። እዚህም ያው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ይንጸባረቃል። ወዲያውኑ ቀዝቀዝ ያሉ መጠጦችን ይዘን እንቀመጣለን። ከአንድ በአነስተኛ መስታወት ውስጥ ከተቀመጠ በአረብኛ ከተጻፈ ጥቅስ በስተቀር በግድግዳ ላይ የተሰቀለ አንድም ሃይማኖታዊ ሥዕል አናይም። ከዕብራውያን አባቶች አንዱ የሆነውን አብርሃምን በመጥቀስ መጽሐፍ ቅዱስንና ቁራንን የሚያገናኝ ነገር እንዳለ እንጠቅሳለን። አምላክ በዘሩ የምድር አሕዛብ ሁሉ እንደሚባረኩ ቃል እንደገባለት እንጠቅሳለን። ይህ ቃል ኪዳን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚፈጸም ነው። አንዳንድ እስላሞች አምላክ ልጅ አለው የሚለውን ሐሳብ ይቃወማሉ። ስለዚህ የመጀመሪያው ሰው አዳም በአምላክ በመፈጠሩ የአምላክ ልጅ ሊባል እንደቻለ ሁሉ ኢየሱስም በዚሁ መንገድ የአምላክ ልጅ እንደተባለ እንገልጻለን። አምላክ እንዲህ ያሉ ልጆችን ለማፍራት ቃል በቃል ሚስት አታስፈልገውም። እስላሞች በሥላሴ ትምህርት ስለማያምኑ ይሖዋ አምላክ ከሁሉ የላቀ መሆኑን ለማስረዳት በዚህ የጋራ መሠረት እንጠቀማለን።
አሁን የምሳ ሰዓት ደርሷል። የቡድናችን አባላትም ወደ ከተማ የምትወስዳቸውን አውቶብስ ለመጠበቅ ከሸንኮራ አገዳ ማሳዎቹ እየወጡ ወደ መንገዱ በመመለስ ላይ ናቸው። ትንሽ የደከማቸው ቢሆንም ሁሉም ጠዋት ባከናወኑት ‘ዓሣ የማስገር’ ሥራ ደስ ብሏቸዋል። በየቤቱ የሚያጋጥሙትን የተለያዩ ሁኔታዎችና እምነቶች በተሻለ ሁኔታ ለመያዝ ያደረጉት የአቀራረብ ለውጥ ጥሩ ውጤት አስገኝቷል።
የፊጂ ባሕሮችና የዛጎል ክምሮች በብዙ ዓይነት አሦች የተሞሉ ናቸው። ስኬታማ ለመሆን የፊጂው ጎኔንዶ (አሣ አጥማጅ) በሥራው ጥሩ ችሎታ ያዳበረ መሆን ይገባዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲያከናውኑት የሠጣቸው ‘ዓሣ የማስገር’ ሥራም ልክ እንደዚሁ ነው። ክርስቲያን ‘ዓሣ አስጋሪዎች’ ከሕዝቡ የተለያዩ እምነቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ለመቅረብ ለሥራው ጥሩ ችሎታ ያዳበሩ፣ አቀራረባቸውንና በምክንያታዊነት የሚያደርጉትን ውይይት ከሁኔታዎች ጋር የሚያጣጥሙ መሆን አለባቸው። (ማቴዎስ 4:19) ይህ በፊጂ አስፈላጊ መሆኑ ጥርጥር የለውም። ፊጂዎች፣ ህንዶች፣ ሮቱማዎችና ከተለያዩ እምነቶች የመጡ ሌሎች ቅልቅል ሕዝቦች ይሖዋ አምላክን በአንድነት በሚያመልኩባቸው በየዓመቱ በሚካሄዱት የይሖዋ ምሥክሮች ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ውጤቶቹ ይንጸባረቃሉ። አዎን፣ በፊጂ ባሕሮች በሚከናወነው ‘ዓሣ የማስገር’ ሥራ ላይ በረከቱ ወርዷል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ የተባለውን ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ገጽ 115–17 ተመልከት።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ቪቲ ሌቩ
ቫኑአ ሌቩ
ሱቫ
ሎቶካ
ናንዲ
0 100 ኪ.ሜ
0 161 ኪ.ሜ
18°
180°
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቡሬ ወይም ባሕላዊ ቤት
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በፊጂ የሚገኝ የሂንዱ ቤተ መቅደስ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፊጂ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የሚሆን ስኬታማ ‘ ዓሣ የማስገር’ ሥራ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Fiji Visitors Bureau