በኢትዮጵያ የተደረገው “መለኮታዊ ትምህርት” የወረዳ ስብሰባ ልዩ የደስታ ጊዜ ነበር
በኢትዮጵያ ውስጥ ነፃነት ከተገኘ ወዲህ የወረዳ ስብሰባ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው ባይሆንም ያሁኑ በጣም ልዩ ነበር። በዚህች አገር ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ኅዳር 11 ቀን 1991 (እ.ኤ.አ.) ሕጋዊ እውቅና ካገኙ ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ባለው በትልቁ ስታዲየም ማለትም በመሐል አዲስ አበባ በሚገኘው የከተማው ስታዲየም ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ መሰብሰባቸው ነው። እሁድ ዕለት በስታዲየሙ መጠቀም ስላልተቻለና ያን የሚያክል ሕዝብ ለመያዝ የሚችል ሌላ የመሰብሰቢያ ቦታ ስላልነበረ የስብሰባው ፕሮግራም በሦስት ቀን ውስጥ ማለትም ከሐሙስ እስከ ቅዳሜ ይኸውም ከጥር 13 እስከ 15, 1994 ትንሽ አጠር ተደርጎ ቀርቧል።
እነዚያ ሦስት ቀናት ጥርት ባለው ሰማይና ደስ በሚለው ሞቃታማ አየር ብቻ ሳይሆን ቦግ ባለ ‘የመለኮታዊ ትምህርት’ መንፈሳዊ ብርሃን ደምቀው ነበር የሰነበቱት። የመድረኩ ዙሪያ በሚያማምሩ አበቦች ከማጌጡም በላይ የስብሰባው አጠቃላይ መልእክት በትልልቅ የአማርኛ ፊደላት ተጽፎ ጎላ ብሎ ይታይ ነበር።
ይሁን እንጂ ስብሰባውን ልዩ ያደረገው ምን ነበር? ከቀረበው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ፕሮግራም ሌላ ሰዉ ሁሉ ዓለም አቀፋዊ በሆነው ፍቅራዊ ወንድማማችነታችንና የአምላክን በረከት በግልጽ በሚያሳየው በመንግሥቱ አስፋፊዎች እድገት ላይ አተኩሮ ነበር። በስብሰባው ላይ ለመገኘት ከ16 አገሮች የመጡ ወደ 270 የሚጠጉ እንግዶች ነበሩ። ከጅቡቲና ከየመን ሳይቀር እንግዶች መጥተዋል። ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የመጡት ከአውሮፓና ከሰሜን አሜሪካ ሲሆን በነዚያ አገሮች ደግሞ ወቅቱ ክረምት ነበር። ከእንግዶቹ መካከል ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባላት ማለትም ወንድም ሎይድ ባሪና ወንድም ዳንኤል ሲድሊክ ይገኙበት ነበር።
በኢትዮጵያውያን የእንግዳ ተቀባይነት ባሕል ላይ ከውጭ አገር ለመጡት ወንድሞቻቸው ያላቸው ከልብ የመነጨ ፍቅር ታክሎበት የቋንቋ ገደብ ያልገታው ፍልቅልቅ የደስታ ስሜት ይታይ ነበር። ኢትዮጵያውያኑ ሰላምታ የሚለዋወጡት እንዲሁ በመጨባበጥ ብቻ አይደለም፤ እርስ በርስ ይተቃቀፋሉ፤ ይሳሳማሉ፤ አንዳንድ ጊዜም እስከ ስድስት ጊዜ ድረስ! ብዙዎቹ እንግዶች በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የመንግሥቱ ሥራ ከዚህ ቀደም በጽሑፍ የተገለጸውን አንብበው ነበር። ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው በደረሱባቸው የእስራትና ሌሎችም ዓይነት ስደቶች የጸኑ፣ የተፈተኑ ፍጹም አቋም ጠባቂዎች መሆናቸውን ያውቁ ነበር።a ወደ ስብሰባው የመጡትን እንግዶች በተለይ ያስደነቃቸው ነገር ዛሬ በብዙ አገሮች እየጠፋ ያለውን ሰውን አክባሪነት የተላበሱና ፊታቸው በደስታ የሚያበራ በጣም ብዙ ወጣቶችን ማየታቸው ነው። ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን እህቶች የለበሱት የሚያምር ጥለት ያለው የአገር ልብስ ለስብሰባው ድምቀት ጨምሮለት ነበር።
ዓርብ ዕለት የተከናወነው የጥምቀት ፕሮግራም በጣም ደስ ይል ነበር። ዕድሜያቸው ከ10 እስከ 80 ዓመት የሆኑ ራሳቸውን የወሰኑ 530 አዳዲስ ሰዎች በረጅሙ በመሰለፍ የስታዲየሙን ሜዳ እስከ አጋማሹ ድረስ ሞልተውት ነበር። የተጠማቂዎቹ ብዛት ማንም ከጠበቀው በላይ የነበረ ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ምሥክሮች ውስጥ ከሰባቱ አንዱ የተጠመቀው በዚህ ጊዜ ነበር ማለት ነው። ይሖዋ በዚህች አገር የሚገኙ ምሥክሮቹን እየባረከ ለመሆኑ ይህ ራሱ አንድ ትልቅ ማስረጃ ነው። ብዙዎች ይህንን ሲያዩና ከ40 በላይ የሚሆኑት ከጣሊያን የመጡ ወንድሞች የጥምቀት ሥርዓቱ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ የዘመሯቸውን አስደሳች መዝሙሮች ሲሰሙ የደስታ እንባ አፍስሰዋል። ብዙዎች በኢሳይያስ 60:5 ላይ ያለውን “በዚያን ጊዜ የባሕሩ በረከት ወደ አንቺ ስለሚመለስ፣ የአሕዛብም ብልጥግና ወደ አንቺ ስለሚመጣ፣ አይተሽ ደስ ይልሻል፣ ልብሽም ይደነቃል ይሰፋማል” የሚለው ትንቢት ትዝ ብሏቸው ነበር።
ለደስታ ምክንያት የሆኑ ልዩ ነገሮች
ዓርብ ዕለት በተደረጉት ቃለ ምልልሶች ላይ የመንግሥቱ ሥራ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለነበረው አነስተኛ አጀማመር ሲነገር የይሖዋ በረከት ይበልጥ ጎላ ብሎ ታይቷል። ቃለ ምልልሶቹ የተደረጉት በ1950ዎቹና በ1970ዎቹ በኢትዮጵያ ያገለግሉ ከነበሩት ሚስዮናውያን ጋር ነበር። ሬይ ካሰን፣ ጆን ካምፐስ እና ሄይዉድ ዎርድ አዲስ አበባ ከደረሱበት ከመስከረም 14 ቀን 1950 (እ.ኤ.አ.) አንስተው መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ያስተምሩ እንደነበረ ሲተርኩ በስታዲየሙ የተገኘው ከ8,000 በላይ የሚሆን ሕዝብ አዳምጧቸዋል። በዚያን ጊዜ የነበረው ንጉሠ ነገሥታዊ መንግሥት ትምህርት ቤት ከፍታችሁ የቀለም ትምህርት መስጠት አለባችሁ አላቸው። ስለዚህ በከተማው መሐል የጎልማሶች ትምህርት ቤት ከፈቱና ልዩ ልዩ ትምህርቶችን ያስተምሩ ጀመር። እነዚህ ሚስዮናውያን ከትምህርት ሰዓት ውጪ ባለው ጊዜያቸው በመለኮታዊ ትምህርት ላይ ያተኮረ ትምህርት ለመስጠት ጥረት ያደርጉ ነበር። 250 ፊደላት ያሉትን ውስብስቡን የአማርኛ ቋንቋ ለመማር ከፍተኛ ትግል ማድረግ ነበረባቸው። የመጀመሪያውን የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸውን የመሩት ወደዚች አገር ከመጡ ከስድስት ወር በኋላ ነበር። ከ43 ዓመታት በኋላ ተመልሰው ሲመጡ በየመንገዱ ላይ በቀድሞ አስተማሪነታቸው የሚያስታውሷቸውን ሰዎች አግኝተዋል። በስብሰባው ላይ ደግሞ በእምነት ከጠነከሩት ከብዙዎቹ የቀድሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻቸው ጋር እንደገና ለመገናኘት በመብቃታቸውና እነዚህ ጥናቶቻቸው ደግሞ የየራሳቸውን መንፈሳዊ ልጆችና የልጅ ልጆቻቸውን ስላስተዋወቋቸው በጣም ተደስተዋል።—1 ተሰሎንቄ 2:19, 20
በጣም የተደሰቱትና በጥሞና ያዳምጡ የነበሩት ተሰብሳቢዎች ከበፊቶቹ ሚስዮናውያን ጋር ቃለ ምልልስ በሚደረግበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከብሪታንያ፣ ከካናዳ፣ ከጀርመን፣ ከእስራኤል፣ ከጣሊያን፣ ከኬንያ፣ ከኔዘርላንድ እና ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡ ተወካዮች ሪፖርት አቅርበው ይዘው የመጡትን ሰላምታ አስተላልፈው በጨረሱ ጊዜ ሁሉ ለረጅም ጊዜ ያጨበጭቡ ነበር። ይህም የአምላክ ሕዝቦች ያላቸውን ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት ይበልጥ አጉልቶታል። ከአስተዳደር አካል የመጡት ቅቡዓን ወንድሞች የሰጧቸው ዋና ዋና ንግግሮችና ያቀረቧቸው ጸሎቶች የአድማጮችን ልብ በጥልቅ ነክተዋል። የእውነት በሚመስልና ሕያው በሆነ መንገድ የቀረበው በወጣትነታቸው ፈጣሪያቸውን ስላስታወሱ ወጣቶች የሚገልጸው ድራማ፣ በስታዲየሙ የተገኙት ወጣቶች ራሳቸውን በድራማው ውስጥ በነበሩት ገጸ ባሕርያት ቦታ በማስቀመጥ እንዲመለከቱ አስችሏቸዋል። በእንግሊዝኛ ከወጡት አዳዲስ ጽሑፎች በተጨማሪ ሌሎች ሦስት ጽሑፎች በአማርኛ መውጣታቸው ከፍተኛ ደስታ አስገኝቷል።b
በእረፍት ሰዓትና በሌሎችም ጊዜያት ውድ ከሆኑ ብዙ ግለሰቦች ጋር ለመተዋወቅ የሚያስችሉ ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎች ነበሩ። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ካሉት አስፋፊዎች ሁሉ በዕድሜ የሚበልጡት አስፋፊ ወንድም ቱሉ መኩሪያ በመጀመሪያው መደዳ ከፊት በኩል ከዘራ ይዘው ተቀምጠው ነበር። የዕድሜ ባለጸጋው ባለፈው ዓመት በ113 ዓመታቸው ከይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንዱ በመሆን ተጠመቁ። በዚህ ስብሰባ ላይ ደግሞ የ80 ዓመቷ ባለቤታቸው የርሳቸውን ምሳሌ በመከተል ተጠምቀዋል፣ ስለዚህ መንፈሳዊ እህታቸውም ለመሆን በመብቃታቸው በጣም ተደስተዋል። በሁሉም የስብሰባው ፕሮግራሞች ላይ መገኘታቸው ለብዙ ወጣቶች መልካም ማነቃቂያ ሆኗቸዋል። የ16 ዓመቱ ተማሪ ዮሐንስ ጎረምስ ይህ ስሜት ከተሰማቸው አንዱ ነበር። የዘወትር አቅኚ ሆኖ ማገልገል ከጀመረ አራት ዓመቱ ነው። እሱና የዘወትር አቅኚዎች የሆኑ ሌሎች ተማሪዎች (በዕድሜ ከእርሱ ያነሱትም ጭምር) ጠዋት ጠዋት ወደ ትምህርት ቤታቸው ሲሄዱ ወይም በዕረፍት ሰዓታቸው እንዲሁም ከትምህርት ቤት መልስ ለማገልገል ጊዜያቸውን እንዴት ማብቃቃት እንደሚችሉ ተምረዋል።
እንዴት ያሉ የፍጹም አቋም ጠባቂነት ምሳሌዎች ናቸው!
በስብሰባው ላይ ከተገኙት ውስጥ በመቶ የሚቆጠሩት በፊተኞቹ መንግሥታት ሥቃይ ያዩ ናቸው። ማንደፍሮ ይፍሩ በዚህ ዓይነት ሁኔታ በእስር ቤት ያሳለፋቸውን አምስት ዓመታት ያስታውሳቸዋል። አሁን ግን የትርጉምና የኅትመት ሥራ በሚካሄድበትና የሥነ ጽሑፍ ማከፋፈያ በሆነው በአዲስ አባባ በተከፈተው አዲስ ቢሮ ውስጥ በማገልገሉ እየተደሰተ ነው። ከሱ ጋር አብሮ የሚያገለግለው ዘካርያስ እሸቱ የሚባል ሌላ ወጣት ደግሞ ከስምንት ዓመታት በፊት አባቱ በክርስቲያናዊ ገለልተኝነቱ ምክንያት ለሦስት ዓመታት ታስሮ ከቆየ በኋላ ቢገደልም ከዓላማው ዝንፍ ሳይል ቆሟል። ከአምስቱ ልጆች አንዱ የሆነው ዘካርያስ አባቱ ወደ ወኅኒ ሲወርድ ገና የአሥር ዓመት ልጅ ነበር። የአሥራዎቹን ዕድሜያቸውን እያገባደዱ ያሉት ተማሪ መሥዋዕት ግርማና እህቱ ዮአዳንም አባታቸው በፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ በመሆኑ ምክንያት በድንገት በተረሸነበት ጊዜ በጣም ትንንሽ ልጆች ስለነበሩ አባታቸውን የሚያውቁት በፎቶግራፍ ብቻ ነው። በአባታቸው የታማኝነት አቋም በመነሳሳት እሱ በሞተበት ጊዜ ተሰልፎበት የነበረውን የዘወትር አቅኚነት ሥራ እነሱም ገብተውበታል።
ሌላው የፍጹም አቋም ጠባቂ ታምራት ያደቴ ሲሆን ባሁኑ ጊዜ በስምጥ ሸለቆው ውስጥ ውብ በሆነ አካባቢ ልዩ አቅኚ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው። በክርስቲያናዊ ገለልተኝነቱ የተነሣ በሰባት የተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ ሦስት ዓመት አሳልፏል። አንዳንድ ጊዜ በእግር ብረት ታስሮ ከፍተኛ ድብደባ ይደርስበት ነበር። ይሁን እንጂ በእስር በቆየባቸው ጊዜያት ከአሥራ ሁለት የሚበልጡ ሰዎች ከአምላክ መንግሥት ጎን እንዲቆሙ ረድቷል።
አሁን በክልል የበላይ ተመልካችነት እያገለገለ ያለው ተስፉ ተመልሶ ደግሞ ልዩ አቅኚ ሆኖ ሲያገለግል በነበረባቸው ዓመታት 17 ጊዜ ተይዞ ታስሯል። በእስር ቤት እያለ በደረሰበት ድብደባ ብዙ ጠባሳዎች ያሉት ቢሆንም በፊት ተመድቦ ያገለግል በነበረባቸው አካባቢዎች በአሁኑ ጊዜ ጉባኤዎች ተቋቁመው በማየቱ ደስተኛ ነው። በአቃቂ ጉባኤ የሚገኙ ብዙ ወንድሞችና እህቶች እስራትና ኢ–ሰብዓዊ የሆኑ የጭካኔ ድርጊቶች የተፈጸመባቸው ቢሆንም ጉባኤው አሁን ከመቶ በላይ አስፋፊዎች በማፍራት በቁጥር አድጓል። እነዚህ ወንድሞች በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያውን የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ለመሥራት በቅተዋል። ከአገሪቱ ዋና ከተማ በስተሰሜን 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ደስ በሚል አካባቢ ላይ በምትገኘው በደሴ ከተማ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ከሞት አፋፍ ያመለጡ አምስት ሰዎች በስብሰባው ላይ ተገኝተው ነበር። አብሯቸው ታስሮ የነበረው አንድ ወንድም ግን ታስሮ በሚማቅቅበት ጊዜ በደረሰበት ድብደባ ሳቢያ ከጊዜ በኋላ ሞቷል። ከመካከላቸው አንዱ የነበረው ማስረሻ ካሳ የተባለ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግል ወንድም ለስድስት ዓመታት ታስሮ የነበረ ቢሆንም ጸንቶ ሊወጣ የቻለው ልዩ ሰው ስለነበረ ሳይሆን በይሖዋ ላይ ይደገፍ ስለነበረ ብቻ መሆኑን ገልጿል።—ሮሜ 8:35–39፤ ከሥራ 8:1 ጋር አወዳድር።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ቢሆን ሌሎች ወንድሞች ፈተና ደርሶባቸው ታማኝነታቸውን ጠብቀዋል። ገለልተኞች በመሆናቸው የተነሣ ፖሊሶች የሚደርስባቸውን ጥቃት እንዳይከላከሉላቸው፣ የይለፍ ወረቀትና የጋብቻ ማረጋገጫ ሰነድ እንዳይሰጣቸው፣ የሕክምና እርዳታ እንዳያገኙ፣ ከሥራም እንዲባረሩ ከተደረገበት አጎራባች አገር ብዙ ምሥክሮች በስብሰባው ላይ ለመገኘት መጥተው ነበር። ምፅዋ በምትባል በቀይ ባሕር በኩል ያለች አንዲት የኤርትራ ወደብ ላይ ጦርነቱ ተፋፍሞ በነበረበት ጊዜ የቀድሞው መንግሥት አካባቢውን በቦምብ ሲደበድብ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ የአንድ ጉባኤ አስፋፊዎችና ልጆቻቸው በድምሩ 39 የሚሆኑ ሰዎች ለአራት ወራት ያህል በበረሃ ውስጥ በሚገኝ አንድ ድልድይ ሥር ተጠልለው አብረው ኖረዋል። በዚያ ሐሩር ብቻቸውን በነበሩበት ጊዜ የዕለት ጥቅስ ውይይት ማድረጋቸውና ሌሎች ስብሰባዎችንም ማድረጋቸው ከፍተኛ ጥንካሬ የሰጣቸው ከመሆኑም በላይ ከይሖዋ ጋር እንዲሁም እርስ በርሳቸው በጣም እንዲቀራረቡ ረድቷቸዋል። ጥቁር አባይ በሚነሣበት አካባቢ የሚያገለግሉት ልዩ አቅኚ የሆኑ ሁለት እህቶች በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅስቀሳ ሳቢያ ረብሻና ዛቻ ቢያደርሱባቸውም በዚህ ሁሉ ባለመበገራቸው ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻቸው በዚህ ስብሰባ ላይ በመገኘት ራሳቸውን መወሰናቸውን በጥምቀት ሲያሳዩ ሊመለከቱ ችለዋል።
በሥራ ቅያሪ ምክንያት ከሶማሊያ ብዙም በማይርቀው ገለልተኛና በረሃማ በሆነው የኡጋዴን አካባቢ የሚኖር አንድ ወንድም ያጋጠመውን ተሞክሮ ተናግሮ ነበር። ይህ ወንድም ፍላጎት ላሳዩ አዲሶች በመመሥከርና ከነዚህ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ጋር ስብሰባ በማድረግ በመንፈሳዊ ሕያው ሆኖ ሊቆይ ችሏል። ፍላጎት ካሳዩት መካከል ዶክተሮች የሚገኙበት ሲሆን እነሱም የመለኮታዊ ትምህርት ተጠቃሚዎች በመሆን በአሁኑ ጊዜ ሌሎችን በማስተማር ላይ ይገኛሉ። ሌላው ጥሩ ምሳሌ የሚሆን የፍጹም አቋም ጠባቂ ደግሞ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚያገለግል አንድ ልዩ አቅኚ ሲሆን በ1992 የኦርቶዶክስ ቄሶች የቀሰቀሷቸው ሰዎች ረብሻ በማስነሣት በጭካኔ ደብድበው በሞትና በሕይወት መካከል ትተውት ነበር። አሁን ግን ተሽሎት በዚያው አካባቢ ማገልገሉን መቀጠሉ የሚያስደስት ነው። በፊቱ ላይ የሚነበበው ብሩህ ፈገግታ ምንም እንዳልተማረረ ያሳያል። ለሱና ፈተና ለደረሰባቸው ለሌሎች ወንድሞችና ለአዳዲሶች ይህ “መለኮታዊ ትምህርት” የተባለው የወረዳ ስብሰባ ልዩና አስደሳች የሆነ መንፈሳዊ ድግስ ነበር።
ስብሰባው በጥሩ ቅንብር ይካሄድ ስለነበረ ከውጭ አገር የመጡት እንግዶች በዝግጅቱ ላይ የተካፈሉት ፈቃደኛ ሠራተኞች የብዙ ዓመት ልምድ ያላቸው መስሏቸው ነበር። ባለፉት ሁለት ዓመታት ፈጣን እድገት አሳይተዋል። የሦስት ቀኑ ስብሰባ አጭር መስሎ ነበር የታየው። ቅዳሜ ዕለት የነበረው ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር 9,556 ነበር። የአገሪቱ ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮና ጋዜጣ ስብሰባውን በሚመለከት ጥሩ ዜና አቅርበው ነበር። ይሖዋ ሕዝቡን በመንፈሳዊ እያበለጸጋቸው እንዳለ ሁሉም ለመመልከት ችለዋል። በስብሰባው ላይ ከተገኙት አድማጮች መካከል ‘ከመለኮታዊው ትምህርት’ ጥቅም እያገኙ ያሉ በሺህ የሚቆጠሩ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ነበሩ። ወደ 50 ሚልዮን የሚጠጋ ሕዝብ ባለባት በዚህች አገር ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሰፊ የሥራ መስክ ተከፍቶላቸዋል። የወረዳ ስብሰባውም ይህ የነገሮች ሥርዓት በቀረው ጊዜ ውስጥ ቅን የሆኑ ሰዎች ከመለኮታዊው ትምህርት ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ለመርዳት ሁሉም ያላቸውን ቁርጥ ውሳኔ አጠንክሮላቸዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን የ1992 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ተመልከት።
b ወጣትነትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት፣ የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው እንዲሁም እንደ አንድ አካል ሆነው በዓለም ዙሪያ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉት የይሖዋ ምሥክሮች።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አዲስ አበባ፣ ጥር 13–15, 1994
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአዲስ አበባ የሚገኝ አንድ የአቅኚዎች ቡድን (በስተቀኝ)፤ ታስረው የነበሩ ፍጹም አቋም ጠባቂዎች (ከታች)፤ የ113 ዓመቱ ምሥክርና ባለቤቱ