“ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁ”
“ከየት መጣሁ?” ይህ አብዛኞቹ ሕፃናት አንድ ወቅት ላይ ሲደርሱ የሚጠይቁት ጥያቄ ነው። ሕፃናቱ እያደጉ ሲሄዱ ግን ብዙውን ጊዜ “ሕይወት ከየት መጣ?” የሚል ከበድ ያለ ጥያቄ ያቀርባሉ። ይህ ጥያቄ ለብዙ ሺህ ዓመታት ሰዎችን ሲያወያይ ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜ ግን ብዙ ሳይንቲስቶች የሕይወትን አመጣጥ በተመለከተ ግራ ሲያጋባ ለቆየው ጥያቄ ከሁሉ የተሻለ አጥጋቢ መልስ ዝግመተ ለውጥ ነው የሚል አመለካከት አላቸው። የዝግመተ ለውጥ አማኞች የሚሰጡት ማብራሪያ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ ሕይወት በአጋጣሚ ጀምሯል ማለት ነው።
የዛሬ 3,000 ዓመት ገደማ ንጉሥ ዳዊት “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁ” ሲል ጽፎ ነበር። (መዝሙር 139:14) ስለ ሕይወት ብዙ ባወቅን መጠን እነዚህ ቃላት እውነት መሆናቸውን ይበልጥ እየተገነዘብን እንሄዳለን። የፊዚክስ ሊቅ የሆኑት ፍሬድ ሆይል “ባዮኬሚስቶች ስለ ሕይወት እጹብ ድንቅ ውስብስብነት አዳዲስ ነገር ባገኙ ቁጥር ሕይወት በአጋጣሚ የመጀመሩ ዕድል እጅግ አነስተኛ ከመሆኑ የተነሣ ግምት ውስጥ ሊገባ የማይችል መሆኑ ግልጽ ነው። ሕይወት በአጋጣሚ ሊመጣ አይችልም” በማለት ጽፈዋል።
ታዲያ የሕይወት ምንጭ ምን ይሆን? የዚህ መጽሔት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ርዕሶች ለዚህ ጥያቄ ማብራሪያ ይሰጣሉ። ተጨማሪ ማብራሪያ ብንሰጥዎ ደስ የሚልዎት ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች፣ የፖ. ሣ. ቁ. 5522፣ አዲስ አበባ ብለው ወይም በገጽ 2 ላይ ካሉት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው ይጻፉ።