ቅዱስ አገልግሎትህን በአድናቆት ተመልከተው
አንድ ጠቃሚ ግብ ላይ ለመድረስ ከፈለግን አንዳንድ መሥዋዕቶችን ለመክፈል ዝግጁ መሆን አለብን። ዶክተር ለመሆን ለብዙ ዓመታት መማርና ቆራጥነት እንዲሁም ገንዘብ ያስፈልጋል። የተዋጣለት የጅምናስቲክ ትርዒት ማሳየት የሚችል ሰው እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የቻለው ሞያውን ጠንቅቆ ለማወቅ ባለው ፍላጎት በመነሳሳት አብዛኛውን የወጣትነት ዘመኑን እያደር እየጠጠረ የሚሄድ እልህ አስጨራሽ የዕለት ተዕለት ልምምድ በማድረግ ስላሳለፈው ነው። አንድ የተዋጣለት ስፖርተኛ የወጣትነት ዕድሜውን ያሳለፈው ያን ስፖርት በደንብ እስኪችለው ድረስ በየጊዜው ከባባድና ተደጋጋሚ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን ያለማቋረጥ በመሥራት ነው። አንድ ጎበዝ የፒያኖ ተጫዋችም እንዲሁ ልምምዱን ሥራዬ ብሎ በመያዝ ያሳለፋቸውን ዓመታት መለስ ብሎ ማስታወስ ይችላል።
ይሁን እንጂ ከተከፈለለት ከምንም ዓይነት መሥዋዕትነት እጅግ በጣም የሚበልጥ ዋጋ የሚያስገኝ አንድ ግብ አለ። ያ ግብ ምንድን ነው? ከሁሉ በላይ የሆነው የይሖዋ አምላክ አገልጋይ የመሆን መብት ነው። በጊዜያችን፣ በገንዘባችን፣ ወይም በጉልበታችን ምንም ዓይነት መሥዋዕትነት ብንከፍል ለፈጣሪያችን ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ ያለን መብት የሚያስገኝልን ሽልማት ከምንም ነገር ጋር አይወዳደርም። “እግዚአብሔርን መምሰል [ለአምላክ ያደሩ መሆን አዓት] . . . የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፣ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረው ቃል እውነት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) ይህ እንዴት እውነት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ አምላክ ስንማር
ምሥራቹን ተቀብለው ማጥናት የጀመሩ አብዛኞቹ ሰዎች ይህ እርምጃቸው ወደፊት በሕይወታቸው ውስጥ ምን ያህል ትልልቅ ለውጦች ማድረግን እንደሚጠይቅባቸው በደንብ አይገነዘቡትም። በመጀመሪያ አዲሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ አንዳንድ ድርጊቶች አምላክን የማያስከብሩ መሆናቸውን በመረዳቱ እንደ በፊቱ ከጓደኞቹ ጋር ስለማይተባበር ይህን የሚያደርግበትን ምክንያት ያልተረዱ ሰዎችን ጓደኝነት ያጣል። (1 ጴጥሮስ 4:4) አንዳንዶች ከቤተሰባቸው ተቃውሞ ሊደርስባቸው እንዲሁም እነሱ የሚወዷቸው ሰዎች ይሖዋን እንደማይወዱት እንዲያውም እንደሚጠሉት ሲያሳዩ ሊያዝኑ ይችላሉ። (ማቴዎስ 10:36) ይህ በጣም ከባድ መሥዋዕትነት መክፈል ማለት ሊሆንባቸው ይችላል።
ከዚህም ሌላ በመሥሪያ ቤትም ሆነ በትምህርት ቤት የሚከፍሉት መሥዋዕትነት ይኖራል። አዲሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ከጊዜ በኋላ በዓለማዊ ድግሶች (ፓርቲዎች) ላይ መገኘቱንና በሌሎች በዓላት ላይ መካፈሉን ያቆማል። የሥራ ባልደረቦቹ ወይም የትምህርት ቤት ጓደኞቹ የሚናገሯቸውን አጸያፊ ንግግሮች አያዳምጥም። ከነሱም ጋር ጸያፍ ቀልድ አይቀልድም። በዚህ ፈንታ በኤፌሶን 5:3, 4 ላይ የሚገኘውን ቀጥሎ ያለውን ጥብቅ ምክር በተግባር ለማዋል ጥረት ያደርጋል:– “ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኩሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፤ የሚያሳፍር ነገርም የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ የማይገቡ ናቸውና አይሁኑ፣ ይልቁን ምስጋና እንጂ።”
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው ይህን የመሰሉ ለውጦች ማድረጉ ባይተዋር መስሎ እንዲታይ ሊያደርገው ይችላል። ይህ በተለይ ለወጣት ተማሪዎች በጣም ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። ወጣት ክርስቲያኖች ተደጋጋሚ በዓላት እንዲሁም እንደ ዝግመተ ለውጥ ያሉ አምላክን የሚፃረሩ ትምህርቶች ስለሚያጋጥሟቸው በተጨማሪም ሰው እንደሆነው እንዲሆኑ ከፍተኛ ግፊት ስለሚመጣባቸው ለእምነታቸው ከፍተኛ ተጋድሎ ለማድረግ ይገደዳሉ። የአምላክን መንገድ መከተላቸው ከሌሎች የተለዩ ስለሚያደርጋቸው የክፍል ጓደኞቻቸውና አስተማሪዎች ሊያሾፉባቸው ይችላሉ። ይህ ሁኔታ በተለይ ስሜታቸው ቶሎ በሚነካባቸው የአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ላሉ ወጣቶች ከበድ ይልባቸዋል። ሆኖም የአምላክን ሞገስ ማግኘቱ ይህ መሥዋዕት ሊከፈልለት የሚገባው ነው።
በእርግጥ መሥዋዕትነት ነውን?
በመጀመሪያ ላይ መሥዋዕቶች መስለው የታዩ አንዳንድ ነገሮች ደግሞ በኋላ በረከት ይሆናሉ። አንዳንዶች የሲጋራ ሱሳቸውን መተው ይኖርባቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ይህ ትግል የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል፤ በመጨረሻ ግን ከዚህ መጥፎ ልማድ ሲላቀቁ እንዴት ያለ በረከት ይሆንላቸዋል! የሌሎች ዕፆችን ወይም የአልኮል ሱስን ማሸነፍም እንዲሁ ነው። ከእንዲህ ዓይነቶቹ ጎጂ ልማዶች ነፃ የሆነ ሕይወት ምን ያህል የተሻለ ነው! ሌሎች ደግሞ ጋብቻቸውን ማስተካከል ይኖርባቸው ይሆናል። ሳይጋቡ እንዲሁ አብረው የሚኖሩ ሰዎች ወይ መጋባት አለዚያም አብረው መኖራቸውን ማቆም አለባቸው። (ዕብራውያን 13:4) ብዙ ሚስቶች ያሏቸው ደግሞ ከልጅነት ሚስታቸው ጋር ብቻ ተወስነው መኖር ይገባቸዋል። (ምሳሌ 5:18) እነዚህን የመሳሰሉ ማስተካከያዎች ማድረጉ መሥዋዕትነት መክፈልን ይጠይቃል፤ ሆኖም ማስተካከያዎቹ በቤት ውስጥ ሰላም ያመጣሉ።
በአጸፋው የሚገኙትን ጥቅሞች አስብ
የአምላክን ሕግጋት የሚታዘዝ ማንኛውም ሰው እውነተኛ ጥቅም እንደሚያገኝ የተረጋገጠ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው በሕይወቱ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈጣሪውን በስሙ እየጠራ ማለትም ይሖዋ እያለ ማነጋገር ይጀምራል። (መዝሙር 83:18 አዓት) ተማሪው ይሖዋ ለሰው ልጆች ስላደረጋቸውና ወደፊት ስለሚያደርጋቸው አስደናቂ ነገሮች እየተማረ ሲሄድ እርሱን መውደድ ይጀምራል። ሙታን በሚፈሩበት አገር የሚኖር ሰው ሙታን እንዳንቀላፉና ትንሣኤን እንደሚጠብቁ ስለሚያውቅ ከዚህ በአጉል እምነት ላይ ከተመሠረተ ፍራቻ ይላቀቃል። (መክብብ 9:5, 10) ደግሞስ ይሖዋ ሰዎችን ለዘላለም በሲኦል ውስጥ እንደማያሰቃይ ማወቅ እንዴት ያለ እፎይታ ነው! አዎን፣ በእርግጥም እውነት ነፃ ያወጣዋል።—ዮሐንስ 8:32
ተማሪው አኗኗሩን ከይሖዋ የአቋም ደረጃዎች ጋር ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እያስማማ ሲሄድ ንጹሕ ኅሊና ያገኛል፤ እንዲሁም ለራሱ አክብሮት ይኖረዋል። እንደ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ሆኖ መኖርን መማሩ ቤተሰቡን ይበልጥ በተሻለ ሁኔታ እንዲይዝ ይረዳዋል፤ ይህም እርካታና ደስታ ያመጣለታል። በመንግሥት አዳራሹ በሚገኙ ስብሰባዎች ላይ መገኘትም አለ። ይህ እንዴት የሚያስደስት ነው! መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ሕዝቦች ለይቶ ሊያሳውቃቸው እንደሚገባ የሚናገርለትን ሞቅ ያለ ፍቅር በማያጠያይቅ ሁኔታ የሚያሳዩ ሰዎችን እዚህ ማግኘት ይቻላል። (መዝሙር 133:1፤ ዮሐንስ 13:35) “የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ” በሚያወሩበት ጊዜ አነጋገራቸው የታረመና የሚያንጽ ነው። (ሥራ 2:11) አዎን፣ “ከመላው የወንድማማች ማኅበር” ጋር መገናኘት ደስ ያሰኛል። (1 ጴጥሮስ 2:17 አዓት) ይህ ዓይነቱ መልካም ቅርርብ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው” እንዲለብስ ይረዳዋል።—ኤፌሶን 4:24
ራስን የመወሰን እርምጃ
አንድ ሰው በመንፈሳዊ እያደገ ሲሄድ ውሎ አድሮ ለአምላክ ያለው ፍቅር ሕይወቱን ለርሱ እንዲወስንና ራሱን መወሰኑንም በውኃ ጥምቀት እንዲያሳይ ይገፋፋዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ይህን እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ወጪውን እንዲያሰሉት መክሯል። (ሉቃስ 14:28) አንድ ራሱን የወሰነ ክርስቲያን የይሖዋን ፈቃድ እንደሚያስቀድምና በሥጋዊ ነገሮች ላይ ጀርባውን እንደሚያዞር አስታውስ። ‘የሥጋን ሥራዎች’ ለማቆምና ‘የመንፈስን ፍሬ’ ለመኮትኮት ጠንክሮ ይጥራል። (ገላትያ 5:19–24) በሮሜ 12:2 ላይ የሚገኘው ምክር በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ያመጣል:– “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።” ስለዚህ አንድ ራሱን ለአምላክ የወሰነ ክርስቲያን አዲስ ዓይነት ዓላማ ያለው ሕይወት መኖር ይጀምራል።
ይሁን እንጂ በአጸፋው የሚያገኘውን ጥቅም እስቲ አስበው። በመጀመሪያ ደረጃ አሁን ከጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ጋር የግል ዝምድና አለው። የአምላክ ወዳጅ ይሆን ዘንድ እንደ ጻድቅ ተቆጥሯል። (ያዕቆብ 2:23) አምላክን “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ” በማለት ጥልቅ ትርጉም ባለው መንገድ ሊጠራው ይችላል። (ማቴዎስ 6:9) ራሱን የወሰነው አዲሱ ግለሰብ የሚያገኘው ሌላው በረከት ደግሞ ሕይወት በእርግጥ ዓላማ እንዳለው ማወቁ፣ እንዲሁም ከዚያ ዓላማ ጋር ተስማምቶ መኖሩ ነው። (መክብብ 12:13) የኢየሱስን አርዓያ በመከተል የታመነ ሆኖ በመኖር ዲያብሎስ ሐሰተኛ መሆኑን ሊያረጋግጥ ይችላል። ይህ ለይሖዋ ልብ እንዴት ያለ ደስታ ያመጣለታል!—ምሳሌ 27:11
እርግጥ አንድ ክርስቲያን ከታማኝነት መንገድ ዝንፍ ሳይል ለመጓዝ ተጨማሪ መሥዋዕትነት መክፈል ይኖርበታል። በግሉና በጉባኤ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን ትርጉም ባለው መንገድ ማጥናት ጊዜ ይጠይቃል። (መዝሙር 1:1–3፤ ዕብራውያን 10:25) በመስክ አገልግሎት የሚያሳልፈው ሰዓት እንዲኖረው ከሌሎች ሥራዎቹ ላይ ጊዜ መዋጀት አለበት። (ኤፌሶን 5:16) በይሖዋ ምሥክሮች የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት እንዲሁም ወደ ክልልና ወረዳ ስብሰባዎቻቸው ለመሄድ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ለመንግሥት አዳራሹና ለዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ የገንዘብ አስተዋፅኦ ለማድረግ መስዋዕትነትን ሊጠይቅ ይችላል። ይሁን እንጂ በነዚህ ነገሮች ከልብ ተሳትፎ ማድረጉ ደስታ እንደሚያስገኝ በሚልዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ሊመሠክሩ ይችላሉ። ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [ደስተኛ አዓት] ነው” ብሏል።—ሥራ 20:35
ለይሖዋ ሥራ ድጋፍ በመስጠት የምናገኘው ጥቅም ካወጣነው ወጪ እጅግ የሚበልጥ ነው። ይበልጥ እየጎለመስን ስንሄድ አገልግሎታችንም የበለጠ ፍሬያማና አስደሳች እየሆነልን ይሄዳል። በእውነቱ አንድን ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አስተምረን ሰውዬው የይሖዋን አምልኮ ይዞ ከማየት የበለጠ እርካታ የሚያስገኝ ምንም ሥራ የለም። አዲሱ አምላኪ የቤተሰባችን አባል ምናልባትም “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” አሠልጥነን ያሳደግነው ልጃችን ከሆነ ደግሞ ልዩ ደስታ ያመጣልናል። (ኤፌሶን 6:4) “ከእርሱ [ከአምላክ] ጋር አብረን የምንሠራ” ለመሆን ጥረት ስናደርግ የተትረፈረፈውን የአምላክን በረከት እናገኛለን።—1 ቆሮንቶስ 3:9
በታማኝነት ከማገልገል የሚገኙ ሌሎች ጥቅሞች
እውነት ነው፤ ይህ የነገሮች ሥርዓት እስካለ ድረስ ችግሮች ይመጣሉ። ዲያብሎስ ጊዜው እያለቀበት ሲሄድ ደግሞ ችግሮቹ እየበረቱ መሄዳቸው የማይቀር ነው። ስደት ወይም የሚያሳስት ፈተና ሊያጋጥመን ይችላል። ይሁን እንጂ አምላክ ከኛ ጋር እንደሆነ ማወቃችን ለመጽናት የሚያስችለንን ኃይል ይሰጠናል። (1 ቆሮንቶስ 10:13፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:12) አንዳንድ ክርስቲያኖች ለብዙ ዓመታት ከባድ ሥቃይ ደርሶባቸዋል። ይሁን እንጂ ለአምላክ ፍቅር ስላላቸው ሊጸኑ ችለዋል። የተለያዩ መከራዎች ደርሰውባቸው ከአቋማቸው ሳይነቃነቁ የተቋቋሟቸው ሰዎች ሐዋርያት ተገርፈው በተፈቱ ጊዜ የተሰማቸውን ዓይነት ስሜት ይሰማቸዋል። ሥራ 5:41 እንዲህ በማለት ይናገራል:– “እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቆጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ።”
በአሁኑም ጊዜ ቢሆን እንኳን ጽናት የሚያስገኘው ዋጋ ከከፈልነው መሥዋዕትነት በእጅጉ ይበልጣል። ሆኖም ለአምላክ ያደሩ መሆን ‘ለአሁንና ለሚመጣው ሕይወት ተስፋ’ እንዳለው አስታውስ። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) የሚጸና ሰው የሚያገኘው ሽልማት እንዴት ታላቅ ነው! አንተም ታማኝ ከሆንክ የዚህ የነገሮች ሥርዓት ማክተሚያ ከሆነው ከታላቁ መከራ በሕይወት ትተርፋለህ። ወይም ይህ የአዲስ ምዕራፍ መክፈቻ ወቅት ከመምጣቱ በፊት ከሞትክ ከዚያ በኋላ በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ትንሣኤ ታገኛለህ። (ዳንኤል 12:1፤ ዮሐንስ 11:23–25) “በይሖዋ እርዳታ ለዚህ በቃሁ!” ማለት በምትችልበት በዚያ ጊዜ የሚኖርህን ደስታ እስቲ አስበው! በዚያን ጊዜ “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን . . . እግዚአብሔርን በማወቅ” በተሞላች ምድር ላይ መኖር እንዴት የሚያስደስት ይሆናል!—ኢሳይያስ 11:9
አዎን፣ አምላክን ማገልገል የተወሰነ መሥዋዕትነት መክፈልን ይጠይቃል። ሆኖም በአጸፋው ከሚገኘው ሽልማት ጋር ሲወዳደር ከምንም አይቆጠርም። (ፊልጵስዩስ 3:7, 8) ነገሩን አምላክ ለአገልጋዮቹ ካደረገላቸውና ወደፊት ከሚያደርግላቸው ነገሮች አንጻር ስናየው “ስላደረገልኝ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምንን እመልሳለሁ?” የሚሉትን የመዝሙራዊውን ቃላት እናስተጋባለን።—መዝሙር 116:12