የተደራጁና ደስተኛ ሕዝብ የሆኑት የአምላክ አገልጋዮች
“ይሖዋ አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው!”—መዝሙር 144:15 አዓት
1, 2. (ሀ) ይሖዋ ለአገልጋዮቹ የጠባይ ደረጃዎችን ለማውጣት መብት ያለው ለምንድን ነው? (ለ) ልንኮርጃቸው የሚገባን ሁለት የይሖዋ ጠባዮች በተለይ የትኞቹ ናቸው?
ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ፣ ሁሉን ቻይ አምላክና ፈጣሪ ነው። (ዘፍጥረት 1:1፤ መዝሙር 100:3) ስለዚህ አገልጋዮቹ የሚበጃቸውን ነገር ስለሚያውቅ ሊደርሱበት የሚገባቸውን የጠባይ ደረጃ የማውጣት መብት አለው። (መዝሙር 143:8) ለአገልጋዮቹ ዋነኛ ምሳሌያቸው ነው፤ ባሕሪዎቹንም ሊኮርጁአቸው ይገባል። አንድ ሐዋርያ “እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ [የምትመስሉ አዓት] ሁኑ” ሲል ጽፏል።—ኤፌሶን 5:1
2 ልንኮርጀው የሚገባን አንዱ የአምላክ ጠባይ አደራጅነቱ ነው። እርሱ “የሁከት አምላክ አይደለም።” (1 ቆሮንቶስ 14:33) አምላክ የፈጠራቸውን ነገሮችን በጥሞና ስናስብ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከማንም በላይ የተደራጀ አካል እርሱ ነው ብለን ለመደምደም እንገደዳለን። ይሁን እንጂ አምላክ “ደስተኛ አምላክ” ስለሆነ አገልጋዮቹ ይህንንም ጠባይ እንዲኮርጁት ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 አዓት) ይህም በመሆኑ የማደራጀት ችሎታው ከደስታ ጋር እኩል የሚራመድ ነው። አንዱ ጠባይ ሌላውን ጠባይ በመጫን ልቆ አይታይም።
3. በከዋክብት የተሞሉት ሰማያት የይሖዋን የማደራጀት ችሎታ የሚያሳዩት እንዴት ነው?
3 ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ያሉት ይሖዋ የሠራቸው ነገሮች በሙሉ በተደራጀ ሁኔታ የሚሠራ አምላክ መሆኑን ይመሠክራሉ። ለምሳሌ ግዑዙን ጽንፈ ዓለም ተመልከት። በብዙ ቢልዮን የሚቆጠሩ ከዋክብትን ያቀፈ ነው። ሆኖም እነዚህ ከዋክብት በዘፈቀደ የተቀመጡ አይደሉም። በከዋክብት ጥናት ምሁር የሆኑት ጆርጅ ግሪንስቲን “የከዋክብት አደረጃጀት የተወሰነ መልክ” አለው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። ከዋክብት በቡድን በቡድን የተደራጁ ናቸው። ይህም የከዋክብት ረጨቶች ተብሎ ይጠራል። ከእነዚህ የከዋክብት ረጨቶች መካከል አንዳንዶቹ በብዙ ቢልዮን የሚቆጠሩ ከዋክብትን የያዙ ናቸው። በዚህ ላይ ደግሞ በቢልዮን የሚቆጠሩ የከዋክብት ረጨቶች እንዳሉ ይገመታል! የከዋክብት ረጨቶቹም የተደራጁ ናቸው። በርካታዎቹ (አነስተኛ ከዋክብትን ካቀፉት አንሥቶ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ከዋክብትን ያቀፉትን ጨምሮ) በአንድነት በመከማቸት ክላስተር የተባለ የከዋክብት ረጨቶችን ስብስብ ፈጥረዋል። እነዚህ ክላስተሮች ደግሞ በመደራጀት ሱፐርክላስተር የሚባሉ ይበልጥ ግዙፍ የሆኑ የከዋክብት ክምችቶችን እንደፈጠሩ ታውቋል።—መዝሙር 19:1፤ ኢሳይያስ 40: 25, 26
4, 5. በምድር ባሉት ሕያዋን ነገሮች ላይ የተደራጀ አሠራር መኖሩን የሚያሳዩ ምሳሌዎች ጥቀስ።
4 እንከን የማይወጣለት የአምላክ ፍጥረታት አደረጃጀት በየትም ሥፍራ ከእይታ የተሰወረ አይደለም። በግዑዛን ሰማያት ላይ ብቻ ሳይሆን ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን ሕያዋን ነገሮች በሚርመሰመሱባት ምድር ላይም በግልጽ ይታያል። የፊዚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ፖል ዴቪስ ይህን ሁሉ አስመልክተው ተመራማሪዎች “ግዑዙ ዓለም ባለው ግርማ ሞገስና ውስብስብ በሆነው አደረጃጀቱ በጣም ይደነቃሉ” ሲሉ ጽፈዋል።—መዝሙር 104:24
5 በሕያዋን ነገሮች ላይ የሚገኘውን ‘ውስብስብ አደረጃጀት’ የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎችን ተመልከት። የነርቭ ቀዶ ሕክምና ዶክተር የሆኑት ጆሴፍ ኢቫንስ ስለ ሰው አንጎልና አከርካሪ ሲናገሩ “በተደራጀ መልክ የተከወነውን አሠራራቸውን መረዳት አዳጋች ነው ማለት ይቻላል” ብለዋል። በዓይን የማትታየውን ሕያው ሕዋስ በተመለከተ በባክቴሪያ ጥናት ጠበብት የሆኑት ጄ ሾኔሲ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፦ “በዓይን የማይታዩ ነፍሳትን ያቀፈው ዓለም ያለው ውስብስብነትና ማራኪ አደረጃጀት እጅግ በሚያስደንቅ መንገድ የተገነባ በመሆኑ በመለኮታዊ ኃይል የተነደፉት ሥርዓቶች አንዱ ክፍል ይመስላል።” የሞሎኪላር ባዮሎጂ ጠበብት የሆኑት ሚካኤል ዴንተን በአንድ ሕዋስ ውስጥ ስለሚገኘው ወደ ቀጣይ ዘሮች የሚተላለፉትን ሁለንተናዊ ባሕርያት ስለሚወስነው ንድፍ (ዲ ኤን ኤ) ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “እስከ ዛሬ ድረስ በፕላኔቷ ላይ የኖሩትን ሕያዋን ነገሮች በሙሉ ለመሥራት የሚያስፈልገውን ንድፍ ለማውጣት የሚያስችሉትን አስፈላጊ . . . መረጃዎች በሙሉ መያዝ ይችላል። . . . ይህ ሁሉ መረጃ በአንድ የሻይ ማንኪያ ሊያዝ ይችላል። እንደዚያም ሆኖ ማንኪያው ላይ እስከ ዛሬ ድረስ በተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ ላይ ያሉትን መረጃዎች በሙሉ መያዝ የሚችል ቦታ ይተርፋል።”—መዝሙር 139:16ን ተመልከት።
6, 7. በመንፈሳዊ ፍጥረታት ዘንድ ምን ዓይነት አደረጃጀት ይታያል? ለሠሪያቸው ያላቸውን አድናቆት የገለጹትስ እንዴት ነው?
6 ይሖዋ ያደራጀው የሚታዩ ፍጥረታቱን ብቻ አይደለም። በሰማይ ያሉትን መንፈሳዊ ፍጥረታቱንም አደራጅቷቸዋል። ዳንኤል 7:10 ‘እልፍ አእላፋት የሆኑ መላእክት በይሖዋ ፊት እንደቆሙ’ ይነግረናል። በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ብርቱ መንፈሳውያን ፍጥረታት ያሉ ሲሆን እያንዳንዱ የተመደበለት ሥራ አለው! እንዲህ ዓይነቱን ከፍተኛ ቁጥር ለማደራጀት ምን ዓይነት የአእምሮ ብቃት እንደሚያስፈልግ ለመገመትም እንኳ ያዳግታል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል በትክክል ይገልጻል፦ “ቃሉን የምትፈጽሙ፣ ብርቱዎችና ኃያላን፣ የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ መላእክቱ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ። [የመላእክት] ሠራዊቱ ሁሉ፣ ፈቃዱን የምታደርጉ አገልጋዮቹ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ።”—መዝሙር 103:20, 21፤ ራእይ 5:11
7 የፈጣሪ የእጅ ሥራዎች ምንኛ የተደራጁና በተቀላጠፈ መንገድ የሚሠሩ ናቸው! በሰማያዊው ዓለም የሚገኙት ኃያላን ፍጥረታት አክብሮታዊ ፍርሃትንና ተገዢነትን በሚገልጽ መንገድ እንዲህ ብለው ማወጃቸው አያስደንቅም፦ “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል።”—ራእይ 4:11
8. ይሖዋ በምድር ያሉትን አገልጋዮቹን የሚያደራጅ መሆኑን የትኞቹ ምሳሌዎች ያሳያሉ?
8 ይሖዋ በምድር ያሉትን አገልጋዮቹንም ያደራጃል። በኖኅ ዘመን በ2370 ከዘአበ የውኃ መጥለቅለቅን ባመጣ ጊዜ ኖኅና ሌሎች ሰባት ሰዎች አንድ ቤተሰባዊ ድርጅት በመሆን ከጥፋት ውኃ ተርፈዋል። በ1513 ከዘአበ ይሖዋ በሚልዮን የሚቆጠር ሕዝቡን ከግብጻውያን ቀንበር በማላቀቅ የዕለት ተዕለት ጉዳዮቻቸውንና አምልኮአቸውን ለማደራጀት እያንዳንዱን ጉዳይ የሚመለከቱ ሕግጋትን ሰጣቸው። ከጊዜ በኋላም በተስፋይቱ ምድር በአሥር ሺህ የሚቆጠሩት በቤተ መቅደሱ ለሚከናወነው ልዩ አገልግሎት ተደራጁ። (1 ዜና መዋዕል 23:4, 5) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤዎች በመለኮታዊ መመሪያ መሠረት ተደራጅተው ነበር፦ “እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ ሌሎቹም ነቢያት፣ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፣ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ . . . ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራት።”—ኤፌሶን 4:11, 12
ዘመናዊ አገልጋዮችም የተደራጁ ናቸው
9, 10. በጊዜያችን ይሖዋ ሕዝቡን ያደራጀው እንዴት ነው?
9 በተመሳሳይም ይሖዋ ለአምላክ አክብሮት የሌለው የአሁኑ የነገሮች ሥርዓት ከመጥፋቱ በፊት በጊዜያችን መሠራት ያለበትን የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩን ሥራ ውጤታማ በሆነ መንገድ ማከናወን እንዲችሉ ዘመናዊ አገልጋዮቹን አደራጅቷቸዋል። (ማቴዎስ 24:14) ይህ ዓለም አቀፋዊ ሥራ ምን ምን ነገሮችን እንዳካተተና ጥሩ አደረጃጀት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተመልከት። በሚልዮን የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ሌሎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለማስተማር በመሠልጠን ላይ ናቸው። ለዚህ ማሠልጠኛ እገዛ ለማድረግ ከፍተኛ ብዛት ያላቸው መጽሐፍ ቅዱሶችና የመጽሐፍ ቅዱስ ማስተማሪያ ጽሑፎች ታትመዋል። እንዲያውም እያንዳንዱ የመጠበቂያ ግንብ እትም በ118 ቋንቋዎች ከ16 ሚልዮን ቅጂዎች በላይ ይታተማል። የንቁ! መጽሔት ደግሞ በ73 ቋንቋዎች ወደ 13 ሚልዮን በሚጠጉ ቅጂዎች ይታተማል። ሁሉም እትሞች እኩል ይወጣሉ ማለት ይቻላል። ስለዚህም ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች በአብዛኛው በአንድ ጊዜ አንድ ዓይነት መንፈሳዊ ገበታ ይቀርብላቸዋል።
10 በተጨማሪም ዘወትር በመሰብሰብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ለመስጠት ከ73,000 በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ተደራጅተዋል። (ዕብራውያን 10:24, 25) በየዓመቱ የሚካሄዱ የክልል ስብሰባዎችንና የወረዳ ስብሰባዎችን የመሰሉ በሺህ የሚቆጠሩ ትላልቅ ስብሰባዎችም አሉ። በዓለም ዙሪያ አዳዲስ ወይም እድሳት የሚደረግላቸው የመንግሥት አዳራሾች፣ የክልል ስብሰባ አዳራሾች፣ የቤቴል ቤቶችና ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ኅትመት የሚያገለግሉ ተቋሞች ሰፊ የግንባታ ሥራም ይካሄዳል። በምድር ዙሪያ ባሉ አገሮች ውስጥ የሚካሄዱ ሚስዮናውያን የሚሠለጥኑበትን የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤትንና የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤትን የመሰሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪነት ከፍተኛ ሥልጠና የሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች አሉ።
11. በአሁኑ ጊዜ ጥሩ አደረጃጀትን መማር ወደፊት ምን ጥቅም ያስገኛል?
11 ይሖዋ እርሱን በሚያገለግሉት መላእክት እየደገፈ ሕዝቡ ‘አገልግሎታቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲፈጽሙ’ በምድር ላይ ምንኛ በሚገባ አደራጅቷቸዋል! (2 ጢሞቴዎስ 4:5፤ ዕብራውያን 1:13, 14፤ ራእይ 14:6) አምላክ በአሁኑ ጊዜ አገልጋዮቹ በጥሩ አደረጃጀት እንዲሠሩ በማድረግ ሌላም ነገር እያከናወነ ነው። አገልጋዮቹ ከዚህ የነገሮች ሥርዓት ጥፋት በሕይወት አልፈው የአዲሱን ዓለም ኑሮ ሲጀምሩ ቀደም ብለው የተደራጁ ሆነው ይገኛሉ። ከዚያም ይሖዋ የሚሰጣቸውን መመሪያ እየተቀበሉ በተደራጀ መልክ ዓለም አቀፋዊቷን ገነት መገንባት ይጀምራሉ። ሰዎች በሕይወት ለመኖር እንዲችሉ ማሟላት ያለባቸውን አምላክ ያወጣቸውን ብቃቶች ከሞት ለሚነሡት በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አንድ በአንድ ለማስተማርም በደንብ የተዘጋጁ ይሆናሉ።—ኢሳይያስ 11:9፤ 54:13፤ ሥራ 24:15፤ ራእይ 20:12, 13
የተደራጁ ግን ደስተኞች
12, 13. ይሖዋ ሕዝቡ ደስተኛ እንዲሆኑ ይፈልጋል ብለን መናገር የምንችለው ለምንድን ነው?
12 ይሖዋ እጅግ አስደናቂ የሆነ ሠራተኛና እንከን የማይወጣለት አደራጅ ቢሆንም እንኳ ደንታ ቢስ፣ ግትር ወይም ስሜት አልባ እንደሆነ ማሽን የሚሠራ አምላክ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ፍቅራዊ ስሜት ያለው፣ ደስተኛና ለእኛም ደስታ የሚያስብ አምላክ ነው። “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና” በማለት 1 ጴጥሮስ 5:7 ይገልጻል። ለአገልጋዮቹ ያለውን አሳቢነትና እነርሱ ደስተኛ እንዲሆኑ ያለውን ፍላጎት ለሰው ልጆች ከሠራቸው ነገሮች መረዳት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል አምላክ ፍጹሞቹን ወንድና ሴት በፈጠረ ጊዜ ያኖራቸው ደስታ በሞላባት ገነት ውስጥ ነበር። (ዘፍጥረት 1:26–31፤ 2:8, 9) እጅግ የላቀ ደስታ ለማግኘት የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ሰጣቸው። ይሁን እንጂ በዓመፅ ምክንያት ሁሉንም ነገር አጡ። በሠሩት ኃጢአት የተነሣ እኛም አለፍጽምናንና ሞትን ወረስን።—ሮሜ 3:23፤ 5:12
13 እኛ የሰው ልጆች ምንም እንኳ በአሁኑ ጊዜ ፍጹማን ባንሆንም አምላክ በሠራቸው ነገሮች ደስታ ማግኘት እንችላለን። ግርማ ሞገስ የተላበሱ ተራራዎችን፣ ማራኪ ሐይቆችን፣ ወንዞችን፣ ውቅያኖሶችንና የባሕር ዳርቻዎችን፣ በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ ጣፋጭ ሽታ ያላቸው አበቦችንና ዓይነታቸው ተቆጥሮ የማይዘለቅ ሌሎች ቅጠላ ቅጠሎችን፣ የተትረፈረፉ ጣፋጭ ምግቦችን፣ ምን ጊዜም የማይሰለቸንን እጅግ የሚመስጠውን የፀሐይ መጥለቅ፣ በምሽት ወደ ላይ አንጋጠን በመመልከት እያሰላሰልን የምንደሰትባቸውን በከዋክብት የተሞሉ ሰማያት፣ ስፍር ቁጥር የሌለው ዓይነት ያላቸውን እንስሳትንና የሚቦርቁና የሚፈነጥዙ ደስ የሚሉ ግልገሎችን፣ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ሙዚቃዎችን፣ አስደሳችና ጠቃሚ ሥራን እንዲሁም ጥሩ ጓደኞችን የመሳሰሉ ደስታ የሚያስገኙልን ብዙ ነገሮች አሉ። እነዚህን የመሰሉ ነገሮችን ያዘጋጀው አካል ራሱ ሌሎችን በማስደሰት የሚደሰት ደስተኛ አካል እንደሆነ ምንም አያጠያይቅም።
14. ይሖዋ እሱን ስንመስለው ምን ዓይነት ሚዛናዊነት እንድናሳይ ይፈለግብናል?
14 ስለዚህ ይሖዋ የሚፈልገው ለሥራ ቅልጥፍና በሚረዳ የተደራጀ መልክ መሥራትን ብቻ አይደለም። እርሱ ደስተኛ እንደሆነ ሁሉ አገልጋዮቹም ደስተኛ እንዲሆኑ ይፈልጋል። ደስታቸውን በሚያጠፋ የማያወላዳ መንገድ ነገሮችን እንዲያደራጁ አይፈልግም። ኃያሉ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ባለበት ቦታ ሁሉ ደስታ ስላለ አገልጋዮቹም የማደራጀት ችሎታቸው ከደስታ ጋር ጎን ለጎን እንዲራመድ ማድረግ አለባቸው። አምላክ የሚሠራው በዚሁ መንገድ ነው። እንዲያውም በሕዝቡ ላይ የሚሠራው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ሁለተኛው ፍሬ “ደስታ” እንደሆነ ገላትያ 5:22 ያሳያል።
ፍቅር ደስታን ያመጣል
15. ደስተኞች እንድንሆን ፍቅር እጅግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
15 መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ብሎ መናገሩ በጣም የሚያስደስት ነው። (1 ዮሐንስ 4:8, 16) “እግዚአብሔር ድርጅት ነው” አይልም። የአምላክ ዋነኛ ባሕርይ ፍቅር ነው። አገልጋዮቹም ይህን ባሕርይ መኮረጅ አለባቸው። በገላትያ 5:22 ላይ ከተዘረዘሩት የአምላክ መንፈስ ፍሬዎች ውስጥ “ፍቅር” “ደስታን” በማስከተል በአንደኝነት የሰፈረው ለዚህ ነው። ፍቅር ደስታን ያመጣል። አፍቃሪ ሕዝብ ደስተኛ ሕዝብ ስለሆነ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት የይሖዋን ፍቅር ስንኮርጅ ደስታም ተከትሎ ይመጣል።
16. ኢየሱስ የፍቅርን አስፈላጊነት በተግባር ያሳየው እንዴት ነው?
16 አምላካዊ ፍቅርን የመኮረጅ አስፈላጊነት በኢየሱስ ትምህርቶች ላይ ጎላ ብሎ ተገልጿል። ኢየሱስ ‘አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገራለሁ’ ብሏል። (ዮሐንስ 8:28) ኢየሱስ ለሌሎች መልሶ ያስተማረው የትኛውን ከአባቱ የተማረውን ትምህርት ነው? አምላክንና ሰውን መውደድ እንደሚገባ የሚገልጹትን ሁለቱን ታላላቅ ትእዛዛት ነው። (ማቴዎስ 22:36–39) ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር በተግባር አሳይቷል። ‘አብን እወደዋለሁ’ ብሏል። ይህንንም የአምላክን ፈቃድ እስከ ሞት ድረስ በመፈጸም አረጋግጧል። ለሰዎች በመሞትም ለእነርሱም ያለውን ፍቅር አሳይቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ የኤፌሶን ክርስቲያኖችን ‘ክርስቶስ ወዷችኋል፤ ስለ እናንተም ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷል’ ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 14:31፤ ኤፌሶን 5:2) ስለዚህም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በእርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት” ብሏቸዋል።—ዮሐንስ 15:12, 13
17. ለሌሎች ፍቅር ማሳየት የግድ አስፈላጊ መሆኑን ጳውሎስ የገለጸው እንዴት ነው?
17 ጳውሎስ ቀጥሎ ያለውን በመናገር ይህ አምላካዊ ፍቅር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ገልጿል፦ “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ፣ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፣ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፣ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። . . . እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።”—1 ቆሮንቶስ 13:1–3, 13
18. ደስታችንን የሚያጎለብት ምን ነገር ከይሖዋ መጠበቅ እንችላለን?
18 ይሖዋ “መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት” ስለሆነ የእሱን ፍቅር በምንኮርጅበት ጊዜ ሌላው ቀርቶ ስሕተት ስንሠራ እንኳ ለእኛ ካለው ፍቅር የተነሣ እንደማይተወን ልንተማመን እንችላለን። (ዘጸአት 34:6) ስሕተት በምንፈጽምበት ጊዜ ከልባችን ንስሐ ከገባን አምላክ የሠራነውን ስሕተት አይቆጥርብንም። ከዚህ ይልቅ በፍቅር ይቅር ይለናል። (መዝሙር 103:1–3) አዎን፣ “ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነው።” (ያዕቆብ 5:11) ይህን ማወቃችን ደስታችንን ያጎለብትልናል።
በአሁኑ ጊዜ የምናገኘው አንጻራዊ ደስታ
19, 20. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ ሙሉ ደስታ ማግኘት የማይቻለው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ዘመን አንጻራዊ ደስታ ማግኘት እንደምንችል መጽሐፍ ቅዱስ የሚያሳየው እንዴት ነው?
19 ይሁን እንጂ በሽታና ሞት ተጋርጠውብን በሚገኙበት በዚህ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለ በወንጀል በተሞላ፣ ዓመፀኛና ብልሹ ዓለም የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ እየኖርን ደስተኛ መሆን እንችላለንን? እርግጥ ነው፣ በአምላክ ቃል ውስጥ የሰፈረውን “እነሆ፣ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም። ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሤት አድርጉ” የሚለውን በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የምናገኘውን ደስታ ያህል አሁን እናገኛለን ብለን መጠበቅ አንችልም።—ኢሳይያስ 65:17, 18
20 የአምላክ አገልጋዮች የእሱን ፈቃድ ስለሚያውቁና ገነት በምትሆነው አዲስ ዓለም ውስጥ በቅርቡ ስለሚመጡት አስደናቂ በረከቶች ትክክለኛ እውቀት ስላላቸው በአሁኑ ጊዜ አንጻራዊ ደስታ ሊያገኙ ይችላሉ። (ዮሐንስ 17:3፤ ራእይ 21:4) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሊል የቻለው ለዚህ ነው፦ “የሠራዊት አምላክ ሆይ፣ በአንተ የታመነ ሰው ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው።” “እግዚአብሔርን የሚፈሩት ሁሉ፣ በመንገዶቹም የሚሄዱ ምስጉኖች [ደስተኞች አዓት] ናቸው።” “የዋሆች ብፁዓን [ደስተኞች አዓት] ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና።” (መዝሙር 84:12፤ 128:1፤ ማቴዎስ 5:5) ስለዚህ በጊዜያችን ልንቋቋማቸው የሚገቡ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም በቀላሉ የማይገመት ደስታ ልናገኝ እንችላለን። ሌላው ቀርቶ መጥፎ ነገሮች ሲደርሱብንም እንኳ ይሖዋን እንደማያውቁትና የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች ከመጠን በላይ አናዝንም።—1 ተሰሎንቄ 4:13
21. የይሖዋ አገልጋዮች ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን ለሌሎች ጥቅም ማዋላቸው ለደስታቸው አስተዋጽኦ ያበረከተው እንዴት ነው?
21 የይሖዋ አገልጋዮች ሌሎችን በተለይም በሰይጣን ዓለም ውስጥ እየተሠራ ባለው ‘ርኩሰት የሚያለቅሱና የሚተክዙ ሰዎችን’ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለማስተማር ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጥሪታቸውን ስለሚያውሉም ደስታን ያገኛሉ። (ሕዝቅኤል 9:4) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው፤ እግዚአብሔር በክፉ ቀን ያድነዋል። እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፣ ሕያውም ያደርገዋል፣ በምድርም ላይ ያስመሰግነዋል [ደስ ብሎት እንዲኖር ያደርጋል የ1980 ትርጉም]።” (መዝሙር 41:1, 2) ኢየሱስ እንዳለው “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [ደስተኛ አዓት] ነው።”—ሥራ 20:35
22. (ሀ) የአምላክ አገልጋዮች ያላቸውን ደስታ እርሱን የማያገለግሉ ሰዎች ካላቸው ደስታ ጋር አወዳድር። (ለ) ደስታን እናገኛለን ብለን ተስፋ ማድረግ የሚገባን በምን ልዩ ምክንያት የተነሳ ነው?
22 ስለዚህ የአምላክ አገልጋዮች በአሁኑ ዘመን የተሟላ ደስታ እናገኛለን ብለው መጠበቅ ባይችሉም አምላክን የማያገለግሉ ሰዎች የሌላቸውን ደስታ ማግኘት ይችላሉ። ይሖዋ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “እነሆ፣ ባሪያዎቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ፣ እናንተ ግን ከልባችሁ ኀዘን የተነሣ ትጮኻላችሁ፣ መንፈሳችሁም ስለ ተሰበረ ወዮ ትላላችሁ።” (ኢሳይያስ 65:14) አምላክን የሚያገለግሉ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የሚደሰቱበት ልዩ የሆነ ምክንያትም አላቸው። “እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ” አላቸው። (ሥራ 5:32) የአምላክ መንፈስ ባለበት ቦታ ሁሉ ደግሞ ደስታ እንዳለ አስታውስ።—ገላትያ 5:22
23. በሚቀጥለው ጥናታችን የምንመረምረው ነገር ምንድን ነው?
23 ዛሬ ባለው የአምላክ አገልጋዮች ድርጅት ውስጥ በጉባኤዎች ውስጥ የመሪነቱን ቦታ የያዙት “ሽማግሌዎች” የይሖዋ ሕዝብ ደስታ እንዲያገኝ አስተዋጽኦ በማበርከት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። (ቲቶ 1:5) እነዚህ ወንድሞች ኃላፊነቶቻቸውንና ከመንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እኅቶቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዴት መመልከት ይኖርባቸዋል? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ያብራራል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ይሖዋ የተደራጀ መሆኑን ፍጥረት የሚመሠክረው እንዴት ነው?
◻ ይሖዋ ጥንትም ሆነ አሁን አገልጋዮቹን ያደራጃቸው እንዴት ነው?
◻ ይሖዋ ምን ዓይነት ሚዛናዊነት እንድናሳይ ይፈልግብናል?
◻ ደስተኞች እንድንሆን ፍቅር ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
◻ በጊዜያችን ምን ዓይነት ደስታ እናገኛለን ብለን መጠበቅ እንችላለን?
[ምንጭ]
ከላይ፦ Courtesy of ROE/Anglo-Australian Observatory, photograph by David Malin