ስደተኞች ቢሆኑም አምላክን እያገለገሉ በመሆናቸው ደስተኞች ናቸው
ጦርነት፣ ረሀብ፣ የተፈጥሮ አደጋና ብጥብጥ። ለአንዳንድ ሰዎች እነዚህ በዜና የሚሰሟቸው ነገሮች ብቻ ናቸው። ለሌሎች ብዙ ሰዎች ግን የዕለት ተዕለት ኑሯቸው ክፍል ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮችም ዓለም አቀፍ ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ስላላቸው ጦርነት በተነሣ ጊዜ ወይም የተፈጥሮ አደጋ በደረሰ ጊዜ ሁሉ በዓለም ዙሪያ ካሉት ወንድሞቻቸው ውስጥ በዚህ ሁኔታ የሚሠቃዩ ሊኖሩ እንደሚችሉ በሚገባ ያውቃሉ። ሰዎች ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሸሹ ወንድሞቻችንም ለመሸሽ ይገደዳሉ።
ለብዙ ዓመታት በብዙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ያሉ ምሥክሮች ይህን የመሰሉ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል። ብዙዎቹ መሸከም የሚችሉትን ያህል ዕቃ ጠቅልለው የሆነ ቦታ መጠለያ ለማግኘት ይሄዳሉ። ምንም እኳን ጥቂቶች በመጓጓዣ ማለትም በብስክሌት የሄዱ ቢሆንም አብዛኞቹ የሚሄዱበት ቦታ ለመድረስ ለቀናት ምናልባትም ለሳምንታት በእግራቸው መጓዝ ነበረባቸው።
ከሚሄዱባቸው ቦታዎች አንዷ እምቦኪ የተባለች በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ነች። ባለፉት ዓመታት በሺህ የሚቆጠሩ ወንዶችና ሴቶች፣ ወጣቶችና አዛውንቶች ወደዚች ከተማ ጎርፈዋል። ከነሱም መካከል በርከት ያሉ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ይገኙበታል። በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ በባንጉዊ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ የሚሠሩ መሰል ክርስቲያኖች እነዚህን ስደተኞች አግኝተው እርዳታ ለመስጠት ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው። በ1,300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በባንጉዊ የሚገኙት ምሥክሮች በልግስና ያዋጡትን ገንዘብ፣ ምግብ፣ ልብስና መድኃኒት ለማድረስ አንድ ተወካይ አምስት ጊዜ ተመላልሷል። ምንም እንኳን ይህንን የልግስና እርዳታ የሰጡት ወንድሞች ራሳቸው ኑሯቸው ዝቅተኛ ቢሆንም የቻሉትን ያህል በማድረጋቸው ደስ ብሏቸዋል።
ወደ እምቦኪ መሄድ
የቅርንጫፍ ቢሮው ወንድሞች ስደተኞቹን በመንፈሳዊ ለመርዳትና ሊደረግ የሚገባው ሌላ ምን ነገር እንዳለ ለማወቅ ፈለጉ። ስለዚህ እኔና ባለቤቴ እንዲሁም ሳንፎርየን የተባለ ልዩ አቅኚና ባለቤቱ አራቱንም ጎማዎቹን ማሽከርከር በሚችል ላንድ ክሩዘር ሆነን ጉዞ ጀመርን። ሳንፎርየን መንገዱን በደንብ ያውቀዋል። የእምቦኪ ስደተኞች የሚናገሩትንም ዛንዴ የተባለ ቋንቋ መናገር ይችላል። እዚያ ለመድረስ አራት ረጃጅምና አድካሚ ቀናት ፈጅቶብናል።
የመጨረሻውን የ400 ኪሎ ሜትር መንገድ የተጓዝነው በሚያምር የገጠር አካባቢና በትልልቅ ባኦባብ ዛፎች መካከል ነበር። እዚህም እዚያም ያሉትን ትንንሽ መንደሮች እያለፍን ሄድን። ባለቤቴ በዚህ መንገድ ላይ 50 ድልድዮች ቆጥራለች። ብዙዎቹ ድልድዮች መጥፎ ሁኔታ ያላቸው ሲሆን በአንዳንዶቹ ላይ ማለፍ አይቻልም። አንዳንዶቹን ድልድዮች በእንጨትና በበሰበሱ ግንዶች ጠጋግነን መኪናችንን አስነሥተን ከጸለይን በኋላ በከፍተኛ ጥንቃቄ አለፍናቸው። በአቅራቢያው አንድ ትንሽ መንደር ካለ የመንደሩ ወጣቶች ትንሽ ገንዘብ እንድንከፍላቸው እየሮጡ ይመጡና ይረዱን ነበር። ከረጃጅሞቹ ሣሮችና ከጫካው ውስጥ ከድልድዩ ላይ የተነቀሉ እንጨቶችና ሳንቃዎች ይዘው መምጣታቸው አስገረመን። ምናልባት ማለፍ የሚፈልጉ ባለመኪኖችን እያስከፈሉ ለማሳለፍ ራሳቸው ከድልድዮቹ ላይ እየነቃቀሉ ደብቀዋቸው ይሆን? ብለን እንድናስብ አደረገን።
ሦስት ጊዜ ሊረዱን የመጡትን ወጣቶች አንፈልግም ብለን መለስናቸው። ምክንያቱም ድልድዮቹ በጣም ከመበላሸታቸው የተነሣ በላያቸው ላይ ማለፍ አይቻልም ነበር። ስለዚህ ከመንገዱ ወጣንና ውኃው ውስጥ ገባን፤ ከዚያም በድንጋዮቹ ላይ እየነዳን እንደገና ወደላይ በመውጣት ወደ መንገዱ ተመለስን። ወቅቱ ዝናብ የማይዘንብበት በመሆኑ ደስ አለን። አለበለዚያ በሄሊኮፕተር ካልሆነ በስተቀር በምንም መንገድ ወደዚህ ስፍራ መምጣት አንችልም ነበር።
እምቦኪ ምን ትመስል ይሆን? ማቆሚያ የሌለው በሚመስለው “ፔስት” (በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ ውስጥ አሸዋና ጠጠር የፈሰሰበት እንዲሁም ኮሮኮንች የሆነና በጣም ብዙ ትንንሽ ጉድጓዶች ያሉበት መንገድ የሚጠራበት የፈረንሳይኛ ቃል ነው) መንገድ ላይ ስንጓዝ ይህ ጥያቄ ብዙ ጊዜ በአእምሮአችን ውስጥ ይመላለስ ነበር።
በአራተኛው ቀን ቀትር ላይ ሲንፎርየን በፓፓያ ዛፍና በካሳቫ እርሻ ወደተከበቡ የሣር ክዳን ያላቸው ጎጆዎች እያመለከተ “ቭዋላ! (ያችውና!) እምቦኪ የምትጀምረው እዚህ ነው” ብሎ ጮኸ። ባየነው ነገር በጣም ተገረምን። “እምቦኪ ማለት ይህቺ ናት? ታዲያ ካምፑ የታለ?” ብለን ጠየቅነው። ምክንያቱም የምናየው ቤቶችን ነበር። ቤቶቹ የሣር ክዳን ያላቸው ትንንሽ ጎጆዎች ሲሆኑ ንጹሕ ናቸው። በየቦታው ዛፎችና ቁጥቋጦዎች አሉ። ነዋሪዎቹ ከቤታቸው አጠገብ እህል ይዘራሉ። እምቦኪ እንደጠበቅናት ዓይነት ካምፕ አይደለችም። ከጫፍ እስከ ጫፍ ወደ 35 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላት አንዲት ሰፊ መንደር ናት።
ከወንድሞች ጋር መገናኘት
በእምቦኪ ያሉ ወንድሞች እንደምንመጣ አስቀድመው ቢያውቁም መንገዱ አምስት ቀን የሚፈጅብን መስሏቸው ነበር። የመኪናችንን ድምፅ ሲሰሙ እየሮጡ መጡ። ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ሁሉ ከየጎጆአቸው ከየግቢያቸውና ከየእርሻ ቦታቸው እየተሯሯጡ ሰላም ሊሉን መጡ። ሁሉም ፈገግታ ነበራቸው፣ ይስቁ ነበር፣ የተቻላቸውን ያህል ብዙ ጊዜ ጨበጡን። ሴቶቹ ሕፃናት አቅፈው በመምጣት ሰላም አሉን። ሁሉም ሰላም ሊሉንና በመምጣታችን ከልባቸው እንደተደሰቱ ሊገልጹልን ፈልገው ነበር።
እኔና ባለቤቴ ቋንቋቸውን ስለማናውቅ ለጊዜው ብዙ ልናነጋግራቸው አልቻልንም። ትንሽ ትንሽ በፈረንሳይኛ፣ በሳንጎ፣ በእንግሊዝኛና በአረብኛ ልናነጋግራቸው ሞከርን። አብዛኞቹ ወንድሞቻችን በዛንዴ ቋንቋ መናገር ማንበብና መጻፍ ይችላሉ። ሲንፎርየን የጉብኝታችንን ፕሮግራም በማብራራት አስተረጎመልን።
ከዚያ ትንሽ ኪሎ ሜትሮች ከተጓዝን በኋላ መንግሥት አዳራሹ ደረስን። ከየትኛውም ሃይማኖት በፊት በእምቦኪ ባሉ ስደተኞች የተሠራ የመጀመሪያው “ቤተ ክርስቲያን” ይህ አዳራሽ ነው። ተጨማሪ ወንድሞችና ልጆቻቸው እንዲሁም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች መጡና ጨበጡን። ብዙ የአካባቢው ልጆችም ጭምር ከወንድሞች ጋር መጥተው ጨበጡን።
ወንድሞቻችን ለኛ ለጎብኚዎች ማረፊያ የሚሆኑ በአካባቢው ያሉ ቤቶችን የሚመስሉ ሁለት ትንንሽ ጎጆዎች አዘጋጅተውልን ነበር። ቤቶቹ በጣም ንጹሖች ነበሩ። ንጹሕ ውኃ በባልዲ ተቀድቶ ተቀምጦልን ነበር። ምንም ነገር ላይገኝ ይችላል ብለን በማሰብ እንዲሁም በወንድሞቻችን ላይ ሸክም ለመሆን ስላልፈለግን የራሳችንን ምግብና የመጠጥ ውኃ ይዘን መጥተን ነበር። ዕቃችንን ከመኪናው ላይ እያወረድን ሳለ አንዲት ወጣት መጥታ ‘ዶሮውን እንዴት ብናዘጋጅላችሁ ይሻላችኋል? የዶሮ ጥብስ ወይስ የዶሮ ወጥ?’ ብላ ጠየቀችን። በጭራሽ ያልጠበቅነው ነገር ነበር። እነሱ ከምን ጋር እንደሚበሉት ጠየቅናት። እሷም ከካሳቫ ጋር ነው ብላ መለሰችልን። ስለዚህ ወጡ ይሻለናል አልናት። ማታ ርቦን ስለነበረ እስክንጠግብ በላን። እነሱ ግን በየቀኑ ምሳም ራትም ያበሉን ነበር። ስደተኞቹ ለራሳቸው ብዙ ነገር ባይኖራቸውም እኛን እየመገቡንና እየተንከባከቡን መሆናቸውን ማመን አቃተን።
ደስተኛ የሆነ ትንሽ ጉባኤ
ያለነው በጣም ሩቅ ቦታ ቢሆንም በ21 ወንድሞቻችን መካከል ነበርን። እዚህ ከመምጣታቸው በፊት የተጠመቁት ወንድሞች ሁለቱ ብቻ ናቸው። የተቀሩት ወደዚህ ሲመጡ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ነበሩ። እዚህ ከመጡ ወዲያ ማጥናታቸውን ቀጥለው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ተጠመቁ። በጉብኝታችን ወቅት አራት ተጨማሪ ሰዎች አቅራቢያቸው ያለ ወንዝ ውስጥ ተጠምቀዋል።
አንዱ ጎልቶ የሚጠቀስ ምሳሌ ፋውስቲኖ ነው። ወደ እምቦኪ ከመምጣቱ በፊት እውነትን ከአንድ ጓደኛው ይሰማል። ፋውስቲኖ ለተማረው ነገር አድናቆት አደረበት። ብዙም ሳይቆይ እሱና ጓደኛው ለሌሎች መስበክ ይጀምራሉ። ግን ተቃውሞ ይነሣባቸውና በሃይማኖታቸው “ሕዝቡን ረብሸዋል” ተብለው ይታሰራሉ። እስር ቤት እያሉ የፋውስቲኖ ጓደኛ በፍርሃት ተሸንፎ አቋሙን ለወጠና ከእስር ቤት ተለቀቀ። ከሁለት ወር በኋላ ፋውስቲኖ ፍርድ ቤት ይቀርባል። ሆኖም የቀረበበት ክስ መሠረተ ቢስ መሆኑ በግልጽ ስለታወቀ እሱም ተፈታ። በኋላም በአካባቢው ጦርነት በመቀስቀሱ ፋውስቲኖ ሸሽቶ ወደ መካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ መጣ። እዚያም ወንድሞችን አግኝቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ቀጠለና በሐምሌ 1991 ተጠመቀ። በ1992 የዘወትር አቅኚ በመሆን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመረ።
ደስተኛና የወዳጅነት መንፈስ ያለበት ትንሹ የእምቦኪ ጉባኤ አሁን አንድ ልዩ አቅኚና 21 አስፋፊዎች አሉት። ሁለት እንግሊዝኛ ተናጋሪ ወንድሞች ሽማግሌዎች ሆነው የሚያገለግሉ ሲሆን ከባንጉዊ ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር ጥሩ ግንኙነት ለማድረግ ችለዋል። ስደተኛ ወንድሞቻችን በጣም አስከፊና የሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ ያሉ መስሎን ነበር፤ ሁኔታቸው ግን እንደዚያ አልነበረም። ምንም እንኳን ድሆች ቢሆኑም በሁኔታው የሚማረር፣ የሚጨነቅ ወይም የሚያጉረመርም የለም። ወንድሞች እዚህ ከመጡ በኋላ ጎጆዎችና ቤቶች ሠርተው እህል መዝራትና ዶሮ ማርባት ጀመሩ። አሁን ያላቸው በፊት ከነበራቸው በጣም ያነሰ ቢሆንም በሕይወት ይኖራሉ፤ ደግሞም ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር ናቸው።
እምቦኪ ውስጥ ከ17,000 እስከ 20,000 የሚደርሱ ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን በየወሩ ተጨማሪ ስደተኞች ይመጣሉ። ስለዚህ ወንድሞቻችን ሰፊ የአገልግሎት መስክ አላቸው። አብረናቸው ልንሰብክ ሄድን፤ በእውነቱ በጣም ደስ ይል ነበር። ብዙውን ጊዜ የሚጠቀሙት በዛንዴ ቋንቋ በተተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እንዲሁም በግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በብዙ ቦታዎች የአምላክ ስም ይገኝበታል። ለነዚህ ሰዎች አምላክ “እምቦሊ” (በዛንዴ “አምላክ” ማለት ነው) ብቻ ሳይሆን “ይኮቫ” ነው። የአምላክን የግል ስም የሚጠሩት እንዲህ ብለው ነው። “እምቦሊ ይኮቫ” በጣም የተለመደ አባባል ነው። በሌሎች የአፍሪካ ቋንቋዎች የተተረጎሙ ብዙዎቹ የፕሮቴስታንት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ዓይነት ትክክለኛ አተረጓጓም አይከተሉም። ከዚህ ይልቅ “ይሖዋ” የሚለውን “ንዛፓ”፣ “ንዛምቤ” ወይም አፍሪካውያን አምላክ ለሚለው ቃል በሰጡት ሌላ ስም ይተኩታል።
በክርስቶስ ትንቢት መሠረት የመንግሥቱ ምሥራች በዓለም በሙሉ በእምቦኪም ሳይቀር እየተሰበከ ነው። (ማቴዎስ 24:14) አሁን ጉባኤያቸው በሚፈልጉት ቋንቋ የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሶች፣ መጻሕፍት፣ መጽሔቶች፣ ቡክሌቶችና ትራክቶች አሉት። ምናልባት ወደፊት ደግሞ ተጨማሪ ጽሑፎች በዛንዴ ቋንቋ ያገኙ ይሆናል።
የማይፈናቀሉበትን ቋሚ መኖሪያ ይጠብቃሉ
በመጀመሪያው ምሽት በማኅበሩ የተዘጋጀውን “የምሥራቅ አውሮፓ ደስተኛ ተሰብሳቢዎች ይሖዋን አመሰገኑ” የተባለውን የስላይድ ፊልም አሳየናቸው። በማግሥቱ ማታ ፕሮግራማችን “በፍጻሜው ዘመን ብዙዎችን ወደ ጽድቅ ማምጣት” የተባለው የስላይድ ፊልም ነበር። ፊልሞቹ የታዩት እደጅ፣ መንግሥት አዳራሹ አጠገብ ሲሆን ጥርት ባለው ሰማይ ጨረቃዋ ወለል ብላ ትታይ ነበር። ሁኔታው እንዴት ደስ የሚል ነበር! እነዚህን የስላይድ ፊልሞች ለመመልከት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መጡ። ወንድሞችም በጣም ተደስተው ነበር፤ ለሕዝቡ አንድ ልዩ ነገር ለማሳየት በመቻላቸውም ኩራት ተሰማቸው።
ሰኞ ዕለት ተመልሰን ለመሄድ ተዘጋጀን። በዚያው መጥፎ መንገድ ላይ እነዚያኑ 50 ድልድዮች አቋርጠን ለአራት ቀናት መጓዝ ይኖርብናል። አንዲት እህት ለመንገድ የሚሆናችሁ ምግብ ካላዘጋጀሁ ብላ ለመነችን። የተጠበሱና በነጭ ሽንኩርት የጣፈጡ ሁለት ዶሮዎች አዘጋጀችልን። ጠዋት መንገድ ላይ እያለን ላንድ ክሩዘሩ ውስጥ ሽታው ሲያውደን ቆይቶ ነበር። ከዚያ በምሳ ሰዓት በቁጥቋጦዎች መካከል ቁጭ ብለን የእምቦኪ ወንድሞቻችንን እያሰብን ያን የተጠበሰ ዶሮ ተመገብን። ምንም እንኳን ስደተኞች ለመሆን ቢገደዱም አምላክ እንደሚያመጣው ቃል በገባልን አዲስ ዓለም ውስጥ የማይፈናቀሉበትን ቋሚ የሰላም ቤታቸውን በመጠባበቅ ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ናቸው። (2 ጴጥሮስ 3:13)—አንድ ወንድም ጽፎ የላከልን