ክፉዎች የሚበለጽጉት ለምንድን ነው?
“ስለ ምን ኃጢአተኞች [ክፉዎች አዓት] በሕይወት ይኖራሉ?” ይህን ጥያቄ ከረጅም ጊዜ በፊት የጠየቀው ታማኙ ኢዮብ ነበረ። ይህ ጥያቄ ከእሱ ዘመን አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ በተደጋጋሚ ሲጠየቅ ቆይቷል። አሳዛኝ በሆነው ጦርነት በሚሠቃዩት በቀድሞዋ ዩጐዝላቪያ ውስጥ (በመጽሔቱ ሽፋን ላይ እንደምትታየው ሴት) ባሉ ብዙ ሰዎች አእምሮ ውስጥም እንደሚመላለስ አያጠራጥርም። ክፉ ሰዎች በሕይወት የሚኖሩት አልፈው ተርፈው የሚበለጽጉት ለምንድን ነው? ኢዮብ እንደተናገረው ብዙውን ጊዜ “ቤታቸው ከፍርሃት ወጥቶ የታመነ [ሰላም አዓት] ነው፣ የእግዚአብሔርም በትር የለባቸውም።”—ኢዮብ 21:7, 9
ታዲያ ይህ አምላክን ማገልገል፣ ሰውን መውደድና መጥፎ ነገር ከማድረግ መቆጠብ ምንም ጥቅም የለውም ማለት ነውን? በጭራሽ! መጽሐፍ ቅዱስ “በክፉዎች ላይ አትቅና፣ ዓመፃንም በሚያደርጉ ላይ አትቅና፤ እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፣ እንደ ለመለመ ቅጠልም ይረግፋሉና። በእግዚአብሔር ታመን፣ መልካምንም አድርግ” በማለት ሊኖረን የሚገባውን ትክክለኛ አመለካከት ይገልጽልናል።—መዝሙር 37:1–3
አዎን፣ የክፉዎች ብልጽግና ጊዜያዊ ነው። ሕይወታቸውም በጣም አጭር ነው። አምላክን የሚያገለግሉ ግን ክብራማ የወደፊት ተስፋ አላቸው። “[አምላክ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” ሲል አምላክ የሰጠው ተስፋ በቅርቡ ይፈጸማል። (ራእይ 21:4) ይህን ጊዜ የሚያዩት ጻድቃን ብቻ እንጂ ክፉዎች አይደሉም። በዙሪያችን ያሉት ሰዎች የቱንም ያህል ክፉዎች ቢሆኑ እኛ ወደ አምላክ እንድንጠጋና ፈቃዱን ማድረግን እንድንማር ይህ በጣም ያበረታታናል!
በዚህ በመከራ በተሞላ ዓለምም እንኳ ስለ አምላክ፣ ስለ መንግሥቱና እርሱ ለሰው ልጆች ስላለው አስደናቂ ዓላማ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በማግኘት ደስተኛ መሆን ይችላሉ። ተጨማሪ መረጃ ብንሰጥዎ ደስ የሚልዎት ከሆነ ወይም አንድ የይሖዋ ምሥክር መጥቶ እንዲያነጋግርዎትና መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ክፍያ እንዲያስተምርዎ የሚፈልጉ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች፣ የፖ.ሣ.ቁ 5522፣ አዲስ አበባ ብለው ወይም በገጽ 2 ላይ ካሉት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው ይጻፉ።