‘ሥራው ተከተለው’
ሐሙስ ሐምሌ 28, 1994 ልክ ከጠዋቱ 2:50 ሲሆን ጆርጅ ዲ ጋንጋስ ምድራዊ አገልግሎቱን ፈጸመ። የ98 ዓመት ሰው ነበር። ከቅቡዓን አንዱ የነበረው ጆርጅ ጋንጋስ ከጥቅምት 15, 1971 ጀምሮ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል ነበር።
ወንድም ጋንጋስን የሚቀርቡት ሁሉ እንደሚያውቁት ጽድቅን የሚወድና ዓመፅን የሚጠላ ነበር። ሰይጣንን አስፈሪ፣ አረመኔ፣ ኃጢአተኛ፣ ወራዳና የተናቀ ሐሰተኛ መሆኑን ብዙ ጊዜ ይናገር እንደነበረ ያስታውሳሉ። በተቃራኒው ግን ስለ ይሖዋ አፍቃሪ፣ ደግ፣ ርኅሩኅ፣ አዛኝና ተንከባካቢ አባት እንደሆነ ይናገር ነበር። ብዙዎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይወድ እንደነበረ ያስታውሳሉ። በማንኛውም ጭውውት ላይ ምን ጊዜም ጥያቄዎቹን ያቀርባል። አንዳንዶቹ ቀላል ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ አእምሮን የሚያመራምሩ ነበሩ። በእርግጥም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ይወድ ነበር።
ወንድም ጋንጋስ ሐምሌ 15, 1921 ተጠመቀ። መጋቢት 1928 የሙሉ ጊዜ የስብከት አገልግሎቱንም (አቅኚነት) ቋሚ ሥራው አድርጎ ጀመረ። ስለዚህ በጠቅላላው ለ66 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አሳልፏል። ጥቅምት 31, 1928 ብሩክሊን በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ፣ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ ከሚያገለግሉት ሠራተኞች አንዱ ሆነ።
የሕይወት ታሪኩ በጥቅምት 15, 1966 መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጥቷል። መጠበቂያ ግንቡ በእውነትም መንፈሳዊ የአምላክ ሰው መሆኑን ገልጾ ነበር። ወንድም ጋንጋስ በዚያ እትም ላይ የሚከተለውን ልብን በደስታ የሚያሞቅ አስተያየት ሰጥቷል፦ “ሕይወትን ስለምወድ ወንድሞቼም ሕይወትን እንዲያገኙ እፈልጋለሁ። እኔም ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቆጥራለሁ።’”—ፊልጵስዩስ 3:8
ወንድም ጋንጋስ በሚያደርገው ነገር ሁሉ በእርግጥ ሕይወትን የሚወድ መሆኑን አሳይቷል፤ እንዲሁም በጉጉት “የክርስቶስ ኢየሱስን እውቀት” ለሌሎች አካፍሏል። አብሮን አለመሆኑ ይሰማናል፤ ቢሆንም አሁን ሰማያዊ ሽልማቱን በመቀበሉ ምን ያህል ደስተኞች ነን! አሁን ‘ከድካሙ ሁሉ ያርፋል፤ ሥራው ይከተለዋልና።’—ራእይ 14:13
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]