“አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም”
በታሪክ ዘመናት ሁሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ስሜትን በኃይል የሚያስጨንቁ ጊዜያትን አሳልፈዋል። ዛሬም የምንኖረው “በሚያስጨንቅ ዘመን” እንደመሆኑ መጠን ይህ ሁኔታ በይበልጥ ጎልቶ ይታያል! (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን የሚያስጨንቃቸውን ነገር ሁሉ በጸሎት በይሖዋ ላይ እንዲጥሉ መክሯቸዋል። ከምንስ ውጤት ጋር? “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።”—ፊልጵስዩስ 4:7
“የእግዚአብሔር ሰላም” ምንድን ነው? ከፈጣሪ ጋር የተቀራረበ ዝምድና በመመስረት የሚገኝ የተረጋጋ መንፈስ ነው። እንዲህ ዓይነቱ የቅርብ ግንኙነት ጭንቀታችን ምንም ያህል ቢሆን እንኳ ይሖዋ “ሕዝቡን አይጥልም፤ የእርሱ የሆኑትንም አይተዋቸውም” የሚል ትምክህት እንዲኖረን ያደርጋል።—መዝሙር 94:14 የ1980 ትርጉም
ይህ ማለት ደግሞ መከራ እንዳይደርስብን ክትባት ተከትበናል ማለት አይደለም “የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው” በማለት መዝሙራዊው ጽፏል። (መዝሙር 34:19) ነገር ግን የአምላክ ሰላም እፎይታን ሊያመጣልን ይችላል። እንዴት?
“አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ” የእግዚአብሔር ሰላም በማለት ጳውሎስ ጽፏል፤ ወይም የ1980 ትርጉም እንደሚለው “ከሰው ማስተዋል በላይ የሆነው” ብሏል። ኃይለኛ ጭንቀት አሳዛኝ የስሜት መቃወስ ሊያመጣብን ይችላል። (መክብብ 7:7) ይሁን እንጂ የአምላክ ሰላም ሊያረጋጋን ይችላል፤ በተለይም ደግሞ “ከወትሮው በላይ የሆነ ኃይል” በሚያስፈልገን ጊዜ።—2 ቆሮንቶስ 4:7 አዓት ፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:7
ከዚህ በላይ የአምላክ ሰላም ከለላ ነው። “ልባችሁንና አሳባችሁን ይጠብቃል” በማለት ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች እንደጻፈው ሊጠብቀን ይችላል። እዚህ ላይ “ይጠብቃል” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በመጠበቂያው ግንብ ላይ ቆሞ ሌሊትም ቀንም በጥንቃቄ የሚጠብቅን አንድ ዘብ በሕሊናችን የሚስል ወታደራዊ ቃል ነው። በተመሳሳይ መንገድም የአምላክ ሰላም 24 ሰዓት ሙሉ ልባችንንና የማሰብ ኃይላችንን በሚገባ የሚጠበቅ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 10:13፤ ከኤፌሶን 4:26 ጋር አወዳድር።
ዛሬ የሚያጋጥሙንን አስጨናቂ ችግሮች ስንመለከት ከአምላክ ለምናገኘው ሰላም አመስጋኝ መሆን አይገባንምን?—መዝሙር 18:2፤ ከዘጸአት 40:38 ጋር አወዳድር።