በቅርቡ ያበረታታኸው ሰው አለን?
ዶክተሮች ኢሌናን ከመረመሯት በኋላ የማኅፀን ካንሰር እንዳለባት ሲገነዘቡ ገና 17 ዓመቷ ነበር። ማሪ የተባለችው እናቷ ኢሌና ክፉኛ ስትሠቃይ ማየት የሚያስከትልባትን ጭንቀት መቋቋም ነበረባት።
በመጨረሻም ኢሌና በካናሪ ደሴቶች ውስጥ ከሚገኘው ቤቷ 1,900 ኪሎ ሜትር ርቆ በስፔይን ማድሪድ ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ ሆስፒታል ተዛወረች። በማድሪድ ውስጥ የሚገኝ አንድ የዶክተሮች ቡድን ያለ ደም የቀዶ ሕክምና ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር። (ሥራ 15:28, 29) ይሁን እንጂ የቀዶ ሕክምናው መካሄድ ከጀመረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የኢሌና ሁኔታ ከሞት እንደማትተርፍ በግልጽ የሚያሳይ ሆነ። ካንሰሩ በጠቅላላው ሰውነቷ ውስጥ ስለተሰራጨ የቀዶ ሕክምና ሐኪሞቹ ለችግሩ መፍትሔ ሊያመጡ አልቻሉም። ኢሌና ማድሪድ ከደረሰች ከስምንት ቀናት በኋላ አረፈች።
ማሪ ይህን አሳዛኝ መከራ ብቻዋን አልተጋፈጠችም። ሁለት ክርስቲያን ሽማግሌዎች በራሳቸው ወጪ ከእሷና ከትልቅ ልጅዋ ጋር ማድሪድ ድረስ ሄደው ነበር፤ ኢሌና እስከሞተችበት ጊዜ ድረስም እዚያው ቆይተዋል። “በውስጤ የተሰማኝን የተስፋ መቁረጥና የባዶነት ስሜት እንድቋቋም ረድተውኛል” ስትል ማሪ ገለጸች። “የሰጡኝን ማበረታቻ በፍጹም አልረሳውም። መንፈሳዊ ድጋፋቸውና ተግባራዊ እርዳታቸው ተመን የለውም። በእርግጥም ‘ከነፋስ መሸሸጊያ’ ነበሩ።”—ኢሳይያስ 32:1, 2
ይሖዋ እነዚህን የመሰሉ አፍቃሪ እረኞች በጎቹን በርኅራኄ ሲጠብቁ ይደሰታል። (ምሳሌ 19:17፤ 1 ጴጥሮስ 5:2–4) ይሁንና ማበረታቻ መስጠት ለሽማግሌዎች ብቻ የተሰጠ መብት አይደለም። ሁሉም ክርስቲያኖች መንፈሳዊ መመሪያ ለማግኘትና ‘እርስ በርስ ለመበረታታት’ አብረው ይሰበሰባሉ። (ዕብራውያን 10:24, 25 የ1980 ትርጉም) ማበረታቻ መስጠት የክርስቲያናዊ ኅብረት አስፈላጊ ክፍል ነው።
ማበረታታት ምንን ይጨምራል?
አንዲት ውብ አበባ ውኃ ስታጣ እንደምትጠወልግ ሁሉ በቤተሰብም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ማበረታቻ ሲያጡ ሊደክሙ ይችላሉ። በሌላ በኩል በተገቢው ጊዜ የተሰጠ ማበረታቻ ፈተና የደረሰባቸውን ሊያበረታ፣ የተጨነቁትን ሊያጽናናና ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉትን ኃይላቸውን ሊያድስ ይችላል።
“ማበረታቻ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አይዞህ ማለት፣ ማደፋፈርና ማጽናናት የሚሉትን ሐሳቦች ያቅፋል። ስለዚህ ማበረታታት አንድ ሰው ጥሩ እንደሠራ በመንገር ብቻ የተወሰነ አይደለም። ተግባራዊ እርዳታና መንፈሳዊ ድጋፍ መስጠትንም ሊጨምር ይችላል።
እርግጥ “ማበረታቻ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል፣ ቃል በቃል ሲተረጎም “ከጎኔ ሁን” ማለት ነው። ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ጎን ለጎን መሄዳችን ከእነሱ መካከል አንዱ ቢደክም ወይም ቢደናቀፍ ፈጣን ድጋፍ እንድንሰጥ ያስችለናል። (መክብብ 4:9, 10) ደስ የሚለው የይሖዋ ሕዝቦች “እጅ ለእጅ ተያይዘው ያገለግሉታል።” (ሶፎንያስ 3:9 አዓት) ሐዋርያው አንድን ክርስቲያን “በሥራዬ አብረህ የተጠመድህ” ሲል ጠርቶታል። (ፊልጵስዩስ 4:3) በአንድ ቀንበር ሥር እጅ ለእጅ ሆኖ መሥራት በተለይ በመንፈሳዊ ጠንካሮች ላልሆኑት ሸክሙን ቀላል ያደርግላቸዋል።—ከማቴዎስ 11:29 ጋር አወዳድር።
ማበረታቻ ሰጥተዋል
ማበረታቻ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ እስቲ ይህን በተመለከተ አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎችን እንመልከት። የአምላክ ነቢይ የነበረው ሙሴ ሊሞት አቅራቢያ ኢያሱ የእስራኤላውያን መሪ እንዲሆን ይሖዋ ሾመው። ይህ ሙሴ ራሱ እንደሚያውቀው ቀላል ሥራ አልነበረም። (ዘኁልቁ 11:14, 15) ስለሆነም ይሖዋ ‘ኢያሱን እንዲያዘው፣ እንዲያበረታታውና እንዲያጸናው’ ለሙሴ ነገረው።—ዘዳግም 3:28
በእስራኤል መሳፍንት ዘመን የዮፍታሔ ሴት ልጅ በይሖዋ መቅደስ ውስጥ ለማገልገል ስትል የራሷን ቤተሰብ መመሥረት የሚያስችላትን አጋጣሚ ትታ ከአባቷ ስእለት ጋር በፈቃደኝነት ተስማማች። የከፈለችው መሥዋዕትነት ሳይስተዋል ቀረን? አልቀረም፤ ምክንያቱም መሳፍንት 11:40 ይላል፦ “የእስራኤልም ሴቶች ልጆች በዓመት በዓመቱ እየሄዱ የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በዓመት አራት ቀን ሙሾ እንዲያወጡ [“እንዲያመሰግኑ” አዓት] በእስራኤል ዘንድ ልማድ ሆነ።” እንዲህ ዓይነቱ ጥየቃ የራሷን ጥቅም የሠዋችውን የዮፍታሔን ሴት ልጅ አበረታቶ መሆን አለበት።
ማበረታቻ መስጠት አንዳንድ ጊዜ ድፍረትን ይጠይቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ የመጀመሪያ ሚስዮናዊ ጉዞውን ባደረገበት ወቅት በትንሿ እስያ በሚገኙ አንዳንድ ከተማዎች ውስጥ ኃይለኛ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። ከአንጾኪያ ተባርሯል፤ በኢቆንዮን ከተደረገበት የግድያ ሙከራ ለጥቂት ተርፏል፤ እንዲሁም በልስጥራን በድንጋይ ከወገሩት በኋላ የሞተ መስሏቸው ትተውት ሄደዋል። ይሁን እንጂ ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጳውሎስና ጓደኞቹ ወደነዚህ ከተማዎች ተመልሰው ‘በእምነታቸው እንዲጸኑ በማበረታታትና በመምከር “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ብዙ መከራ መቀበል አለብን”’ አሏቸው። (ሥራ 14:21, 22 የ1980 ትርጉም) ጳውሎስ እነዚህን አዲስ ደቀ መዛሙርት ለማበረታታት ሲል ሕይወቱን አደጋ ላይ ለመጣል ዝግጁ ነበር።
ሆኖም ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸው ክርስቲያኖች አዲስ ደቀ መዛሙርት የሆኑት ብቻ አይደሉም። ከብዙ ዓመታት በኋላ ጳውሎስ ለፍርድ ወደሚቀርብበት ወደ ሮም ሲሄድ አስቸጋሪ ጉዞ አጋጥሞት ነበር። ወደሚሄድበት ቦታ በቀረበ መጠን በሆነ መንገድ ተስፋ ሊቆርጥ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ከሮም በስተ ደቡብ ምሥራቅ 74 ኪሎ ሜትር የሚርቅ ቦታ ላይ ሲደርስ ተበረታታ። ለምን? ምክንያቱም ከሮም የመጡ ክርስቲያኖች አፍዩስ ፋሩስና ሦስት ማደሪያ እስከሚባለው የገበያ ስፍራ ድረስ መጥተው ስለተቀበሉት ነው። “ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ ልቡም ተጽናና።” (ሥራ 28:15) ይህን በመሰሉ አጋጣሚዎች የእኛ መኖር ብቻ የእምነት ጓደኞቻችንን ሊያበረታታቸው ይችላል።
ማበረታቻ ለመስጠት የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች ተጠቀምባቸው
ማበረታቻ የምንሰጥባቸው አጋጣሚዎች በእርግጥም ብዙ ናቸው። አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ባቀረቡት ጥሩ የተማሪ ንግግር ልብህ ተነክቷልን? በጉባኤው ውስጥ በመንፈሳዊ የበረቱ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በመኖራቸው ተደስተሃልን? የአረጋውያን ጽናት አድናቆት ያሳድርብሃልን? ከአቅኚዎች አንዱ ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል ጥቅሶችን የሚጠቀምበት መንገድ አስደንቆህ ነበርን? እንዲህ ከሆነ ምስጋና አቅርብና አንድ የሚያበረታታ ነገር ተናገር።
ማበረታቻ በቤተሰብም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ወላጆች ልጆቻቸውን ‘በጌታ ምክርና ተግሣጽ እንዲያሳድጉ’ ይረዳቸዋል። (ኤፌሶን 6:4) አንድን ልጅ ጥሩ ሠርተሃል ማለትና ጥሩ የሠራበትን ምክንያት መግለጽ በጣም ሊያበረታታው ይችላል። ወጣቶች ብዙ ፈተናና ግፊቶች በሚያጋጥሟቸው በአሥራዎቹ ዕድሜአቸው ወቅት የማያቋርጥ ማበረታቻ በጣም አስፈላጊ ነው።
በልጅነት ወቅት ማበረታቻ አለማግኘት በጣም ሊጎዳ ይችላል። ዛሬ ማይክል ተግባቢ ክርስቲያን ሽማግሌ ቢሆንም እንዲህ አለ፦ “አባቴ አንዴም ጥሩ ሠርተሃል ብሎኝ አያውቅም ነበር። ስለዚህ በራስ የመተማመን መንፈስ ሳይኖረኝ አደግኩ። . . . 50 ዓመት ቢሞላኝም ጓደኞቼ ሽማግሌ ሆኜ ጥሩ ሥራ እየሠራሁ እንዳለ በመንገር ሲያበረታቱኝ ደስ ይለኛል። . . . የራሴ ተሞክሮ ለሌሎች ማበረታቻ መስጠት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ስላስተማረኝ ይህን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አደርጋለሁ።”
ማበረታቻ የሚያስፈልገው ማን ነው?
ተግተው የሚሠሩ ሽማግሌዎች ማበረታቻ ሊሰጣቸው ይገባል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “ወንድሞቸ ሆይ፣ በመካከላችሁ የሚደክሙትን በጌታም የሚገዙአችሁን የሚገሥጹአችሁንም ታውቁ ዘንድ፣ ስለ ሥራቸውም በፍቅር ከመጠን ይልቅ ታከብሩአቸው [“ታስቡላቸው” አዓት] ዘንድ እንለምናችኋለን።” (1 ተሰሎንቄ 5:12, 13) ሽማግሌዎች ለሚሠሩት ሥራ አድናቆት ሳይገልጹ ከጥቅሙ መጋራት ቀላል ነው። ይሁን እንጂ ልባዊ የአድናቆትና የማበረታቻ ቃል ሸክማቸውን ሊያቀልላቸው ይችላል።
በመካከላችን ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ጸንተው የተቋቋሙ ሰዎችም ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይመክራል። (1 ተሰሎንቄ 5:14 አዓት) ነጠላ ወላጆች፣ መበለቶች፣ አረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች አንዳንዴ ጭንቀት ከሚሰማቸውና በመንፈሳዊ ከሚደክሙት መካከል ይገኙበታል።
ማሪያ የምትባል አንዲት ክርስቲያን ባሏ በድንገት ጥሏት ሄደ። “ልክ እንደ ኢዮብ ሞትን የምመኝበት ጊዜ ነበር። [ኢዮብ 14:13] ሆኖም ማበረታቻ አግኝቼ ስለነበር ተስፋ አልቆረጥኩም። በደንብ የማውቃቸው ሁለት ሽማግሌዎች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መቀጠል ያለውን ጥቅም እንድገነዘብ በመርዳት ብዙ ሰዓት አሳለፉ። ከዚህም ሌላ የሰው ችግር የሚገባቸው ሁለት እህቶች የልቤን ሳካፍላቸው በትዕግሥት በማድመጥ አጽናኑኝ። በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመው ነገሮችን ከይሖዋ አመለካከት አንፃር እንዳያቸው አስቻሉኝ። መዝሙር 55:22ን ምን ያህል ጊዜ ደጋግመን እንዳነበብነው ባላውቅም ይህን ምክር በሥራ ላይ በማዋል ቀስ በቀስ መንፈሳዊና ስሜታዊ ሚዛኔን መልሼ እንዳገኘሁ አውቃለሁ። ይህ ሁሉ የሆነው ከ12 ዓመት በፊት ሲሆን እስከ አሁን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንደቀጠልኩ ስናገር በጣም ደስ ይለኛል። አልፎ አልፎ የስሜት ሥቃይ ቢከሰትብኝም ሕይወቴ የሚያረካና የሚያስደስት ነው። እንዲህ ባለው ጊዜ ማበረታቻ ማግኘት በአንድ ግለሰብ ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ አምናለሁ።”
አንዳንዶች ከዚህ በፊት ስሕተት ሠርተው አሁን ይህን ስሕተት ለማስተካከል እየታገሉ ስላሉ ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ምናልባት ፍቅራዊ ወቀሳ ተሰጥቷቸው ይሆናል። (ምሳሌ 27:6) የወቀሷቸው ሽማግሌዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ውሎ ሲያዩ ለማመስገን ንቁ ሊሆኑ ይችላሉ። የማበረታቻ ቃሎቻቸው እጥፍ ጠቀሜታ አላቸው፤ ይኸውም የተሳሳተው ሰው “ከልክ በሚበዛ በኀዘን እንዳይዋጥ” ለእሱ ያላቸውን ፍቅር ያረጋግጣሉ፤ እንዲሁም ምክሩን በሥራ ላይ ማዋል የሚያስገኘውን ጥቅም ያሳስቡታል።—2 ቆሮንቶስ 2:7, 8
አንድ ሽማግሌ ከባድ ስህተት ሠራና ጉባኤውን የመጠበቅ መብቱን አጣ። “ከሽማግሌነት እንደወረድኩ ማስታወቂያ ሲነገር የእኔ ከእነሱ ጋር መሆን ወንድሞችን አያስደስታቸውም ብዬ አስቤ ነበር” ይላል። “ሆኖም ሽማግሌዎች ጉዳዩን በምሥጢር ይዘው እኔን ለማበረታት ከፍተኛ ጥረት አደረጉ። የተቀሩትም የጉባኤው አባላት ፍቅርንና ወዳጅነትን አልነፈጉኝም፤ ይህም የፊተኛውን መንፈሳዊ አቋሜን መልሼ እንዳገኝ እንደረዳኝ ግልጽ ነው።”
የምታበረታታ ሁን
በዚህ ሩጫ በበዛበት ሕይወታችን ማበረታቻ መስጠት በቀላሉ ቸል ሊባል ይችላል። ሆኖም ማበረታታት ምንኛ ጠቃሚ ነው! ውጤታማ ማበረታቻ ለመስጠት ሁለት ነገሮችን በአእምሮህ መያዝ አለብህ። አንደኛ ማበረታቻህ ግልጽ እንዲሆን ስለምትናገረው ነገር አስብ። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ምስጋና ወይም ማበረታቻ ሊሰጠው የሚገባውን ሰው ቀርበህ ለማነጋገር የሚያስችሉህን አጋጣሚዎችን ፈልግ።
ይህን ባደረግህ መጠን ይበልጥ ደስተኛ ትሆናለህ። እንዲያውም ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ደስተኛ ነው” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ሥራ 20:35 አዓት) ሌሎችን በማበረታት ራስህንም ታበረታታለህ። በየቀኑ አንድን ሰው ለማበረታታት ለምን ግብ አታወጣም?