የፈጠራ ችሎታ—የአምላክ የደግነት ስጦታ ነው
ይሖዋ በፈጠራ ሥራዎቹ ደስተኛ ነው። (መዝሙር 104:31) በፈጠራ ሥራ የሚያገኘው ከፍተኛ እርካታ በዘፍጥረት 1:31 ላይ እንዲህ ተብሎ ተገልጿል፦ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፣ እነሆም እጅግ መልካም ነበር።”
ይሖዋ ይህ ደስታ ለእሱ ብቻ እንዲሆን አላደረገም። ሌሎች ነገሮች ሁሉ በኢየሱስ አማካኝነት እንዲፈጠሩ በማድረግ የወኪልነትን ወይም እንደ መሣሪያ ሆኖ የማገልገልን መብት ሰጥቶታል። (ዮሐንስ 1:3፤ ቆላስይስ 1:16, 17) “ዋና ሠራተኛ” እንደመሆኑ መጠን ኢየሱስ ‘በይሖዋ ፊት ሁልጊዜ ደስተኛ ነበር።’—ምሳሌ 8:30, 31
ነገር ግን የፈጠራ ችሎታ በሰማይ ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ዩጄን ራውድሴፕ ሀው ክሪኤቲቭ አር ዩ? (የፈጠራ ችሎታህ ምን ያህል ነው?) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “የፈጠራ ችሎታ ከሰው ዘር ጋር አብሮ የተፈጠረ ነው” በማለት ጽፈዋል። ይህም ሰው በአምላክ መልክ ስለ ተፈጠረ የተገኘ እንጂ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም። (ዘፍጥረት 1:26) በዚህ መንገድ ይሖዋ ለሰው ዘር የሚያረካ የፈጠራ ችሎታን ለግሶታል።—ያዕቆብ 1:17
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ መዝፈን፣ መጨፈር፣ ሽመና፣ ምግብ ማብሰል፣ ስለ እጅ ጥበብና ስለ ሌሎችም በጥረት ሊገኙ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎች በአድናቆት መናገሩ የሚያስደንቅ አይደለም። (ዘጸአት 35:25, 26፤ 1 ሳሙኤል 8:13፤ 18:6, 7፤ 2 ዜና መዋዕል 2:13, 14) የእጅ ጥበብ አዋቂው ባስልኤል “በጥበብ ሥራ” ያለውን ችሎታ የመገናኛውን ድንኳን ሥራ ለማገዝ ተጠቅሞበታል። (ዘጸአት 31:3, 4) በግ ጠባቂው ያባል የድንኳንን ሥራ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘው እሱ ነው ለማለት ይቻላል፤ ይህም ለዘላንነት ኑሮ የሚመች በጥረት የተገኘ የፈጠራ ሥራ ነው። (ዘፍጥረት 4:20) ዳዊት ሙዚቀኛና የሙዚቃ ደራሲ ብቻ አልበረም፤ ከዚህ ይልቅ አዳዲስ የሙዚቃ መሣሪያዎችንም ይፈለስፍ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 7:6፤ መዝሙር 7:17፤ አሞጽ 6:5) ማርያምም እስራኤላውያን በተአምራዊ ሁኔታ ከቀይ ባሕር በዳኑ ጊዜ የነበረውን የደስታ ዘፈንና ጭፈራ አቀነባብራ ሊሆን ይችላል።—ዘጸአት 15:20
የፈጠራ ችሎታ ንጹህ አምልኮን በማስፋፋት ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ኢየሱስ መልእክቱን ለማያያዝ ምሳሌዎችንና በሚታይ ነገር ትምህርት የመስጫ መንገዶችን ከራሱ በማፍለቅ ያስተምር ነበር። በተመሳሳይም ተከታዮቹ “በመስበክና በማስተማር የሚደክሙ” እንዲሆኑ ተመክረዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:17) አዎን፣ የስብከት ሥራቸው እንዲሁ በልምድ የሚደረግ አይደለም። የማስተማር ዘዴዎች መፍጠርን የሚጠይቅ ጥበብ ነው። (ቆላስይስ 4:6) ይህ ጥበብ በተለይ አንድ ሰው ልጁን በሚያስተምርበት ጊዜ የግድ አስፈላጊ ነው።—ዘዳግም 6:6, 7፤ ኤፌሶን 6:4
በዚህ መንገድ ይሖዋ መፍጠር ለሱ የሚሰጠውን ደስታ ለሌሎችም አካፍሏል። እንዴት ያለ የደግነት ስጦታ ነው!