የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 2/1 ገጽ 31
  • የአንባብያን ጥያቄዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአንባብያን ጥያቄዎች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 2/1 ገጽ 31

የአንባብያን ጥያቄዎች

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት ፍልስጤማውያን እነማን ነበሩ?

መጽሐፍ ቅዱስ የጥንት የአምላክ ሕዝቦች የተስፋይቱን ምድር ሲወርሱ በከንዓን ይኖሩ የነበሩትን ፍልስጤማውያን በመባል ይጠሩ የነበሩ ሕዝቦች በተደጋጋሚ ይጠቅሳል። ዳዊት ከግዙፉ ፍልስጤማዊ ጀግና ጋር እንደተጋጠመ በተዘገበው ታሪክ ላይ እንደጎላው እነዚህ የጥንት ፍልስጤማውያን የአምላክን ሕዝቦች ለረጅም ጊዜ ተቃውመዋል።—1 ሳሙኤል 17:1–3, 23–53

መጽሐፍ ቅዱስ የጥንት ፍልስጤማውያን ከከፍቶር ተነሥተው ወደ ደቡብ ምዕራባዊው የከንዓን ጠረፍ እንደፈለሱ ይጠቁማል። (ኤርምያስ 47:4) ከፍቶር የት ነበረች? ዘ ኢንተርናሽናል ስታንደርድ ኢንሳይክሎፔድያ (1979) እንዲህ በማለት አስተያየቱን ይሰጣል፦ “ምንም እንኳ ቁርጥ ያለ መልስ ለመስጠት የሚያስችል መረጃ ባይኖርም በአሁኑ ወቅት ያለው እውቀት ከፍቶር የክሬት (የቀርጤስ) ደሴት (ወይም ከክሬት ጋር ያለት የኤጂያን ደሴቶች ጭምር) የሚገኙበት ቦታ እንደነበር ይጠቁማል።”—ጥራዝ 1፣ ገጽ 610

ከዚህ ጋር በመስማማት አዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም አሞጽ 9:7 ላይ እንዲህ ይነበባል፦ “የእስራኤል ልጆች ሆይ፣ ‘እናንተ ለእኔ እንደ ኩሽ ልጆች አይደላችሁምን?’ ይላል ይሖዋ። ‘እስራኤልን ከግብፅ ምድር፣ ፍልስጥኤማውያንንም ከክሬት፣ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን?’”

እነዚህ በባሕር አካባቢ ይኖሩ የነበሩ የጥንት ሕዝቦች ከክሬት ተነሥተው በኢዮጴና በጋዛ መካከል ወደሚገኘው ደቡባዊ ጠረፍ ማለትም ፍልስጤም ወደ ተባለው የከንዓን ምድር መቼ እንደፈለሱ አይታወቅም። በአብርሃምና በይስሐቅ ዘመን በዚህ ዝቅተኛ ሜዳዎች ባሉበት የጠረፍ ክልል የነበሩ ይመስላል።—ዘፍጥረት 20:1, 2፤ 21:32–34፤ 26:1–18

እስራኤላውያን አምላክ ቃል የገባላቸውን ምድር ከወረሱ በኋላም ፍልስጤማውያን ለረጅም ጊዜ በክልሉ ላይ ኃይለኛ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ቀጥለው ነበር። (ዘጸአት 13:17፤ ኢያሱ 13:2፤ መሳፍንት 1:18, 19፤ 3:3, 4፤ 15:9, 10፤ 1 ሳሙኤል 4:1–11፤ 7:7–14፤ 13:19–23፤ 1 ነገሥት 16:15) ፍልስጤማውያን እስከ ይሁዳ ንጉሥ ዖዝያን የግዛት ዘመን ድረስ ከጌት፣ ከየብና እና ከያሽዶድ ከተሞቻቸው አልወጡም ነበር። (2 ዜና መዋዕል 26:6 የ1980 ትርጉም) በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ዘገባዎች ውስጥ ጎላ ብሎ የተጠቀሱት ሌሎች ከተሞቻቸው ኢክሮን፣ አስቀሎና እና ጋዛ ነበሩ።

ታላቁ እስክንድር ጋዛ የተባለችውን የፍልስጤም ከተማ ያዘ፤ ከጊዜ በኋላ ግን የፍልስጤማውያን ልዩ ሕዝብ መሆን ያከተመለት ይመስላል። ፕሮፌሰር ሎውሬንስ ስቴጀር ቢቢሊካል አርክዎለጂ ሪቪው (ግንቦት/ሰኔ 1991) በተባለ መጽሔት ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ፍልስጤማውያንም ወደ ባቢሎን በምርኮ ተወስደው ነበር። . . . ይሁንና በምርኮ የተወሰዱት ፍልስጤማውያን ምን እንደደረሰባቸው የሚያሳይ ምንም መረጃ የለም። ከናቡከደነፆር ድል በኋላ ምናልባት በአስቀሎና የቀሩት ፍልስጤማውያን በብሔር ደረጃ የሚያሳውቃቸውን ባሕርይ ያጡ ይመስላል። ከታሪክ ገጾች ጠፉ።”

ፓለስቲና የሚለው ዘመናዊ ቃል ከላቲንና ከግሪክኛ ቃላት የመጣ ሲሆን “ፍልስቲያ” ወደሚለው የጥንት የዕብራይስጥ ቃል ይወስዳል። አንዳንድ የአረብኛ ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ፍልስጤማውያን” ለሚለው ቃል የሚጠቀሙበት ቃል ዘመናዊ ፓለስቲናውያን ከሚጠሩበት ቃል ጋር በቀላሉ የሚምታታ ቃል ነው። ሆኖም ቱዴይስ አረቢክ ቨርሽን የተለየ አረብኛ ቃል በመጠቀም በጥንት ፍልስጤማውያንና በዘመናዊ ፓለስቲናውያን መካከል ያለውን ልዩነት ያስቀምጣል።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ የአስቀሎና ፍርስራሾች

[ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ