የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 2/15 ገጽ 8-12
  • ጻድቃን ከሞት ይነሣሉ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጻድቃን ከሞት ይነሣሉ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በግ መሰል ሰዎችን ማሰባሰብ
  • የትንሣኤ ተስፋ
  • ‘ጻድቃን ሆነው የተቆጠሩ’ አማኞች
  • ምድራዊው ትንሣኤ
  • የሚያጽናና ተስፋ
  • ትንሣኤ—በአንተ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ትምህርት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • የትንሣኤ ተስፋ የሚሰጠው ብርታት
    እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ
  • የትንሣኤ ተስፋ ኃይል አለው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • የትንሣኤ ተስፋ—ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 2/15 ገጽ 8-12

ጻድቃን ከሞት ይነሣሉ

“ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ . . .ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ።”—ሥራ 24:15

1. አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩበት ጊዜ ጀምሮ በሰው ዘር ሁሉ ላይ ምን ሁኔታ ነግሦ ቆይቷል?

“አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ።” (መክብብ 9:10) ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን በእነዚህ ምርጥ የሆኑ ጥቂት ቃላት የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩበት ጊዜ ጀምሮ በሁሉም የሰው ልጆች ላይ ነግሦ የቆየውን ሁኔታ ገልጿል። ሞት ማንንም ሳይመርጥ፣ ሀብታሙንም ሆነ ድሃውን፣ ንጉሡንም ሆነ ተራውን ሰው፣ ታማኙንም ሆነ ከሐዲውን ሲያግበሰብስ ቆይቷል። እውነትም ሞት ‘ነግሦአል።’—ሮሜ 5:17

2. በዚህ የመጨረሻ ዘመን አንዳንድ ታማኝነታቸውን የጠበቁ ሰዎች የተከዙት ለምን ሊሆን ይችላል?

2 በሕክምና ሳይንስ ረገድ ትልቅ እድገት ቢገኝም በዛሬው ጊዜም እንኳ ሞት በሰው ልጆች ላይ መንገሡ አልቀረም። ይህ አዲስ ነገር ባይሆንም አንዳንዶች በመጨረሻ ከዚህ የረጅም ዘመን ጠላት ጋር ፊት ለፊት ሲፋጠጡ ያልጠበቁት ነገር በመሆኑ ተክዘዋል። ለምን እንዲህ ሆነ? በ1920ዎቹ ዓመታት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር “በአሁኑ ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሞትን ፈጽሞ አያዩም” የሚል መልእክት ያውጅ ነበር። እነዚህ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እነማን ናቸው? ኢየሱስ ስለ በጎችና ፍየሎች በሰጠው መግለጫ ላይ የተጠቀሱት “በጎች” ናቸው። (ማቴዎስ 25:31–46) እነዚህ በግ መሰል ሰዎች በፍጻሜው ዘመን ብቅ እንደሚሉ ተተንብዮ ነበር፤ ተስፋቸውም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ነው። ጊዜው እየገፋ በሄደ መጠን የአምላክ ሕዝቦች እነዚህ “በጎች” በይሖዋ ዓላማዎች ውስጥ ስላላቸው ቦታ የተሻለ ግንዛቤ አግኝተዋል። እነዚህ ታዛዦች ከትዕቢተኞቹ “ፍየሎች” እንደሚለዩና ፍየሎቹ ከጠፉ በኋላ በጎቹ የተዘጋጀላቸውን የመንግሥቲቱን ምድራዊ ግዛት እንደሚወርሱ መገንዘብ ተችሎ ነበር።

በግ መሰል ሰዎችን ማሰባሰብ

3. ከ1935 ጀምሮ የይሖዋ ሕዝቦች ያተኮሩት በምን ሥራ ላይ ነው?

3 ከ1935 ጀምሮ ‘ታማኙ ባሪያ’ ያተኮረው እነዚህን በግ መሰል ሰዎች ወደ ይሖዋ ድርጅት እንዲሰባሰቡ በማድረጉ ሥራ ላይ ነው። (ማቴዎስ 24:45፤ ዮሐንስ 10:16) እነዚህ ለመማር ፈቃደኛ የሆኑ ክርስቲያኖች ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ በይሖዋ ሰማያዊ መንግሥት ላይ እየገዛ እንዳለና ይህ ክፉ ሥርዓት የሚጠፋበትና ጽድቅ የሚኖርበት አዲስ ዓለም የሚጀምርበት ጊዜ በጣም እንደቀረበ ተገንዝበዋል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 12:10) በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ “ሞትን ለዘላለም ይውጣል” የሚሉት አጽናኝ የኢሳይያስ ቃላት ፍጻሜአቸውን ያገኛሉ።—ኢሳይያስ 25:8

4. ምንም እንኳን የይሖዋ ሉዓላዊነት በአርማጌዶን ሲረጋገጥ ለመመልከት በጉጉት ቢጠባበቁም የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት ብዙዎች ምን ደርሶባቸዋል?

4 የሰይጣን ዓለም የሚጠፋበት ጊዜ በጣም በመቅረቡ ምክንያት በግ መሰል ክርስቲያኖች የይሖዋ ሉዓላዊነት በታላቂቱ ባቢሎንና በተቀረው የሰይጣን ዓለም ላይ በሚወርደው በመጪው ታላቅ መከራ ወቅት እስከሚረጋገጥበት ጊዜ ድረስ በመኖር እጅግ ይደሰታሉ። (ራእይ 19:1–3, 19–21) ብዙዎቹ ግን ይህን ለማየት አልቻሉም። ሞትን ፈጽሞ ከማያዩት “በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች” መካከል ለመሆን ተስፋ ያደርጉ የነበሩ ብዙ ሰዎች ሞተዋል። አንዳንዶቹ ለእውነት ሲሉ በእስር ቤቶችና በማጎሪያ ካምፖች ወይም በሃይማኖታዊ አክራሪዎች እጅ በሰማዕትነት ሞተዋል። ሌሎች ደግሞ በአደጋ ምክንያት ወይም የተፈጥሮ ምክንያቶች ናቸው በሚባሉት በእርጅናና በበሽታ ሞተዋል። (መዝሙር 90:9, 10፤ መክብብ 9:11) ወደፊትም ቢሆን መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የሚሞቱ እንደሚኖሩ ግልጽ ነው። ታዲያ እነዚህ በግ መሰል ሰዎች ጽድቅ ስለሚኖርባት አዲስ ዓለም የተሰጠው ተስፋ ሲፈጸም ለማየት የሚችሉት እንዴት ነው?

የትንሣኤ ተስፋ

5, 6. ከአርማጌዶን በፊት የሚሞቱ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ምን ዓይነት የወደፊት ጊዜ ይጠብቃቸዋል?

5 ሐዋርያው ጳውሎስ በሮማዊው ገዥ በፊልክስ ፊት ቆሞ በተናገረው ቃል መልሱን ሰጥቶናል። ጳውሎስ በሥራ 24:15 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ . . . ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ” በማለት በድፍረት ተናግሯል። የትንሣኤ ተስፋ በጣም ከባድ የሆነውን መከራ እንኳን ለመቋቋም የሚያስችል ድፍረት ይሰጠናል። የታመሙና እሞታለሁ ብለው የሚሰጉ ውድ ወዳጆቻችን ይህ ተስፋ ስላላቸው ከመጠን በላይ ተስፋ አይቆርጡም። ምንም ይምጣ ምን የታማኝነታቸውን ዋጋ ማግኘታቸው እንደማይቀር ያውቃሉ። በአሳዳጆች እጅ እስከ መገደል የሚደርሱት ታማኝ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የትንሣኤ ተስፋ በመኖሩ አሳዳጆቻቸው ሊያሸንፏቸው የሚችሉበት ምንም ዓይነት መንገድ እንደሌለ ያውቃሉ። (ማቴዎስ 10:28) በጉባኤያችን ውስጥ አንድ ሰው ሲሞት ይህን ሰው በማጣታችን እናዝናለን። ያም ሆኖ ግን እሱ ወይም እርሷ የሌሎች በጎች ክፍል ከሆኑ እነዚህ የእምነት ባልደረቦቻችን እስከ መጨረሻው ታማኝነታቸውን ጠብቀው በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የመኖር ተስፋቸው ተረጋግጦላቸው በማንቀላፋታቸው እንደሰታለን።—1 ተሰሎንቄ 4:13

6 አዎን፣ የትንሣኤ ተስፋ የእምነታችን አንዱ ትልቅ ክፍል ነው። ይሁን እንጂ በትንሣኤ ላይ ያለን እምነት ይህን ያህል ጠንካራ የሆነው ለምንድን ነው? ከዚህ ተስፋ የሚካፈሉትስ እነማን ናቸው?

7. ትንሣኤ ምንድን ነው? እርግጠኛነቱን የሚገልጹ አንዳንድ ጥቅሶችስ የትኞቹ ናቸው?

7 ትንሣኤ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አናስታሲስ ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎም “መነሣት” ማለት ነው። መሠረታዊ ትርጉሙ የሚያመለክተው ከሙታን መነሣትን ነው። የሚገርመው ነገር “ትንሣኤ” የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አይገኝም፤ ይሁን እንጂ የትንሣኤ ተስፋ በዚህ የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል ውስጥ በግልጽ ተቀምጧል። ለምሳሌ ያህል ኢዮብ በመከራ ላይ በነበረበት ጊዜ በተናገረው ቃል ላይ ተገልጾ እናገኘዋለን፦ “በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ! . . . ቀጠሮም አድርገህ ምነው ባሰብኸኝ ኖሮ!” (ኢዮብ 14:13) በተመሳሳይም በሆሴዕ 13:14 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “ከሲኦል እጅ እታደጋቸዋለሁ፣ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤ ሞት ሆይ፣ ቸነፈርህ ወዴት አለ? ሲኦል ሆይ፣ ማጥፋትህ ወዴት አለ?” ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 15:55 ላይ እነዚህን ቃላት በመጥቀስ ሞት ድል እንደሚነሳ የተተነበየው ትንቢት በትንሣኤ አማካኝነት እንደሚፈጸም አመልክቷል። (እርግጥ ጳውሎስ በዚህ ጥቅስ ላይ እየተናገረ የነበረው ስለ ሰማያዊ ትንሣኤ ነው።)

‘ጻድቃን ሆነው የተቆጠሩ’ አማኞች

8, 9. (ሀ) ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች በጻድቃን ትንሣኤ እንዴት ሊካፈሉ ይችላሉ? (ለ) በሞት በማይቀጨው ሕይወት ላይ ያለን ተስፋ በምን ላይ የተመሠረተ ነው?

8 አንቀጽ 5 ላይ በተጠቀሰው ጳውሎስ ለፊልክስ በተናገረው ቃል ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሡ ተናግሯል። ከሞት የሚነሡት ጻድቃን እነማን ናቸው? እንደሚታወቀው በተፈጥሮው ጻድቅ የሆነ አንድም ሰው የለም። ሁላችንም ከልደታችን ጀምረን ኃጢአተኞች ነን፤ እንዲሁም በሕይወት ዘመናችን በሙሉ ኃጢአት እንሠራለን። ይህም በሁለት ነገሮች የተነሣ ሞት የሚገባን እንድንሆን ያደርገናል። (ሮሜ 5:12፤ 6:23) ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም “ጻድቅ ሆኖ መቆጠር” የሚል አነጋገር እናገኛለን። (ሮሜ 3:28) ይህ ሐረግ የሚያመለክተው ፍጽምና የጎደላቸው ቢሆኑም ይሖዋ ኃጢአታቸውን ይቅር ያለላቸውን ሰዎች ነው።

9 ይህ ሐረግ በይበልጥ የተሠራበት ሰማያዊ ተስፋ ያላቸውን ቅቡዓን ክርስቲያኖች በተመለከተ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 5:1 ላይ “እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን [“ጻድቅ ሆነን ከተቆጠርን” “አዓት”] በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ” ብሏል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ በእምነት የተነሣ ጻድቅ ሆነው ተቆጥረዋል። ጻድቅ ሆነው የተቆጠሩት በምን ስላመኑ ነው? ጳውሎስ በሮሜ መጽሐፍ ውስጥ ሰፋ አድርጎ እንደገለጸው በኢየሱስ ክርስቶስ ስላመኑ ነው። (ሮሜ 10:4, 9, 10) ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ ከሞተና ከተነሣ በኋላ ሰብዓዊ ሕይወቱ ያስገኘልንን ዋጋ ለማቅረብ ወደ ሰማይ አርጓል። (ዕብራውያን 7:26, 27፤ 9:11, 12) ይሖዋ ይህን መሥዋዕት ሲቀበል ኢየሱስ የሰውን ዘር ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ገዝቶታል። በዚህ ዝግጅት የሚያምኑ ከዝግጅቱ በእጅጉ ይጠቀማሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:45) በዝግጅቱ አማካኝነት ታማኝ የሆኑ ወንዶችና ሴቶች ጨካኝ ጠላት በሆነው በሞት የማይቀጭ ሕይወት የመውረስ ተስፋ አግኝተዋል።—ዮሐንስ 3:16

10, 11. (ሀ) ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ትንሣኤ ይጠብቃቸዋል? (ለ) በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ አምላኪዎች ምን ዓይነት ትንሣኤን ተስፋ ያደርጉ ነበር?

10 የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ምስጋና ይግባውና ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጻድቅ ሆነው በመቆጠር እንደ ኢየሱስ የማይሞቱ መንፈሳዊ ፍጥረቶች ሆነው ከሞት የመነሣት የተረጋገጠ ተስፋ አግኝተዋል። (ራእይ 2:10) እነርሱ የሚያገኙት ትንሣኤ በራእይ 20:6 ላይ እንደሚከተለው ተገልጿል፦ “በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፣ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።” ይህ ሰማያዊ ትንሣኤ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ትንሣኤ “ፊተኛው ትንሣኤ” ብሎ እንደጠራው ልብ በሉ። ይህም ሌሎች ብዙ ሰዎች እንደሚነሱ ያመለክታል።

11 ጳውሎስ በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ በይሖዋ አምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ያሳዩ በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ ብዙ የአምላክ አገልጋዮችን ዘርዝሯል። እነዚህም በትንሣኤ ያምኑ ነበር። ጳውሎስ በዚህ ምዕራፍ በቁጥር 35 ላይ እንደሚከተለው በማለት በእስራኤላውያን ዘመን ተፈጽመው ስለነበሩ ተአምራዊ ትንሣኤዎች ገልጿል፦ “ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ።” እነዚህ የጥንት ታማኝ ምሥክሮች ኤልያስንና ኤልሣዕን የመሰሉ ሰዎች ከፈጸሟቸው ትንሣኤዎች የበለጠ ትንሣኤ እንደሚያገኙ ተስፋ ሊያደርጉ ይችሉ ነበር። (1 ነገሥት 17:17–22፤ 2 ነገሥት 4:32–37፤ 13:20, 21) ተስፋቸው ከሙታን ተነሥተው የአምላክ አገልጋዮች በእምነታቸው ምክንያት መከራ በማይቀበሉበት ዓለም፣ ሴቶች የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት በማያጡበት ዓለም ለመኖር ነበር። አዎን፣ እኛም ለመኖር ተስፋ በምናደርግበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ተስፋ ያደርጉ ነበር። (ኢሳይያስ 65:17–25) ይሖዋ ስለዚህ አዲስ ዓለም ለእኛ የገለጸውን ያህል አልገለጸላቸውም ነበር። ያም ሆኖ ግን ይህ ዓለም እንደሚመጣ ያውቁ ነበር፤ በዚያም ለመኖር ይፈልጉ ነበር።

ምድራዊው ትንሣኤ

12. በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ ታማኝነታቸውን የጠበቁ ሰዎች ጻድቃን ሆነው ተቆጥረዋልን? አብራራ።

12 እነዚህ በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚያገኙት ትንሣኤ ጻድቃን የሚያገኙት ትንሣኤ ክፍል ነው ብለን ማሰብ ይኖርብናልን? አዎን፣ ማስረጃው እንደሚያመለክተው እንደዚያ ብለን ማሰብ ይኖርብናል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ሰዎች ጻድቃን ብሎ ይጠራቸዋል። ለምሳሌ ያህል ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ በጥንት ዘመን ጻድቃን ሆነው የተቆጠሩ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ጠቅሷል። ሰውዬው የዕብራውያን አባት የሆነው አብርሃም ነው። ስለ አብርሃም እንዲህ እናነባለን፦ “አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ፣ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት . . . የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ።” ሴቲቱ ደግሞ በይሖዋ ላይ እምነት ያሳየችውና እስራኤላዊት ያልሆነችው ረዓብ ነች። እሷም ‘ጻድቅ ሆና ተቆጥራለች፤’ እንዲሁም የዕብራውያን ብሔር ክፍል ሆናለች። (ያዕቆብ 2:23–25) በመሆኑም በይሖዋና በይሖዋ ተስፋዎች ያመኑና እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ በታማኝነት የጸኑ የጥንት ታማኝ ወንዶችና ሴቶች በእምነታቸው ምክንያት በይሖዋ ዘንድ ጻድቅ ሆነው ስለተቆጠሩ ‘ከጻድቃን ትንሣኤ’ እንደሚካፈሉ ጥርጥር የለውም።

13, 14. (ሀ) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ጻድቃን ሆነው ሊቆጠሩ እንደሚችሉ እንዴት እናውቃለን? (ለ) ይህ ለእነርሱ ምን ትርጉም አለው?

13 ይሁን እንጂ ምድራዊ ተስፋ ያላቸውና ራሳቸውን የወሰኑ በዚህ የመጨረሻ ዘመን ታማኝነታቸውን ጠብቀው የሚሞቱ በግ መሰል ግለሰቦችስ? ከጻድቃን ትንሣኤ ተካፋዮች ይሆናሉን? እንደሚሆኑ ግልጽ ነው። እነዚህ እጅግ ብዙ የሆኑ ታማኝ ሰዎች ሐዋርያው ዮሐንስ በተመለከተው ራእይ ላይ ታይተዋል። እነዚህን ሰዎች እንዴት እንደገለጻቸው ልብ በል፦ “ከዚህ በኋላ አየሁ፣ እነሆም፣ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮኹ፦ በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ።”—ራእይ 7:9, 10

14 እነዚህ ገሮች እንደሚድኑ ጠንካራ እምነት ያላቸው መሆኑን ልብ በል፤ የሚያድኗቸው ይሖዋና “በጉ” ኢየሱስ እንደሆኑም ተናግረዋል። ከዚህም በላይ በይሖዋና በበጉ ፊት የቆሙት ነጭ ልብስ ለብሰው ነው። ነጭ ልብስ የለበሱት ለምንድን ነው? አንድ ሰማያዊ ፍጡር ዮሐንስን “ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ” በማለት ነግሮታል። (ራእይ 7:14) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነጭ የንጽሕናና የጽድቅ ምሳሌ ነው። (መዝሙር 51:7፤ ዳንኤል 12:10፤ ራእይ 19:8) እጅግ ብዙ ሰዎች ነጭ ልብስ ለብሰው መታየታቸው ይሖዋ እንደ ጻድቃን አድርጎ ያያቸዋል ማለት ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ልብሳቸውን በበጉ ደም ስላጠቡ ነው። በፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ስለሚያምኑ ከታላቁ መከራ በሕይወት የማለፍ ተስፋ ያላቸው የአምላክ ወዳጆች ለመሆን እንዲችሉ ጻድቃን ሆነው ተቆጥረዋል። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ከ“እጅግ ብዙ ሰዎች” አንዱ የሆነ ከታላቁ መከራ በፊት የሚሞት ማንኛውም ራሱን የወሰነ ታማኝ ክርስቲያን በምድራዊው የጻድቃን ትንሣኤ ላይ በመጀመሪያ ከሚነሡት አንዱ እንደሚሆን እርግጠኛ ሊሆን ይችላል።

15. ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት የሚነሡ ከሆነ የጻድቃን ትንሣኤ ጥቅሙ ምንድን ነው?

15 ይህ ምድራዊ ትንሣኤ በራእይ ምዕራፍ 20 ቁጥር 13 ላይ በሚከተሉት ቃላት ተገልጿል፦ “ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፣ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፣ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ።” ስለዚህ በታላቁ የይሖዋ የሺህ ዓመት የፍርድ ቀን በአምላክ መታሰቢያ ውስጥ ያሉ ሁሉ፣ ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት ይነሣሉ። (ሥራ 17:31) ይሁን እንጂ የጻድቃኑ ሁኔታ ከዓመፀኞቹ ምንኛ የተሻለ ይሆናል! ቀደም ሲሉ የእምነት ኑሮ ኖረዋል። ቀደም ሲሉ ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና መሥርተዋል፤ ይሖዋ ዓላማዎቹን የሚፈጽም አምላክ ስለመሆኑም ጠንካራ እምነት አዳብረዋል። ከክርስትና ዘመን በፊት የነበሩ ጻድቃን ምሥክሮች ከሞት ተነሥተው ይሖዋ ስለ ዘሩ የሰጠው ተስፋ እንዴት እንደተፈጸመ በጉጉት ይማራሉ። (1 ጴጥሮስ 1:10–12) ይሖዋ እንደ ጻድቅ አድርጎ የሚያያቸው የዘመናችን ሌሎች በጎች ከሞት ተነሥተው በዚህ ሥርዓት ምሥራቹን በሚያውጁበት ጊዜ የተናገሩለት ምድራዊ ገነት መቋቋሙን በጉጉት ይመለከታሉ። ምንኛ አስደሳች ጊዜ ይሆናል!

16. በጊዜያችን ስለሚሞቱ ሰዎች የፍርድ ቀን ትንሣኤ ምን ለማለት እንችላለን?

16 በሰይጣን ሥርዓት የመጨረሻ ዓመታት ታማኝነታቸውን ጠብቀው የሞቱ እነዚህ ሰዎች በሺህ ዓመት የፍርድ ቀን ውስጥ የሚነሡበት ትክክለኛ ጊዜ መቼ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አይናገርም። ይሁን እንጂ በዘመናችን የሚሞቱ ጻድቃን ሆነው የተቆጠሩ ሰዎች አርማጌዶንን በሕይወት ካለፉ እጅግ ብዙ ሰዎች ጋር በአንድነት ከእነርሱ አስቀድሞ የነበሩትን ትውልዶች ከሞት በመቀበሉ ሥራ መካፈል እንዲችሉ ቀደም ብለው ይነሣሉ ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ አይሆንምን? በእርግጥም ምክንያታዊ ነው!

የሚያጽናና ተስፋ

17, 18. (ሀ) የትንሣኤ ተስፋ ምን መጽናኛ ይሰጣል? (ለ) ስለ ይሖዋ ምን ብለን ለመናገር እንገፋፋለን?

17 የትንሣኤ ተስፋ በአሁኑ ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖች በሙሉ ብርታትና ማጽናኛ ይሰጣል። በታማኝነት ከጸናን ማንኛውም ድንገተኛ አጋጣሚም ሆነ ጠላት ሽልማታችንን ሊነጥቀን አይችልም! ለምሳሌ ያህል በ1992 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ገጽ 177 ላይ እምነታቸውን ከመካድ መሞትን የመረጡ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ደፋር ክርስቲያኖች ፎቶግራፎች ይታያሉ። ከፎቶግራፋቸው ግርጌ የሚገኘው መግለጫ “በትንሣኤ ለማየት የምንጠብቃቸው ፊቶች” ይላል። እነዚህንና እስከ ሞት ድረስ በመጽናት ተመሳሳይ የታማኝነት አቋም ያሳዩ ሌሎች ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎችን መተዋወቅ መቻል ምንኛ ታላቅ መብት ነው!

18  በእርጅና ወይም በሕመም ምክንያት እስከ ታላቁ መከራ ለመዝለቅ ያልቻሉ ወዳጆቻችንና ዘመዶቻችንስ? ከትንሣኤ ተስፋ ጋር በሚስማማ ሁኔታ በታማኝነት ከጸኑ በጣም አስደናቂ የሆነ የወደፊት ተስፋ አላቸው። እኛም በድፍረት በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ያለንን እምነት ጠብቀን ብንኖር በጣም አስደናቂ የወደፊት ተስፋ አለን። ለምን? ምክንያቱም እንደ ጳውሎስ “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ” ተስፋ እናደርጋለን። ይሖዋ ይህን ተስፋ ስለ ሰጠን ከልብ እናመሰግነዋለን። በእርግጥም “ክብሩን ለአሕዛብ ተኣምራቱንም ለወገኖች ሁሉ ንገሩ፤ እግዚአብሔር ታላቅ ምስጋናውም ብዙ ነውና፣ በአማልክትም ሁሉ ላይ የተፈራ ነውና” የሚሉትን የመዝሙራዊው ቃላት ደግመን ደጋግመን ለማስተጋባት እንገፋፋለን።—መዝሙር 96:3, 4

ልታብራራ ትችላለህን?

◻ በምድራዊ ትንሣኤ ላይ ያለንን ተስፋ ለማጠናከር የሚረዱን የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?

◻ ክርስቲያኖች በአሁኑ ጊዜ ጻድቃን ሆነው የሚቆጠሩት በምን መሠረት ነው?

◻ የትንሣኤ ተስፋ ድፍረት የሚሰጠንና ቆራጥ አቋም እንድንወስድ የሚያደርገን እንዴት ነው?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቅቡዓን ክርስቲያኖች ልክ እንደ ጳውሎስ ሰማያዊ ትንሣኤን ተስፋ ያደርጋሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ