የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 2/15 ገጽ 23-26
  • ዶሚኒካን ሪፑብሊክ አሁንም ለግኝት ክፍት ናት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዶሚኒካን ሪፑብሊክ አሁንም ለግኝት ክፍት ናት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሌላ ዓይነት ግኝት
  • ምሥራቹን በማዳረስ የተገኙ በረከቶች
  • ወጣቶች ያሳዩት ግሩም ምላሽ
  • ከሌሎች አገሮች የመጡ “አሳሾች”
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 2/15 ገጽ 23-26

ዶሚኒካን ሪፑብሊክ አሁንም ለግኝት ክፍት ናት

ክርስቶፎር ኮሎምበስ ገና ወጣት ሳለ ባሁኑ ወቅት ዌስት ኢንዲስ በመባል የሚታወቁትን ደሴቶች ያስገኘለትን የባሕር ላይ ሕይወት ጀመረ። በታኀሣሥ 1492 ሳንታ ማሪያ የተሰኘችው ሰንደቅ ዓላማው የሚውለበለብባት መርከቡ በእስፓኞላ፣ ባሁኑ ወቅት ደግሞ ሂስፓኒዮላ በምትባለው በሃይቲና በዶሚኒካን ሪፑብሊክ መካከል በምትገኘው ደሴት ሰሜናዊ ጠረፍ ደረሰች። እዚያም ኮሎምበስ የመጀመሪያውን የአውሮፓውያን ሠፈር መሠረተና ላ ናቪዳድ ሲል ሰየመው። ይህች ደሴት ከዚያ በኋላ ላደረገው አሰሳ ማዕከል ሆነች።

ኮሎምበስ በደሴቲቱ ውስጥ በጣም የተዋቡ፣ እምነት የሚጣልባቸውና እንግዳ ተቀባይ የሆኑ የሚባሉ ሕዝቦች እንደሚኖሩ ተገነዘበ። በዚያን ወቅት 100,000 የሚገመቱ ታይኖ ኢንዲያንስ በዚያ ይኖሩ ነበር። ይሁን እንጂ ቀደምት ፍላጎታቸው ወርቅ መፈለግ የነበረው ወራሪዎች በጣም ስላጉላሏቸው የአገሩ ተወላጆች ቁጥር በፍጥነት እየቀነሰ ሄደ። በ1570 የቀሩት 500 የሚያህሉ ቲያኖ ኢንዲያንስ ብቻ እንደነበሩ ተዘግቧል።

የዛሬዋ ዶሚኒካን ሪፑብሊክ የቀድሞ አባቶቻቸው በዚያ ለመኖር የፈለሱ ብዙ ዘሮችና የተለያየ የቆዳ ቀለም ያሏቸው ሰዎች ይኖሩባታል። ቢሆንም እነዚህ ሕዝቦች ብዙዎቹ የታይኖዎች መልካም ጠባዮች ይታዩባቸዋል፤ የወዳጅነትና የተግባቢነት መንፈስ አላቸው። ይህ ሁኔታ በልባቸው በአምላክ ከማመናቸውና ለመጽሐፍ ቅዱስ ካላቸው አክብሮት ጋር ተጣምሮ በዚህ አገር የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጉትን የስብከትና የማስተማር ሥራ በአስደናቂ ሁኔታ ስኬታማ አድርጎታል።

ሌላ ዓይነት ግኝት

ሌናርትና ቪርጂኒያ ጆንሰን የተባሉት የመጀመሪያዎቹ የመጠበቂያ ግንብ ሚስዮናውያን ዶሚኒካን ሪፑብሊክ የገቡት በአምባገነኑ ትሩጂሎ ዘመን ነበር። ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክታቸውን ወዲያውኑ አዎንታዊ በሆነ መንገድ እንደተቀበሉ ሲገነዘቡ ተደሰቱ። ሆኖም ባለ ሥልጣኖችና ሃይማኖታዊ አማካሪዎቻቸው ይህን አልወደዱትም። ብዙም ሳይቆይ የስደት ማዕበል ተነሳና የመጀመሪያዎቹ የዶሚኒካን የይሖዋ ምሥክሮች እምነት ክፉኛ ተፈተነ። እስከ ሞት ድረስ ያሳዩት እምነትና ታማኝነት እስካሁን ብዙ ይነገርለታል።

ባሁኑ ወቅት ቁጥራቸው 16,000 የደረሰው በዚህች አገር የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች በሰፊው የታወቁ ናቸው። ከጥቂት ጊዜ በፊት አምስት የቴሌቪዠን ጣቢያዎች የይሖዋ ምሥክሮች—ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት የተባለውን የቪዲዮ ካሴት በመላው የአገሪቱ ክፍል አስተላልፈው ነበር።a

ይህም የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በትልልቅ ከተማዎች ብቻ ሳይሆን በአነስተኛ ከተማዎችና በአንዳንድ የገጠር አካባቢዎችም ጭምር በሰፊው እንዲታወቅ አድርጓል። ሰዎች ያሳዩትን ፍላጎት ተከታትለው ለመርዳት ሲሉ የምሥራቹን ራቅ ወዳሉ ሥፍራዎች ለማዳረስ የሚያስችል ልዩ ዘመቻ አቀናጁ።

ምሥራቹን በማዳረስ የተገኙ በረከቶች

ወጣት፣ ታታሪና ቀናተኛ የሆኑ ብዙ ምሥክሮች በእነዚህ ራቅ ያሉ ክልሎች በመስበክ የሁለት ወራት ጊዜ ለማሳለፍ ፈቃደኛ ሆነዋል። ጥረታቸው ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። በአንድ አካባቢ ሁለት ምሥክሮች ልዩ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን አገኙ። ጊዜው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል የሚከበርበት ወቅት ስለነበር ዝግጅት አድርገው በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ሰዎችን ጋበዙ። አዳራሹ ጢም ብሎ ሞላ፤ ስብሰባውንም መሩ። ስብሰባው ካለቀ በኋላ ሌሎች ብዙ ሰዎች አዳራሹ በራፍ ላይ ሆነው ለመግባት ሲጠባበቁ ሲያዩ በጣም ተገረሙ። ስለዚህ እንዲገቡ ጋበዟቸውና ፕሮግራሙን በድጋሜ አካሄዱ። አሁን በዚያ ስፍራ ጉባኤ ተቋቁሟል።

የሕዝቡ የለጋስነትና የተግባቢነት መንፈስ ብዙውን ጊዜ በመማር ላይ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለቤተሰቦቻቸውና ለሌሎች ሰዎች እንዲያካፍሉ ይገፋፋቸዋል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ከቤት ወደ ቤት አገልግሎት ለመሳተፍ ሲበቃ በደስታ ተፍለቀለቀ። ቀደም ሲልም ቢሆን ለጎረቤቶቹ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ይመራ ነበር፤ ይሁን እንጂ በአገልግሎት ከዚህ የበለጠ ተሳትፎ ማድረግ በመቻሉ ተደስቶ ነበር።

የመንግሥቱ አስፋፊዎች ብዙውን ጊዜ ባልሠሩባቸው ክልሎች በአውቶቡሶች ላይና ወደ ከተማዎች ለመነገድ ወይም ለመገብየት ለሚመጡት ለመስበክ ጥረት ተደርጓል። ለቅርንጫፍ ቢሮው በተላከ ደብዳቤ ላይ በተገለጸው አንድ ተሞክሮ እንደታየው ይህ አስደሳች ውጤቶችን አስገኝቷል። ደብዳቤው የተላከው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከሚፈልጉ በገጠር አካባቢ ከሚገኙ ሁለት ሰዎች ነበር። አንድ ምሥክር ሊያነጋግራቸው ሲሄድ ግን “ሰዎቹ” የ10 እና የ11 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች ሆነው ተገኙ። ግን መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የሚያስችል ዝግጅት እንዳለ እንዴት ሊያውቁ ቻሉ? አንድ የዚያ መንደር ነዋሪ ለንግድ ወደ ዋና ከተማው መጥቶ ነበር። ሰውዬው ከአንድ ምሥክር ጋር በመንገድ ላይ ተገናኘና ምሥክሩ ትራክት ካበረከተለት በኋላ ነፃ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግለት ጋበዘው። ሰውዬው ወደሚኖርበት መንደር ሲመለስ ትራክቱን ጎረቤቱ ለሆነች አንዲት የ12 ዓመት ልጅ ሰጣትና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ስላለው ዝግጅት ነገራት። ልጅቷም በተራዋ ለሁለቱ ልጆች ያገኘችውን እውቀት አካፈለች፤ እነሱም ወዲያው ደብዳቤውን ጻፉ። ለልጆቹ፣ ለልጅቷ፣ ለሰውዬውና ለሰውዬው ሁለት ልጆች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ ላቸው።

ወጣቶች ያሳዩት ግሩም ምላሽ

በእውነት ውስጥ ያደጉትም ሆነ ሌሎች ወጣቶች የይሖዋን አምልኮ በቁም ነገር ይዘውታል። ለምሳሌ ታማር እና ኬይላ የተባለችው እህቷ በ10 ዓመታቸው ተጠምቀው 11 ዓመት ሲሆናቸው ወደ ሙሉ ጊዜ የአቅኚነት አገልግሎት ገብተዋል። ዌንዲ ካሮሊና ራስዋን መወሰኗን በውኃ ጥምቀት ስታሳይ 12 ዓመቷ ነበር፤ ከዚያም በ1985 ማለትም ከተጠመቀች ከሁለት ዓመታት በኋላ የዘወትር አቅኚ ሆነች። ዛሬ የተዋጣላት የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ስትሆን እስካሁንም በሙሉ ጊዜ አገልግሎቷ ቀጥላለች። በ10 ዓመቱ ተጠምቆ በ11 ዓመቱ የዘወትር አቅኚ የሆነው ወጣት ሆቫኒ አራት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አሉት። የአሥር ዓመቱ ሬይ በአንድ አሮጌ መጽሐፍ ተራ በይሖዋ ምሥክሮች የታተመ ቡክሌት እንዳለ ሲገነዘብ እናቱ እንድትገዛለት ለመናት። ከዳር እስከ ዳር አነበበው። ተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ ከቅርንጫፍ ቢሮው ጋር እንዲገናኝ አደረገው። ዛሬ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተደሰተ ሲሆን እናቱም አምላክን በማገልገል ላይ ነች።

እነዚህንም ሆነ ሌሎች ወጣቶችን የመንፈሳዊ ነገሮችን ጠቀሜታ እንዲገነዘቡ የረዳቸው ምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ ትክክለኛ የወላጆች ሥልጠና ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ክርስቲያን ወላጆቹ መምህራን የሆኑት የሆስዋ ሁኔታ ይህ ነበር። አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ወላጆች ቢያንስ ከልጆቻቸው አንዱ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ እንዲሆን እንዲረዱ ሐሳብ ሲያቀርብ ወላጆቹ በሆስዋ ላይ ትኩረት አደረጉ። ሆስዋ ጎበዝ ተማሪ ስለነበር ምህንድስናን ለማጥናት የሚያስችል የነፃ ትምህርት ዕድል አገኘ። በዩኒቨርሲቲው ለአንድ ዓመት ተኩል ከተማረ በኋላ የዶሚኒካን ሪፑብሊክ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚደረገውን የሕንፃ ግንባታ ፕሮጀክት እንዲረዳ ሲጋበዝ ግብዣውን ተቀበለ። ወላጆቹ ልጃቸውን ለይሖዋ አገልግሎት በመስጠታቸው የተሰማቸውን ጥልቅ እርካታ ገልጸዋል።

ከሌሎች አገሮች የመጡ “አሳሾች”

“መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ለዚህ መስክ ይስማማሉ። (ማቴዎስ 9:37) ያለው ከፍተኛ የአገልጋዮች እጥረትና ሰዎች የሚሰጡት አዎንታዊ ምላሽ ከሌሎች አገሮች ምሥክሮች እንዲመጡና በክልሉ ውስጥ የሚገኙትን ዘመናዊ ውድ ሀብቶች ማለትም ቅን ልብ ያላቸውን እውነት ፈላጊዎች በመፈለጉ ሥራ እንዲካፈሉ ገፋፍቷቸዋል።

ፖርቶሪኮ ከምትባለው አጓራባች ደሴት የመጡ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦች በተለያዩ የዶሚኒካን ሪፑብሊክ ክልሎች በማገልገል እውነተኛ እርካታ አግኝተዋል። አንድ የቤተሰብ ራስ “ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች እምነትህንና ተስፋህን መግለጽ እውነት ሕያው እንዲሆንልህ ያደረጋል” ሲል በአድናቆት ተናግሯል። እዚህ ያለውን የአገልጋዮች እጥረት በመገንዘብ ከስዊድን ሲስሊያ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ኒያ ከብዙ ሌሎች ወጣት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ጋር አብረው ለመሥራት ወደ ዶሚኒካን መጡ። በአሁኑ ወቅት የመሬቱ ከፍታ ከፍተኛ በሆነና ለስላሳ የአየር ጠባይ ባለበት በመሃል አገር እያገለገሉ ነው። በተመሳሳይም በጥድ በተሸፈኑ ቀዝቃዛ ተራራዎች ላይ ከሚኖር ከዩናይትድ ስቴትስ ከተመለሰ አንድ የዶሚኒካን ተወላጅ ቤተሰብ ጋር ሁለት ካናዳዊ ቤተሰቦች አብረው እየሠሩ ናቸው። እነዚህ ቤተሰቦች የአንድ አነስተኛ ጉባኤ አባሎች ሲሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ላለፉት አሥር ዓመታት ያላነጋገሯቸውን ሰዎች በማዳረስ ላይ ናቸው።

አልፍሬዶና ሉርዶስ እንዲሁም አምስት ልጆቻቸው ከኒው ዮርክ ከተማ ተመልሰው ጎብኚዎች ከሚያርፉባቸው በባሕር ዳር ካሉ ውብ ከተሞች በአንዱ ውስጥ ከሚገኘው አንድ አነስተኛ ጉባኤ ጋር እየተሰበሰቡ ነው። ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች በማግኘት ጉባኤው እንዲያድግ ለመርዳት በመቻላቸው ተደስተዋል። ከኦስትሪያ የመጣው የኮምፒዩተር ኦፕሬተር የሆነው ሮናልድና ሚስቱ ዩታ ሞቃታማና ደረቅ በሆነው የአገሪቷ ደቡባዊ ክፍል ይኖራሉ። እነሱ ከመጡ በኋላ አዲስ ጉባኤ ሲቋቋም በማየታቸው ተደስተዋል። በአቅራቢያው በምትገኘው ከተማ ከካሊፎርኒያ የመጡ ሦስት አቅኚ እህቶችና አንድ ባልና ሚስት የሚገኙበት ቡድን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስላገኘ ሁሉንም መምራት እንዳልቻለ ሪፖርት አድርጓል። ስለዚህ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በአካባቢው በሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ እንዲገኙ ያበረታቷቸውና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚፈልጉ ሰዎች ተራ በሚይዙበት መዝገብ ውስጥ ይመዘግቧቸዋል። የዩታ ወንድም ስቲፈን በአገሪቱ ደቡብ ምሥራቃዊ ክፍል በምትገኘው ሳማና በተባለች ውብ ከተማ በሚገኝ አንድ አነስተኛ ጉባኤ ውስጥ በታማኝነት እያገለገለ ነው። በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ በዚያ የሚገኙት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር እጥፍ ለመሆን በቃ።

እነዚህና ሌሎች ለእርዳታ የመጡ ወንድሞች ያሳዩት ፍቅርና ቅንዓት በእውነትም የሚያስመስግን ነው። በማያውቁት አካባቢ ከሚገኙት ልማዶችና ባሕሎች ጋር መላመድ ብቻ ሳይሆን በግ መሰል የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት ሲሉ ሌላ ቋንቋ የመማርን ይበልጥ ተፈታታኝ የሆነ ሁኔታ ተጋፍጠዋል። ጥረታቸው ከአካባቢው ሕዝቦች አዎንታዊ ምላሽ አስገኝልቶላቸዋል።

አንዳንድ የዶሚኒካን ቤተሰቦች በትላልቅ ከተማዎች ውስጥ የነበራቸውን የተደላደለ ኑሮ ትተው ወደ ገጠር ተንቀሳቅሰዋል። ሁሉም ውድ ሀብት የሆኑትን ቅን ልብ ያላቸው እውነት ፈላጊዎች በማግኘታቸው በጣም ተክሰዋል።

የ15ኛው መቶ ዘመን ሀብት ፈላጊዎች የአገሩ ተወላጆች ለሆኑት ለቲያኖ ሕዝቦች ያተረፉት በረከት ሳይሆን ባርነትና በቃላት ሊነገር የማይችል መከራ ነው። ኮሎምበስ ራሱም እንኳ ካገኘው አዲስ ክፍለ ዓለም ውድ ሀብት አልተጠቀመም። ከጊዜ በኋላ ተያዘና እጁ በሰንሰለት ተጠፍሮ ራሱ ካገኛት ደሴት ወደ ስፔይን ተወሰደ።

ዛሬ ለየት ያለ አሰሳ እየተካሄደ ነው፤ ከዚህ በፊት ከተገኘው የበለጠ ዋጋ ያለው ውድ ሀብት እየተገኘ ነው። የይሖዋ ሕዝቦች የመንግሥቱን ምሥራች የሚቀበሉ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች በመፈለጉ ሥራ ተጠምደዋል። በውጤቱም ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ብዙ ሰዎች የአምላክ ቃል ብቻ የሚሰጠውን ነፃነት በማግኘት እየተደሰቱ ነው። (ዮሐንስ 8:32) ተራራዎች፣ አስደሳች ፏፏቴዎች፣ ውብ የባሕር ዳርቻዎችና ማራኪ ዋሻዎች ያሉባት ይህች አገር ገነታዊ ደሴት ብቻ ሳትሆን ምድርን በጠቅላላ የሚሸፍነው የአዲሱ ዓለም ክፍል የምትሆንበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ።—2 ጴጥሮስ 3:13

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀ።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ዶሚኒካን ሪፑብሊክ

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ወጣቶች የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን በመከታተል የመንፈሳዊ ነገሮችን ጠቀሜታ ተገንዝበዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ