የጸሎቶችህን ይዘት ይበልጥ ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው?
ይሖዋ አምላክ ካዘጋጃቸው ፍቅራዊ ዝግጅቶች መካከል ጸሎት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ስጦታ ነው። ተቃዋሚዎች መጽሐፍ ቅዱስህን ሊቀሙህ ወይም አብረውህ አምላክን ከሚያገለግሉት ጋር እንዳትሰበሰብ ሊያደርጉህ ይችሉ ይሆናል፤ እንዳትጸልይ ሊከለክልህ የሚችል ግን ማንም ሰው የለም። የጸሎትን ዋጋማነት አቅልለን ልንመለከተው አንችልም። ስለዚህ እያንዳንዳችን ያገኘነውን የጸሎት መብት እንደ ውድ ሀብት በአድናቆት ማየትና ከእርሱም ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ መሆናችን አስፈላጊ ነው። ጸሎቶችህን ይበልጥ ለማሻሻል ምን ሊረዳህ ይችላል?
መጽሐፍ ቅዱስ የጸሎት መጽሐፍ አይደለም። ይሁን እንጂ ከሁሉ የላቀ የሰው ልጆች የጸሎት መማሪያ መጽሐፍ ተብሎ ሊገለጽ ይቻላል። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ብቻ ከ150 የሚበልጡ ጸሎቶችን ይዘዋል። አንዳንዶቹ አጫጭሮች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ረዣዥሞች ናቸው። ጸሎቶቹ በድል ወይም በመከራ ጊዜ ነገሥታት ወይም ምርኮኞች በሕዝብ ፊት ወይም በግል ያቀረቧቸው ናቸው። ዳዊት በመዝሙር 65:2 ላይ እንደዘመረው ‘ሥጋ ሁሉ ጸሎትን ወደሚሰማው’ ወደ ይሖዋ ድምፃቸውን ያሰማሉ። አምላክ እንደነዚህ ያሉ የተመረጡ ጸሎቶችን በስፋት መዝግበው እንዲያስቀምጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን በመንፈሱ ያነሳሳቸው ለምንድን ነው?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ 2 ጢሞቴዎስ 3:16ን (አዓት) እንመርምር። “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው” ይላል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጸሎቶች ቅዱስ ጽሑፋዊ ትንቢቶች፣ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ታሪኮች እንደመሆናቸው መጠን ለኛ መመሪያ እንዲሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ተቀምጠዋል። እነዚህ ጸሎቶች እኛን ሊጠቅሙን የሚችሉት እንዴት ነው?
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጸሎቶችን በመመርመር እኛ ባለንበት ተመሳሳይ ሁኔታ ሥር የቀረቡትን ጸሎቶች ለይተን ለማወቅ እንችላለን። ጸሎቶች ምን ያህል በዓላማቸውና በአቀራረባቸው እንደሚለያዩ ልንረዳ እንችላለን። ከዚህም በላይ አዳዲስ የውዳሴና የማመስገኛ አነጋገሮች እንዲሁም ለልመናና ለምልጃ ልንጠቀምባቸው የምንችል አዳዲስ ቃሎችን እናገኛለን። ባጭሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጸሎቶች የራሳችንን ጸሎቶች ይበልጥ ለማሻሻል ሊረዱን ይችላሉ።
በኋላ የኢየሱስ እናት የሆነችው ማሪያም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ በሚገኝ አንድ ጸሎት ላይ ከቀረቡት አገላለጾች የተጠቀመች ሴት ነበረች። በመለኮታዊ እርዳታ አማካኝነት ሁለቱም ወንድ ልጅ ከጸነሱ በኋላ ማሪያም ዘመዷ የሆነችውን ኤልሳቤጥን ልትጠይቃት ሄደች። ማሪያም ለአምላክ የውዳሴና የምስጋና ጸሎት አቀረበች፤ የሚያስገርመው ግን ለጸሎት የተጠቀመችባቸው አንዳንድ ቃሎቿ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሚገኝ አንድ ጸሎት ላይ ከተለጹት ሐሳቦች ጋር ተመሳሳይነት ነበራቸው። ማሪያም የነቢዩ ሳሙኤል እናት የነበረችው ሐና ያቀረበችውን ጸሎት በደንብ ታውቀው እንደነበረ ምንም አያጠራጥርም። 1,000 ዓመት ቀደም ብሎ ሐናም በአምላክ ርዳታ ወንድ ልጅ ጸንሳ ነበር። ማሪያም የራሷን ስሜት የሚገልጽ በመሆኑ ይህን ጸሎት እያሰላሰለች አስባበት ይሆን?—1 ሳሙኤል 2:1–10፤ ሉቃስ 1:46–55
ስለ አንተስ ምን ለማለት ይቻላል? አንተ ባለህበት ተመሳሳይ ሁኔታ ሥር ባሉ ሰዎች የቀረበ ጸሎት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማስታወስ ትችላለህ? እንደነዚህ ያሉትን ጸሎቶች ፈልጎ ማግኘት፣ ማንበብና ማሰላሰል ከአምላክ ጋር ያለህን የግል የሐሳብ ግንኙነት ይበልጥ ለማሻሻል ይረዳሃል። በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሰፈሩ ሦስት ጸሎቶችን እንድትመረምር እንጋብዝሃለን። ጸሎቶቹ በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር የቀረቡና ምናልባትም ከአንተ ጋር የሚመሳሰሉ ሊሆኑ ይችላሉ።