መልስ የሚያገኙት የእነማን ጸሎቶች ናቸው?
ይሖዋ ለጸሎት መልስ የሚሰጥ አምላክ ነው። እንዲያውም የራሱ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ “ጸሎት ሰሚ” በማለት ይጠራዋል። (መዝሙር 65:2) ይሖዋ ጸሎት ለመስማት ፈቃደኛ ነው። ይሁን እንጂ እርሱ የሚሰማው የእነማንን ጸሎት ነው?
አምላክ እርሱን የሚያስደስቱትን ግለሰቦች ጸሎት ይመልሳል። እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች “ዋላ ወደ ውሃ ምንጭ እንደሚናፍቅ አቤቱ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች። ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች። መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ?” ያለውን መዝሙራዊ የመሰለ የአክብሮት ዝንባሌ አላቸው። (መዝሙር 42:1, 2) ሆኖም ይሖዋ የእውነተኛ አምላኪዎቹን ጸሎት እንደሚሰማ የሚያረጋግጥ ምን ማስረጃ አለ?
አምላክ ለጸሎት መልስ እንደሚሰጥ የሚያረጋግጥ ማስረጃ
መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ የታማኝ አገልጋዮቹን ጸሎት እንደሚሰማ የሚያረጋግጥ ሰፊ የታሪክ መዝገብ ይዞልናል። ለምሳሌ ያህል የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ይሖዋ እንዲያድነው በለመነ ጊዜ አምላክ ጸሎቱን ሰማና ጠላቶቹ እርስ በርሳቸው እንዲጋደሉ በማድረግ ድል ሰጠው። (2 ዜና መዋዕል 20:1-26) ንጉሥ ሕዝቅያስም በተመሳሳይ አስፈሪ የጦር ኃይል ባጋጠመው ጊዜ አምላክ እንዲረዳው በትሕትና ጸለየ። አንድ መልአክ በአንድ ሌሊት 185,000 አሦራውያንን በገደለ ጊዜ ሕዝቅያስ የይሖዋን ማዳን አየ።—ኢሳይያስ 37:14-20, 36-38
አምላክ እነዚህን ጸሎቶች የሰማው ለምን ነበር? በሁለቱም ጸሎቶች ረገድ ነገሥታቱ በጦርነቱ ቢሸነፉ የይሖዋ ስም እንደሚዋረድ በማሰብ ስለተማጸኑ ነው። (2 ዜና መዋዕል 20:6-9፤ ኢሳይያስ 37:17-20) እነርሱን ያሳሰባቸው የይሖዋ ስም ወይም ዝና ነበር። “የጸሎት ዋነኛ ዓላማ” ይላል ዘ ኢንተርናሽናል እስታንዳርድ ባይብል ዲክሽነሪ “የጸለዩት ሰዎች መልካም ነገር ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን የአምላክ ስም መከበሩ ነው።” ስለዚህ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች “ስለ ስሙ ሲል” እንደሚረዳቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ጸሎቶች መልስ እንዳገኙ የሚያረጋግጡት የታሪክ መዝገቦች የአምላክ ሕዝቦችም ጸሎታቸው መልስ እንደሚያገኝ እርግጠኛ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።—መዝሙር 91:14, 15፤ 106:8፤ ምሳሌ 18:10
ይሁን እንጂ ሁኔታው የይሖዋን ስም የሚነካ በሚሆንበት ጊዜ እንኳ ጸሎቶችን ለመመለስ ወይም ላለመመለስ የሚወስነው አምላክ ነው። አንዳንድ ጸሎቶችን ላለመመለስ ተገቢ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላሉ። ጸሎታችን እንዳልተሰማልን የሚሰማን ከሆነ ይህን ከግምት ማስገባቱ መልካም ነው።
አንዳንድ ጸሎቶች መልስ የማያገኙት ለምንድነው?
አንድ ጊዜ ይሖዋ ለእሥራኤላውያን “ልመናም ብታበዙ አልሰማችሁም” ብሏቸዋል። ምክንያቱንም ሲገልጽ “እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል” ብሎአል። (ኢሳይያስ 1:15) አንድ ሰው የይሖዋን ሕግ ንቆ እንዴት በእሱ ዘንድ ተደማጭነት ሊኖረው ይችላል? የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ሕግን ከመስማት ጆሮውን የሚመልስ ጸሎቱ አስጸያፊ ናት” በማለት በግልጽ ይመልስልናል።—ምሳሌ 28:9
መጽሐፍ ቅዱስ “ትለምናላችሁ። ሆኖም ለሥጋዊ ደስታ (ተድላ) ታውሉት ዘንድ ለተሳሳተ ዓላማ ትለምናላችሁ፣ አትቀበሉም” ሲል አንዳንድ ጸሎቶች መልስ የማያገኙበትን ሌላ ምክንያት ይሰጠናል። (ያዕቆብ 4:3) የለም ይሖዋ የተሳሳተ ምኞቶችን ለማርካት ሲባል ለሚቀርብ ጸሎት መልስ አይሰጥም። በተጨማሪም ይሖዋ ከሰዎች ትዕዛዝ እንደማይቀበል ማስታወስ አለብን። ለጸሎቶቻችን እንዴት መልስ እንደሚሰጥ የሚወስነው እሱ ነው።
በተገቢ የልብ ግፊት የቀረቡ፣ ከንጹሕ ልብ የመነጩና ይሖዋ በወሰነው መንገድ ማለት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የቀረቡ ጸሎቶች መልስ እንደሚያገኙ የተረጋገጠ ነው። (ዮሐንስ 14:6, 14) ይሁን እንጂ ጸሎቶቻቸው እነዚህን ብቃቶች የሚያሟሉ ሰዎችም እንኳን አንዳንዴ እንዳልተሰሙ ተሰምቷቸዋል። አምላክ የአገልጋዮቹን አንዳንድ ጸሎቶች ወዲያውኑ መልስ የማይሰጠው ለምንድነው?
ይሖዋ ለጸሎት መልስ የሚሰጥበትን የተሻለ ጊዜ ያውቃል። አንድ ልጅ ብስክሌት እንዲሰጠው ቢለምን ልጁ አድጎ ካለምንም አደጋ መንዳት እስኪችል ድረስ አባቱ ላይሰጠው ይችላል። አምላክን የሚያፈቅሩ ሰዎች የሚያቀርቧቸው ጸሎቶችም እንደዚያው ሊሆኑ ይችላሉ። አምላክ ለእነሱ የተሻለው ነገር ምን እንደሆነ ስለሚያውቅ የፈለጉትን ነገር ይበልጥ ተስማሚ በሆነው ጊዜ ይሰጣቸዋል።
ሆኖም የይሖዋ አገልጋዮች የሚለምኑትን ነገር ሁሉ አያገኙም። ፍጹማን ስላልሆኑ የማይበጃቸውን ነገር ይመኙ ይሆናል። አፍቃሪው ሰማያዊ አባት “የበጐ ሥጦታና የፍጹም በረከት” ሰጪ ስለሆነ ምንም ዓይነት ጐጂ ነገር አይሰጣቸውም። (ያዕቆብ 1:17) በተመሳሳይ አምላክ በራሱ አመለካከት አስፈላጊ ያልሆነ ነገር ላይሰጥ ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 12:7-10) ለጸሎት መልስ የሚሰጠው ከፈቃዱና ለሕዝቡ ካለው ዓላማ ጋር በመስማማት ነው።—1 ዮሐንስ 5:14, 15
የኢየሱስ ጸሎት ተሰሚነት አግኝቶአል
ኢየሱስ ክርስቶስ የጸሎት ሰው ነበር። (ማቴዎስ 6:9-13፤ ዮሐንስ 17:1-26) ሰማያዊ አባቱ ጸሎቱን ሰምቶ መልስ እንደሚሰጠው ሙሉ ትምክህት ነበረው። ኢየሱስ አንድ ጊዜ እንዲህ ብሏል፦ “አባት ሆይ . . . ሁልጊዜ እንድትሰማኝ አውቃለሁ።” (ዮሐንስ 11:41, 42) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ መጨረሻ ላይ ተደናግጦ አልነበረምን? “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?” ብሎ አልጮኸም ነበርን?—ማቴዎስ 27:46
ኢየሱስ እነዚህን ቃላት ሲናገር ስለአሟሟቱ የተነገረውን ትንቢት መፈጸሙ ነበር። (መዝሙር 22:1) ኢየሱስ ጥርት ባለ አነጋገር ይሖዋ ጥበቃውን እንዳነሣበትና ታማኝነቱን እስከመጨረሻው ነጥብ ድረስ ለመፈተን ሲል ልጁ የስቃይና አሳፋሪ ሞት እንዲሞት መፍቀዱን መናገሩ ሊሆን ይችል ነበር። በዚያ የኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት መጨረሻ የተፈጸሙትን ሁኔታዎች ብንመረምር አምላክ ጸሎቱን እንደሰማለት መረዳት እንችላለን።
ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት በጌተሰማኒ የአትክልት ቦታ ሆኖ ይጸልይ ነበር። ሦስት ጊዜ “አባቴ ቢቻልስ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ” እያለ ተማጽኗል። (ማቴዎስ 26:39, 42, 44) ኢየሱስ እምነት ለሚያሳዩ የሰው ልጆች ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት አላመነታም። እሱን ያሳሰበው እንደ አንድ የተረገመና አምላክን የሰደበ ሰው በስቃይ እንጨት ላይ ተሰቅሎ በመሞት፣ እጅግ የሚያፈቅረውን አባቱን እንዳያዋርድ ነበር። ታዲያ ይሖዋ የኢየሱስን ጸሎት ሰምቷልን?
ዓመታት ካለፉ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ “(ክርስቶስ) በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ እግዚአብሔርንም ስለመፍራቱ ተሰማለት” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 5:7፤ ሉቃስ 22:42, 44) አዎ ከሞቱ ዕለት በፊት በነበረው አስጨናቂ ምሽት የኢየሱስ ጸሎት ተቀባይነት አግኝቶ ተሰምቶለታል። ግን እንዴት?
ይሖዋ “የሚያበረታው መልአክ” ሰዶለት ነበር። (ሉቃስ 22:43) በመሆኑም ኢየሱስ ተበረታትቶ በስቃይ እንጨት ላይ ሞትን ለመጋፈጥ ቻለ። በግልጽ እንደሚታየው በእንጨት ላይ መሞቱ በመለኰታዊው ስም ላይ ውርደት ማምጣቱ ቀርቶ እንዲያውም ስሙን እንደሚቀድሰው ይሖዋ አረጋግጦለታል። እውነትም ኢየሱስ በስቃይ እንጨት ላይ መሞቱ በሕጉ ሥር በእርግማን ለነበሩት አይሁድ ከሞት ኩነኔ የሚድኑበትን መንገድ ከፍቶላቸዋል።—ገላትያ 3:11-13
ይሖዋ ከሦስት ቀን በኋላ ኢየሱስን ከሞት አስነስቶ ወደላቀ ሰማያዊ ሥልጣን ከፍ ከፍ ስላደረገው ከማንኛውም ዓይነት ክስ ነጻ መሆኑን አረጋግጦለታል። (ፊልጵስዩስ 2:7-11) ኢየሱስ “ጽዋውን” በሚመለከት ያቀረበውን ጸሎት ግሩም በሆነ ሁኔታ መልሶለታል። ይህ ጸሎት ይሖዋ በመረጠው መንገድ ምላሽ አግኝቶአል። ኢየሱስ ለሰማያዊ አባቱ “የእኔ ፈቃድ አይሁን ያንተ እንጂ” በማለቱ ግሩም በረከቶች አጋጥመውታል።—ሉቃስ 22:42
ይሖዋ ዛሬ ለጸሎት ምላሽ የሚሰጠው እንዴት ነው?
እንደ ኢየሱስ ይሖዋን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ምን ጊዜም የአምላክ ፈቃድ እንዲሆን መለመን አለባቸው። ይሖዋ ጸሎታቸውን የበለጠ በሚጠቅማቸው መንገድ እንደሚመልስ እምነት ሊኖራቸው ያስፈልጋል። እንዲያውም “ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ያደርጋል።”—ኤፌሶን 3:20
ከማያምኑ ወላጆቿ ጋር ትኖር የነበረች አንዲት ወጣት ክርስቲያን ሴት የዚህን ጥቅስ እውነተኛነት በራሷ ተሞክሮ አይታለች። ከመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በተላከላት ደብዳቤ ላይ አንድ ልዩ የሚስዮናዊነት ሥራ ለመቀበል በጸሎት እንድታስብበት ተጠየቀች። ልባዊ ፍላጐቷ በቤት ቆይታ ወላጆቿን ክርስቲያኖች እንዲሆኑ መርዳት ቢሆንም አምላክን በጸሎት “ፈቃድህ ምንድነው? ወላጆቼ ቢቃወሙኝም ይህን ግብዣ እንድቀበል ነው ወይስ ከወላጆቼ ጋር ኖሬ እነሱን እንድረዳ?” ብላ ጠየቀች። በጸለየች ቁጥር ሕሊናዋ ግብዣውን እንድትቀበል ይነግራት ነበር። ይህ የአምላክ መልስ እንደሆነ ወሰነች።
ይህች ሴት በውሳኔዋ እንድትጸና አምላክ አበረታት። ጃፓን ውስጥ ወደምትገኝ አዋጂ የምትባል ደሴት እንድትዛወር በተጠየቀች ጊዜ ወላጆቿ ደነገጡና ተቃውሞአቸውን አጠነከሩባት። ይሁን እንጂ ሐሳቧን ማስለወጥ ሲያቅታቸው ልጃቸው እንዲህ ዓይነት ውሣኔ ለምን እንዳደረገች ለማየት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ወሰኑ። ከሦስት ወራት በኋላ ወላጆቿ ሊጠይቋት ሄዱ። የይሖዋ ምሥክሮች እንዴት በእንክብካቤ እንደያዟት ሲያዩ አባቷ በጣም ተደነቁና ተደብቀው አለቀሱ። ወዲያው እሳቸውም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። ከጊዜ በኋላ የዚህች ወጣት ሴት ወላጆች ተጠመቁና ይሖዋን በታማኝነት ማገልገል ጀመሩ። ይህችን ክርስቲያን ሴት ይሖዋ እጅግ አብዝቶ አልባረካትምን?
ጸሎቶቻቸው መልስ አገኙ
በፊተኛው አንቀጽ ላይ የተጠቀሰችው ሴት የተናገረቻቸውን ቃላት ታስታውሳለህን? ጸሎቷ እንደተመለሰላት ተሰምቷት አያውቅም። ሆኖም አምላክ ጸሎቷን እየመለሰላት እንደነበረ በኋላ አስተዋለች። ሴትየዋ የጸለየችባቸውን ነገሮች መዝግባ ይዛ ነበር። አንድ ቀን ማስታወሻ ደብተሯን ስታገላብጥ ይሖዋ አብዛኞቹን ጸሎቶቿን፣ እሷ ራሷ የረሳቻቸውንም ሳይቀር እንደመለሰላት ተገነዘበች። በመሆኑም አምላክ እንደሚያስብላትና እሷን ከሁሉ ይበልጥ በሚጠቅማት መንገድ ለጸሎቶቿ በርህራሄ መልስ እንደሚሰጥ አወቀች።
ጸሎቶችህ መልስ እንደማያገኙ ከተሰማህ ራስህን “የጸሎት ሰሚ” ከሆነው ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና አለኝን? ካልሆነ ስለሱ ለመማርና ከውስን አገልጋዮቹ አንዱ ለመሆን እርምጃ እየወሰድኩ ነውን?’ ብለህ ጠይቅ። አምላክ የሚያፈቅሩትና ፈቃዱን የሚያደርጉ ሰዎች ለሚያቀርቡለት ጸሎት መልስ ይሰጣል። “በጸሎት ይጸናሉ።” እርሱም እንደ ኢየሱስ ይሰማቸዋል። (ሮሜ 12:12) ስለዚህ ለይሖዋ “ልብህን አፍስስ” እና ፈቃዱን አድርግ። (መዝሙር 62:8) ከዚያም ጸሎትህ ይሰማል።
በዛሬው ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለአንድ ልዩ ነገር እየጸለዩ ነው። አዎን ጸሎታቸውም እየተሰማ ነው። እንዲህ ዓይነት ጸሎቶች እንደሚሰሙ ለምን እርግጠኞች መሆን እንደምንችል እንመልከት።