የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 3/15 ገጽ 21-24
  • ጡረታ መውጣት አያስፈልገንም!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጡረታ መውጣት አያስፈልገንም!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ደስተኛ ያደረጋቸው ምንድን ነው?
  • ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ለመለማመድ ፈቃደኛ መሆን
  • የጤና ችግሮችን መቋቋም
  • አሁንም ሥራውን እያከናወኑ ነው
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 3/15 ገጽ 21-24

ጡረታ መውጣት አያስፈልገንም!

በጃፓን ቶኪዮ ውስጥ የሚገኘውን አንድ ለየት ያለ መኖሪያ ቤት ስትጎበኝ “ጡረታ መውጣት አያስፈልገንም” የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ነገር ትመለከታለህ። በአማካይ የ70 ዓመት ዕድሜ ያላቸው 22 ወንዶችና ሴቶችን ያቀፈ አንድ ቤተሰብ በዚህ ቤት ውስጥ ይኖራል። እዚህ በአንድነት እንዲኖሩ ያስቻላቸው ሥጋዊ ዝምድና ሳይሆን አንድ የጋራ ፍላጎት ነው። ይህም የሚስዮናዊ አገልግሎት ነው። እነዚህ ሚስዮናውያን በጠቅላላ ለ1,026 ዓመታት በሙሉ ጊዜ የስብከት ሥራ ያለመታከት በጽናት አገልግለዋል! በዕድሜ ከሁሉም የላቁት ሦስቱ የቤተሰቡ አባላት የተወለዱት በ1910 ነበር። ሰባቱ ደግሞ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የጀመሩት ገና በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እያሉ ነበር። ዘጠኙ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በጃፓን የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ከጅምሩ አንስቶ ያደረገውን እድገት ተመልክተዋል።—ኢሳይያስ 60:22

ይሁን እንጂ ይህ ባለ ስድስት ፎቅ የቀድሞ የመጠበቂያ ግንብ ቅርንጫፍ ሕንፃ በውስጡ የሚኖሩት ሚስዮናውያን በሚያሳዩት መንፈስና በሰዎች ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ በሚያሳድረው ዝንባሌያቸው የተነሣ መበረታቻ የሚገኝበት ቦታ ነው። ምንም እንኳን አብዛኞቹ ከዕድሜ መግፋትና ከጤና ችግር ጋር በተያያዘ አካላዊ አቅማቸው ውስን ቢሆንም ከእነዚህ መንፈሳዊ ተዋጊዎች መካከል ሥራውን ለመተው የፈለገ የለም። የጃፓን ወንድሞች ሕንፃውን ሙሉ ለሙሉ አድሰው ለመውጫና ለመውረጃ የሚያገለግል አሳንሱርና በምድር ቤት ውስጥ የመንግሥት አዳራሽ ሠርተውላቸዋል።

ደስተኛ ያደረጋቸው ምንድን ነው?

እነዚህ ሚስዮናውያን በተሰጣቸው የሥራ ምድብ ላይ ረዥም ዓመታት በማሳለፋቸው ምክንያት ይህ ሕንፃ እንደ ቤታቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። “ባለፈው የክረምት ወር በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ አውስትራሊያ ተመልሼ በሄድኩኝ ጊዜ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ወደ ቤቴ ለመመለስ ተቻኩዬ ነበር!” በማለት በዕድሜ በጣም ከገፉት የቤተሰቡ አባላት መካከል አንዷ ተናግራለች። የሚያገለግሉትን ሕዝብ ያፈቅራሉ፤ እንዲሁም ለሕዝቡ የጠለቀ የመውደድ ስሜት አዳብረዋል። ከብዙ ዓመታት በፊት ያከናወኗቸውን የሥራ እንቅስቃሴዎች የሚያስታውሱዋቸው ስሜታቸውን የሚኮረኩሩ ደብዳቤዎችና የስልክ ጥሪዎች ይደርሷቸዋል።

ይህ በትጋት ማገልገላቸው ያስገኘላቸው ውጤት ነው። ሚስዮናውያኑ ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር ተገፋፍተው በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር የአምላክን ቃል በጥድፊያ ስሜት ሰብከዋል። (ከ2 ጢሞቴዎስ 4:2 አዓት ጋር አወዳድር።) በጃፓን ለ37 ዓመታት ያገለገለችው ቬራ መካይ “ይሖዋን እያገለገልን በመሆናችን ደስተኞች እንድንሆን ራሳችንን አሠልጥነናል” በማለት ተናግራለች። “በር ስናንኳኳ ማንም ሰው ብቅ ባይልም እንኳን ስለ ይሖዋ ለመመሥከር ደጃፋቸው ላይ ተገኝተናል።”

ከእነዚህ ሚስዮናውያን መካከል አሥራ ሁለቱ ጨርሶ ያላገቡ ቢሆንም ሐሳባቸው ሳይከፋፈል ጌታን ለማገልገል በመቻላቸው ደስተኞች ናቸው። (1 ቆሮንቶስ 7:35) ከእነዚህ መካከል ለ43 ዓመታት በሚስዮናዊነት ያገለገለችው ግላደስ ግሪጎሪ ትገኝበታለች። “ለይሖዋ አገልግሎት ከበፊቱ የበለጠ ሰፊ ነፃነት ለማግኘት ስል ወደ አቅኚነት ሥራ፣ ከዚያም ወደ ጊልያድ [የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት] ከዚያም ወደ ሚስዮናዊነት ሥራ ገባሁ። ነጠላ ለመሆን ባልሳልም እንኳን በነጠላነት ኖሬአለሁ። እንደሌሎች ብዙ ጓደኞቼ ሁሉ እኔም በዚህ ተጸጽቼ አላውቅም።”

ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ለመለማመድ ፈቃደኛ መሆን

አንዳንድ ሰዎች በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ ሐሳበ ግትር የሚሆኑ ቢሆንም ሚስዮናውያኑ ግን ራሳቸውን ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ለማለማመድ ፈቃደኞች ነበሩ። ሎኧስ ዲየር፣ ሞሊ ሄሮን፣ እንዲሁም ሌና እና ማርግሪት ቪንትለር በቶኪዮ መኖሪያዎች በብዛት በሚገኙበት በአንድ ትንሽ የሚስዮናውያን መኖሪያ ቤት ውስጥ ይኖሩ ነበር። እዚያም ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት ኖረዋል። በእዚያ አካባቢ ከሚኖሩ ሰዎችም ጋር በደንብ ተወዳጅተው ነበር። ሁለቱ እህትማማቾች ሌና ቪንትለርና ማርግሪት ቪንትለር በአገልግሎት ክልላቸው ውስጥ 40 የመጽሔት ደንበኞች ነበሯቸው፤ ሞሊ እና ሎኧስ ደግሞ በእነርሱ የአገልግሎት ክልል ውስጥ 74 የመጽሔት ደንበኞች ነበሯቸው። ከዚያም በመሃል ቶኪዮ ወደሚገኘው ባለ ስድስት ፎቅ የሚስዮናውያን መኖሪያ ቤት እንዲዛወሩ ማኅበሩ ጥያቄ አቀረበላቸው። “በመጀመሪያ አዝኜ ነበር፤ ደስ አላለኝም ነበር” በማለት ሌና ሐቁን ተናግራለች። ይሁን እንጂ ሁል ጊዜም እንደሚያደርጉት ራሳቸውን ከአዲሱ የመኖሪያ ሁኔታ ጋር አለማምደዋል። አሁን እንዴት ይሰማቸዋል? “በጣም ደስተኞች ነን” በማለት ሌና ትመልሳለች። “አሁን ምግብ የሚያዘጋጁልንና ቤት የሚያጸዱልን ሁለት የቤቴል ወንድሞች እዚህ አሉ። ጥሩ እንክብካቤ እናገኛለን።” ሁሉም “የይሖዋ ድርጅት የሚያደርግልን ፍቅር የተሞላበት እንክብካቤ በጽናት መጓዝ እንድንችል ረድቶናል” ብላ ከተናገረችው ከሎኧስ አባባል ጋር ይስማማሉ።

ኖሪን ቶምሶንም ራሷን ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር አለማምዳለች። “በጃፓን ጉባኤዎች በአንድ አውራጃ ይጠቃለሉ በነበረበት ጊዜ ለ15 ዓመታት ባለቤቴ [የኒውዚላንድ ተወላጅ ነው] የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኖ ሲሠራ አብሬው የማገልገል መብት አግኝቼአለሁ” ስትል ትናገራለች። ይሁን እንጂ የባለቤቷ ጤንነት እየተቃወሰ ሄደ። ከ18 ዓመት በፊት በሞተው ባሏ ምክንያት በሕይወቷ ውስጥ የገጠማትን ታላቅ ፈተና መቋቋም ነበረባት። “በጸሎትና በአገልግሎት በመጠመድ ከማገኘው እርዳታ በተጨማሪ በጠቅላላው ጃፓን የሚገኙ ወንድሞች ያሳዩኝ የነበረው ፍቅር በዚያን ጊዜ በሚስዮናዊነት ሥራ እንድቀጥል አስችሎኛል” በማለት ተናግራለች።

የጤና ችግሮችን መቋቋም

“አብዛኞቹ የጤና ችግር አለባቸው። ይሁን እንጂ ደስተኞች ናቸው፤ ለማገልገል ያላቸው ፍላጎት ደግሞ አስደናቂ ነው” በማለት የሚስዮናውያኑ መኖሪያ ቤት የበላይ ተመልካች የሆነው አልበርት ፓስተር ይናገራል። ሚስዮናውያኑን ለመንከባከብ አንድ ዶክተርና ነርስ የሆነችው ሚስቱ በዚህ መኖሪያ ውስጥ እንዲሠሩ ተመድበዋል።

አንድ ቀን ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት የጊልያድ ትምህርት ቤት የ11ኛው ክፍል ምሩቅ የሆነችው ኤልሲ ታኒጋዋ በድንገት የግራ ዓይኗ ማየት ተሳነው። ከአራት ወራት በኋላ የቀኝ ዓይኗም ተደገመ። “ከዚህ ቀደም አገለግል እንደነበረው ማገልገል ባለመቻሌ አንዳንድ ጊዜ የኀዘን ስሜት ይሰማኛል። ይሁን እንጂ በማኅበሩ የደግነት ዝግጅትና በጓደኛዬና በሌሎች ፍቅራዊ ርዳታ አማካኝነት በይሖዋ አገልግሎት ደስታ ማግኘቴን ቀጥያለሁ” በማለት ኤልሲ ተናግራለች።

ከኤልሲ ጋር አብረው ከጊልያድ የተመረቁት ሺኒቺ ቶሃራ እና ሚስቱ ማሳኮ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከጤናቸው ጋር በተያያዘ ብዙ ፈተናዎች አጋጥመዋቸዋል። የተዋጣለት ተናጋሪ የሆነው ሺኒቺ በዓይኑ መታወር ምክንያት የያዛቸውን ማስታወሻዎች ማንበብ አለመቻሉ ትልቅ ፈተና ሆኖበታል። በቅርብ ዓመታት ቀላልና ከባድ የቀዶ ሕክምና ቢደረግለትም እንኳ አሁን እየረዳው ስላለው የ90 ዓመት ዕድሜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ሲናገር ዓይኖቹ ብሩህ ሆነው ይታያሉ።

ምንም እንኳን እነዚህ ሚስዮናውያን ‘የሥጋ መውጊያ’ ቢኖርባቸውም ድካማቸውን በተመለከተ “ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና” እንዳለው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት አቋም አላቸው። (2 ቆሮንቶስ 12:7–10) በእርግጥም ኃይለኞች ናቸው! በየቀኑ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ላይ ለሚደረገው የማለዳ አምልኮ ለመገኘት ቀደም ብለው ከእንቅልፋቸው ይነሳሉ። ቁርስ ከተመገቡ በኋላ አገልግሎት ለመውጣት አካላዊ አቅማቸው የሚፈቅድላቸው ወደ መስክ አገልግሎት በማለዳ ይሰማራሉ።

አዘውትረው ወደ አገልግሎት ከሚሄዱት መካከል ሪቻርድ እና መርትል ሺሮማ ይገኙበታል። መርትል በ1978 አርተሪኦስከለሮሲስ የተባለ በሽታ ስለያዛት በአንጎሏ ውስጥ ደም ይረጋና ራሷን እንድትስት ያደርጋት ነበር። ይሁን እንጂ እስከ ኅዳር 1987 ድረስ ከባሏ ጋር በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ አብራ አገልግላለች። አሁን የ70 ዓመት አዛውንት የሆነው ሪቻርድ መርትልን በሁሉም ነገር ይረዳታል። ከሌሊቱ 11 ሰዓት ይነሳና ከአልጋ ላይ ያወርዳታል፣ ያጥባታል፣ ያለብሳታል፣ ያሰማምራትና እያጎረሰ ይመግባታል። ከዚያም በተሽከርካሪ ወንበሯ ላይ ያስቀምጣትና በየቀኑ ጠዋት ጠዋት ወደ መስክ አገልግሎት ይዟት በመሄድ ለአንድ ሰዓት ያህል ከቤት ወደ ቤት ያገለግላሉ፤ ከዚያም በአውቶቡስ ፌርማታዎች ለሰዎች ይመሠክራሉ። መርትል በአሁኑ ጊዜ መናገር አትችልም። ይሁን እንጂ ለመጨረሻ ጊዜ የተናገረቻቸው ቃላት ዴንዶ ዴንዶ የሚሉትን ቃላት ነበር። ይህም በጃፖንኛ “ስብከት ስብከት” ማለት ነው።

ሳንድራ ሱሚዳ የተባለችው ሴት ልጃቸው እነርሱን ለመርዳት ወደ ሚስዮናውያን መኖሪያ ቤት ተዘዋውራለች። ሳንድራ የምትወደውን ባሏን በልብ በሽታ ምክንያት በሞት አጥታለች። እርሷና ባሏ ሚስዮናዊ ሆነው ያገለግሉ ከነበሩበት ከጉዋም እንደገና ወደ ጃፓን እንድትመለስ በማድረጉ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርን የደግነት ዝግጅት ታደንቃለች። “እኔ የነበርኩት በጉዋም ስለነበር ወላጆቼን ብዙም መርዳት እንደማልችል ሁል ጊዜ ይሰማኝ ነበር” በማለት ትናገራለች። “እህቴ ጆአን በዚህ መኖሪያ ቤት ውስጥ ሆና ትንከባከባቸው ነበር። ስለዚህ አጋጣሚ ሳገኝ ደስታ ተሰማኝ። ባለቤቴ በድንገት ስለሞተብኝ በዚህ ቦታ እንደማስፈልግ ማወቄ ለኔ ፈውስ የማገኝበት ሕክምና ሆኖልኛል።”

አሁንም ሥራውን እያከናወኑ ነው

ምንም እንኳን ሚስዮናውያኑ እርጅና እየተጫጫናቸው ቢሆንም ያላቸው የሚስዮናዊነት መንፈስ እንዲጠፋ አልፈቀዱም። (መዝሙር 90:10፤ ሮሜ 5:12) መጀመሪያ ወደ ጃፓን ከመጡት የጊልያድ ተመራቂዎች መካከል የሆኑት ጄሪ እና ዮሺ ቶማ በሺቡያ ከተማ ውስጥ ወደሚገኘው የንግድ ማዕከል በመሄድ አሁንም ያገለግላሉ። “በ1949 በዚህ ሥፍራ ላይ ወደተሠራው ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ ስንመጣ ከአንዱ ሰው ሠራሽ ዋሻ ወደ ሌላው እንሄድ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ቶኪዮ ትልቅ ከተማ ሆናለች። አሁን ስላረጀን በፊት እናከናውን የነበረውን ያህል መሥራት አንችልም። ይሁን እንጂ ከስብከት ስንመለስ መንፈሳችን በጣም ይታደሳል።” በማለት ዮሺ ትናገራለች።

ሊሊያን ሳምሶን ሚስዮናዊ ሆና በጃፓን ለ40 ዓመታት ያገለገለች ሲሆን አገልግሎቷንም በጣም ትወደዋለች። “በሽተኛ እናቷን ለማስታመም ወደ ሃዋይ የሄደችው ሚስዮናዊ ጓደኛዬ አደሊን ናኮ ታስጠናት የነበረችውን የ80 ዓመት ዕድሜ ያላትን ሴት አሁን በመርዳት ላይ ነኝ። ሴትየዋ ከቀድሞ አባቶች አምልኮ ጋር በተያያዘ የነበረባትን ችግር ተቋቁማ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የመንግሥቱ አስፋፊ ሆናለች። ወደ ቤተ መቅደስ ሄዳ ለቄሱ ሚስት ‘ወደ ክርስትና ተለውጫለሁ!’” አለቻት። በሕይወቷ እንዲህ ያሉ ደስታዎች በማግኘቷ ሊሊያን በ19 ዓመቷ ዓለማዊ ሥራዋን አቋርጣ አቅኚነት የጀመረችበትን ቀን ስታስታውስ ምንም ዓይነት ጸጸት አይሰማትም።

ከ45 ዓመታት በላይ ሚስዮናዊ ጓደኛሞች ሆነው ያገለገሉት ሩት ኡልሪክ እና ማርታ ሄስ በዚህ የሚስዮናውያን መኖሪያ ቤት ውስጥ ሆነው ለ35 ዓመታት ሠርተዋል። ራሳቸውን ከአገልግሎት ክልሉ ጋር በሚገባ አለማምደው ነበር። አንድ ጊዜ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች “ከቤት ወደ ቤት ለመሄድ ፊትሽን መዋስ እችላለሁ?” ሲል ማርታን ጠይቋታል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ሰዎችን ማነጋገር ሲፈልግ ትንሽ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልገው ነበር፤ ይሁን እንጂ ሰዎቹ ማርታን ስለሚያውቋት በቀላሉ መጽሔት ከእርሷ ይወስዳሉ።

ሩት በጤና መታወክ ምከንያት ማንበብ የማትችል አንዲት የመጽሔት ደንበኛ አለቻት። ያም ሆኖ ግን ሴትየዋ መጽሔት መውሰዷን አላቋረጠችም ነበር፤ እንዲያውም ጠንካራ ሽፋን ያለውን የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ የተባለውንም መጽሐፍ ወሰደች። ሩት ጽሑፎቹን ማንም ሰው የማያነባቸው ከሆነ መጽሔቶቹን ለዚህች ሴት መውሰዴን መቀጠል ይኖርብኛል እንዴ? ስትል አሰበች። ከዚያም አንድ ቀን የሴትየዋ ባል ፍለጋ የተባለውን መጽሐፍ ይዞ ወደ ሩት በመቅረብ “ይህ በጣም ግሩም መጽሐፍ ነው! ሁለት ጊዜ ከዳር እስከ ዳር አንብቤዋለሁ” አላት። ሩት ከእርሱና ከሚስቱ ጋር የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረች።

ይህ የሚስዮናውያን መኖሪያ ቤት ራሱ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ይስባል። አንድ ወጣት በአንድ ምሽት ወደዚህ ቤት መጥቶ እንዲህ አለ፦ “እዚህ ከመጣሁ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እርዳታ ማግኘት እንደምችል አሳምሬ አውቃለሁ።” የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረለት። ይህ ሰው በአንድ የቻይና ሬስቶራንት ውስጥ ምግብ በማብሰል ሥራ ከረዥም ዓመት በፊት ከተወገደች ከአንዲት ሴት ጋር አብሮ ይሠራል። አንድ አስፋፊ በዚህ ሬስቶራንት ውስጥ ያበረከታቸው መጽሔቶች በምግብ ማብሰያው ክፍል ውስጥ ተቀምጠው ያገኟቸዋል። ምግብ የሚያበስለው ይህ ወጣት መጽሔቶቹን ስለወደዳቸው የቀድሞዋን ምሥክር ጥያቄዎችን መጠየቅ ጀመረ። ለጥያቄዎቹ መልስ መስጠት ስላልቻለች ወደ ሚስዮናውያኑ መኖሪያ ቤት እንዲሄድ ነገረችው። አሁን እሱ ዲያቆንና አቅኚ ሆኖ ያገለግላል። ከጊዜ በኋላ የተወገደችውም ሴት ከውገዳ ተመልሳ በአሁኑ ጊዜ የዘወትር አቅኚ ሆናለች።

በዚህ ቤት ውስጥ የሚኖሩት ሚስዮናውያን በጠቅላላ ይሖዋ ያደረገላቸውን ነገሮች ያደንቃሉ። ከአውስትራሊያ፣ ከካናዳ፣ ከሃዋይ፣ ከስዊዘርላንድና ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡ ሲሆን 11ዱ ከ11ኛው ክፍል ወይም ከዚያ ቀደም ካሉት የጊልያድ የሚስዮናውያን ክፍሎች የተመረቁ ናቸው። በጃፓን የመንግሥቱ ሥራ ያደረገውን እድገት ተመልክተዋል። “ጎለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም” በማለት የተናገረው የንጉሥ ዳዊት ዓይነት ስሜት አላቸው። (መዝሙር 37:25) ለአምላክ ፍቅራዊ እንክብካቤ ባላቸው አድናቆት የተነሳ እነዚህ ሚስዮናውያን ጡረታ ለመውጣት ሳይሆን ይሖዋን በማገልገል ለመቀጠል ቆርጠዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ