እውነትን የሚያገኙ ሰዎች የሚጠብቃቸው ደስታ
አንድ ፊንላንዳዊ ዘ ዲቫይን ፕላን ኦቭ ዘ ኤጅዝ (መለኮታዊው የዘመናት እቅድ) የተባለውን መጽሐፍ ጣሪያ ሥር ባለ ቆጥ መሳይ ቦታ አገኘ። ወዲያውኑ መጽሐፉን ማንበብ ጀመረና ብዙም ሳይቆይ ለራሱ ‘እውነት ይህ ነው፣ እውነት ይህ ነው’ አለ። ከጣሪያው ሥር ካለው ቆጥ መሳይ ቦታ እየወረደ ለሚስቱ “እውነተኛውን ሃይማኖት አገኘሁ” አላት።
ይህ ተሞክሮ ይህ ሰው እውነትን ካገኘበት መንገድ አንፃር ሲታይ ያልተለመደ ነው፤ ሆኖም ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ተመሳሳይ ስሜት ሊገልጹ ይችላሉ። ሁሉም እውነትን ማግኘት የሚያመጣውን ደስታ ሊነግሩህ ይችላሉ። የሚከተሉት ተሞክሮዎች ይህን ያጎላሉ።
እውነተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ደስታን ያስገኛሉ
ማርጋሪታ ኮኒገር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመን ሙኒክ ውስጥ ነበር ያደገችው። በወቅቱ በቦምብ የተደበደቡና የተቃጠሉ ቤቶች በብዛት ይታዩ ነበር። ወንድሟ በጦርነት ሞቶ ነበር። በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ስትገኝ ለጀርመን ወታደሮችና ለናዚው መሪ ማለትም ለሂትለር ሲጸለይ ሰማች። ከጦርነቱ በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኝ አንድ ኮሌጅ ውስጥ በተማሪዎች ልውውጥ መልክ የሚደረግ የነፃ ትምህርት እድል አገኘች። ሰዎች የወዳጅነት መንፈስ ስላሳዩአት የሰዎች የተፈጥሮ ፍላጎት በሰላም መኖር ሆኖ ሳለ በጦርነት ወቅት እንዳይተማመኑና እርስ በርስ እንዲጠላሉ የሚገፋፋቸው ነገር ምን እንደሆነ ጥያቄ ፈጠረባት። ወደ ሙኒክ ስትመለስ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘችና ከእነሱ ጋር ባደረገችው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለጥያቄዎቿ መልስ አገኘች። እንዲህ አለች፦ “በነገሩ ውስጥ ክፉ መናፍስት እንዳሉበት ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳዩኝ . . . መጽሐፍ ቅዱስ ‘የዓለም ገዢዎች’ ይላቸዋል፤ እንዲያውም ሰይጣን ‘ዓለምን ሁሉ እያሳተ’ እንዳለ ይናገራል። . . . መንግሥታትና ሰዎች ከሚያደርጓቸው ለአምላክ አክብሮት የሌላቸውና ዲያብሎሳዊ ድርጊቶች አንፃር ሲታይ ይህ መልስ ምንኛ ምክንያታዊና አጥጋቢ ነው!”—ኤፌሶን 6:12፤ ራእይ 12:9
ማርጋሪታ ቀጥላ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “አምላክ የምድርን ችግሮች ለመፍታት ያደረገውን ዝግጅት ማወቄ ከፍተኛ ደስታ አምጥቶልኛል። የሰዎች ችግሮች የሚፈቱት ዓለማውያን ምሁራን እንደሚሉት በሰዎች ፖለቲካ ወይም አስተዳደር አይደለም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ አዲስ ሰማያዊ መንግሥት የምድርን ጉዳዮች እንደሚቆጣጠር ያሳያል። . . . ኢየሱስ ተከታዮቹን ‘መንግሥትህ ትምጣ’ ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸው ነበር። . . . ይህ መንግሥት እውን መስተዳድር እንደሆነና እውነተኛ የሆነ ዓለም አቀፍ ሰላም የሚገኘው በእሱ አማካኝት ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ጀምሬ ነበር።” ማርጋሪታ ለ30 ዓመታት ያህል በአምስት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በሚስዮናዊነት አገልግላለች፤ ከዚህም ውስጥ ያለፉትን 19 ዓመታት በቡርኪናፋሶ ውስጥ ኦጋዱጉ በተባለ ከተማ ለሚገኙ ትሑት ሰዎች እውነትን በማወጅ አሳልፋለች።
የማርጋሪታ ተሞክሮ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ተሞክሮ አይደለም። ብዙ ሰዎች በሁለቱም ተፋላሚ ቡድኖች ወገን የተሰለፉ የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ድል ለማግኘት ወደ አምላክ ሲጸልዩ ሲመለከቱ ተመሳሳይ የሆነ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች፣ አምላክ ሰዎች በሚያደርጓቸው ጦርነቶች ውስጥ ጣልቃ የማይገባ መሆኑን ሆኖም ይህ የሚሆነው ‘ዓለም በሞላው በክፉው ስለ ተያዘ’ እንደሆነ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ ምክንያታዊ እንደሆነ ይገነዘባሉ። እነዚህ እውነት ፈላጊዎች እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘የዓለም ክፍል እንዳይደሉ’ ከዚህ ይልቅ በዓለም ጉዳዮች ገለልተኞች ሆኖ መኖር እንዳለባቸው ይማራሉ። እነዚህ ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ይህን አቋም እንደያዙ ስለሚገነዘቡ እውነትን እንዳገኙ ያምናሉ። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች አምላክ ክፋትን ለምን እንደፈቀደና በመንግሥቱ አማካኝነት በቅርቡ በምድር ላይ እንዴት ሰላምና ጽድቅ እንደሚያሰፍን ሲማሩ ተስፋቸውና ደስታቸው እየጨመረ ይሄዳል።—1 ዮሐንስ 5:19፤ ዮሐንስ 17:16፤ ማቴዎስ 6:9, 10
እውነተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ደስታ ያስገኛሉ
በኢኳዶር የሚገኘው ዳንኤል ሮስሮ ሕይወት ትርጉም አልባ እንደሆነ ተሰማው፤ ስለዚህ መጠጥ በብዛት መጠጣት ጀመረ። የሚሰበሰብበት ቤተ ክርስቲያን ወደፊት የሚጠብቀው ሞትና እሳታማ ሲኦል እንደሆነ አስተምሮታል። እሱ ያሳየው ምላሽ “መቃጠሌ ካልቀረ ለምን አልጠጣም!” የሚል ነበር። ስምንት አባላት የነበሩት ቤተሰብ ቢኖረውም የሚያስፈልጋቸውን ነገር አያሟላላቸውም ነበር፤ ዴሊያ ከተባለችው ሚስቱ ጋር ሁልጊዜ ይጣላ ነበር። አንድ ቀን እሑድ ጠዋት የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው ሲያነጋግሯቸውና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምሩ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ተከሰተ። ዳንኤል ለመጀመሪያ ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች የወረዳ ስብሰባ ላይ ሲገኝ እውነትን እንዳገኘ ተገነዘበ። እንዲህ አለ፦ “ድርጅቱ በአድናቆት እንድዋጥ አድርጎኛል። እጅግ ብዙ ሰዎች በስምምነት አንድ ላይ ሆነው ይታያሉ። በዚህ ብዙ ሕዝብ መሃል መሆን ያስደስትሃል። ማንም አያጨስም። የብልግና አነጋገር አይሰማም። . . . ‘እውነት ይህ ነው!’ ብዬ እንዳሰብኩ ትዝ ይለኛል። እኔን የነካኝ የሞት ፍራቻ ወይም የዓለም መጨረሻ ያስከተለብኝ ፍርሃት አልነበረም። የድርጅቱ ንጽሕና ነበር።”
ጠቅላላው የዳንኤል ቤተሰብ የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ባዋሉ መጠን የቤተሰባቸው ኑሮና ኢኮኖሚያቸው ተሻሻለ። ዴሊያ ሮስሮ እንዲህ ትላለች፦ “በሕይወቴ ውስጥ ያገኘሁት መሻሻል ሁሉ የመጣው በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ምክንያት ነው። ልጆቼ ያለ አምላክ ቃል ቢኖሩ ኖሮ ምን ይደርስባቸው እንደነበር ማን ያውቃል? ሰባቱም የተጠመቁና ሚዛናዊ አቋም ያላቸው ናቸው። እውነት ለእኔ ፍጹም አዲስ ሕይወት፣ ልዩ ደስታ ሆኖልኛል።”
የዳንኤል ቤተሰብ ተሞክሮ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ተሞክሮ አይደለም። በዘመናችን ያሉ አያሌ ሰዎች ብዙ ችግሮች ይደርሱባቸዋል። ለዚህ አንዱ ምክንያት የሚሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ደንቦች በቀድሞቹ ትውልዶች የሚከበሩትን ያህል በአሁኑ ወቅት አለመከበራቸው ነው። የሰዎችን ጠባይ መቻል አሊያም ጊዜው እየተለወጠ ሲሄድ የቀድሞዎቹ የሥነ ምግባር ደንቦች ጊዜ ያለፈባቸው ይሆናሉ በሚል ሰበብ ብዙ ሃይማኖቶች ይህን አዝማሚያ ተከትለዋል። ስለዚህ እንደ ሌሎች ሁሉ የዳንኤል ቤተሰብም ያለ መጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ በጭፍን እንዲሄድ ተትቶ ነበር። ሆኖም እንደነዚህ ያሉት ትሑት ሰዎች አምላክ ለሥነ ምግባርና ለቤተሰብ ኑሮ ያለውን አመለካከት ሲገነዘቡ ወዲያውኑ የተማሩትን ይሠሩበታል። እንዲህ ማድረግ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ከታሪካቸው መመልከት እንችላለን።
ደስታ መኮትኮት አለበት
ይሁን እንጂ ይህ ማለት ክርስቲያን ሁልጊዜ በፍስሐ ይኖራል ማለት አይደለም። ሰዎች በጥቅሉ የሚያጋጥሟቸው እንደ ሥራ ማጣት፣ በሽታና ሞት ያሉት ችግሮች ክርስቲያኖችንም ያጋጥሟቸዋል። በተጨማሪም ክርስቲያኖች ከራሳቸው አለፍጽምናና ድክመቶች ጋር ያለማቋረጥ መታገል አለባቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ሎጥ የሰዶም ከተማ ሰዎች በፈጸሙት ‘በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበር’ ሲል ይገልጻል። ታማኝ ክርስቲያኖች መጥፎ ሁኔታዎችን ሲመለከቱ ከዚህ ዓይነቱ ስሜት ለማምለጥ አይችሉም።—2 ጴጥሮስ 2:7, 8
ሆኖም እውነትን ያወቁ ሰዎች የሚያገኙት ጥቅም አለ። ለምሳሌ ያህል ሰው የሞተበት በሐዘን ላይ ያለ አንድ አማኝ ‘ተስፋ የሌላቸውን ሰዎች ያህል አያዝንም።’ ሐዘኑ ከመጠን በላይ አይሆንም። ይህ በሌሎች ችግሮችም አንፃር ቢሆን እውነት ነው። እውነትን ያወቀ ሰው በአሁኑ ወቅት ያሉት ችግሮች ጊዜያዊ ብቻ እንደሆኑ ያውቃል። ተስፋ በችግር ወቅት መጽናትን ቀላል ያደርግልናል። በተጨማሪም ሚዛናዊ አኗኗር መያዝ ይጠቅማል።—1 ተሰሎንቄ 4:13
ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፣ ደስ ይበላችሁ” ሲል መክሯል። (ፊልጵስዩስ 4:4) ይህ ጥቅስ ደስታ ሁላችንም ልናገኘው የምንችለው ነገር ቢሆንም ላይገኝም እንደሚችል ያሳያል። ይህ አሮጌ ሥርዓት የሚያስከትላቸው ጭንቀቶች ለደስታ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ መንፈስ ፍሬዎች አንዱ የሆነውን ደስታን መኮትኮት እንደሚያስፈልገን ይነግረናል። (ገላትያ 5:22) የእውነት እውቀትን መውሰድህን ከቀጠልክና አሁን ያመጣልህንና ወደፊት የሚያመጣልህን መንፈሳዊ ሀብቶች ካስታወስክ ደስታህ እንዳይጠፋ ማድረግ ትችላለህ። አምላክ ከሰዎች ዓይኖች ‘እንባዎችን ሁሉ ወደሚያብስበት’ እና ‘ሐዘንም ቢሆን ወይም ሥቃይ ወደማይኖርበት’ ጊዜ በቀረብን መጠን ደስታህ ይበልጥ እየጨመረ ይሄዳል።—ራእይ 21:4
[በገጽ 8 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ብዙዎች በይሖዋ ምሥክሮች ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ባዩት ደስታና ግሩም አደረጃጀት ተማርከዋል