ሞዛምቢክ ውስጥ “ጨው መሸጥ”
የሞዛምቢክ የአገር ኮሚቴ አባል የሆነው ፍራንሲስኮ ኮና “በተሃድሶ ካምፕ” ውስጥ አሥር ዓመት አሳልፎ ነበር። የራሱን ተሞክሮ እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “ለተወሰኑ ጊዜያት በዚህ ቦታ እንደምንቆይ ስለ አወቅሁ የዘወትር አቅኚ ሆኜ መቀጠል እችል እንደሆነ የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ጠየቅሁት። በአቅኚነት ለመቀጠል ከአንድ አቅኚ የሚፈለገውን ሰዓት ማሟላት እንደሚኖርብኝ ነገረኝ። በካምፑ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው ሳለ እንዴት በሕዝብ ፊት ለሚደረገው አገልግሎት በቂ ጊዜ ማዋል እንደምችል ጠየቀኝ። የምሰብክላቸው ሰዎች ለማግኘት ካለንበት ቦታ 47 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኝ ሚላንዥ ወደተባለች ከተማ እንደምሄድ ነገርኩት።
“ምንም እንኳ ከካምፑ እንድንወጣ በግልጽ ባይፈቀድልንም ይህ መመሪያ በጥብቅ ሥራ ላይ አልዋለም ነበር። ቁጥቋጦ ወደሚገኝበት ቦታ በመሄድ ለአካባቢው ሰዎች መመሥከር የምችልበት መንገድ እንዳገኝ ተንበርክኬ እጸልይ እንደነበር አስታውሳለሁ። ይሖዋ ወዲያውኑ ለጸሎቴ መልስ ሰጠኝ።
“ብስክሌት ካለው አንድ ሰው ጋር ተገናኘሁ። ስለዚህ ከእርሱ ጋር አንድ ውል ተዋዋልን። ወደ አንድ ሄክታር የሚጠጋ የእርሻ መሬቱን የዝናብ ወቅት ከመጀመሩ በፊት ካለማሁለት ለድካሜ ዋጋ ይህችን ብስክሌት እንደሚሰጠኝ ተስማማ። ስለዚህ በየቀኑ ጠዋት ጠዋት የእርሱን እርሻ ቦታ በመኮትኮት አሳለፍኩ። ይሖዋ ይህንን ስምምነት ባርኮታል፤ ምክንያቱም በመጨረሻ የራሴ የሆነ ብስክሌት አግኝቻለሁ።
“በውጤቱም ትልቅ ወደ ሆነችው ሚላንዥ ከተማ ለመሄድና በዚህ ፍሬያማ መስክ አቅኚነቴን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ችያለሁ። ሥራችን ታግዶ ስለነበር ለሰዎች እውነትን ለመንገር አንድ እቅድ ማውጣት ነበረብኝ። መጽሐፎችንና መጽሔቶችን ከሸሚዜ ውስጥ ሥር እሸጉጣለሁ፤ በአንድ ከረጢት ደግሞ ጥቂት ጨው እይዝና እሸጣለሁ። በ5 ሜቲኪስ (የሞዛምቢክ ገንዘብ) በመሸጥ ፋንታ 15 ሜቲኪስ አስከፍል ነበር። (በጣም ርካሽ ከሆነ ሰዎቹ ሁሉንም ይገዙትና ስብከቴን ለመቀጠል የሚያስችለኝ ምንም ጨው አይኖረኝም!) የማነጋግራቸው እንዲህ ነበር፦
“‘ጤና ይስጥልኝ! ጨው እየሸጥኩ ነው።’
“‘ስንት ስንት ነው?’
“‘አሥራ አምስት ሜቲኪስ’።
“‘አይ፣ ይቅርብኝ። በጣም ውድ ነው!’
“‘እውነት ነው፤ ውድ እንደሆነ እኔም እስማማለሁ። አሁን ውድ ነው ብለው ቢያስቡም እንኳ ወደፊት ትንሽ ከቆዩ ከዚህ የባሰ ውድ ይሆናል። ስለዚህ ጉዳይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስቀድሞ እንደተነገረ ያውቃሉ?’
“‘መጽሐፍ ቅዱሴ ውስጥ ይህንን ፈጽሞ አንብቤ አላውቅም’
“‘መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለ። እስቲ የርስዎን መጽሐፍ ቅዱስ ያምጡና ላሳይዎት።’
“በዚህ መንገድ የሰውዬውን መጽሐፍ ቅዱስ በመጠቀም ውይይት እናደርግ ስለነበር የኔ መጽሐፍ ቅዱስ ሸሚዜ ሥር እንደተሸጎጠ ይቆያል። ስለ አስጨናቂ ሁኔታዎችና ስለ ምግብ እጥረት የሚናገረውን ራእይ ምዕራፍ 6 እጠቅስላቸዋለሁ። አዎንታዊ ምላሽ እንዳላቸው ከተረዳሁ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት ወይም ደስተኛ የሚያደርግህ ምሥራች (በእንግሊዝኛ የሚገኝ) የተባለውን መጽሐፍ አወጣና መደበኛ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እጀምር ነበር።
“በውጤቱም በሚላንዥ ከተማ 15 ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን የያዘ አንድ ቡድን ለመመሥረት ችያለሁ። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ባለ ሥልጣኖች እንቅስቃሴያችንን ደረሱበት። አንድ ቀን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየመራሁ ሳለ ፓሊሶች ሳይታሰብ ወደ ቤት ገቡና ያዙን። የቤተሰቡን ትንንሽ ልጆች ጨምሮ ሁላችንም ወደ ከተማው እስር ቤት ተወሰድን። እዚያም አንድ ወር ካሳለፍን በኋላ ሁላችንም እንደገና ወደ ካምፑ ተላክን።”
ይህ ተሞክሮ የወንድሞቻችንን ቅንዓት አላሟሸሸውም። ከዚህ ይልቅ በአሁኑ ጊዜ ፍራንሲስኮና ቤተሰቡ በካምፑ ውስጥ ይኖሩ ከነበሩ በሺህ የሚቆጠሩ ወንድሞቻቸው ጋር በመሆን አምልኮታቸውንና ስብከታቸውን ሞዛምቢክ ውስጥ በነፃነት እያከናወኑ ነው።