“የሚንቀሳቀስ” ተራራ
በምዕራብ አየርላንድ የሚገኘው ድንቅ የሆነ ሾጣጣ ቅርጽ ያለው ክሮ ፓትሪክ ከአካባቢው ተራሮች ጎላ ብሎ ይታያል። በየዓመቱ የሐምሌ ወር የመጨረሻ እሁድ ላይ ለዓመታዊው ሃይማኖታዊ ጉዞ ወጣት ሽማግሌ ሳይባል 30,000 የሚያክሉ ሰዎች ወደ ተራራው አናት (765 ሜትር) ሲወጡ የተራራው ጫፍ የሚንቀሳቀስ ይመስላል።
በዚህ ቀን ተሳላሚዎች የሚወጡትና የሚወርዱት ጠባብና ኮሮኮንች በሆነ መንገድ እንዲሁም አደገኛ በሆኑ ቦታዎች ነው። እንዲያውም ወደ ላይ የሚደረገው ጉዞ ማገባደጂያ (ሦስት መቶ ሜትር ገደማ) ከፍተኛ አቀበት የሆነና በሚፈነቀሉ ድንጋዮች የተሞላ ነው፤ ይህም ተራራውን መውጣት አደገኛ እንዲሁም አድካሚ እንዲሆን አድርጎታል።
አንዳንዶች ተራራውን በባዶ እግራቸው ይወጣሉ፤ እንዲያውም ጥቂቶች የተወሰኑ ቦታዎችን በእምብርክክ ይወጣሉ። ባለፉት ጊዜያት ሃይማኖታዊው ጉዞ በምሽት በጨለማ ይጀመር ነበር።
ክሮ ፓትሪክ በጣም ብዙ ለሆኑ ሰዎች እንዲህ ያለ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ልማድ የሆነው ለምንድን ነው?
ሃይማኖታዊ ጉዞ የሚደረግበት ቦታ ሆኖ ከተቋቋመ ረዥም ጊዜ ሆኖታል
በአምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ መጀመሪያ ላይ የሮማው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪክን ሚስዮናዊ ጳጳስ አድርጎ ወደ አየርላንድ ላከው። ዋነኛ ዓላማው አየርላንዶችን ወደ ክርስትና ሃይማኖት መለወጥ የነበረ ሲሆን በሰበከባቸውና በሕዝቡ መካከል በሠራባቸው ዓመታት በዚያ ቦታ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት እንደጣለ ይታመናል።
ሥራው በመላ አገሪቱ ወደ ብዙ ቦታዎች እንዲጓዝ አድርጎታል። ከተጓዘባቸው ቦታዎች አንዱ ምዕራብ አየርላንድ ነበር፤ አንዳንድ ምንጮች እንደሚጠቁሙት 40 ቀንና ሌሊት በዚህ ሥፍራ በአንድ ተራራ ጫፍ ላይ ያሳለፈ ሲሆን ከዚያ በኋላ ይህ ተራራ ክሮ ፓትሪክ በመባል በእርሱ ተሰይሟል (“የፓትሪክ ኮረብታ” ማለት ነው)። እዚያም ተልዕኮው የተሳካ እንዲሆን ጾሟል እንዲሁም ጸልዮአል።
ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ስለሠራቸው ተግባራት የሚናገሩ ብዙ አፈ ታሪኮች ተስፋፉ። በጣም ታዋቂ ከሆኑት አፈ ታሪኮች አንዱ ፓትሪክ በተራራው ላይ በነበረበት ጊዜ ሁሉንም እባቦች ከአየርላንድ አስወገዳቸው የሚለው ነው።
በተራራው አናት ላይ ትንሽ ቤተ ክርስቲያን እንደገነባ በዘልማድ ይነገራል። ሕንፃው ከብዙ ጊዜያት በፊት የጠፋ ቢሆንም እንኳ የመጀመሪያው መሠረት እስካሁን ይገኛል፤ እንዲሁም ይህ ቦታና ተራራው ለብዙ ዓመታት ሃይማኖታዊ ጉዞ የሚደረግበት ቦታ ሆኖ ቆይቷል።
የሃይማኖታዊው ጉዞ ገጽታዎች
በዕድሜ ለገፋ ወይም ተራራ የመውጣት ልምድ ለሌለው አንድ ሰው አስቸጋሪውን የአምስት ኪሎ ሜትር ሽቅብ ጉዞ አጠናቅቆ በሰላም መመለሱ ብቻ አንድ ከፍተኛ ክንውን ነው።
ፈጥኖ ደራሽ ቡድኖች በአካል ላይ ለሚደርሱ የተለያዩ ጉዳቶች እርዳታ ለመስጠት ምቹ በሆኑ ስፍራዎች ላይ በተጠንቀቅ ይቆማሉ።
በጉዞው ወቅት ተሳላሚዎቹ የተለያዩ ኃጢአትን የመናዘዝ ሥርዓቶች የሚፈጽሙባቸው ሦስት ቦታዎች ወይም ጣቢያዎች አሉ። እነዚህም ተራራውን ለመውጣት ጉዞ የሚጀመርበት ቦታ ላይ በሚገኘው ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ሙሉ በሙሉ ተብራርተዋል።—ሣጥኑን ተመልከት።
ተራራውን የሚወጡት ለምንድን ነው?
ብዙዎች ይህንን በጣም ከባድ የሆነ ሃይማኖታዊ ጉዞ የሚያደርጉት ለምንድን ነው? አንዳንዶች ተራራውን በሚወጡበት ጊዜ እንዲህ ያለ ከልክ ያለፈ ተግባር የሚያከናውኑት ለምንድን ነው?
አንዳንዶች በሃይማኖታዊው ጉዞ ወቅት መጸለይ ለግል ጥቅማቸው የሚያቀርቡትን ልመና ይበልጥ ተሰሚ እንደሚያደርገው ያምናሉ። ሌሎች ለሠሯቸው አንዳንድ መጥፎ ድርጊቶች ይቅርታ ለማግኘት ይህንን ያደርጋሉ። የተቀሩት ደግሞ አመስጋኝነታቸውን የሚገልጡበት መንገድ ነው። ብዙዎች ለሃይማኖታዊው ጉዞ ክብረ በዓል ሲሉ እንደሚሄዱ ጥርጥር የለውም። ‘የመተባበር መንፈስና የማኅበረሰባዊ ፍቅር መግለጫ’ ነው በማለት አንድ ባለሥልጣን ሐሳባቸውን ሰጥተዋል። ክሮ ፓትሪክን መውጣት “የቅዱስ ፓትሪክን የሕይወት መንገድ የሚከተሉበትና ከእርሱ የተቀበሉትን የሃይማኖት ውለታ በግልጽ የሚያደንቁበት መንገድ ነው” በማለት ጨምረው ተናግረዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ተራራውን መውጣት “ንስሐ የሚፈጸምበት አንዱ መንገድ ነው፤ ምክንያቱም ተራራውን ሲወጡ የሚፈጠረው አካላዊ ድካም እውነተኛ የሆነ ኃጢአትን የመናዘዝ ሥርዓት ነው። ወደ ጫፍ የሚደረገው አዝጋሚ ጉዞ ረጅም ጊዜ የሚወስድ የጸጸት መግለጫ ነው” በማለት አክለዋል።
አንድ ሰው 25 ጊዜ ተራራውን ወጥቶ እንደነበር በኩራት ተናገረ። ለምን ይህንን እንዳደረገ ሲናገር “ለመናዘዝ ብዬ ነው!” ብሏል። አንድ ሌላ ሰው ደግሞ “ካልሠሩ አይገኝ መከሩ!” በማለት ምክንያቱን ተናግሯል።
የግድ አስፈላጊ ባይሆንም እንኳ ብዙዎች ተራራውን በባዶ እግራቸው ይወጣሉ። ይህንን የሚያደርጉት ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ መሬቱን “ቅዱስ” አድርገው ስለሚመለከቱት ጫማቸውን ያወልቃሉ። ሁለተኛ ደግሞ ‘ራስን በመቅጣት ንስሐ መግባት’ ከሚለው ዓላማቸው ጋር ለመስማማት ነው። በተጨማሪም ይህ ሁኔታ አንዳንዶች ተንበርክከው በየጣቢያዎቹ የተለያዩ ኃጢአትን የመናዘዝ ሥርዓቶች ለምን እንደሚፈጽሙ ግልጽ ያደርግልናል።
ፈጣሪን ለማድነቅ ተገፋፉ
ነገር ግን አንድ ሰው በአንድ የተለየ ቀን ተራራውን የሚወጡ ተሳላሚዎች ባላቸው ሃይማኖታዊ አመለካከት ባይካፈልስ? የአየሩ ሁኔታ ተስማሚ በሚሆንበት ጊዜ ጠንካራ ጫማ ተጫምቶ በማንኛውም ጊዜ ተራራውን መውጣት ይቻላል። ተራራውን የወጣነው ብዛት ያላቸው ተሳላሚዎች ወደ ተራራው አናት በሚተሙበት ጊዜ አልነበረም። ለማረፍ በተደጋጋሚ ቆም በምንልበት ወቅት ተራራውን ስለመውጣትና በብዙ ሰዎች ላይ ስላሳደረው ተጽዕኖ ለማሰላሰል ችለናል። በሺህ የሚቆጠሩ ተሳላሚዎች ይህንን አድካሚ ተራራ የመውጣት ጉዞ አከናውነው የተለያዩ ኃጢአትን የመናዘዝ ሥርዓቶች እንደሚፈጽሙ ስናስብ ‘አምላክ እንድናደርግ የሚፈልገው ይህንን ነውን? ተራራውን በመውጣት የሚፈጸመው ሃይማኖታዊ ሥርዓት ወይም በአንዳንድ መታሰቢያ ሐውልቶች ዙሪያ ጸሎቶችን በተደጋጋሚ እያነበነቡ መዞር በእርግጥ አንድን ሰው ወደ አምላክ ያቀርበዋልን?’ ብለን እንድንጠይቅ ገፋፍቶናል። ኢየሱስ ጸሎትን ስለመደጋገም በማቴዎስ 6:6, 7 ላይ የሰጠው ምክር ምንድን ነው?
ወደ ተራራው የወጣነው አንድ ሃይማኖታዊ ልማድ ለማከናወን ብለን እንዳልሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው። ቢሆንም በየትኛውም ሥፍራ የሚገኙ ተራሮች በምድር ላይ ካሉት አስደናቂ ነገሮች አንዱ እንደመሆናቸው መጠን የእርሱን ፍጥረት ለማድነቅ በመቻላችን ወደ ፈጣሪያችን ይበልጥ እንደቀረብን ተሰምቶናል። ከተራራው አናት ላይ ሆነን ወለል ብሎ በሚታየው ውብ የመሬት አቀማመጥ ለመደሰት የቻልን ሲሆን እዚያ ላይ ሆነን የብሱ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ጋር የሚገናኝበትን ቦታ እንኳ ለማየት ችለናል። ከበታቻችን ባለው ባሕረ ሰላጤ ውስጥ የሚያንጸባርቁ ትንንሽ ደሴቶች በሌላኛው ወገን ካለው ድንጋያማና ጠፍ ከሆነው ተራራማ አካባቢ ጋር ሲነጻጸሩ ልዩነታቸው የጎላ ነው።
ስለ ሦስቱ ጣቢያዎች አስበን ነበር። ኢየሱስ ለእውነተኛ ተከታዮቹ “አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ” በማለት የተናገራቸው ቃላት ወደ አእምሯችን መጡ።—ማቴዎስ 6:7
ተራራው በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በአድካሚ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት አስሮ የያዘ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ልማድ ክፍል እንደሆነ ተገነዘብን። ሐዋርያው ዮሐንስ “ትእዛዛቱን [የአምላክን] ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም” ብሎ ከተናገረው ነፃነት ጋር ምን ያህል ጉልህ ልዩነት እንዳላቸው አመዛዘንን።—1 ዮሐንስ 5:3
ክሮ ፓትሪክን መውጣት ጨምሮ በመዝናኛ ጉዟችን ተደስተን ነበር። ሁሉም የሰው ዘር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካልሆኑ ወጎች የሚላቀቅበትንና አፍቃሪውን የምድር ፈጣሪ “በመንፈስና በእውነት” ማምለክ የሚችልበትን ጊዜ በናፍቆት እንድንጠባበቅ ገፋፍቶናል።—ዮሐንስ 4:24
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የሃይማኖታዊው ጉዞ ዋነኛ ገጽታዎች
በቅዱስ ፓትሪክ ቀን ወይም በስምንቱ ቀናት ቆይታ ወቅት አለዚያም በሰኔ፣ በሐምሌ፣ በነሐሴና በመስከረም ወራት ውስጥ ባለው በማናቸውም ጊዜ ወደ ተራራው የሚወጣና በጸሎት ቤቱ ውስጥ ወይም በአቅራቢያው ሆኖ ጳጳሱ ያሰቡት ነገር እንዲሳካላቸው የሚጸልይ እያንዳንዱ ተሳላሚ በተራራው አናት ላይ ወይም በሳምንቱ ውስጥ በሚከናወኑት የኃጢአት ኑዛዜና ቅዱስ ቁርባን በመካፈል ኃጢአት ከሚያመጣው ቅጣት ነጻ መሆን ይችላል።
የተለመዱት ጣቢያዎች
ሦስት “ጣቢያዎች” አሉ (1) ተራራው ሥር ያለው ወይም ሊያክት ቤኖን፣ (2) ተራራው አናት ላይ፣ (3) ረሊግ ሙሬ፤ በሊካንዊ [ከተማ] በኩል ባለው የተራራው ወገን ወረድ ብሎ የሚገኝ ነው
1ኛ ጣቢያ – ሊያክት ቤኖን
ተሳላሚው 7 ጊዜ አባታችን ሆይ፣ 7 ጊዜ እመቤታችን ማርያም ሆይ እንዲሁም አንድ ጊዜ ጸሎተ ሃይማኖት እየደገመ በተቆለለው ድንጋይ ዙሪያ ሰባት ጊዜ ይዞራል
2ኛ ጣቢያ – የተራራው አናት
(ሀ) ተሳላሚው ይንበረከክና 7 ጊዜ አባታችን ሆይ፣ 7 ጊዜ እመቤታችን ማርያም ሆይ እንዲሁም አንድ ጊዜ ጸሎተ ሃይማኖት ያቀርባል
(ለ) ተሳላሚው በጸሎት ቤቱ አቅራቢያ ሆኖ ጳጳሱ ያሰቡት ነገር እንዲሳካላቸው ይጸልያል
(ሐ) ተሳላሚው 15 ጊዜ አባታችን ሆይ፣ 15 ጊዜ እመቤታችን ማርያም ሆይ እንዲሁም አንድ ጊዜ ጸሎተ ሃይማኖት እያቀረበ የጸሎት ቤቱን 15 ጊዜ ይዞራል
(መ) ተሳላሚው 7 ጊዜ አባታችን ሆይ፣ 7 ጊዜ እመቤታችን ማርያም ሆይ እንዲሁም አንድ ጊዜ ጸሎተ ሃይማኖት እያቀረበ 7 ጊዜ ሊያባ ፎሪግ [የፓትሪክ አልጋ] የሚባለውን ይዞራል
3ኛ ጣቢያ – ረሊግ ሙሬ
ተሳላሚው 7 ጊዜ አባታችን ሆይ፣ 7 ጊዜ እመቤታችን ማርያም ሆይ እንዲሁም አንድ ጊዜ ጸሎተ ሃይማኖት እያቀረበ 7 ጊዜ በእያንዳንዱ የድንጋይ ክምር [ሦስት የድንጋይ ክምሮች አሉ] ይዞርና በመጨረሻም እየጸለየ መላውን የረሊግ ሙሬ ክልል 7 ጊዜ ይዞራል።