የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 5/1 ገጽ 4-7
  • በቅርቡ ድህነት ፈጽሞ ይወገዳል!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በቅርቡ ድህነት ፈጽሞ ይወገዳል!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ለድሆች የሚሆን እርዳታ
  • ድህነትን ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ
  • በመጨረሻ ድህነት ይወገዳል!
  • የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ለድሆች አሳቢነት እናሳይ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • በቅርቡ ድህነት የሌለበት ዓለም ይመጣል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ድህነት ለዘለቄታው ይወገድ ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • ለድሆች ተስፋ ፈንጥቁላቸው
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2007
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 5/1 ገጽ 4-7

በቅርቡ ድህነት ፈጽሞ ይወገዳል!

“እነሆ፣ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ።” (ሉቃስ 2:10) እነዚህን ስሜት ቀስቃሽ ቃላት የሰሙት ኢየሱስ በተወለደበት ሌሊት በቤተ ልሔም አቅራቢያ የነበሩ በሁኔታው የተገረሙ የበግ እረኞች ናቸው። ከዚህ እወጃ ጋር በመስማማት ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ስለ ‘ምሥራቹ’ ጎላ አድርጎ ገልጿል። የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማሟላት ገንዘብ በጣም በሚያስፈልገን በአሁኑ ጊዜ ስለ ኢየሱስ የተነገረው ምሥራች ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ “ለድሆች ወንጌልን [“ምሥራች” አዓት]” ሰብኳል። (ሉቃስ 4:18) ማቴዎስ 9:35 እንደሚገልጸው “ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፣ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፣ . . . በከተማዎችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር።” በእርግጥም መልእክቱ በተለይ በድህነት የተጠቁ ሰዎችን የሚያጽናና ነበር። “ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፣ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።” (ማቴዎስ 9:36) እውነት ነው፣ ኢየሱስ “ድሆችስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና” ብሎ ተናግሯል፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ቃላት ችግረኛ የሆኑ ሰዎች ምንም ተስፋ የላቸውም የሚል ሐሳብ ያስተላልፋሉ ብለን መደምደም አይኖርብንም። (ዮሐንስ 12:8) ችግር ውስጥ እንዲዘፈቁ ያደረጋቸው ምክንያት ምንም ይሁን ምን ይህ ክፉ ሥርዓት እስካለ ድረስ ድሀ የሆኑ ሰዎች ይኖራሉ። የአምላክ ቃል የድህነትን እውነታ በቸልታ አያልፍም፤ በአንፃሩም የድህነትን መጥፎ ገጽታዎች በመተንተን የተሞላ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ የሚያስጨንቁ ነገሮችን ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ ያቀርባል።

ለድሆች የሚሆን እርዳታ

“አንድ ሰው ማንም ስለ እሱ ደንታ እንደሌለው ሲያውቅ የሚሰማውን ስሜት ያህል ለመሸከም የሚከብደው ነገር የለም” የሚል የታወቀ አባባል አለ። ምንም እንኳን አብዛኞቹ ሰዎች የርኅራኄ ስሜት የማያሳዩአቸው ቢሆንም ድሀ ለሆኑ ሰዎች ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ ጊዜ የሚሆን ምሥራች አለ።

ብዙ ሰዎች ድሆችን ለመርዳት ምንም ዓይነት ፍላጎት የሌላቸው መሆኑ ያሳዝናል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ በሚለው መሠረት አንዳንዶች “በኅብረተሰብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሕይወታቸውን ለማቆየት ትግል ያደርጋሉ። . . . የተሻሉ ግለሰቦች ኃይለኞችና ሀብታሞች ይሆናሉ” ብለው ያምናሉ። ሶሻል ዳርዊኒዝም ተብሎ በሚጠራው በዚህ ንድፈ ሐሳብ የሚያምኑ ሰዎች ድሆችን እንደ ሰነፍ ወይም እንደ አባካኝ አድርገው ይመለከቷቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ በገጠር ያሉ የቀን ሠራተኞች፣ ሥራ ለማግኘት አካባቢአቸውን ትተው የሚሄዱ ሠራተኞችና ሌሎች ሠራተኞች የሚከፈላቸው ደሞዝ አነስተኛ ቢሆንም እንኳን ቤተሰባቸውን ለመመገብ ሲሉ ዘወትር ጠንክረው ይሠራሉ።

በብዙ አገሮች ድህነት በሰፊው የተዛመተ ነው። በመሆኑም አብዛኞቹ በድህነት የሚኖሩ ሰዎች ኑሮ እንዳልሰመረላቸው ሆኖ አይሰማቸውም። ያም ሆኖ ግን በእንዲህ ዓይነት አገሮች ውስጥ በድህነት መካከል በቅንጦት የሚኖሩ ሰዎች አሉ። ምቹና ትልልቅ ቪላ ቤቶች ከተጨናነቁና ለጤና ጎጂ ከሆኑ ደሳሳ ቤቶች አጠገብ ቆመው ይታያሉ። ወፍራም ደሞዝ የሚከፈላቸው ሰዎች ውድ የሆኑ መኪኖቻቸውን ምስኪንና ሥራ አጥ በሆኑ ሰዎች በተጨናነቁ መንገዶች ላይ ያሽከረክራሉ። እንደዚህ ባሉ አገሮች የሚኖሩ ድሆች ችግረኛ መሆናቸውን ሲገነዘቡ ከፍተኛ የብስጭት ስሜት ይሰማቸዋል። እውነት ነው፣ “ድሆች የተሟላ ምግብ ባለማግኘት፣ መጥፎ ሁኔታ ላይ በሚገኝ ቤትና በቂ የሕክምና እንክብካቤ በማጣት ብቻ ሳይሆን ስላሉበት ሁኔታ በማሰብ በሚደርስባቸው የማያቋርጥ ጭንቀትም ይሠቃያሉ” በማለት ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ ይናገራል። “ቋሚ ሥራ አግኝተው ለመሥራት ስላልቻሉ ለራሳቸው የነበራቸውን አክብሮትና በራስ የመተማመን ስሜት በሙሉ አጥተዋል።” ታዲያ በጣም ድሀ ከሆኑት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ያሉበትን ሁኔታ ሊቋቋሙ የሚችሉት እንዴት ነው? ስለ ኢየሱስ የሚናገረው ምሥራች ድህነትን በመቋቋም ረገድ ምን ድርሻ ሊያበረክት ይችላል?

በመጀመሪያ፣ ድህነት በመጥፎ ልማዶች አማካኝነት የበለጠ ሊባባስ እንደሚችል አስታውስ። ለምሳሌ በብራዚል የሚኖረው ቫልዴሲር ሚስቱና ትንንሽ ልጆቹ የሚላስ የሚቀመስ አጥተው እያለ እሱ ግን ሥነ ምግባር በጎደለው አኗኗር በመኖር ገንዘብ ያባክን እንደነበረ በአመኔታ ተናግሯል። እንዲህ አለ፦ “ሥራ ያለኝ ቢሆንም ለቤተሰቦቼ የምሰጣቸው ገንዘብ ኖሮኝ አያውቅም። ይሁንና የተለያዩ የሎተሪ ትኬቶች ምንጊዜም ከኪሴ አይጠፉም ነበር።” ሚልተን ከመጠን በላይ የሚጠጣና የሚያጨስ ሰው ስለነበር ከሌሎች 23 ሠራተኞች ጋር ከሥራ ተባረረ። እንዲህ አለ፦ “ወደ ቤት መሄድ አቅቶኝ በመንገድ ላይ ስለማድር ቤተሰቤ በእኔ ምክንያት በጣም ይሠቃይ ነበር።”

ዣው የተባለውም ሰው በመጥፎ ምግባር ደሞዙን አባክኗል። “ብዙ ጊዜ ከቤት ውጪ አድር ነበር። የማገኘው ደሞዝ ርካሽ ልማዶቼን ለማርካትና ለውሽሞቼ አይበቃም ነበር። ሁኔታው ትዕግሥት የሚያስጨርስ ስለሆነ ባለቤቴ እንድንለያይ ፈለገች።” ካለበት የገንዘብና የትዳር ችግር በተጨማሪ ሌሎችም ችግሮች ነበሩት። እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “በዘመዶቼና በጎረቤቶቼ ላይ ችግር ፈጠርኩ፤ በተለይም በሥራ ቦታ ችግሮች ነበሩብኝ። በዚህም ሳቢያ በመጨረሻ ከሥራ ተባረርኩ።” ዡልዮ የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ በማለት ስለ ሁኔታው ያብራራል፦ “የማገኘው ደሞዝ የአደንዛዥ ዕፅ ልማዴን ሊያረካልኝ ስላልቻለ ከአደንዛዥ ዕፅ ግዢ ለመገላገል ስል አደንዛዥ መድኃኒቶችን መነገድ ጀመርኩ።”

ስምንት ልጆች ባሉበት ድሀ ቤተሰብ ውስጥ ያደገው ዦዜ ለራሱ የሚሆን አንድ የሆነ ነገር ለማግኘት ፈለገ። ከዚህ የባሰ ምንም እንደማይመጣበት በመገመት ከሌሎች ወጣቶች ጋር ሆኖ ሰዎችን መዝረፍ ጀመረ። ተስፋው የጨለመበት አንድ ሌላ ወጣት ሄድባንገርስ ተብሎ በሚጠራ የወሮበሎች ቡድን አባል ሆነ። እንዲህ በማለት ያብራራል፦ “አብዛኞቻችን በጣም ድሆች ስለነበርን ዕቃዎችን በመሰባበርና ሰዎችን በማጥቃት እርካታ እናገኝ ነበር።”

አሁን ግን እነዚህ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው ለኑሮ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በማጣት ወይም በምሬትና በብስጭት ስሜት አይሠቃዩም። የከንቱነት ወይም የተስፋ መቁረጥ ስሜት አይሰማቸውም። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ የሰበከውን ምሥራች ስላጠኑ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ሠርተውበታል፤ እንዲሁም በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ካሉ ተመሳሳይ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች ጋር ዝምድና መሥርተዋል። ስለ ሀብትና ድህነት አንዳንድ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ተምረዋል።

ድህነትን ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ

አንደኛ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ከዋሉ በድህነት አማካኝነት የሚመጡ መጥፎ ውጤቶች ሊቀንሱ እንደሚችሉ አውቀዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የጾታ ብልግናን፣ ስካርን፣ ቁማርንና አደንዛዥ መድኃኒቶችን አላግባብ መጠቀምን ያወግዛል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) እንደነዚህ ያሉ ነገሮች ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ናቸው። ሀብታም የሆነውን ሰው ሊያደኸዩት ድሀ የሆነውን ደግሞ የበለጠ ያጣ የነጣ ድሀ ሊያደርጉት ይችላሉ። እነዚህንና እነዚህን የመሰሉ ሌሎች መጥፎ ልማዶችን ማስወገድ የአንድን ቤተሰብ የኢኮኖሚ ሁኔታ የበለጠ ያሻ ሽላል።

ሁለተኛ፣ በሕይወት ውስጥ ከሀብት የበለጡ ሌሎች ጠቃሚ ነገሮች እንዳሉም ተረድተዋል። “የጥበብ ጥላ እንደ ገንዘብ ጥላ ናትና፤ የእውቀትም ብልጫዋ ጥበብ ገንዘብ ላደረጋት ሕይወትን እንድትሰጥ ነው” በሚሉት በመንፈስ አነሳሽነት በተነገሩ ቃላት ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት ተገልጿል። (መክብብ 7:12) አዎን፣ ገንዘብ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ስለ አምላክ ዓላማዎች የሚናገረው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ጥበብና እውቀት ደግሞ የበለጠ ጠቃሚ ነው። እውነት ነው፣ ብዙ ገንዘብ ያካበተ ሰውም ጥበብ የጎደለው ከሆነ ምንም የሌለውን ሰው ያህል ሊቸገር ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊው “ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ፤ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ፣ እንዳልጠግብ እንዳልክድህም፦ እግዚአብሔርስ ማን ነው? እንዳልል፤ ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም፣ በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል” በማለት በጥበብ ጸልዮአል።—ምሳሌ 30:8, 9

ሦስተኛ፣ አንድ ሰው ኢየሱስ ከሰበከው ምሥራች ጋር በሚስማማ መንገድ የሚኖር ከሆነ መቼም ቢሆን የተጣለ ሆኖ ሊሰማው እንደማይገባ ተገንዝበዋል። ምሥራቹ ከአምላክ መንግሥት ጋር የተሳሰረ ነው። መልእክቱ “የመንግሥቱ ምሥራች” ተብሎ ተጠርቷል፤ በአሁኑ ጊዜም በምድር ዙሪያ እየተሰበከ ነው። (ማቴዎስ 24:14 አዓት) ተስፋችንን በዚህ መንግሥት ላይ ካደረግን ድጋፍ እንደምናገኝ ኢየሱስ ተናግሯል። “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” ብሏል። (ማቴዎስ 6:33) አምላክ በጣም ልዩ የሆኑ መኪናዎች ወይም የቅንጦት ቤቶች እሰጣችኋለሁ ብሎ ቃል አልገባም። ኢየሱስ የተናገረው ምግብና ልብስን ስለመሳሰሉ ለሕይወት አስፈላጊ ስለሆኑ ነገሮች ነው። (ማቴዎስ 6:31) ኢየሱስ የገባው ቃል እምነት ሊጣልበት የሚችል እንደሆነ በጊዜያችን የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሊመሠክሩ ይችላሉ። አንድ ሰው፣ ሌላው ቀርቶ በጣም ድሀ የሆነ ሰው እንኳ መንግሥቱን ካስቀደመ ሙሉ በሙሉ የተተወ አይሆንም።

አራተኛ፣ የአምላክን መንግሥት ያስቀደመ አንድ ሰው በኢኮኖሚ ችግር እንደማይማረር ተገንዝበዋል። እርግጥ ነው፣ ድሀ የሆነ ሰው ጠንክሮ መሥራት አለበት። ይሁን እንጂ አምላክን ካገለገለ ከፈጣሪው ጋር ውድ ዝምድና ይኖረዋል። መጽሐፍ ቅዱስም ይህን ፈጣሪ አስመልክቶ ሲናገር “እርሱ ድኾችን አይንቅም፤ ሥቃያቸውንም ቸል አይልም፤ ከእነርሱ አይርቅም፤ ወደ እርሱ በሚጮኹበትም ጊዜ ይሰማቸዋል” ይላል። (መዝሙር 22:24 የ1980 ትርጉም) በተጨማሪም ድሀ የሆነ አንድ ሰው በሕይወት የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ ያገኛል። እንደ እርሱ ክርስቲያን ከሆኑ ሰዎች ጋር ባለው ሞቅ ያለ ወዳጅነት ይደሰታል፤ እንዲሁም ይሖዋ በገለጠው ፈቃዱ ላይ እውቀትና እምነት ይኖረዋል። እንደዚህ ያሉ ነገሮች “ከወርቅ፣ እንዲያውም ከተጣራ ንጹሕ ወርቅ ይልቅ” ይወደዳሉ።—መዝሙር 19:10 የ1980 ትርጉም

በመጨረሻ ድህነት ይወገዳል!

በመጨረሻም፣ ምሥራቹን የተቀበሉ ሰዎች ይሖዋ አምላክ ድህነትን በመንግሥቱ አማካኝነት ለአንዴና ለመጨረሻ ለማስወገድ ዓላማ እንዳለው ይማራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ድሀ ለዘላለም አይረሳምና፣ የችግረኞችም ተስፋቸው ለዘላለም አይጠፋም” በማለት ተስፋ ይሰጣል። (መዝሙር 9:18) መንግሥቲቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ የሆነላት በሰማይ የተቋቋመች እውን መስተዳድር ናት። በቅርብ ጊዜ ይህች መንግሥት ሰብዓዊ ጉዳዮችን የማስተዳደሩን ሥልጣን ከሰብዓዊ መንግሥታት ትወስዳለች። (ዳንኤል 2:44) ከዚያን ጊዜ በኋላ ዙፋን ላይ የተቀመጠው ንጉሥ ኢየሱስ “ለድኾችና ለደካሞች ይራራል፤ በችግር ላይ ያሉትን ሰዎች ከሞት ያድናል። የእነርሱ ሕይወት በእርሱ ዘንድ ውድ ስለሆነ፣ ከጭቆናና ከዐመፅ ይታደጋቸዋል።”—መዝሙር 72:13, 14 የ1980 ትርጉም

ያንን ጊዜ አሻግሮ በመመልከት ሚክያስ 4:3, 4 እንዲህ ይላል፦ “የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሮአልና እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።” እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? ለአምላክ መንግሥት የሚገዙ ሁሉ ናቸው። ይህች መንግሥት የሰው ዘሮችን እያጠቁ ያሉትን ችግሮች በሙሉ፣ ሌላው ቀርቶ እንደ በሽታና ሞት ያሉ ችግሮችን እንኳን ሳይቀር ታስወግዳለች። “ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።” (ኢሳይያስ 25:8፤ 33:24) ያ ዓለም እንዴት ያለ የተለየ ዓለም ይሆናል! እነዚህ ተስፋዎች በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተነገሩ ስለሆኑ ልናምናቸው እንደምንችል አስታውስ። አምላክ እንዲህ ብሏል፦ “ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ በታመነም ቤት በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል።”—ኢሳይያስ 32:18

በአምላክ መንግሥት ላይ እምነት መጣል ብዙውን ጊዜ በድህነት ምክንያት የሚመጣውን በራስ ያለመተማመን ስሜት ያሸንፋል። ድሀ የሆነ አንድ ክርስቲያን ሀብታም የሆነ ክርስቲያንን ያህል በአምላክ ፊት ዋጋማ እንደሆነ ያውቃል። አምላክ ሁለቱንም እኩል ይወዳቸዋል፤ እንዲሁም ሁለቱም አንድ ዓይነት ተስፋ አላቸው። ሁለቱም ድህነት በአምላክ መንግሥት ግዛት ወቅት ያለፈ ነገር የሚሆንበትን ጊዜ በናፍቆት ይጠባበቃሉ። እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ ይሆናል! በመጨረሻ ድህነት ጨርሶ ይወ ገዳል!

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ሰው በቁማር፣ በማጨስ፣ በስካር፣ አደንዛዥ መድኃኒት አላግባብ በመጠቀም ወይም ብልሹ በሆነ አኗኗር ገንዘቡን ለምን ያባክናል?

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ሰብዓዊ ድህነት የሚያስከትላቸውን ችግሮች ያስወግዳል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ