የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ—ስዊድን
ስዊድን ምሥራቃዊውን የስካንዲኔቭያን ባህረ ገብ ምድር ይዛ እስከ ላይኛው የአርክቲክ ክልል ድረስ ተንጣላ የምትገኝ አገር ናት። ጥቅጥቅ ብለው በሸፈኗትና ከዓመት እስከ ዓመት ልምላሜን ተላብሰው በሚታዩት ደኖቿ እንዲሁም በሐይቆቿና በተራራዎቿ በዓለም ዙሪያ በጣም የታወቀች ናት፤ እንዲሁም ስዊድን ሰዎች ሳይጨናነቁ ከሚኖሩባቸው የአውሮፓ አገሮች አንዷ ናት። የሆነው ሆኖ የይሖዋ ምሥክሮች ከ1800ዎቹ የመጨረሻ ዓመታት ጀምሮ እውነትን የሚያፈቅሩ ሰዎችን ፈልገው ማግኘት ችለዋል። አንድ በቅርብ ጊዜ የተከናወነ ምሳሌ ተመልከት።
አንዲት ሴት ከምሥክሮቹ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ታጠና ነበር፤ ባሏ ግን ይህን ጥናቷን አልወደደላትም ነበር። ሚስቱ ጥናቷን እንድታቆም ነገራት፤ እርሷም የተባለችውን አደረገች። ይህ ሰው በአንድ የቢራ ማምረቻ መጋዘን ውስጥ ይሠራ ነበር። አንድ ቀን አንድ የከባድ መኪና ሾፌር ከአሥር ዓመት የልጅ ልጁ ጋር ወደ መጋዘኑ መጣ። አያትዬው ዕቃውን መኪናው ላይ እስኪጭን ድረስ ልጁን እንዲጠብቅለት ሰውዬውን አደራ አለው። ሰውዬው እንዲያው ጨዋታ ለመጀመር ብሎ ልጁን በቅርቡ ባከበረው የልደት በዓሉ ላይ ምን ዓይነት ስጦታ እንደተሰጠው ጠየቀው። ልጁ እሱና ወላጆቹ የይሖዋ ምሥክሮች ስለሆኑ የልደት በዓል እንደማያከብሩ ሲነገረው ሰውዬው በጣም ተገረመ። በተጨማሪም ልጁ አፍቃሪና አሳቢ ወላጆች ስላሉት በዓመቱ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ስጦታዎችን እንዳገኘና ምንም የቀረበት ነገር እንደሌለ ነገረው። ጨምሮም አፍቃሪና አሳቢ የሆነን ቤተሰብ የሚተካከል ዋጋ ያለው ስጦታ የለም አለው።
ልጁ ከአያቱ ጋር ደጋግሞ ወደዚህ ቦታ መጣ። ሰውዬው ልጁ በመጣ ቁጥር ብዙ ጥያቄዎችን ይጠይቀው ነበር፤ ልጁ ያለምንም ማንገራገር በሚሰጠው እውነተኛና ቀጥተኛ መልስ በጣም ተገረመ። በተጨማሪም ልጁ እውነተኛ ዋጋ ላላቸው ነገሮች በሚሰጠው ክብደት ሲበዛ ተደነቀ። አንድ ቀን ሰውዬው ዓለማችን ያለችበትን አስከፊ ሁኔታ የሚያሳይ አንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ከተመለከተ በኋላ መንፈሳዊ ነገሮችን በቁም ነገር መመርመር እንዳለበት አስተዋለ። ቀደም ሲል ሚስቱን ታስጠና ወደ ነበረችው ምሥክር ደወለና እንድትመጣ ጠየቃት። ብዙም ሳይቆይ ከአንድ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ፤ ፈጣን እድገትም አሳየ። ሚያዝያ 10, 1994 ተጠመቀ። አሁን ሚስቱም ተጠምቃለች።
እድገቱ የግንባታ ሥራ ይጠይቃል
ስዊድን ከሌላ አገር ለመጡ ብዙ ስደተኞች መኖሪያ ናት፤ የስዊድን ምሥክሮች ለእነዚህ ስደተኞች በመስበክ ጥሩ ውጤቶች አግኝተዋል። ባጠቃላይ በስብከቱ ሥራ እንዲህ ያለ ስኬታማነት በመገኘቱ ከእድገቱ ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች አስፈልገዋል። ከ1986 እስከ 1993 በፈጣን የግንባታ ሥራ ዘዴ 37 የመንግሥት አዳራሾች ሲሠሩ 8 የሚሆኑ አዳራሾች ደግሞ ሰፋ ተደርገው ታድሰዋል። በ1994 ብቻ እንኳ ሰባት የመንግሥት አዳራሾች ሲሠሩ ሦስት ደግሞ ታድሰዋል።
በአሁኑ ጊዜ 65 የሚሆኑ ጉባኤዎች አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ለመሥራት ወይም ያላቸውን ለማስፋት ወይም ለማደስ እርዳታ እየጠበቁ ነው። ወደ 2,500 የሚጠጉ ፈቃደኛ ሠራተኞች እንዲህ ያለውን የግንባታ ፕሮጀክት በማካሄዱ ሥራ የረዱ ሲሆን ጉባኤዎቹም ፍቅራዊ ድጋፋቸውን እጅግ በጣም አድንቀዋል።
እስከ ላይኛው የአርክቲክ ክልል ድረስ የተንሰራፋው ሰሜናዊው የስዊድን ምድር አንዳንድ ጊዜ እኩለ ሌሊትም ፀሐይ የማትጠልቅበት ምድር ይባላል። ይህ የሆነበት ምክንያት በአንዳንድ የበጋ ወራት በዚያ ምድር ላይ ፀሐይ ፈጽሞ አትጠልቅም። ይሁን እንጂ የእውነት ብርሃንም በመላዋ ስዊድን ቦግ ብሎ ማብራቱን ቀጥሏል። በይሖዋ በረከት መንፈሳዊው ብርሃን ፈጽሞ አይደበዝዝም፤ ከዚህ ይልቅ ይበልጥ እየደመቀና ብሩህ እየሆነ ይሄዳል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአገሪቱ ሪፖርት መግለጫ
የ1994 የአገልግሎት ዓመት
የምሥክሮቹ ከፍተኛ ቁጥር፦24,246
ከሕዝቡ ብዛት ጋር ሲነጻጸር፦1 ምሥክር ለ362 ሰዎች
የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች፦40,372
የአቅኚዎች ብዛት በአማካይ፦2,509
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በአማካይ፦11,306
የተጠማቂዎች ብዛት፦850
የጉባኤዎች ብዛት፦358
ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኝበት ቦታ፦አርቦጋ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአርቦጋ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮና የቤቴል ቤት
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሂጆ የነበሩት የቀድሞዎቹ ምሥክሮች ወደ 5,000 ስኴር ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ክልል ለመሸፈን ይህን አነስተኛ አውቶቡስ ይጠቀሙ ነበር