“ደስተኛ አወዳሾች” የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ
የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በስፋት የሚሰጥባቸው ሦስት ቀናት ከፊትዎ ይጠብቁዎታል። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ እንኳን 180 ትልልቅ ስብሰባዎች ለማድረግ ታቅዷል፤ እርስዎ በሚኖሩበት አቅራቢያም አንድ ስብሰባ መደረጉ የማይቀር ነው። ዓርብ ዕለት ከጠዋቱ 3:40 ላይ ፕሮግራሙ በሙዚቃ ሲከፈት ለመገኘት ይሞክሩ።
ዓርብ በጠዋቱ ፕሮግራም እንኳን ደህና መጣችሁ የሚል መልእክት የሚያስተላልፉ ሐሳቦችና “በዓለም ዙሪያ ደስተኛ አወዳሾች በመሆን ከሌሎች ለየት ብሎ መታየት” የሚለው የስብሰባውን አጠቃላይ መልእክት የሚገልጽ ንግግር ይቀርባል። ከሰዓት በኋላ ፕሮግራሙ በወጣቶች፣ በወላጆችና በትምህርት ላይ ያተኩራል። “ለጋብቻ ኃላፊነቶች ብቁ ነኝን?” የሚለው ንግግር ወጣቶችን ሊያመልጣቸው የማይገባ ንግግር ነው። “በልጆቻቸው ደስታ የሚያገኙ ወላጆች” የሚለውን ንግግር ወላጆች በጥንቃቄ ማዳመጥ አለባቸው። የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም “ትምህርትን ይሖዋን ለማወደስ ተጠቀሙበት” በሚለው ንግግር ይደመደማል። በዚህ ንግግር ላይ የሚብራራው ሐሳብ ወጣቶች በትምህርት ቤት በተሳካ ሁኔታ መግፋት እንዲችሉ ሊረዳቸው ይገባል።
በቅዳሜው ጠዋት ፕሮግራም የጥምቀት ሥነ ሥርዓት የሚኖር ሲሆን ብቃቱን ያሟሉ ሁሉ መጠመቅ የሚችሉበት አጋጣሚ ተዘጋጅቶላቸዋል። በከሰዓት በኋላው ፕሮግራም ሰይጣን ከጥንት ጀምሮ በጾታ ምኞት ሰዎችን ለማጥመድ እንዴት እንደተጠቀመ በግልጽ ይብራራል። በተጨማሪም “ከዲያብሎስ ወጥመዶች ራቁ” የሚል ኃይለኛ ንግግር ይኖራል። “የሰው ዘር የአምላክ እውቀት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?” በሚለው ዓቢይ ንግግር የቀኑ ፕሮግራም ይደመደማል።
እሁድ ዕለት ጠዋት “በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ውስጥ የሚኖሩ ደስተኛ አወዳሾች” የሚል ርዕስ ያለው ሲምፖዝየም በፊታችን በተደቀኑት ዓለማችንን የሚያናጉ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። ተከታታይ ንግግሩ በማቴዎስ 24:21 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረለት “ታላቁ መከራ” ከመጀመሩ በፊት ከጥፋት መሸሽ ወደሚቻልበት ሥፍራ የማምለጥን አጣዳፊነት አጥብቆ ያሳስባል።
የእሁድ ጠዋቱ ፕሮግራም “ብድራት የሚገባቸውን አረጋውያን በክብር መያዝ” በተሰኘው በጣም ጠቃሚ የሆነ ድራማ ይደመደማል። ፕሮግራሙ በመቀጠል ከሰዓት በኋላ “ዘላለማዊውን ንጉሥ አወድሱ!” የተባለው የሕዝብ ንግግር ይቀርባል። ይህ ንግግር የአውራጃ ስብሰባው ዋነኛ ጎላ ያለ ክፍል ይሆናል።
በስብሰባው ላይ ለመገኘት አሁኑኑ እቅድ ያውጡ። ይህ ስብሰባ በአቅራቢያዎ የሚደረግበትን ቦታ ማግኘት እንዲችሉ በአካባቢዎ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ሄደው ያነጋግሯቸው፤ አለዚያም ለዚህ መጽሔት አዘጋጂዎች ይጻፉ። የሰኔ 8 ንቁ! መጽሔት (የእንግሊዝኛው) እትም በዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝና አየርላንድ ውስጥ እነዚህ ስብሰባዎች የሚደረጉባቸውን የሁሉንም ቦታዎች አድራሻ ይዘረዝራል።