“እውነተኛ ሚስዮናውያን” የሆኑት የጊልያድ ምሩቃን
“ሚስዮናዊ ምንድን ነው?” ይህ ጥያቄ የዛሬ አርባ ዓመት ገደማ በአንድ ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ ላይ ቀርቦ ነበር። ጸሐፊው እውነተኛ ሚስዮናውያን ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሃድሶ ለማካሄድ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች እንደሆኑ ሐሳብ ሰጥቷል። ነገር ግን እሁድ መጋቢት 5, 1995 ጀርሲ ሲቲ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የትልቅ ስብሰባ አዳራሽ ከዚህ በጣም የተለየ መልስ ጠበቅ ተደርጎ ተገልጿል። ይህንን ለማንሳት ያስቻለው አጋጣሚ ምን ነበር? ወደ ሁሉም የምድር ክፍሎች ሚስዮናውያንን የሚልከው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት የ98ኛ ክፍል ምረቃ ነበር!
ከመክፈቻው መዝሙርና ጸሎት በኋላ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው አልበርት ዲ ሽሮደር በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙትን 6,430 ተሰብሳቢዎች ሞቅ ባለ መንፈስ እንኳን ደህና መጣችሁ አለ። ወንድም ሽሮደር በመግቢያው ላይ የጊልያድ ምሩቃን ራሳቸውን ሚስዮናውያን ብለው ከሚጠሩ ሌሎች ሰዎች እንዴት እንደሚለዩ በግልጽ አብራራ። “መጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ዋንኛ ማስተማሪያ መጽሐፍ ነው” በማለት ገልጿል። የጊልያድ ምሩቃን የሰለጠኑት ማኅበራዊ እርዳታ ለመስጠት ሳይሆን የአምላክ ቃል አስተማሪዎች እንዲሆኑ ነው። ይህም በመሆኑ ምሩቃኑ ከአገራቸው ውጪ ባሉ መስኮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን መንፈሳዊ ፍላጎት እንዴት ማሟላት እንደሚቻል ልዩ ብቃት አግኝተዋል።
ከዚህ በመቀጠል ንግግር ያቀረቡት ተናጋሪዎች የጊልያድ ምሩቃን “እውነተኛ” ሚስዮናውያን መሆናቸውን የሚያስመሰክሩባቸው ሌሎች በርከት ያሉ መስኮችን ዳስሰዋል። ቻርልዝ ሞልሃን “በሚስዮናዊነት መልካም ፍሬ ማፍራታችሁን ቀጥሉ” በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበላቸው። ወንድም ሞልሃን በቆላስይስ 1:9, 10 አዓት ላይ በሚገኙት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት በመጠቀም በጊልያድ ያሳለፏቸው አምስት ወራት “በእግዚአብሔር ትክክለኛ እውቀት” እንዲያድጉ ረድቷቸው እንደነበረ ተመራቂዎቹን አስታወሳቸው። ይህም የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች በማሳየትና የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለሌሎች በማካፈል በሁለት መንገዶች ፍሬ እንዲያፈሩ ይረዳቸዋል።
በመቀጠል የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ዳንኤል ሲድሊክ “ሕይወታችሁን ፈጽሞ ለድርድር አታቅርቡ” የሚል ትልቅ ቁም ነገር ያዘለ ንግግር አቀረበ። “ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?” የሚለውን የኢየሱስን ጥያቄ ጠቅሶ ነበር። (ማቴዎስ 16:26) “ሰዎች ምንም ድካምና ጥረት የማይጠይቅ ቀላል አኗኗር ለመኖር ሲሉ ሕይወታቸውን የሚያሳጣ ነገር መርጠዋል” በማለት ወንድም ሲድሊክ ተናገረ። ነገር ግን ሕያው እምነት ያላቸው ሰዎች መከራና ፈተና ሲያጋጥማቸው አቋማቸውን ሊያላሉ አይችሉም። የኢየሱስ ቃላት አንድ ሰው ነፍሱን ወይም ሕይወቱን ለማግኘት ከፈለገ ‘ለመስጠት’ ማለትም የራሱን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን እንዳለበት ያሳያሉ። አዲሶቹ ሚስዮናውያን ይሖዋን በሙሉ ነፍስ እንዲያገለግሉት ማለትም ለእርሱ በሚያከናውኑት አገልግሎት የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ተሰጣቸው።
በመቀጠልም የአገልግሎት ኮሚቴ አባል የሆነው ዊሊያም ቫን ዲ ዎል “ሐዋርያው ጳውሎስ ልንመስለው የሚገባ ምሳሌ” በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበ። “ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይካሄድ በነበረው የሚስዮናዊነት ሥራ ግንባር ቀደም ሆኗል” በማለት ወንድም ቫን ዲ ዎል ተናገረ። ከዚያም ሐዋርያው ጳውሎስ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ሚስዮናውያን ጥሩ ምሳሌ ትቶ ያለፈባቸው አራት መስኮች መጉላታቸው ተገቢ ነበር። እነርሱም፦ (1) ጳውሎስ ለሰዎች የነበረው ልባዊ አሳቢነትና ፍቅር (2) በአገልግሎቱ የነበረው ውጤታማነት (3) ቦታውን የሚጠብቅ ከመሆኑ የተነሳ ራሱን ከፍ ከፍ ለማድረግ አለመፈለጉ (4) በይሖዋ ላይ የነበረው የማያወላውል እምነት ናቸው።
“በአዲሱ የአገልግሎት ምድባችሁ ይሖዋ እንዲመረምራችሁ አድርጉ” የሚል ርዕስ ያለው ንግግር የአስተዳደር አካል አባል በሆነው በሊማን ኤ ስዊንግል ቀረበ። ወንድም ስዊንግል የዕለቱ ጥቅስ በሆነው መዝሙር 139:16 በመጠቀም አዲስ ሚስዮናውያን እንደመሆናቸው መጠን በተመደቡበት የአገልግሎት መስክ ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸውና ይሖዋ የችግሮቹን መፍትሔዎች እንደሚያውቅ ገለጸ። “እርዳታ እንዲሰጣችሁ ጠይቁት፤ ችግር ሲኖራችሁ አነጋግሩት። ፍቃዱ ምን እንደሆነ ለመረዳት ጣሩ” በማለት አጥብቆ አሳሰባቸው።
ከዚያም የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ጆን ኢ ባር “እምነታችሁ በጣም እያደገ ነው” በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበ። (2 ተሰሎንቄ 1:3) ኢየሱስ በሉቃስ 17:1 ላይ “መሰናክል ግድ ሳይመጣ አይቀርም” በማለት የተናገረውን እናነባለን። አንዳንዶች አብረዋቸው በሚሠሩት ሚስዮናውያን ባሕርይ ተሰናክለዋል። ቢሆንም ወንድም ባር ይቅር ለማለት የሚያስችል እምነት እንዲኖራቸው ሚስዮናውያኑን አበረታታቸው። እንዲያውም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “እምነት ጨምርልን” በማለት የለመኑት ከዚህ ጥቅስ ትንሽ ዝቅ ብሎ ነበር። (ሉቃስ 17:2–5) የሚስዮናውያኑ እምነት በተለያዩ ድርጅታዊ ማስተካከያዎችም ሊፈተን ይችላል። “እነዚህን ማስተካከያዎች ለመቀበል የሚያስችል እምነት አግኝተናል ወይስ ማስተካከያዎቹ ተራራ መሰል እንቅፋቶች ይሆኑብናል?” በማለት ወንድም ባር ጥያቄ አቅርቧል።
ቀጥሎ በሁለት የጊልያድ አስተማሪዎች አማካኝነት አንዳንድ ምክሮች ተሰጡ። ጃክ ሬድፎርድ አዎንታዊ አመለካከት ይዘው እንዲቀጥሉ ተመራቂዎቹን አጥብቆ አሳሰባቸው። አብረዋት የሚሠሩት ሚስዮናውያን በእርሷ ላይ በማሾፋቸው የሚስዮናዊነት አገልግሎቷን ስላቆመች አንዲት እህት ተናገረ። ነገር ግን ቅዱሳን ጽሑፎች በረባ ባልረባው እንዳንቀየም ያስጠነቅቁናል። (መክብብ 7:9) “ትክክለኛ አመለካከት ይኑራችሁ። በዙሪያችሁ ያሉ ሰዎችን ስሕተቶችና አለፍጽምናዎች ይቅር የምትሉ ሁኑ” በማለት አሳስቧቸዋል።
ከዚያም የጊልያድ ሬጂስትራር የሆነው ዩ ቪ ግላስ “‘ጊዜና ድንገተኛ ክስተቶች’ የሚያመጣባቸሁን ነገር በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት ተዘጋጅታችኋልን”? በማለት ጠየቀ። (መክብብ 9:11 አዓት) “በሕይወታችን ውስጥ ምን ጊዜም አዳዲስ ክስተቶች ያጋጥሙናል፤ አንዳንዶቹ ክስተቶች ደግሞ በጣም አሳዛኝ ሊሆኑ ይችላሉ” በማለት ወንድም ግላስ አስታወቀ። የተወሰኑ ሚስዮናውያን ድንገት የጤና ማጣት፣ ሕመም፣ የቤተሰብ ችግር አጋጥሟቸዋል፤ እነዚህ ችግሮች አንዳንዶች የሚስዮናዊነት አገልግሎታቸውን እንዲያቆሙ ያደረጉ ናቸው። ወንድም ግላስ እንዲህ በማለት ተናገረ፦ “ድንገት የተከሰተው ነገር ምንም ዓይነት ሊሆን ቢችልም ይሖዋ እንደሚያውቀውና እንደሚያሳስበው እናውቃለን። ትምክህታችንን በእርሱ ላይ ከጣልን ድል አድራጊዎች እንደምንሆን እናውቃለን!”
“ለሚስዮናዊ አገልግሎት የተለያችሁ ሁኑ” የሚል ርዕስ ያለው ንግግር የጠዋቱ ተከታታይ ንግግሮች መደምደሚያ ነበር። የአስተዳዳር አካል አባል የሆነው ቲዎዶር ጃራስ “ሚስዮናዊ ምንድን ነው?” የሚለውን በመግቢያው ላይ የተነሳውን ጥያቄ ካነሳ በኋላ ለመልሱ ስለ ጳውሎስና በርናባስ የሚስዮናዊነት ሥራ የሚናገሩትን የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 13 እና 14 አብራራ። ይህ ሥራ ያተኮረው የኅብረተሰቡን ችግር በመፍታት ላይ ሳይሆን ‘ምሥራቹን በመስበክ’ ላይ እንደ ነበረ ግልጽ ነው። (ሥራ 13:32) “ጳውሎስና በርናባስ ከአንድ እውነተኛ ሚስዮናዊ የሚጠበቀውን ሁሉ አከናውነዋል ቢባል አትስማሙን?” በማለት ወንድም ጃራስ ጥያቄ አቅርቧል። ከዚያም ሜክሲኮ ውስጥ በሚስዮናዊነት ረጅም ጊዜ ያሳለፈው ሮበርት ትሬሲ በወንጌላዊነት ካጋጠሙት አስደሳች ተሞክሮዎቹ መካከል ጥቂቶቹን እንዲያካፍል ተጠየቀ።
ወንድም ሽሮደር ለ48ቱ ተመራቂዎች ዲፕሎማ ከሰጠ በኋላ የጠዋቱ ፕሮግራም ተደመደመ። አድማጮች ሚስዮናውያኑ የተመደቡባቸው 21 አገሮች ባርባዶስ፣ ቤኒን፣ ቦሊቪያ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ፣ ኮስታ ሪካ፣ ኮት ዲቩዋር፣ ኢኳዶር፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኢስቶኒያ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ሆንዱራስ፣ ላትቪያ፣ ሊዋርድ አይላንድስ፣ ሞሪሺየስ፣ ሞዛምቢክ፣ ኒካራጓዋ፣ ፓራጓይ፣ ፔሩ፣ ሴኔጋል፣ ታይዋንና ቬኔዙዌላ መሆናቸውን ሲሰሙ ተደስተው ነበር።
ከምሳ ዕረፍት በኋላ አድማጮች እንደገና ተሰብስበው የአገልግሎት ዲፓርትመንት አባል በሆነው ሮበርት ፒ ጆንሰን መሪነት ስሜት ቀስቃሽ የሆነ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ተካፈሉ። የ98ኛው ክፍል አባላት ጥያቄዎቹን መለሱ። ከዚያም በመቀጠል በጊልያድ ትምህርት ቤት የሚሠሩ ወንድሞች በተከታታይ ለተመራቂዎቹ አስደሳች ቃለ መጠይቆች አቀረቡላቸው። ተመራቂዎቹ በመስክ ያጋጠማቸውን ተሞክሮና ስለተሰጣቸው የሚስዮናዊነት የአገልግሎት ምድቦች ምን እንደተሰማቸው ሲናገሩ አድማጮች በጣም ተበረታተው ነበር።
የጊልያድ ትምህርት ቤት ለስድስት ዓመት ተኩል ያህል ዎልኪል ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሕንፃዎቸ ውስጥ ይገኝ ነበር። ነገር ግን ሚያዝያ 1995 ትምህርት ቤቱ ፓተርሰን ኒው ዮርክ ወደሚገኘው አዲሱ የመጠበቂያ ግንብ ትምህርት ማዕከል ተዘዋውሯል። ዎልኪል የሚገኙት የቤቴል ቤተሰብ አባላት ስለዚህ ለውጥ ምን ተሰማቸው? በዚህ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ በርከት ላሉ የዎልኪል ቤቴል ቤተሰብ አባላት ቃለ መጠየቅ ተደርጎላቸው ነበር። ልብ የሚነካው አነጋገራቸው የጊልያድ ተማሪዎች የማይጠፋ ትዝታ እንደጣሉባቸው ያሳያል። በእርግጥም እነዚህ ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀረቡ ወንዶችና ሴቶች ትሑት፣ የራሳቸውን ጥቅም የሚሰዉ፣ ሌሎችን ለመርዳት በጣም የሚደክሙ እውነተኛ ሚስዮናውያን ናቸው።
የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ሲደመደም የጊልያድ ትምህርት ቤት ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት ሲያከናውን የቆየውን እውነተኛ ሚስዮናውያን የማፍራት ሥራ ወደፊትም በተሳካ ሁኔታ እንደሚቀጥል ሁሉም ተሰብሳቢዎች እርግጠኛ ነበሩ!
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ስለ ተመራቂዎቹ የቀረበ አኃዛዊ መረጃ
ሚስዮናውያኑ የተውጣጡባቸው አገሮች፦ 8
የተመደቡባቸው አገሮች፦ 21
የተማሪዎቹ ብዛት፦ 48
አማካይ ዕድሜ፦ 32.72
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ፦ 15.48
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ፦ 10.91
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት የተመረቀው 98ኛ ክፍል
ከዚህ ቀጥሎ ከፊት ለፊት በቆሙት ተማሪዎች በመጀመር ከግራ ወደ ቀኝ ስማቸው እንደሚከተለው ተዘርዝሯል።
(1) ኤስሊንገር ኤ፣ ማን ቲ፣ ሪቬራ ጂ፣ ባርዊሮ ኤም፣ ቫዝ ኤም፣ ዱርጋ ኬ፣ ሲልቨርክስ ኤች፣ አልቫራዶ ዲ፣ (2) ቶዝ ቢ፣ ሴጋራ ኤስ፣ ሃርት አር፣ ሮሪክ አይ፣ ኤስኮባር ፒ፣ ኢስትረፕ ጄ፣ ስሊ ኤል፣ ሪቬራ ኢ፣ (3) አርቻርድ ዲ፣ ስኔዝ ኤስ፣ ማርሴል ፒ፣ ኮልየነን ዲ፣ ዋዴል ኤስ፣ ብላክበርን ኤል፣ ኤስኮባር ኤም፣ አርቻርድ ኬ፣ (4) ሃርት ኤም፣ ቶዝ ኤስ፣ ኮልየነን ጄ፣ ቤሪማን ኤች፣ ማን ዲ፣ ብላክበርን ጄ፣ ፓርክ ዲ፣ ቫዝ ኤፍ፣ (5) ሴጋራ ኤስ፣ ስሊ ኤል፣ ሌስሊ ኤል፣ ቤርግማን ቢ፣ ባርዊሮ ደብልዩ፣ አልቫራዶ ጄ፣ ሌስሊ ዲ፣ ፓርክ ዲ (6) ሲልዌርክስ ኬ፣ ኤስሊንገር አር፣ ዋዴል ጄ፣ ስኔዝ ኬ፣ ዱርጋ ኤ፣ ሮሪክ ኤፍ፣ ኢስትረፕ ሲ፣ ማርሴል ዲ።