የአንባብያን ጥያቄዎች
ገላትያ 6:8 እንደሚለው “በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፣ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳልና።” እዚህ ላይ የተጠቀሰው “መንፈስ” ምንድን ነው? ከእርሱስ ሕይወት ልናጭድ የምንችለው እንዴት ነው?
“መንፈስ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃል ብዙ ትርጉም አለው። (1) የአምላክን አንቀሳቃሽ ኃይል፣ (2) በሰውም ሆነ በእንስሳ ውስጥ ያለውን የሕይወት ኃይል፣ (3) አንድን ሰው የሚገፋፋ የአእምሮ ዝንባሌና (4) መንፈሳዊ አካልን ወይም መልአክን ሊያመለክት ይችላል። በገላትያ 6:8 ላይ ለተጠቀሰው “መንፈስ” የተሰጠው ትርጉም በቁጥር አንድ የተጠቀሰው የአምላክ አንቀሳቃሽ ኃይል ነው።
ለማስረጃ እንዲሆነን በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ “መንፈስ” የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰበትን ገላትያ 3:2ን እንመልከት። ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “በሕግ ሥራ ወይም ከእምነት ጋር በሆነ መስማት መንፈስን ተቀበላችሁን?” ሲል ጠይቋል። ከዚያም በገላትያ 3:5 ላይ ይህን “መንፈስ” ተአምር ከማድረግ ጋር አዛምዶታል። ስለዚህ እዚህ ላይ የጠቀሰው “መንፈስ” የአምላክ የማይታይ አንቀሳቃሽ ኃይል ወይም መንፈስ ቅዱስ ነው።
ጳውሎስ ቆየት ብሎ በገላትያ 5:16 ላይ መንፈስንና ሥጋን ያነፃፅራል። እንዲህ እናነባለን፦ “ነገር ግን እላለሁ፣ በመንፈስ ተመላለሱ፣ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ።” “የሥጋ ምኞት” ሲል ኃጢአተኛ የሆነውን የሰው ሥጋ ምኞት ማለቱ ነው። በዚህም ምክንያት በገላትያ 5:19–23 ላይ ‘የሥጋን ሥራዎች’ ‘ከመንፈስ ሥራዎች’ ጋር በማነፃፀር ዘርዝሯል።
ስለዚህ በገላትያ 6:8 ላይ የተጠቀሰው ‘በሥጋ የሚዘራ ሰው’ ኃጢአተኛ በሆኑ ሰብዓዊ ፍላጎቶች እየተነዳ ‘የሥጋን’ ሥራዎች” የሚፈጽም ሰው መሆን ይኖርበታል። ካልተለወጠ ደግሞ በአምላክ መንግሥት ሆነ በአምላክ መንግሥት በምትተዳደረው ምድር ላይ ሕይወት ሊያገኝ አይችልም።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10
እንደ አንድ ታማኝ ክርስቲያን መጠን ‘በአምላክ መንፈስ ለመዝራት’ እንፈልጋለን። በአምላክ መንፈስ መዝራት ማለት መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ላይ ምንም ነገር ሳያደናቅፈው እንዲሠራና ፍሬዎቹን እንድናሳይ እንዲረዳን መፍቀድ ማለት ነው። ምን እንደምናነብ ወይም የትኛውን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለማየት እንደምንፈልግ ስንወስን ይህን ማስታወስ ይኖርብናል። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርበውን ትምህርት ስናዳምጥና በመንፈስ የተሾሙ ሽማግሌዎች የሚሰጡትን ምክር ሥራ ላይ ለማዋል ስንጥር በመንፈስ እንዘራለን።—ሥራ 20:28
የሚያስደስተው ገላትያ 6:8 ምክሩን የሚደመድመው እነዚህን ነገሮች ስናደርግ ‘ከመንፈስ የዘላለም ሕይወት እንደምናጭድ’ ዋስትና በመስጠት ነው። አዎን፣ አምላክ የክርስቶስን ቤዛ መሠረት በማድረግ በመንፈስ ቅዱስ አሠራር አማካኝነት ፍጻሜ የሌለው ሕይወት ይሰጠናል።—ማቴዎስ 19:29፤ 25:46፤ ዮሐንስ 3:14–16፤ ሮሜ 2:6, 7፤ ኤፌሶን 1:7