ሴቶች በዓለም ዙሪያ
የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሰብዓዊ ፍጡራን በአምላክ ላይ ባመፁ ጊዜ ይሖዋ በነሱም ሆነ በዘሮቻቸው ላይ አስከፊ ውጤት እንደሚደርስባቸው አስቀድሞ ተናገረ። ይሖዋ ለሔዋን “ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፣ እርሱም ገዥሽ ይሆናል” አላት። (ዘፍጥረት 3:16) መጽሐፍ ቀዱስ በተደጋጋሚ ለሴቶች አክብሮት መስጠትን ያበረታታል፣ እነርሱም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ላይ ስለሚያውሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሴቶች በጣም አስደሳችና ይበልጥ አርኪ የሆነ ሕይወት ለመኖር ችለዋል።
ሰብዓዊ መብትን አስመልክቶ በቅርቡ የወጣ አንድ ሪፖርት ግን ሌሎች ብዙ ሴቶች በዓለም ዙሪያ ዝቅ ተደርገው እንደሚታዩ፣ ጉልበታቸው አለ አግባብ እንደሚበዘበዝና እንደሚናቁ ዘግቧል። ሪፖርቱን አስመልክቶ ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቡን አስተያየቱን ሲሰጥ፦ “በ193 አገሮች ላይ የተደረገው ጥንቃቄ የተሞላበት ዝርዝር ሪፖርት . . . በየዕለቱ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን አሳዛኝ ጉስቁልናም ሆነ አድሎ በሚገባ ሥሎታል” ብሏል።
ጥቂት ምሳሌዎች፦ በመካከለኛው አፍሪካ ሴቶች አብዛኛውን ከባድ የግብርና ሥራ እንዲሠሩ ይጠበቅባቸዋል እንዲሁም ሴቶች የመማር ዕድላቸው ከወንዶች በአንድ ሦስተኛ ያነሰ ነው። በአንድ አገር ውስጥ ምንዝር መፈጸም ለሴቶች ሕገ ወጥ ድርጊት ሲሆን ለወንዶች ግን አይደለም። የአንድ ሌላ የአፍሪካ አገር ሕግ ደግሞ ባልየው ሚስቱ ስታመነዝር ቢያገኛትና ቢገድላት ሕጉ ይቅርታ ያደርግለታል ነገር ግን ሚስትየው ባሏን በተመሳሳይ ሁኔታ ብታገኘውና ብትገድለው ሕጉ ይቅርታ አያደርግላትም።
ሪፖርቱ በአንዳንድ የደቡብ አሜሪካ አካባቢዎች ባሎቻቸው ለሚደበድቧቸው ሴቶች ፖሊስ ምንም ዓይነት እርዳታ አይሰጥም ይላል። እንዲሁም በሥራ ገበታ ላይ ያሉ ሴቶች ከወንዶች ከ30 እስከ 40 በመቶ ያነሰ ደሞዛቸውን የግድ አሜን ብለው መቀበል አለባቸው።
በአንዳንድ የእስያ አካባቢዎች ሴቶች መሐን እንዲሆኑና እንዲያስወርዱ በሚደረገው የኃይል እርምጃ ተጠቂዎች ናቸው። በአንድ አገር ውስጥ ወደ 500,000 የሚጠጉ ሴተኛ አዳሪዎች ሲኖሩ ብዙዎቹ ወደዚህ ተግባር የተሸጡት አዳዲስ ቤቶችን ለመግዛት ገንዘብ በሚፈልጉ ወላጆቻቸው ነው። በሌላ አገር ደግሞ ፖሊስ እየተስፋፋ የመጣውን “የሰጡት ጥሎሽ በማነሱ የተነሳ የሚገደሉ” ሴቶችን ችግር ለመመልከት ተገዷል፤ ሚስትየው የሰጠችው ጥሎሽ እነሱ ከጠበቁት በታች በመሆኑ ምክንያት በባሏ ወይም በእሱ ቤተሰቦች ትገደላለች።
ኢየሱስን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ፦ “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ከጭንቀት ያድናል። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፤ ስማቸው [ደማቸው አዓት] በፊቱ ክቡር ነው።” በማለት ያረጋግጥልናል (መዝሙር 72:12–14) ስለዚህ ተስፋ የምናደርግበት በቂ ምክንያት አለን፤ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሴቶች በዚያ ጊዜ የሚኖረውን የተሻሻለ ሁኔታ በተስፋ ሊጠባበቁ ይችላሉ።