ማስተዋልን ይበልጥ ማዳበር ትችላለህን?
ማስተዋል “አእምሮ አንድን ነገር ከሌላው የሚለይበት ችሎታ ነው።” በተጨማሪም “ንቃት የተሞላ የማመዛዘን ችሎታ” ወይም “በተለያዩ ነገሮች ወይም አስተሳሰቦች መካከል ያሉትን ልዩነቶች የመገንዘብ ችሎታ” ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለውን ፍቺ የሰጠው ዌብስተርስ ዩኒቨርሳል ዲክሽነሪ ነው። በእርግጥም ማስተዋል ከልብ ልንመኘው የሚገባ ችሎታ ነው። የሚያስገኘው ጥቅም ሰሎሞን እንዲህ ብሎ በተናገራቸው ቃላት ውስጥ ተገልጿል፦ “ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፣ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፤ . . . ማስተዋልም ይጋርድሃል፣ ከክፉ መንገድ አንተን ለማዳን።”—ምሳሌ 2:10–12
አዎን፣ ማስተዋል በዛሬው ጊዜ በስፋት ከሚገኘው “ክፉ መንገድ” እንድንርቅ ይረዳናል። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል። ለምሳሌ ወላጆች ብዙውን ጊዜ ልጆቻቸው ‘ችግሬን አልተረዳችሁልኝም!’ ብለው ሲናገሩ ይሰማሉ። አስተዋይ የሆኑ ወላጆች ጥቂት የምርመራ ጥያቄዎችን በመጠቀም ልጆቻቸውን እያስጨነቁ ያሉትን ስሜቶችና አወዛጋቢ ጉዳዮች እንዴት ማውጣጣት እንደሚችሉ ያውቃሉ። (ምሳሌ 20:5 የ1980 ትርጉም) አስተዋይ የሆነ ባልም ዘሎ ወደ ውሳኔ ከመሮጥ ይልቅ ሚስቱን በማዳመጥ አስተሳሰቧንና ስሜቶቿን ጠለቅ ብሎ ለመረዳት ይጥራል። ሚስትም ለባሏ እንዲሁ ታደርጋለች። በዚህ መሠረት “ቤት በጥበብ ይሠራል፣ በማስተዋልም ይጸናል።”—ምሳሌ 24:3
ማስተዋል አንድ ሰው የሚያጋጥሙትን ሁኔታዎች በተሳካ ሁኔታ እንዲወጣ ይረዳዋል። ምሳሌ 17:27 “ጥቂት ቃልን የሚናገር አዋቂ ነው፣ መንፈሱም ቀዝቃዛ የሆነ አስተዋይ ነው” ይላል። አስተዋይ ሰው ሳያመዛዝን በሁሉም ጉዳዮች ውስጥ ጥልቅ የሚል ግልፍተኛ አይደለም። አንድ ነገር ከማድረጉ በፊት ትርፍና ኪሳራውን በጥንቃቄ ያሰላል። (ሉቃስ 14:28, 29) በተጨማሪም “አስተዋይ አፉ” የሚናገረውን ነገር በጥንቃቄ ለመምረጥ ስለሚያስችለው ከሌሎች ጋር ይበልጥ ሰላማዊ ግንኙነት ይኖረዋል። (ምሳሌ 10:19፤ 12:8 አዓት) ነገር ግን ከሁሉ በላይ አስተዋይ ሰው የራሱን ውስን ችሎታ በትሕትና ከመገንዘቡም በላይ መመሪያ የሚጠባበቀው ከሰው ሳይሆን ከአምላክ ነው። ይህም ይሖዋን ከማስደሰቱም በላይ ማስተዋልን የምናዳብርበት ሌላው ምክንያት ነው።—ምሳሌ 2:1–9፤ ያዕቆብ 4:6
የእስራኤል ማስተዋል ማጣት
አስተዋይ አለመሆን የሚያስከትለው አደጋ በጥንታዊው የእስራኤል ታሪክ ውስጥ በተፈጸመ አንድ ሁኔታ ታይቷል። መዝሙራዊ ያንን ጊዜ መለስ ብሎ በመመልከት በመንፈስ ተነሳስቶ እንዲህ አለ፦ “አባቶቻችን በግብጽ ሳሉ ተአምራትህን አላስተዋሉም፣ የምሕረትህንም ብዛት አላሰቡም፤ በኤርትራ ባሕር ባለፉ ጊዜ ዐመፁብህ።”—መዝሙር 106:7
ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብጽ እየመራ ሲያወጣቸው ይሖዋ ከዚህ በፊት በዚያ ታላቅ የዓለም ኃያል መንግሥት ላይ አሥር መቅሰፍቶችን በማውረድ ኃይሉንና ሕዝቦቹን ነፃ ለማውጣት ያለውን ቁርጥ ሐሳብ አሳይቶ ነበር። ፈርዖን እስራኤላውያንን ከለቀቃቸው በኋላ ሙሴ ወደ ቀይ ባሕር ዳርቻ ወሰዳቸው። ነገር ግን የግብጽ ሠራዊት ተከታትሏቸው መጣ። እስራኤላውያን ወጥመድ ውስጥ የገቡና አዲስ ያገኙት ነፃነት በአጭሩ የተቀጨ መስሎ ነበር። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱሱ ታሪክ “የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፣ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ” ይላል። ከዚህም በላይ “ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻላል” በማለት ሙሴን ተቃወሙት።—ዘጸአት 14:10–12
አሥሩን ተወዳዳሪ የሌላቸው የይሖዋ ኃይል መግለጫዎች አስቀድሞ ተመልክተው እንደነበረ ከዘነጋን ፍራቻቸው በቂ ምክንያት ያለው ሊመስል ይችላል። ሙሴ ከ40 ዓመታት በኋላ “እግዚአብሔርም በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፣ በታላቅም ድንጋጤ፣ በተአምራትም፣ በድንቅም ከግብፅ አወጣን” ብሎ ያሳሰባቸውን ነገር ከምንጩ ያውቁት ነበር። (ዘዳግም 26:8) በዚህ የተነሳ እስራኤላውያን የሙሴን መመሪያ ሲቃወሙ መዝሙራዊው እንደጻፈው “አላስተዋሉም” ነበር። ያም ሆነ ይህ ይሖዋ የግብጽን ሠራዊት ያልተጠበቀ ሽንፈት በማከናነብ ቃል የገባውን በታማኝነት ፈጸመ።—ዘጸአት 14:19–31
መከራ ሲደርስብን የምንጠራጠር ወይም የምንወላውል ከሆነ የእኛም እምነት ልክ እንደዚሁ ሊዳከም ይችላል። ከሚቃወመን ማንኛውም ነገር ይሖዋ በጣም የላቀ መሆኑን እንድናስታውስ በማድረግ ማስተዋል ሁልጊዜ ነገሮችን በአርቆ አሳቢነት እንድንመለከት ይረዳናል። በተጨማሪም ማስተዋል ከዚህ በፊት ይሖዋ ያደረገልንን ነገር እንድናስታውስ ይረዳናል። እርሱ “የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል” የሚለውን ሐቅ በማንኛውም ጊዜ እንዳንዘነጋ ያስችለናል።—መዝሙር 145:18–20
መንፈሳዊ ማስተዋል ማግኘት
ማስተዋል እንዲሁ በዕድሜ የሚመጣ ነገር አይደለም። የግድ ልናዳብረው ያስፈልጋል። በማስተዋሉ ዓለም አቀፍ ዝና ያተረፈው ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ አለ፦ “ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን ነው፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ፤ በወርቅና በብር ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና።” (ምሳሌ 3:13, 14) ሰሎሞን አስተዋይነትን ያገኘው ከየት ነበር? ከይሖዋ ነበር። ምን ዓይነት በረከት ማግኘት እንደሚፈልግ ይሖዋ ሰሎሞንን ሲጠይቀው “በሕዝብህ ላይ መፍረድ ይችል ዘንድ፣ መልካሙንና ክፉውንም ይለይ ዘንድ ለባሪያህ አስተዋይ ልቡና ስጠው” በማለት ሰሎሞን መለሰለት። (1 ነገሥት 3:9) አዎን፣ ሰሎሞን ይሖዋን ረዳቱ በማድረግ በእርሱ ላይ ተመክቶ ነበር። ማስተዋልን እንዲያገኝ ሲጠይቅ ይሖዋ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን ጥበብ ሰጠው። ውጤቱስ ምን ሆነ? “የሰሎሞንም ጥበብ በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ጥበብና ከግብጽ ጥበብ ሁሉ በለጠ።”—1 ነገሥት 4:30
የሰሎሞን ተሞክሮ ማስተዋልን ከየት መፈለግ እንዳለብን ያሳየናል። ልክ እንደ ሰሎሞን ወደ ይሖዋ መመልከት አለብን። እንዴት? ይሖዋ ስለ እርሱ አመለካከት ጠለቅ ያለ ማስተዋል የሚሰጠንን ቃሉ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ ሰጥቶናል። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ለመንፈሳዊ ማስተዋል መሠረት የሚጥል ዋጋማነት ያለው የእውቀት ጉድጓድ እየቆፈርን ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ የሰበሰብነውን እውቀት ማሰላሰል አለብን። እንዲህ ከሆነ ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለማድረግ ሊያገለግል ይችላል። ከጊዜ በኋላ የማስተዋል ችሎታችን ዳብሮ ‘በአእምሮ የበሰልን’ እንሆናለን፤ ይህም “መልካሙንና ክፉውን ለመለየት [ወይም ልዩነታቸውን ለማስተዋል]” ያስችለናል።—1 ቆሮንቶስ 14:20፤ ዕብራውያን 5:14፤ ከ1 ቆሮንቶስ 2:10 ጋር አወዳድር።
ይሖዋ ለሰሎሞን ከሰጠው ማስተዋል እኛም ለመጠቀም መቻላችን የሚያስደስት ነው። እንዴት? ሰሎሞን ጥበብን በምሳሌ መልክ በመግለጽ ረገድ የተካነ ነበር፤ እነዚህ ምሳሌዎች በመለኮታዊ አነሣሽነት የተነገረ ጥበብ በአጭር በአጭሩ የተገለጸባቸው ናቸው። ከእነዚህ አባባሎች መካከል አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ በሆነው በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ተጠብቀው ቆይተዋል። ይህንን መጽሐፍ ማጥናት ከሰሎሞን ማስተዋል ጥቅም ለማግኘትና የራሳችንን ማስተዋል ለማዳበር ይረዳናል።
ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ይበልጥ ለመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በሚረዱት እንደ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ባሉ መጽሔቶች ልንጠቀም እንችላለን። መጠበቂያ ግንብ ከ116 ለሚበልጡ ዓመታት ልበ ቅን ለሆኑ ሰዎች የይሖዋን መንግሥት ሲያውጅ ቆይቷል። ከ1919 ጀምሮ ንቁ! መጽሔትና ቀድሞ በእርሱ ፋንታ የነበሩት መጽሔቶች ዓለም ስለሚገኝባቸው ሁኔታዎች ትንታኔ ሲሰጡ ቆይቷል። እነዚህ ሁለት መጽሔቶች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በጥልቅ ከመመርመራቸውም በላይ ሕዝበ ክርስትና ያስተማረችንንም ሆነ በራሳችን አስተሳሰብ የያዝናቸውን ስህተቶች ለማስተዋል የሚረዳን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የሚሄድ የመንፈሳዊ እውቀት ብርሃን ያቀርቡልናል።—ምሳሌ 4:18
ማስተዋልን ለማዳበር የሚረዳው ሌላው ነገር ጥሩ ባልንጀርነት ነው። ከንጉሥ ሰሎሞን ምሳሌዎች መካከል አንዱ “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል” ይላል። (ምሳሌ 13:20) የንጉሥ ሰሎሞን ልጅ የሆነው ሮብዓም በሕይወቱ ወሳኝ ወቅት ላይ በነበረበት ጊዜ ይህንን ምሳሌ አለማስታወሱ ያሳዝናል። አባቱ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ነገዶች ሸክማቸውን እንዲያቀልላቸው ለመጠየቅ ወደ እርሱ መጡ። ሮብዓም መጀመሪያ ከሽማግሌዎች ጋር ተማከረ፤ የተገዢዎቹን አቤቱታ እንዲሰማ ስለመከሩት እነዚህ ማስተዋል አሳይተው ነበር። ከዚያም ወደ ወጣቶች ሄደ። እነዚህ ለእስራኤላውያኑ በዛቻ እንዲመልስላቸው ሮብዓምን በመምከር ተሞክሮና ማስተዋል እንደሌላቸው አሳዩ። ሮብዓም የወጣቶቹን ምክር ሰማ። ውጤቱ ምን ሆነ? እስራኤላውያን ዓመፁና ሮብዓም የመንግሥቱን ሰፊ ግዛት አጣ።—1 ነገሥት 12:1–17
ማስተዋልን ለማዳበር የሚረዳው ዐቢይ ነገር የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ መሻት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ነህምያ እስራኤላውያን ከግብጽ ምርኮ ከወጡ በኋላ ይሖዋ ምን እንዳደረገላቸው መለስ ብሎ ሲቃኝ እንዲህ አለ፦ “ሊያደርጉት የሚገባቸውን ሁሉ እንዲያውቁ ቸር መንፈስህን ሰጠሃቸው።” (ነህምያ 9:20 የ1980 ትርጉም) የይሖዋ መንፈስም ልናደርገው የሚገባንን እንድናውቅ ያስችለናል። የይሖዋ መንፈስ ማስተዋልን እንዲሰጥህ ስትጸልይ ይሖዋ ‘ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጥ’ ስለሆነ ተማምነህ ጸልይ።—ያዕቆብ 1:5፤ ማቴዎስ 7:7–11፤ 21:22
ጠለቅ ብሎ ማስተዋል
ሐዋርያው ጳውሎስ ለአሕዛብ እውነትን ሲሰብክ ማስተዋል አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል አንድ ጊዜ አቴንስ ውስጥ ሳለ ለአምልኮ የሚጠቀሙባቸውን ጣዖታት ‘እየተመለከተ ያልፍ ነበር።’ ጳውሎስ በጣዖታት ተከቦ ስለነበር መንፈሱ ተበሳጨበት። አንድ ነገር መወሰን ነበረበት። አደጋ የማያስከትልበትን መንገድ በመከተል ዝም ብሎ መቀመጥ አለበትን? ወይስ አደገኛ ቢሆንም እንኳ በጣም ስላበሳጨው የተስፋፋ የጣዖት አምልኮ በግልጽ መናገር ይኖርበታል?
ጳውሎስ ማስተዋል አሳይቶ ነበር። “ለማይታወቅ አምላክ” የሚል የተቀረጸ ጽሑፍ ያለበት መሠዊያ ተመልክቶ ነበር። ጳውሎስ በዘዴ ለጣዖታት ያላቸውን አምልኮታዊ ፍቅር ከተናገረ በኋላ ‘ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ ስለፈጠረው አምላክ’ ለመናገር ያንን መሠዊያ መግቢያ አድርጎ ተጠቀመበት። አዎን፣ ይሖዋ ስለተባለው አምላክ ምንም ነገር አያውቁም ነበር! ጳውሎስ በጉዳዩ በቀላሉ የሚጎዱ መሆናቸውን ግምት ውስጥ ስላስገባ ግሩም ምሥክርነት ለመስጠት ችሏል። ምን ውጤት ተገኘ? ‘በአርዮስፋጎስ ያለው ፍርድ ቤት ፈራጅ ዲዮናስዩስ፣ ደማሪስ የሚሏት አንዲት ሴትና ከእነርሱ ጋር ሌሎች’ ብዛት ያላቸው ሰዎች እውነትን ተቀበሉ። (ሥራ 17:16–34) ማስተዋል በማሳየት ረገድ ጳውሎስ እንዴት ያለ ምሳሌ ነው!
ያለምንም ጥርጥር ማስተዋል ያለጥረት ወይም በተፈጥሮ የሚገኝ አይደለም። ነገር ግን በትዕግሥት፣ በጸሎት፣ ብርቱ ጥረት በማድረግ፣ ከሌሎች ጋር የቀረበ ግንኙነት ስታደርግ ጥበበኛ በመሆን፣ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና ያጠናኸውን በማሰላሰል እንዲሁም በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ላይ በመታመን ማስተዋልን ልታዳብር ትችላለህ።